Font size: +
10 minutes reading time (1950 words)

ስለወለድ እና የወለድ ወለድ አስተሳሰብ ደንቦች በጨረፍታ

ሰዎች ንብረታቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ አንድን ግዴታ ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል ስምምነት ሲፈፅሙ ውል እንዳደረጉ ከኢትዮጵያ የፍትሐብሄር ህግ ቁጥር 1675 መረዳት ይቻላል፡፡ አንድ ውል ከተደረገ በኋላ በአንደኛው ወይም በሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች ላይ ግዴታን ይጥላል፡፡ ይህንን ግዴታ በተባለው ጊዜ አለመፈፀም ወይም ጊዜ ካልተቀመጠ ደግሞ ማዘግየት የሚያስከትለውን ኪሳራ በተመለከተ ተዋዋይ ወገኖች ገደብ ወይም ቅጣት ወይም አንድ የተወሰነ ወለድ ግዴታውን ያልፈፀመ ተዋዋይ ወገን ውሉን ላከበረው ወገን እንዲከፍል ሲዋዋሉ መመልከት ወይም በፍርድ ቤቶች ሲወሰን ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወለድና የወለድ ወለድ (Interest on interest or compound interest) አስተሳሰብ ደንቦችን በተመለከተ እና ተያያዥ ጉዳዮችን የኢትዩጵያ ህጎች ላይ ተመስርተን በጨረፍታ እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡

 1. ትርጓሜ

ወለድ የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ስንመለከተው አንድ ገንዘብ ያበደረ ሰው ተበዳሪው ብድሩን በመጠቀሙ ላበዳሪው ወገን በበኩሉ የሚከፍለው ወይም አንድ የባንክ ደንበኛ ያለውን ገንዘብ በአንድ ባንክ ገንዘብ ተቀማጭ ሲያደርግ በመቶኛ የሚታሰብ ገንዘብን የሚመለከት ወይም ተበዳሪ የወሰደውን ገንዘብ ወይም እቃ በወቅቱ ባለመመለሱ የተነሳ የሚከፈል የገንዘብ ካሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወለድ ለገንዘብ ብድር ብቻ የሚከፈል ሳይሆን አንድ ግዴታን ባለመፈፀም ወይም በማዘግየት እና ይሄ ፍሬ ነገር ሲረጋገጥ የሚከፈል ጭምር ነው፡፡ በተጨማሪም ወለድ በስምምነት ወይም ያለስምምነት ማለትም በህግ አግባብ ሲወሰን ሊከፈል የሚችል ገንዘብ ነው፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ዓላማ ሲባል በመቶኛ የሚታሰበውን ገንዘብን በሚመለከት ብቻ ያለውን እናያለን፡፡

የወለድ ወለድ ማለት በሚከፈል ወለድ ላይ በስምምነቱ ወይም በህግ መሰረት ወለዱን በወቅቱ ያልከፈለ ወገን በወለዱ ላይ የሚከፍለው ተጨማሪ የወለድ ወለድ እንደመቀጫ ያለ ገንዘብ ማለት ነው፡፡

