Font size: +
10 minutes reading time (1908 words)

የቴዲ አፍሮ አልበም ምርቃት ክልከላ እና የመሰብሰብ መብት

የዚህ ጽሑፍ መነሻ የቴዲ አፍሮ የአልበም ምረቃ መከልከል ሲሆን ጽሑፉ ይህን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት በማንኛውም ምክንያት መሰብሰብ አድማሱ እስከምን ነው? የሚለውን መሠረታዊ ነጥብ የሚዳስስ ሲሆን የአልበም ምርቃቱን መከልከል ምክንያቶች በተመለከተ ግን ጸሐፊው በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለውን እውነት በማስረጃ ባለማረጋገጡ አቋም ከመያዝ ተቆጥቧል፡፡ ይሁን እንጂ አጋጣሚው በአስፈፃሚውም ይሁን በስብሰባ አዝጋጆቹ ብሎም በማህበረስቡ ላይ ያለውን መደናገር የመሰብሰብ መብትን አድማስ ለማብራራት ምቹ በመሆኑ ጸሐፊው በርግጥ ለቴዲ አፍሮ የአልበም ምረቃ ፈቃድ ያስፈልግ ነበር? ፈቃድ ካስፈለገውስ መከልከል ይቻል ነበር? የመከልከል ተግባሩ የሚጥሳቸው መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችና መብቶችስ ምንምን ናቸው? ለሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል፡፡

መግቢያ

መሰብሰብ ሰው ሁለት ሆኖ ከተፈጠረበት የታሪክ አውድ ይጀምራል፡፡ ሰው ማህበራዊ እንስሳ ነው ሲባል በሌላ አነጋገር ሰው ይሰበሰባል እንደ ማለት ነው፡፡ ፈጣሪም አዳም ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ሲል ጥንትም ፈጣሪ ሰውን ሲፈጥረው በውስጡ ከሌሎች ጋር የመሆን፣ ከሌሎች ጋር የመምከር፣ ከሌሎች ጋር የመደሰት፣ የመኖር፣ አንድን ነገር በጋራ የማድረግ፣ የማክበር ባሕርይ እንደፈጠረበት ሲያጠይቅ ነው፡፡ እናም መሰብሰብ ከፍ ሲል ፈጣሪ ለአዳም/ለአደም ሄዋንን/ሃዋን ሲፈጥርለት ዝቅ ሲል አዳምና ሄይዋን ቃዬልን ጠርተው ስለ አቤል ጉዳይ ሲጠይቁት ይጀምራል፡፡

እናም ሰዎች በዚህ ማህበራዊ ተፈጥሯቸው ምክንያት ይቀራረባሉ፣ ይወያያሉ፣ ይመካከራሉ ይዘክራሉ በአጠቃላይ ለአንድ የግል ወይም የጋራ ጉዳያቸው ይሰበሰባሉ፡፡ ይህ ሰው ከመሆን ጋር እጅግ የተቆራኘ የመሰብሰብ ወይም የመሰባሰብ ተፈጥሮ መብት ሆኖ መከበር ከጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ታሪክ ይቆየንና ወደ እውነቱ ስንመጣም ይህ የመሰብሰብ መብት በነጭና ጥቁር ጽሑፍ በግልጽ አማርኛ የምድራችን ሕግ (law of the land) በሚባለው የሕዝብ እና የመንግሥት የቃልኪዳን ሰንድ በሆነው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አንቀፅ 30 ላይ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ መብት አለው በሚል ተደንግጎ ይገኛል፡፡ እንግዲህ በሚቀጥሉት አርእስቶች የዚህን ሕገ መንግሥታዊ መብት አድማስና ገደቦች እንዲሁም መብቱ የሚነካቸውን ተያያዥ ጉዳዮችን እያነሳን እንቀጥላለን፡፡

በሕግ ቋንቋ መሰብሰብ ምንድ ነው?

