በዚህ ጽሁፍ መመለስ የምፈልገው ጥያቄ ቀላል ይመስላል፤ እንዴት ያለባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ የተላለፈን ንብረት ማስመለስ፤ የተቋቋመን የመብት ገደብ ማስነሳት ይቻላል የሚለውን ነው፡፡ ቀጥታ ጥያቄውን ወደ መመለሱ ከመሄዴ በፊት፤ ጥያቄው የሚመለከታቸው ሁኔታዎች ምን አይነቶቹን እንደሆነ ግልጽ ላድርግ፡፡

ያለ ሙሉና ነጻ ፈቃድ ሲባል?

እንደሚታወቀው ንብረትን (የማይንቀሳቀስም ይሁን ልዩ ወይም ተራ የማይንቀሳቀስ) ለሌላ ሰው ውልን መሰረት አድርጎ ለማስተላለፍ የባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ባለቤቱ ፈቃዱን ሰጥቷል ነገር ግን ፈቃዱ ሙሉ እና ነጻ አልነበረም የሚባለው የባለቤቱ ፈቃድ በስህተት ወይም በማታለል ወይም በሃይል ተግባር ምክኒያት የተሰጠና በሕጉም መሰረት ውሉ ፈራሽ ውል ሲባል ነው፡፡ ባለቤቱ ፈቃዱን የገለጸው ራሱ ወይም በወኪሉ በኩል ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ የባለቤቱ ፈቃድ ጉድለት አለበት፤ ነገር ግን ንብረቱ ተላልፎ ሊሆን ይችላል ወይም የመብት ገደብ ተቋቁሞ ሊሆን ይችላልና እንዴት ባለቤቱ ንብረቱን ማስመለስ ገደቡን ማስነሳት ይችላል የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ባለቤቱ በምንም አይነት መልኩ ፈቃዱን ሳይገልጽ ከሆነስ?

በሁለተኛ ደረጃ የንብረት ማስመለሱና የመብት ገደቡን የማስመለስ ጥያቄ ሊነሳ የሚችለው ከመጀመሪያውኑ ባለቤቱ በምንም መልኩ ፈቃዱን ያልገለጸ ከሆነ ነው፡፡ ባለቤቱ ፈቃዱን ሳይገልጽ እንዴት ንብረት ይተላለፋል ወይም መብት ይገደባል ለሚል ጥያቄ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሁኔታዎች መልስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

1. አንድ ሰው ህጋዊ ባለቤት ሳይሆን ባለቤት እንደሆነ በማስመሰል ከሌላ ሰው ጋር በመዋዋል ንብረቱን ሊያስተላልፍ ወይም የመብት ገደብ ሊያቋቁም ይችላል፡፡ ንብረቱ ተራ የሚንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ ይህን ለማድረግ ቀላል ነው፡፡ ንበረቱ የማይንቀሳቀስ ወይም ልዩ ተንቀሳቃሽ ቢሆንም ይህን ለማደድረግ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ሰነዶችን ፎርጅድ ማድረግ ሊጠይቅ ወይም የሌላ አካል ትብብርን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ እነዚህ ሰነዶች ይህ ሰው ባለቤት መሆኑን የሚያሳዩ ወይም ንብረቱን አስመልክቶ በባለቤቱ ስም ውል የመዋዋል ስልጣን አንዳለው የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

2. ንብረቱን ያስተላለፈው ወይም የመብት ገደቡን ያቋቋመው ሰው የባለቤቱ ወኪል/እንደራሴ ሆኖ ነገር ግን ንብረቱን ለማስተላለፍ ወይም የመብት ገደቡን ለማቋቋም ስልጣን የሌለው ከሆነ ወይም ወኪል እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ቢኖርም እንኳ ይህ የእንደራሴነቱ ስልጣን ፈራሽ ወይም ዋጋ አልባ ከሆነ ወይም ምንም እንኳ በአንድ ወቅት ስልጣን ቢኖረውም እንኳ ይህ ስልጣኑ በኋላ በባለቤቱ የተነሳ ወይም የተገደበ ወይም ጊዜው ያለፈበት ከሆነ፡፡

ከባለቤቱና ንብረቱ ከተላለፈለት ሰው ወይም መብቱ ከተገደበለት ሰው ውጭ ሌላ ሰው ሊኖርም ላይኖርም ይችላል?

