የዚህ አጭር ጽሑፍ ዋና ትኩረቱን በድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 ላይ በማድረግ አዋጁ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት በአንቀፅ 55(1) ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከተሰጠው ሕግ የማውጣት ስልጣን ጋር ያለውን ተቃርኖ እና የሕገ መንግስቱን የበላይነት ያላከበረ ስለመሆኑ እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ተጠሪነት ላይ የሚነሱ የሕግ ጉዳዮችን በመዳሰስ መፍትሔውን ማስቀመጥ ነው፡፡

በአስራ አንድ ምዕራፎች እና በአንድ መቶ ስድስት አንቀጾች የተዋቀረው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት ህዳር 29 ቀን 1987ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት አፅድቀውት ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ እንደዋለ ከሕገ መንግስቱ መግቢያ እና በአንቀፅ 2 ላይ የተገጾ የምናገኘው ሲሆን ሕገ መንግስቱ በምእራፍ አራት እና አምስት ስለመንግስታዊ አወቃቀር እንዲሁም ስለሥልጣን አወቃቀርና ክፍፍል በሚገልፀው ክፍል ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ስርዓተ መንግስት ፓርላሜንታዊ እንደሆነ፤ በፌዴራል መንግስት እና በክልሎች የተዋቀረ እንደሆነ፤ ክልሎቹም ዘጠኝ (ትግራይ፤ አፋር፤ አማራ፤ ኦሮሚያ፤ ሶማሌ፤ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ፤ ደቡብ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፤ የጋምቤላ ሕዝቦች እና የሐረሪ ሕዝብ ክልል) እንደሆኑ፤ አዲስ አበባም የፌዴራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ እንደሆነችና የከተማ አስተዳደሩም ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሰቱ ሆኖ ዝርዝሩ በሕግ የሚወሰን እራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም በአንቀፅ 51 ላይ የፌዴራሉን መንግስት ስልጣን እና ተግባር የሚዘረዝር ሲሆን በአንቀፅ 55(1) ላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ ለፌዴራሉ መንግስት በተሰጠው የስልጣን ክልል ሕጎችን እንደሚያወጣ ይገልፃል፡፡

በዚሁ ሕገ መንግስት ከተጠቀሱት መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አንዱና ዋነኛው መርህ ደግሞ “የሕገ መንግስቱ የበላይነት መርህ” ነው፡፡ በዚህ መርህ መሠረትም በአንቀፅ 9(1) ላይ እንደተመለከተው ማንኘውም ሕግ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከሕገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው እና ሕገ መንግስቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ እንደሆነ ነው፡፡

በመሆኑም ከላይ በተገለፀው አግባበብ ሕገ መንግስቱ ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሕጎች ይህን የአገሪቱ የበላይ የሆነን ሕግ በማክበር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቀው የወጡ ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የህገ መንግስቱን የበላይነት የማያከብሩ ሕጎችም ታውጀው በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ከእነዚህ ህጎች ውስጥም የዚህ  ጽሑፍ ትኩረት የሆነው የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 ነው፡፡

  1. የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 እና የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሕግ የማውጣት ስልጣን

የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ሐምሌ 23 ቀን 1996 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታውጆ የወጣ ሲሆን አዋጁ ያስፈለገበትን ምክንያቶች በሚገልፀው የአዋጁ የመግቢያ ክፍል ላይ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውስጥ የመጀመሪያው ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠው የድሬዳዋን ከተማ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ወደ ክልላቸው ይዞታ እንዲካለል በወቅቱ(በሽግግርመንግስቱወቅት) አንስተውት የነበረው ጥያቄ በሕግ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ በመንግስት በተወሰነው መሰረት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ለፌዴራሉ መንግስት ተጠሪ ሆኖ ሲተዳደር የቆየ ከተማ በመሆኑ እንዲሁም ለድሬዳዋ ነዋሪ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ለመስጠት በማስፈለጉ የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችንም በመዘርዘር አዋጁ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 55(1) (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ ለፌዴራሉ መንግስት በተሰጠው የስልጣን ክልል ሕጎችን እንደሚያወጣ በተደነገገው) መሰረት መታወጁን ይገልፃል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሕገ መንግስቱ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ አፅድቆ ያወጣው ህግ መሆኑን ከሚከተሉት ሶስት ምክንያቶች መረዳት ይቻላል፡፡