 1. ወለድ እና የወለድ ወለድ ከኢትዮጵያ ህግ አንፃር
  • ወለድ

ወለድን በተመለከተ የፍታብሄር ህጉ አንቀፅ 1751፣ 1803 እና 2478 በዋናነት ገዢ የሆኑ ድንጋጌዎች ሲሆኑ ሌሎች ህጋዊ ወለድን በሚመለከቱ በፍታብሄር ህጉ የተለያዩ መፅሀፎች ላይ ተመልክቷል፡፡ መሰረታዊ ወደሆኑት ድንጋጌዎች ስንመለስ የፍታብሄር ህጉ አንቀፅ 1751 ህጋዊ ወለድ (Legal Rate of Interest) ማለት በውል ያልተወሰነ ወለድ (ጥቅም) ከፋይ የሆነ ሰው በዓመት በመቶ ዘጠኝ (9%) ሂሳብ ይከፍላል በማለት በትርጓሜ መልክ ደንግጓል፡፡ ከዚህም ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው አንደኛ በውል ያልተወሰነ የወለድ መጠንን በተመለከተ የወለድ መጠኑ የሚከፈለው ወይም የሚሰላው በዓመት ሆኖ ምጣኔውም በመቶ ዘጠኝ መሆኑን ነው፡፡ በአጭሩ ህጋዊ ወለድ በዓመት በመቶ ዘጠኝ የሚከፈልበት ገንዘብ ማለት ነው፡፡ ህጋዊ ወይም መደበኛው ወይም ደንበኛው ወለድ ማለት ይህ ከሆነ ተዋዋይ ወገኖች የወለድ መጠናቸውን መወሰን ይችላሉ ወይ? ከቻሉ ምን ያህል ድረስ?

ተዋዋይ ወገኖች ውል ለመዋዋል ችሎታ ያላቸው (Capable) እና የሚዋዋሉበትን ጉዳይ በቂ በሆነ እርግጠኝነት የሚቻል (Possible)፣ ህጋዊ (Legal)፣ እንዲሁም ሞራላዊ ከሆነ የውላቸውን ጉዳይ (Object) የመወሰን መብት (FREEDOM OF CONTRACT) እንዳላቸው ከፍታብሄር ህጉ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችሉ ከሆነ ደግሞ የብድር ውል ሲዋዋሉ ውላቸው ያለወለድ ወይም በወለድ እንዲሆን ለማድረግ መብት አላቸው፡፡ ተዋዋዬቹ በመካከላቸው የሚያደርጉት ውል ከህግና ከሞራል የማይቃረንና የሚፈፀም ወይም የሚቻል ከሆነ በመካከላቸው እንደ ህግ ሆኖ እንደሚያገለግል ከፍ/ህ/ቁ 1731 መረዳት ይቻላል፡፡

ስለውሎች ውጤት በሚደነግገውና ስለውልን ስላለመፈፀም በሚያትተው የፍታብሄር የውል ህግ ክፍል አንቀፅ 1803 (2) ላይ የገንዘብ ዕዳን በማሳለፍ ስለሚከፈል ወለድ ሲያትት

“በውለታው ውስጥ የበለጠ ወለድ የታሰበ እንደሆነ በዚሁ በከፍተኛው ወለድ መታሰቡ ይቀጥላል” በማለት ያስቀምጣል፡፡

ይህ ድንጋጌ የሚያስረዳው በውሉ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ሳይከፈል በቀረ የገንዘብ ዕዳ ላይ የሚታሰበውን የወለድ ምጣኔ ተዋዋዮቹ የተስማሙበት መጠን እንደሆነ የሚደነግግ ነው፡፡ በዚህም አግባብ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ 81857 በቀን ጥር 13/2005 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅና ገዢ ውሳኔና የህግ ትርጉም አመልካች ለተጠሪ በውላቸው መሰረት በዋናው ገንዘብ ላይ የ14% ወለድ እንዲታሰብ መወሰኑ የፍ/ህ/ቁ 1803 (2) ያገናዘበ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ይህም ማለት ማናቸውም ውሎች ከብድር ውል በስተቀር ተዋዋይ ወገኖች እስከፈለጉት የወለድ መጠን ድረስ መዋዋል ይችላሉ፣ ይህም ውላቸው በመካከላቸው በፍ/ህ/ቁ 1731 መሰረት የፀና ይሆናል፡፡ የዳኞች (ፍ/ቤቶች) የውሉን ሁኔታ በማየት ትርጓሜ የሚሰጡበትና ከውሉ በተቃራኒ ወለዱን የሚቀንሱበት ሁኔታ የለም ማለት አይቻልም፡፡