መሰብሰብ ማለት ጥሬ የአማርኛ ትርጉሙ ጉባኤ ማለት ሆኖ ዝርዝሩ አጠራቀመ፣ አከማቸ፣ አንድ ላይ አደረገ በማለት የደስታ ተ/ወልድ መዝገበ ቃላት ፍቺ ይሰጠዋል፡፡

የሕግ ትርጉሙ ደግሞ መሣሪያ ሳይዝ ከሌሎች ጋር በሰላም መሰብሰብ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ትርጉም ሕገ መንግሥቱ ለጉዳዩ የሰጠው አድማስ እንጅ ስብሰባ የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም አይደለም፡፡ መቼም መሰብሰብ የተለያየ ግብና ዓለማ ያለው እንደመሆኑ በ1983 የወጣው የአዋጅ ቁጥር 3 አንቀፅ 2/2/ ለፖለቲካ አላማ ሲባል የሚደረግ ስብሰባን ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በዚህ አግባብም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ማለት ብዙ ሕዝብ በቤት፣ በግቢ በአደባባይ ወይም በሌላ ስብሰባ ምቹ በሆነ ስፍራ የጦር መሣሪያ ሳይዝ፣ የህብረተሰቡን ሰላም ሳያወኩ ካስፈለገ በድምፅ ማጉሊያ መሣሪያ ጭምር እየተጠቀሙ ፖለቲካዊና ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚካሄድበት ስብሰባ ነው በማለት ገልፆታል፡፡

በሌላ በኩል በኃይለ ሥላሴ ግዜ የነበረውና ስለስብሰባ ሥርዓት የሚደነግገው አዋጅ ሰብሰባን ከአዋጅ ቁጥር 3 በተሻለ ደረጃ ትርጉም የሰጠው ሲሆን ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ስብሰባ ማለት በሕዝባዊ ስፍራ ላይ በእሱ ውስጥ ወይም በእሱ አቋርጦ በመሄድ የሚመራ የሕዝብ ሰልፍ ወይም የሀሳብ መግለጫ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ባህላዊ የሆኑትን ስብሰባዎች የሀይማኖት፣ የጋብቻ ወይም የመቃብር ሥነ ሥርዓት እንዲሁም ኦፊሳላዊ የሆኑ ጉባኤዎችን እና በሕግ መሠረት የሚደረጉ ስብሰባዎችን እና እነዚህን የመሳሰሉ ተግባሮችን አይጨምርም በማለት ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ሁሉም ስብሰባ ፈቃድ የማያስፈልገው መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡

በመሆኑም ስብሰባን በሕገ መንግሥቱና ከፍ ሲል ከገለፅነው አዋጅ ቁጥር 3 ተነስተን ስብሰባን

  1. ፖለቲካ ነክ ያልሆነ ስብሰባ፤

                    እና

  1. ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ፤

በማለት በሁለት ልንከፍለው እንችላለን፡፡ አንዳንድ ልዩ ሕጎች በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ስብሰባና ወይም መሰብሰብን እንደ የአዋጆቹ አውድ ሊያጠቡት ወይም ሊያሰፉት የሚችሉበት ሁኔታ ቢኖርም በመደበኛነት የሚታወቁት ስብሰባዎች ግን እነዚህ ሁለቱ ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ አንደኛው ፖለቲካ ነክ ያልሆነ ስብሳባ ፈቃድ ወይም ይሁንታ ከየትኛውም አካል ለመሰብሰብ ፈቃድ ማግኘት የማይፈልግ እንዲሁም ለየትኛውም አካል ስለስብሰባው የማሳወቅ ግዴታ የሌለበት ሲሆን ሁለተኛው ሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብስባ ግን ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ግዴታ ያለበት ነው፡፡

ሁለቱም ስብሰባዎች በሚያነሱት ጭብጥ ምክንያት መሠረታዊ ልዩነት ያላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለቱም ዓይነት ስብሰባዎች ከዚህ በታች የተመለከቱት ገደቦች ይመለከታቸዋል፡፡ ከዚህ ቀጥለን ስለሁለቱም ስብሰባዎች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡               

 

ፖለቲካ ነክ ያልሆነ ስብሰባ                 

በይዘት ረገድ

ከፍ ሲል ለስብሰባዎቹ ከተሰጠው ትርጉም መረዳት እንደሚቻለው መሰብሰብ እንዲሁ ክፍት የተለቀቀ እንደተፈለገ የሚደረግ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይሄውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ እንደተመለከተው ስብሰባ፡-

  • ሰላማዊ መሆን አለበት፣
  • መሣሪያ ተይዞ ሊደረግ አይችልም፣
  • የሌሎችን ሰላም፣ ዴሞክራሲያዊ መብትንና የሕዝብ ሞራል የሚነካ ሊሆን አይገባውም፣
  • የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን አካል፣ መልካም ስም የሚነካ ሊሆን አይችልም፡፡
  • የጦርነት ቅስቀሳዎች የሚደረግበት፣ ሰብአዊ ክብር የሚነካ ሊሆንም አይገባም፡፡