1ኛ. ሕገ መንግስቱ በአንቀፅ 50(1) ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግስት እና በክልሎች የተዋቀረ ስለመሆኑ የሚገልፅ ሲሆን የድሬዳዋ አስረተዳደር ግን በሕገ መንግስቱ ላይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ፌዴራል መንግስቱ አካል ሆና በሕገ መንግስታዊ መዋቅሩ እውቅና ባላገኘችበት ሁኔታ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን ማውጣቱ ተገቢ አይደለም፡፡

2ኛ. በሕገ መንግስቱ በአንቀፅ  55(1)  ድንጋጌ መሰረት በሕገ-መንግስቱ ለፌዴራል መንግስቱ በተሰጠ የስልጣን ክልል ብቻ የሕዝብ ተወካዮች  ም/ቤት ህግ ማውጣት እንደሚችል የሚገልፅ ቢሆንም ድሬዳዋን አስተዳደር በተመለከተ ግን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሕግ ሊያወጣ እንደሚችል በሕገ መንግስቱ ላይ የተገለፀ ነገር በሌለበት ሁኔታ ም/ቤቱ ቻርተሩን ማወጁ ተገቢ አይደለም፡፡

3ኛ. ቻርተር አዋጁ በዋናነት እንዲታወጅ ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠው በ1985ዓ.ም ድሬዳዋ ለፌዴራሉ መንግስት ተጠሪ እንድትሆን የተደረገበት ውሳኔ ሲሆን ይህ ውሳኔ የሕገ-መንግስቱ አከል ባልሆነበት እና ተወሰነ የተባለው ውሳኔም ህግ እንኳ ቢሆን በኋላ ላይ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው ህገ-መንግስት አውቅና የነፈገው በመሆኑ ድሬዳዋን እንደ ፌዴራል መንግስት አካል በመቁጠር የፌዴራሉ መንግስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቻርተር አዋጁን ማወጁ የሕግ መሰረት የለውም፡፡

ስለሆነም ከላይ በተገለፁት ምክንያቶች የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 “የሕገ-መንግስቱን የበላይነት” ያላከበረ እና ኢ-ሕገመንግስታዊ አዋጅ ነው፡፡

  1. የድሬዳዋ አስተዳደር እራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የተጠሪነት ጉዳይ፡-

ለድሬዳዋ ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን መስጠትና የከተማውን አስተዳደር አደረጃጀትና አሰራር ከዲሞክራሲ መርሆችና ከመልካም የአስተዳደር ሥርዓት እንዲሁም ከወቅታዊ የእድገትና የልማት አቅጣጫ ጋር በሚጣጣም መልኩ በህግ መወሰን በማስፈለጉ እንዲሁም ዘላቂ የሆነ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ የድሬዳዋ ከተማ ለጊዜው እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ህጋዊ መሰረት መጣል ለከተማው መልካም አስተዳደርና ልማት መፋጠን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቻርተር አዋጁ እንደ ታወጀ የቻርተሩን አላማ የሚገልፀውክፍል(preamble) ላይ ተገልፆ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ማለት አዋጁ ያስፈለገው የድሬዳዋ አስተዳደር ከፌዴራልም ሆነ ከክልል መንግስታት ተፅዕኖ ውጪ የራሱ የሆነ የሕግ አውጪ፤የሕግ ተርጓሚ እና የሕግ አስፈፃሚ አካላት ኖረውት ነዋሪው እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር እንደሆነ የምንረዳው እውነታ ነው፡፡በተጨማሪም ሕገ-መንግስቱም ቢሆን ድሬዳዋ የፌዴራሉ ወይም የክልል መንግስት አካል እንደሆነች የሚገልፀው ነገር የለም፡፡