የብድር ውልን በተመለከተ ግን ተበዳሪው ወለድ እንዲከፍል የውል ቃል ከሌለ በቀር ላበዳሪው ወለድ መክፈል እንደሌለበት የፍ/ህ/ቁ 2479 ያስረዳል፡፡ ይህ ማለት ግን ባለእዳው ግዴታውን ባለመወጣቱና በውላቸው ላይ ወለድ ባይታሰብ እንኳን በፍ/ቤት ለሚቀርብበት ክስ ሀላፊ ሲሆን በከሳሽ የሚጠየቀውንና በፍ/ቤት የሚወሰነውን ህጋዊውን ወለድ ያስቀራል ማለት አይደለም፡፡  

የብድር ውል ተዋዋዬች ውላቸውን በወለድ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ በወለድ እንዲሆን ሲወስኑ የወለድ መጠኑንም እግረመንገዳቸውን የመወሰን መብትም አላቸው፡፡ በወለድ እንዲሆን ከወሰኑ ከህጋዊው ወለድ ማሳነስ ወይም ማስበለጥ ወይም እኩል ማድረግ ይችላሉ፡፡

የፍታብሄር ህጉ አንቀፅ 2479(1) የብድር ውል ተዋዋይ ወገኖች ተበዳሪው ሊከፍለው የሚገባው የወለድ መጠን በዓመት ከአስራ ሁለት በመቶ (12%) በላይ ሊበልጥ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

ከዚህ ድንጋጌ ሁለት ነገሮችን መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንደኛው- ተዋዋይ ወገኖች የወለድ መጠኑን በተመለከተ እስከ 12% ድረስ መወሰን እንደሚችሉ መብትና ነፃነት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ It is also known as Contract Rate. ሁለተኛው- የክልከላ ይዘት ያለው ሲሆን እሱም ተዋዋዬቹ 12% በላይ መዋዋል እንደማይችሉና የወለድ መጠኑም በዓመት እንጂ በወር ወይም በሳምንት ወይም በሌላ ስሌት ማድረግ እንደማይችሉ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነገር የአራጣ ጉዳይ ነው፡፡ አራጣን በተመለከተ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ የህሊናን ወይም የሰውን ችግር መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ስር በአንቀፅ 712 (1) (ሀ) ላይ እንደተመለከተው

“ማንም ሰው የተበዳዩን ችግረኝነት፣ የበታችነቱን፣ ወይም የገንዘብ ችግሩን፣ ወይም መንፈሰ ደካማነቱን፣ ወይም ልምድ ወይም ችሎታ የሌለው መሆኑን መሰረት በማድረግ በህግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረው እንደሆነ በቀላል እስራት፣ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና በመቀጮ ይቀጣል” በማለት ይደነግጋል፡፡

ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው አራጣ ማለት ህጉ ከፈቀደው የብድር ወለድ መጠን በላይ ተዋውሎ ማበደር ማለት ነው፡፡ በአንቀፁ የተጠቀሱ ሌሎች ወንጀልን የሚያቋቁሙ ነገሮች (Elements) መሟላታቸውን ማረጋገጥ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ህጉ የፈቀደው የብድር ውል ወለድ መጠን በዓመት 12% ድረስ ብቻ ነው፡፡ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚያበድሩትን ከፍተኛ መጠን ያለውን የወለድ መጠን አያካትትም፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በየካቲት 11 ቀን 2005 ዓ.ም በሰ.መ.ቁ 80119 በሰጠው ገዢ የህግ ትርጉምና ውሳኔ በቅፅ 15 እንደታተመው በወር 10% ወለድ ታስቦ እንዲከፈል በመስማማት ገንዘብ ማበደር በአራጣ የወንጀል ድርጊት የሚያስጠይቅ መሆኑን ትንታኔ በመስጠት ተከሳሹ በሁለት የአራጣ የወንጀል ድርጊቶች ጥፋተኛ ተብለው በሶስት አመት ፅኑ እስራትና በብር 4000.00 (አራት ሺህ) የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ በማለት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ አፅንቶታል፡፡ በመሆኑም የብድር ውል ተዋዋዬች የወለድ መጠኑን በሚወስኑበት ሰዓት በህግ ከተፈቀደው በላይ ወለድ እንዳይዋዋሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚያበድሩበት አግባብ እንደተጠበቀ ነው፡፡

ከላይ የተመለከትነው የብድር ውል ወለድ መጠን ባንኮችን ይመለከታል ወይ?