በመሆኑም ስብሰባ ከፍ ካሉት ነገሮች የፀዳ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ስብሰባ ከፍ ካሉት ነገሮች የፀዳ ሲባል አስቀድሞ ስብሰባው ይህ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት ማለት ሳይሆን መሰባሰቡ ከነዚህ ጉዳዮች አንዱን የሚመለከት ከሆነ ተጠያቂነት የሚያስከትል ስለሆነ መንግሥት ጣልቃ ገብቆ የመቆጣጠር ርምጃዎች ለመውሰድ መብትና ግዴታም አለበት እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የስብሰባ ቅድመ ሳንሱር ባይኖረውም በሕግ የተከለከሉ መሠረታዊ ነገሮችን የሚጥስ ከሆነ ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ በዚህም ምክንያት የፀጥታ አካላት ጣልቃ መግባት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

ከቅድሞ ሁኔታዎች አንፃር

መቼም ስብሰባው በሚደረግበት ጊዜ ከሚኖረው የሰው ቁጥር ብዛት፤ ከስብሰባው ባሕርይ አኴያ ከፍ ሲል ከተቀመጡ ገደቦች አንፃር ስብሰባዎቹ ቅድመ ሁኔታ ወይም ዝግጅት ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ ይሄውም በመንግሥት በኩል እንዲሁም በራሱ በስብሰባው አዘጋጅ በኩል ያለ ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡

አዘጋጁ መብቱን በሥራ ላይ በሚያውልበት ጊዜ ከፍ ሲል በይዘት ደረጃ በሕጉ የተመለከቱ ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲፈጸሙ ወይም በመደረግ ላይ ያሉ ስብሰባዎች ወደዚያ አቅጣጫ እንዳያመሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገበዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ያለው ግዴታ ደግሞ ስብሰባው በቁጥር ብዛት በስብሰባው አፈፃፀም ምክንያት የደህንነትና የሰላም ችግር እንዳያጋጥም ተገቢውን ጥበቃ የመሰጠት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ መንግሥት የመሰብሰብ መብትን በላቀ ደረጃ እንዲከበር ያለበት ግዴታ ተደረጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ከፍ ሲል የተገለፁት ጉዳዮችና ቅድመ ሁኔታዎች  በአብዛኛው የሚያስፈልጉት ፖለቲካ ነክ ላልሆነ የስብሰባ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ስብሰባ ከላይ ከተገለፁት ገደቦች በስተቀር ሌሎች ገደቦች የሌሉበት ነው፡፡ ቅድመ ሁኔታዎችም ወይም ገዶቦቹ፡-

  • ስብሰባው በተሻለ ደረጃ እንዲከናወን ለማድረግ፣
  • በስብሰባው ወቅት ወይም በኋላ የሚኖሩ የመብት ጥሰቶች እንዳይኖሩ ለማስቻል፣
  • በስብሰባው ሁከት እና ብጥብጥ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ለማድረግ ወዘተ

ነው፡፡ ፖለቲካ ነክ ያልሆነ ስብሰባ ስብሰባው አስቀድሞ የማንንም ይሁንታ ወይም ፈቃድ የማይጠይቅ የስብሰባ ዓይነት ነው፡፡ ይልቁንስ ዜጎች እንደመብት ባሻቸው ጊዜ የሚያደርጉት ልብላ ልጠጣ ብለን መንግሥትን እንደማናስፈቅደው ሁሉ ስብሰባው ወይም መሰብሰቡ በአሻህ ወይም በፈለክ ጊዜ የምታደረገው ነው፡፡ ለዚህ ዓይነት ስብሰባ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆኑት ሰርግ፣ ልደት፣ ኮንሰርት፣ ማንኛውም ዓይነት ምርቃት፣ የእድር ስብስባ፣ ተሰብስቦ መወያየት፣ መመካከር፣ ሀሳብ መለወጥ፣ በየካፍቴሪያው ሻይ ቡና መባባል እንዲሁም እንደ ስብሰባ የማይቆጠሩ ተራ ስብሰቦዎች ሲሆኑ ከጀምሩም የተለየ ጭንቀትና ጥንቃቄ የማያስፈልጋቸው የዕለት ተዕለት ጉዳዮች ናቸው፡፡