ይሁን እንጂ፡-

1ኛ. በቻርተር አዋጁ የከተማው ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግስትና ለነዋሪው እንደሆነና የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ሊበት ነው እንደሚችል በአንቀፅ 15(1)(2) ላይ የተገለፀ በመሆኑ፤

2ኛ. በቻርተር አዋጁ ለተቋቋሙት ፍ/ቤቶች ዳኞች የሚሾሙት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በእጩ ዳኞቹ ላይ ያለውን አስተያየት ከሰጠ በኋላ እንደሆነ በአንቀፅ 37(1) ላይ የተገለፀ በመሆኑ፤

3ኛ. ከከተማው ሕግ አስፈፃሚ አካላት ውስጥ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆነው ከንቲባው ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግስቱ እና ለከተማው ምክር ቤት እንደሆነ በአንቀፅ 20(1) የተገለፀ በመሆኑ፤

4ኛ. የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት በሚኒስትሮች ም/ቤት በሚወጣ ደንብ መሰረት የሚቋቋም እንደሆነና ተጠሪነቱም ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደሆነ በቻርተር አዋጁ አንቀፅ 26(1)(ሀ) የተገለፀ በመሆኑ፤-

ከዚህም በተጨማሪ በዋናነት በአዋጁ ንቀፅ 51 ላይ የከተማው አስተዳደር የፌዴራሉ መንግስት አካል እንደሆነ እና ተጠሪነቱም ለፌዴራል መንግስቱ እንደሆነ እንዲሁም የከተማው አስተዳደር ዕቅዱን፤በጀቱንና የከተማውን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ዓመታዊና ወቅታዊ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንደሚያቀርብ ከአዋጁ አላማ በተቃረነ መልኩ ተደንግጓል፡፡

ሌላው ጉዳይ የድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ቀበሌዎችን የሚመለከት ሲሆን ድሬዳዋ የገጠር ቀበሌዎችን ባካተተ መልኩ ወሰን እንደሚኖራት ቻርተሩ ላይ ተገልጧል፡፡ በአሁኑ የአስተዳደሩ አወቃቀር ደግሞ 38 የገጠር ቀበሌዎች በአስተዳደሩ ስር ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በገጠር የሚገኘው ነዋሪን በተመለከተ ቻርተር አዋጁ በግልፅ የሚያስቀምጠው ነገር የሌለ በመሆኑና የሚተዳደረውም በድሬዳዋ አስተዳደር ስር በመሆኑ የገጠር ቀበሌዎችም በእጅ አዙር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የፌዴራል መንግስቱ አካል እንደሆኑ መረዳትይቻላል፡፡

በእነዚህ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የድሬዳዋ አስተዳደር ተጠሪነት ጉዳይ ከቻርተር አዋጁ አላማ እንዲሁም ከሕገ-መንግስቱ የተፃረረ በመሆኑ የድሬዳዋን ነዋሪ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን የገደቡ ናቸው፡፡

በመሆኑም በአጠቃላይ በዚህ ጽሑፍ ለተዘረዘሩት ጉዳዮች መሰረታዊ ችግሩ ድሬዳዋ ሕገ መንግስታዊ እውቅና መነፈጓ በመሆኑ በተገቢ ጥናት እና ውይይት ላይ ተመርኩዞ የድሬዳዋን ነዋሪ ስነ-ልቦና መሰረት ባደረገ መልኩ ነዋሪው እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን እንደ ሌሎቹ ክልሎች እና እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች እንዲጎናፀፍ ሕገ መንግስቱን በማሻሻል ድሬዳዋ ራስ ገዝ አስተዳደር ሆና ህገ-መንግስታዊ እውቅና ማግኘት ይኖርባታል፡፡