እንደሚታወቀው ባንኮች ከጥንስሳቸው ጀምሮ የደንበኞቻቸውን ተቀማጭ ገንዘብ በማስቀመጥ ደንበኞቻቸው ላስቀመጡት ገንዘብ ወለድ እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የገንዘብ ችግር ላጋጠመው ደንበኞቻቸው ወይም ኢንቨስትመንቱን ማስፋፋት ለሚፈልግ ባለሀብት ወይም ብድር ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው ብድር በብድር ውል መያዣ በመያዝ ይሰጣሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ /እንደተሻሻለ/ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 5 (4) ስር እንደተመለከተው ብሔራዊ ባንኩ የገንዘብ ብድር አቅርቦት በተፈለገው መጠን መገኘትን፣ እንዲሁም የወለድ ተመንና ሌሎች ክፍያዎችን የመወሰንና የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 27 ብሔራዊ ባንኩ አዋጁንና አዋጁን ተመስርተው የሚወጡ ደንቦችን ለማስፈፀም የሚረዱ መመሪያዎችን ለማውጣት ስልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ አግባብ ብሔራዊ ባንኩ መመሪያ ቁጥር NBE/INT/11/2010 በማውጣት ንግድ ባንኮች የብድር ውል ለደንበኞቻቸው በሚሰጡበት ወቅት ላበደሩት ብድር የወለዱን ምጣኔ በራሳቸው እንዲወስኑ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

በመሆኑም ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ የሚታሰበው የወለድ ምጣኔ ከላይ እንደተመለከተው በፍታብሄር ህጉ እንደተመለከተው የወለድ ጣራው በዓመት እስከ 12 % ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ ማድረግ እንደሚችሉ ነው፡፡

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ፀሀፊው በተመለከተው አንድ በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኝ ባንክ እና በግለሰብ መካከል በተደረገ የብድር ውል ስምምነት ግለሰቡ የብር 364,000 (ሶስት መቶ ስልሳ አራት ሺ) ለመበደር ፈልጎ አበዳሪ ባንኩ በተሰጠው ብድር ላይ በዓመት አስራ ዘጠኝ ነጥብ አራት በመቶ (19.04 %) ወለድ በየእለቱ ቀሪ ገንዘብ ላይ በየቀኑ ይታሰባል፡፡ ይህ የወለድ መጠን ባንኩ በየጊዜው እያሻሻለ በሚያወጣው የወለድ ተመን (Interest Rate) የሚተካ ይሆናል በሚል ውላቸው ውስጥ አካተዋል፡፡

እዚህ ጋር መታየት ያለበት ጉዳይ ንግድ ባንኮች በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸውና ለትርፍ የተቋቋሙ ሆነው ሳለ ሌላኛው ተዋዋይ ወገን በመካከላቸው ያለውን ጉዳይ የመዋዋል ነፃነት ወደጎን የሚል እና ለባንኩ የመደራደር አቅሙን የሚጨምር (Bargaining power) ከመሆኑም በላይ ባንኩ በፈለገው ጊዜ (የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር እንደተጠበቀ ነው) የወለድ ተመኑን የማሻሻል ስልጣን ያለው መሆኑ የተበዳሪውን የገንዘብ ችግር ከግምት የማያስገባ ከመሆኑም በላይ