ይሁን እንጅ ይህ ዓይነቱ ስብሰባ የሌሎችን መብት የሚነካ ለሰላም እና ለደህንነት አስጊ መሆን የለበትም እስከተባለ ድረስ ስብሰባው ቅድመ ፈቃድ የማያስፈልገው ቢሆንም ከሰው ቁጥር ብዛት፣ ከስብሰባው ቦታ እና ከስብሰባው ወይም ከስብስቡ ባህሪ አኳያ በአንድ በኩል የተሰብሳቢዎቹን ሰላም እና ደህንነት በሌላ በኩሉ ከስብሰባው ውጭ ያሉ ማህበረሰቦች መብት እና በስብሰባዎቹ ላይ ከፍ ሲል የተጣሉ ገደቦችን ውጤታማ በማድረግ ሰላማዊ ስብሰባ ለማድረግ አስቀድሞ ለመንግሥት አካል ማሳወቅ፣ በመንግሥት በኩል ቅድመ ዝግጅት አድርጎ የሰው ሀይል እንዲመድብ፤ አዘጋጁም ከቁጥጥሩ የወጣ የፀጥታ ችግር እንዳይገጥመው በተለይም መንግሥት አስቀድሞ ካልተነገረው ሁሉንም ስብሰባ በራሱ ያውቃል ለማለት ስለሚያስቸግር አስቀድሞ ማሳወቅ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ አስቀድሞ ማሳወቅ አስቀድሞ ከማስፈቀድ እጅግ የተለየ በመሆኑ በዚህ ስብሰባ ላይ በሕግ የተጣለ አስቀድሞ የማስፈቀድ  ግዴታ የለም፡፡

ሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባ

ይህ ስብሰባ ስብሰባ እንደመሆኑ ከፍ ሲል በተገለፁት መደበኛ የስብሰባ ዓይነት የተቀመጡ መመዘኛዎች ይመለከተዋል፡፡ ይህ ስብሰባ ከፍ ሲል ከተገለፀው የስብሰባ ዓይነት የሚለየው በአዋጅ ቁጥር 3/83 አንቀፅ 4 መሠረት ስብሰባው ከመዳረጉ ከ48 ሰዓታት በፊት በጽሑፍ ለከተማው አስተዳደር ወይም ከከተማ ውጭ ከሆነ ለወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት የማሳወቅ ግዴታ የስብሰባው አዘጋጅ ድርጅት፣ ቡድን ወይም ግለሰብ ያለበት በመሆኑ ነው፡፡

ስብሰበባው ከሚያነሳው ጉዳይ ባህርይ በአብዛኛው መንግሥትን ከመቃወም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይነሱበታል ተብሎ የሚታሰብ የስብሰባ ዓይነት በመሆኑ አስቀድሞ ማስታወቅ አንድም ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እና ግርግር እንዳያመራ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት በተሰብሳቢዎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ እንዲሁም ስብሰባው የሌሎች ሕዝቦችን ሰላም ደህንነት ስጋት ላይ እንዳይጥል የሚመለከተው አካል ተገቢው ቅድመ ዝግጅትና ጥበቃ እንዲያደርግ ለማስቻል ነው፡፡

ጊዜና ቦታን መቀየር እንጂ መከልከል የማይቻል ስለመሆኑ

ምንም እንኳ ይህ ዓይነቱ ስብሰባ ቅድመ ማሳወቅ እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠበት ቢሆንም የሚመለከተው አስተዳደር አካል ለሕዝብ ጥቅም፣ ለሰላም፣ ሁከትና ግርግር ለማስቀረት በቂ ምክንያት ሲኖር ብቻ የስብሰባውን ጊዜና ቦታ ሊቀየር ከሚችል በቀር በስብሰባው በአጠቃላይ እንዲቀር ለማድረግ በፍፁም አይችልም፡፡

ስብሰባው ለጊዜው እዚህ ቦታ አይደረግም ወይም በዚህ ሰዓት አይደረግም የሚል ከሆነም የመሰብሰብ ጥያቄው በቀረበለት በ12 ሰዓት ውስጥ በጽሑፍ የስብሰባውን ጊዜ ወይም ቦታ የቀየረበትን በቂ ምክንያት በመግለጽ ለአዘጋጆቹ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

የተከለከሉ ቦታዎች

ስብሰባው ቅድመ እውቅናን እንጂ መከልከልን አያስከትልም የቦታና የጊዜ ለውጥ እንጂ ጭራሹኑ ሊቀር አይችልም የተባለ ቢሆንም ከስብሰባው ባህሪ አንፃር ስብሰባው ከሚደረግባቸው ቦታዎች አኳያ ገደቦች በአዋጁ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ይሄውም በሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባ በኤንባሲዎች በአለምአቀፍ ድርጅቶች የሥራ ቦታና መኖሪያ ስፍራ፣ በቤተክርስቲያን፣ በመስጊድ በጸሎት ቤቶች፣ በሆስፒታልና በመካነ መቃብር ዙሪያ ሊደረግ አይችልም፡፡