 1. ተበዳሪው ቅድሚያ ከተስማማበት የወለድ ምጣኔ የበለጠ እንዲከፍል “በቅድሚያ ስምምነት” ስም ብቻና የተበዳሪውን ችግር መሰረት በማድረግ ተበዳሪው ከባድ የውል ግዴታ ውስጥ የሚያስገባውን ሁኔታ ይፈጥራል፤
 2. በህግ ፊት የተፈጥሮ ሰውና በህግ ሰውነት የተሰጣቸውን ሰዎች በአንድ አገር ህግ ውስጥ በእኩል አይን እንዳይታዩ ያደርጋል (በሌላ በኩል ውል የመዋዋል፣የመክሰስና የመከሰስ እኩል መብት እንዳላቸው ልብ ይሏል)፤
 3. ባንኮች ላበደሩት ብድር ክፍያ በወቅቱ ተመላሽ ባይደረግላቸው በመያዣ የያዙትን የተበዳሪውን ንብረት የፍ/ቤት ሂደትን መከተል ሳያስፈልጋቸው (DUE PROCESS OF LAW) በራሳቸው ጊዜ በመሸጥ የሽያጩን ገንዘብ ለብድሩ እዳ ክፍያ የማዋልና ገዢ ካልተገኘም በፍ/ሥ/ሥ/ህጉ መሰረት ሁለት ጊዜ ጨረታ በማውጣት በመያዣ የተያዘውን ንብረት በጨረታው ላይ በወጣው መጠን የራሳቸው ንብረት ለማድረግ እንደሚችሉ ስልጣን የተሰጣቸው መሆኑን ስለ በባንክ በመያዣ ስለተያዘ የማይንቀሳቀሱና የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች የወጣ አዋጅ ቁጥር 97/1990፣ ስለንግድ ተቋም የዋስትና መያዣ የወጣ አዋጅ ቁጥር 98/1990 እና በባንክ በመያዣ ስለተያዘ ንብረት የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 216/1992 “ን” ስንመለከት የግለሰቦችን ሰብዓዊና ህገ-መንግስታዊ ንብረት የማፍራት መብት “በህጋዊ” መንገድ የመንጠቅ አቅም ያላቸው በመሆኑ በህግ አውጪው አካል በጥንቃቄ ሊታዩ ይገባል፡፡
 4. በአጠቃላይ ባንኩ ብድር በሚሰጥበት ጊዜ የሚያስከፍለው ወለድና ሌሎች ወጪዎች ተበዳሪው ከችግሩ የተነሳ ብድሩን መክፈል ሳይችል ቢቀር ከተበደረው ዋና ገንዘብ በላይ ወለዱና ሌሎች ወጪዎች እንደሚበዙ መገመት የማይከብድ ሆኖ ተበዳሪው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለግብር ከፋዩ ዜጋ እና ለመንግስት ሸክም ስለሚሆን ባንኮች በሚሰጡት የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ በጥናት ላይ ተመስርቶ እንደፍታብሄር ህጉ በዓመት 12 % እንዲሆን በማድረግ በሀገሪቱ ላይ ወጥ የሆነ የብድር ወለድ ምጣኔ ህግ እንዲኖር ቢደረግ ወይም የተበዳሪዎችን አቅም ባገናዘበ መልኩ የብድር ወለዱ ምጣኔ ገደብ ቢበጅለት የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
  • የወለድ ወለድ

የፍታብሄር ህጉ አንቀፅ 1804 እና 2481 የወለድ ወለድን በተመለከተ ይደነግጋል፡፡ የወለድ ወለድን በሚመለከት በፍታብሄር ህጋችን ውስጥ አለ ወይስ የለም የሚለውን በተመለከተ የህግ ባለሙያዎች የተለያየ አቋም ያላቸው ሲሆን የፅሁፉ አንዱ ዓላማም ይህንን ፅሁፍ መነሻ በማድረግ ባለሙያዎችንና አንባብያንን ለውይይት መጋበዝ በመሆኑ የፀሀፊውን አቋም እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

በብድር ውል ላይ ተዋዋይ ወገኖች ወለዱ ከዋናው ገንዘብ ጋራ ተጨማሪ ሆኖ ወለድ ይወልዳል ብለው አስቀድመው ለመዋዋል እንደማይችሉ የፍ/ህ/ቁ 2481 (1) በግልፅ ያመለክታል፡፡ በዚህ የህግ ድንጋጌ መሰረት በተሰጠው ብድርና በተስማሙት የወለድ መጠን ላይ ሁለቱ ገንዘቦች በአንድ ላይ ሁነው ሌላ ወለድ እንዲኖር መዋዋል የከለከለው አበዳሪው የተበዳሪውን የገንዘብ ችግር ምክንያት በማድረግ ያለአግባብ ሁለት ጊዜ ወለድ በማስከፈል እንዳይበለፅግ በማሰብ ሲሆን በሌላ በኩል ተበዳሪውን ሊሸከመው የማይችለው እዳ ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ የማመዛዘን ስራ ነው ህጉ የሰራው፡፡ በዚህ የሕግ ድንጋጌ መሰረት በብድር ውል ግንኙነት ላይ የወለድ ወለድ በሀገራችን ህግ የተከለከለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሌላኛው የወለድ ወለድን የሚመለከተው የፍታብሄር ህግ ቁጥር 1804 ሲሆን ንዑስ ቁጥር 1 እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“ከባለእዳው ላይ ያለው ገንዘብ በየጊዜው የሚከፈል ሆኖ ለባለገንዘቡ በየጊዜው የሚገኘው ገቢ የሆነ እንደሆነ ለምሳሌ ኪራይ፣ የርስት አላባ፣ የዘወትር ጡረታ ወይም ለህይወቱ የተወሰነ ጡረታ፣ የአንድ ካፒታል ወለድ፣ ይህ የመሰለ ከሆነ ደንበኛው ወለድ የሚታሰበው ክስ ለአንድ ፍርድ ቤት ከቀረበበት ቀን ጀምሮና ይኸውም ባለእዳው የአንድ ዓመት ሙሉ ሒሳብ ያለበት እንደሆነ ነው፡፡”

ከዚህ የህግ ድንጋጌ የምንረዳው በወለድ ላይ ወለድ በመርህ ደረጃ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ በድንጋጌው ውስጥ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሲሟሉ የወለድ ወለድ ሊኖር የሚችልበትን ሁኔታ ያስረዳል፡፡ እነዚህም ሁኔታዎች፡-

      ሀ) ባለእዳው በየጊዜው የሚከፍለው ገንዘብ እና ለባለገንዘቡ እንደገቢ (በተወሰነ ጊዜ የሚገኝ እንጂ የተከማቸ እዳን አያመለክትም) የሚያገለግል ሲሆን፤

      ለ) እዳውን ለማስከፈል በፍ/ቤት በባለገንዘቡ ክስ ሲመሰረት፤ እና

      ሐ) ባለእዳው ለአንድ ዓመት ክፍያውን ሳይከፍል የቀረ እንደሆነ ወይም ባለገንዘቡ ባለእዳውን የሚጠይቀው የአንድ ዓመት ክፍያን ሲሆን ነው፡፡