እንዲሁም በኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ ግድቦች እንዲሁም አደጋ ሊያስከትሉ በሚችሉ ማንኛውም ቦታዎች ሊደረግ አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ስብሰባው የሚደረገው በጦር ሀይሎች በጥበቃና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት በሚቆጣጠሩ የመንግሥት የሥራ ክፍሎች አካባቢ ከሆን ከነዚህ ቦታዎች 500 ሜትር ርቀት ውጭ መደረግ ይገባዋል፡፡

 

የአዘጋጆቹና የመንግሥት ተጠያቂነት

ስብሰባው የሚያደርገው እንዲሁ መብት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ለውጥና ልዩነት ለመፍጠር እንደመሆኑ ስብሰባው ከፍ ሲል የተገለፁትን ገደቦች በማለፍ የጣሰው ሕግ በሕዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳት ካለ አዘጋጆቹ የተቀመጠው ገደብ በማለፍ ለፈፅሟቸው ስህተቶች ተጠያቂ ሲሆኑ የፀጥታ አስከባሪዎችና መንግሥት ደግሞ በጥበቃና ጥንቃቄ ጉድለት በሕዝብ ወይም በግለሰቦች ላይ ጉዳት ቢደርስ በሕግ ተጠያቂዎች ይሆናሉ፡፡

 

የቴዲ አፍሮ የአልበም ምርቃት ጉዳይ

እሑድ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ እንደሚመረቅ ቀን የተቆረጠለት የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አልበም ምርቃት ፕሮግራም፣ ወቅቱን የጠበቀ የዕውቅና ጥያቄ አልቀረበበትም በሚል ምክንያት የምረቃ ስብሰባው ሳይካሔድ መቅረቱ ይታወሳል፡፡

የቴዲ አፍሮ የአልበም ምርቃት ስብሰባ ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ፖለቲካ ነክ ያልሆነ ስብሰባ መሆኑን ነው፡፡ የቴዲ አፍሮ የአልበም ምርቃት ስብሰባ ሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባ ባለመሆኑ ለሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባ የተቀመጡ ልዩ ገደቦች አይመለከቱትም፡፡ ማለትም ከየትኛውም የመንግሥት አካል ዝግጅቱን ለማካሄድ ቅድመ እውቅና ወይም ይሁንታ አያስፈልገውም፡፡ ይሁን እንጂ አዘጋጆቹ ዝግጅቱ በበለጠ ሰላምና እርጋታ እንዲከናወን ለማስቻል በተለይም በሕግ የተጣለባቸውን ሰላማዊ የሌሎችን ሰላምና መብት ያከበረ ስብሰባ ለማድረግ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ትብብር ከሚጠይቁ በቀር ቅድመ እውቅና አስፈላጊ አይደለም፡፡

በተለይም በስብሰባው ሊገኝ ከሚችለው ተሳታፊ ቁጥር ብዛት አንጻር ስብሳበው ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል አዘጋጁ የሚመለከተውን አካል ፈቃድ መጠየቅ ሳይሆን የጥበቃ ትብብር እንዲደረግለት ለመጠየቅ ይችላል፡፡ አስተማማኝ ጥበቃ ባለበት ሁኔታ ዝግጅቱን ማድረግ መንግሥትም ለዜጎች መስጠት ያለበትን ግዴታ እንዲወጣ እንዲሁም አዘጋጆቹም ሀላፊነት የተሞላበት ዝግጅት እንዲያደርጉ ስለሚያግዝ ጥቅሙ አጠያያቂ አይሆንም፡፡

በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥቱን ለማስፈፀም የወጣ ዝርዝር አዋጅ ወይም ደንብ የሌለ በመሆኑ በሕግ ረገድ ያሉ ክፍተቶች እንደተጠበቁ ሆነው ስብሰባዎችን በሕገ መንግሥቱ በተቀመጡ የመሰብሰብ መብት መሠረት ማደረጉ ተገቢ ነው፡፡

የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የተከለከለው በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከሆነ ድርጊቱ የሚጥሳቸው መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችና እና የከልካዩ አካል ተጠያቂነት

የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 25 /እኩልነት/

ከፍ ሲል እንደተገለፀው የቴዲ አፍሮ የአልበም ምርቃት ስብሰባው ቅድመ እውቅና የማያስፈልገው በመሆኑ ፈቃድ የለውም በሚል ምክንያት ተከልክሎ ከሆነ በከተማችን መሰል የአልበም ምርቃቶች ያለምንም እውቅናና ፈቃድ ይደረጉ የነበረ በመሆኑ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለውንና ማንም ሰው በብሄሩ፣ በቀለሙ፣ በእይታው፣ በሀይማኖቱ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጡ ወይም አቋሙ ምክንያት ልዩነት አይደረግበትም የሚለውን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ ሕገ መንግታዊ ጥሰት ይሆናል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 የአመለካከትና የሀሳብ ነፃነት

ማንም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝ መብት ያለው ሲሆን ይህ ነፃነቱን በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በስነ ጥበብ ሥራዎች የመግለጽ የማሰራጨት የመግለፅ መብት አለው፡፡ ይህ የአልበም ምርቃት ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በሀገር፣ በፍቅር በማህበራዊ ህይወቱ የተሰማውን የግል አቋም ያንፀባረቀበት በመሆኑ ይህን ሀሳብ የያዘው ሲዲ ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ መመረቅ የተፈቀደ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም አልበሙ ያነሳቸው ሀሳቦች ብጥብጥ ያስነሳሉ ከተባለ ዝግጅቱ አስቀድሞ ለሕዝብ የተገለፀ በመሆኑ የዝግጅቱን ቀን ጠብቆ ከመከልከል ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ ማድረግ እንጂ መከልከል በሕግ የተፈቀደ አይደለም፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 30 መሣሪያ ሳይዝ ከሌሎች ጋር መሰብሰብ

ይህ የስብሰባ ዓይነት ከፍ ሲል በተገቢው መንገድ ተብራርቷል፡፡ መሰባሰቡ የሌሎች ሰላም ደህንነት መብት እንዳይነካ አዘጋጆቹ ካለባቸው ሀላፊነትና ተጠያቂነት ውጭ በሕግ የተፈቀደ መብት ስለሆነ የሚከለከል እና ቅድመ ፈቃድ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 የኢኮኖሚ መብት

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራት እና የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፡፡ ይህን መብቱ ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ደግሞ በመንግሥት ገንዘብ ከሚካሄድ ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብትም አለው፡፡

በመሆኑ የአልበም ምረቃት ከሙዚቀኛው የሥራ ባሕርይ አኳያ ሥራውን ማስመረቅና ማስታወቅ የሥራው አካል በመሆኑ አስቀድሞ ማሳወቅ በሚል ምክንያት የሚከላከልበት ሕጋዊ ምክንያት የሌለ ሲሆን እንዲያውም ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ እንዲደረግ መንግሥት ድጋፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለበት፡፡ በመሆኑም የጥበቃ አካላት ስብሰባው እንዳይደረግ ከመከልከል በወቅቱ ትክክለኛው ተገቢ ተግባር ለስብሰባው ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡

መደምደሚያ

በአጠቃላይ ከፍ ሲል በተዘረዘሩት ምክንያቶች የአልበም ምርቃቱ በሚመለከተው አካል ክልከላ ምክንያት የተስተጓጎለ ከሆነ መሠረታዊ የሆኑ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የጣሰ በመሆኑ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲሆን ድርጊቱን በፈፀሙ ሰዎች ላይም ሕጋዊ ሀላፊነት የሚያስከትል ሲሆን አለፍ ሲልም ካሳ የሚያስጠይቅ ድርጊት በመሆኑ ተገቢነት ያለው አልነበረም፡፡

በሌላ በኩል በአሁኑ ግዜ በሥራ ላይ ያለው ሕግ ስለ ሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባ ብቻ የወጣ ሌሎች ስብሰባዎችን የማይመለከት በመሆኑ በሕገ መንግሥቱ ማንኛውንም ስብሰባ በተገቢው ሥርዓት ለማከናውን ሥርዓት ደንብ እንዲወጣ ቢያዝም ይህ ባለመደረጉ ከፍተኛ መደናገር እና የመብት ጥሰት እያስከተለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕግ በሕገ መንግሥቱ ለስብሰባ በተሰጠው ትርጉም ልክ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል በዳበረ ሕግ ሊተካ ይገባዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Case Summary and Issue for Reflections - Formality...
የኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነትና በተግባር የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶች - ክፍል ...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 05 October 2024