በመሆኑም ህጉ የወለድ ወለድን በሁኔታ ላይ ብቻ ተመስርቶ እንዲኖር የፈቀደበት ሀተታ ዘምክንያት አንደኛው ባለገንዘቡ ገንዘቡን ለመቀበል በጣም የሚቸኩልበት ሁኔታ ላይ አይደለም ተብሎ ግምት ስለሚወሰድ ነው ምክንያቱም በየጊዜው የሚከፈል ገንዘብ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የወለድ ወለድ በመርህ ደረጃ ቢፈቀድ ባለእዳው በወለድ ወለዱ መጠራቀም ወይም መከማቸት እዳው በዝቶ ባለእዳውን አደጋ ውስጥ ላለመክተት በማሰብ ነው፡፡ ይህ የህጉ ግምትና ድንጋጌ ባለገንዘቡ ያለውን መብት እና ባለዕዳው ያለበትን ግዴታ በተነፃፃሪ ሁኔታ ባለዕዳው የአንድ ዓመት እዳ ካለበትና ይህንኑ ጥያቄ በፍ/ቤት ክስ ተመስርቶ በባለገንዘቡ ከተጠየቀ ባለገንዘቡ ባለዕዳው ላይ ካለው ያልተከፈለ እዳ እና ወለድ በተጨማሪ የወለድ ወለድ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት እንዳለው መደንገጉ ትክክለኛና አግባብ (Fair) ከሚባል በስተቀር የሚነቀፍ አይደለም፡፡ በወለድ ወለድ ላይ ሌላ ወለድ ማሰብ ፈፅሞ በህጋችን ቦታ የተሰጠው ጉዳይም አይደለም፡፡

 1. መቋጫ

ሌላኛውና የመጨረሻው ጉዳይ በብድር ለተሰጠ ወለድ የመጠየቂያ ጊዜ ምን ያህል ነው የሚለውን ተመልክተን ይህን ፅሁፍ እናበቃለን፡፡ በዚህም መሰረት የፍታብሄር ህጉ አንቀፅ 2024 እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

    ቁ. 2024. በሁለት ዓመት የተወሰነ ጊዜ

     እዳው እንዲከፈል መጠየቅ ከሚገባበት ቀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ሳይከፈል የቀረ ገንዘብ እንደተከፈለ  የሚቆጠረው፤

     () በብድር የተሰጠ የገንዘብ ወለድና በጠቅላላውም የዓመት ጊዜ ተወስኖለት በየዓመቱ ወይም ከዚህ ባነሰ የጊዜ ውሳኔ ውስጥ ሊከፈል የሚገባው ዕዳ የሆነ እንደሆነ ነው፡፡

በድንጋጌው ፊደል (ረ) ስር የተመለከተው ሲታይ በብድር የተሠጠ ወይም በማናቸውም የአከፋፈል ሁኔታ በየአመቱ ወይም ከአመት ባነሰ ጊዜ እየተከፈለ እንዲያልቅ ጊዜ ተቆርጦለት የተሰጠ ገንዘብ ላይ የሚታሰብ ወለድ እዳው ከበሰለበት ወይም በየተወሰነ ጊዜ የሚከፈል ገንዘብ ከሆነ ደግሞ ገንዘቡ ተከፍሎ ማለቅ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ዓመት ያለፈ እንደሆነ በእነዚህ ክፍያዎች (እዳዎች) ላይ ሊጠየቅ የሚችለው የወለድ ክፍያ እንደተከፈለ የህግ ግምት የሚወሰድ መሆኑን ያሳያል፡፡

በመሆኑም ይህ ድንጋጌ አስገዳጅ የሆነ የሕግ ግምት ያለው ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ማናቸውም የተፈጥሮም ሆነ የሕግ ሰው (ባንክና ሌሎች አበዳሪ ተቋማት) የገንዘብ ብድር ካበደረ በኋላ ብድሩ ተከፍሎ  የሚያልቅበትን የጊዜ ገደብ ካበቃ ከሁለት ዓመት በኋላ የብድሩ የወለድ ይከፈለኝ ጥያቄ በሕግ እንደተከፈለ የሚገመት መሆኑን የሚደነግግ ድንጋጌ በመሆኑ ተበዳሪው ወለዱን የመክፈል ግዴታው በህግ ቀሪ ስለሚሆንለት አበዳሪውን በእጅጉ የሚጎዳ ጉዳይ በመሆኑ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Is US action under the Ambit of International Law?...
የሰበር ዓላማ ወጥነትን ማስፈን ወይስ ሕገ-ወጥነትን ማስፋፋት?
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 14 June 2024