ከላይ በተገለጹት ሁለት ሁኔታዎች ያለባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ ንብረት ሊተላለፍ ወይም መብት ሊገደብ እንደሚችል አይተናል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ከባለቤቱን ንብረቱ ከተላለፈለት ሰው ወይም መብቱ ከተገደበለት ሰው ውጭ ሌላ ሰው ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ጉዳዩ የማይንቀሳቀስ ንብረትን ወይም ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረትን የሚመለከት ከሆነ፤ ከባለቤቱን ንብረቱ ከተላለፈለት ወይም መብቱ ከተገደበለት ሰው ውጭ ቢያንስ እነዚህን ንብረቶችን አስመልክቶ የሚፈጸሙ ውሎችን የሚመዘግቡ፤ ወይም እነዚህን ንብረቶች አስመልከቶ የባለቤትነት ማስረጃን የሚሰጡ፤ የመብት ገደብን የሚመዘግቡ፤ ማስረጃዎችን የሚያረገግጡ መንግስታዊ ድርጀቶችንም ይመለከታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ንብረቱ የተላለፈው ወይም መብቱ የተገደበው ከባለቤቱ ፈቃድ ወይም እውቅና ውጭ ከሆነ ተራ ተንቀሳቃሽ ንብረት ከሆን ይህን ንብረት በስርቆት ወይም በአደራ ወይም በሌላ መልኩ ይዞታው ውስጥ በማስገባት ያስላለፈ ሰውን ይጨምራል፡፡ ጉዳዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከት ከሆነ ራሱን የንብረቱ ባለቤት በማስመሰል (በፎርጅድ ሰነድ) ወይም ራሱ ንብረቱን ለማስተላለፍ ወይም መብቱን ለማስገደብ ስልጣን እንዳለው የሚያስብ ወይም የሚያስመስል ሰውን ይጨምራል፡፡

ከባለቤቱ ውጭ ያሉ ወገኖች (ንብረቱ የተላለፈለትን ወይም መብቱ የተገደበለትን ጨምሮ) እና የእውቀት ደረጃቸው

ከባለቤቱ ውጭ ያሉ ወገኖች እላይ የተገለጹት እና ንብረቱ የተላለፈለት ወይም መብቱ የተገደበለት ሰውን ጨምሮ፤ ጥያቄ የተነሳበትን ግብይት በቅን ልቦና ወይም ያለቅን ልቦና ያደረጉት ሊሆን ይችላል፡፡

1. ለምሳሌ በመጀመሪያ ግብይቱን ለማከናወን ሙሉ ስልጣን ኖሮት ነገር ግን ስልጣኑ በጊዜ ማለፍ ምክንያት ወይም ባለቤቱ ስላነሳው ወይም ስለገደበው፤ ግብይቱን ሲያከናውን ስልጣን የለለው ሆኖ ነገር ግን ስልጣን እንደሌለው ወይም ስልጣኑ እንደተገደበ ወይም እንደተነሳ የማያውቅና ማወቅ የማይጠበቅበት ሰው በቅል ልቦና ነው ውሉን የፈጸመው ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ሰው ውሉን የፈጸመው እያወቀ ወይም ማወቅ እየተጠበቀበት ሊሆን ይችላል፡፡

2. ሰውየው የባለቤቱ እንደራሴ ሆኖ ነገር ግን እንዲህ አይነት ውሎችን የመዋዋል ስልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህ ሰውዬ ግን ስልጣኑ እንዲህ አይነት ውሎችን ይጨምር አይጨምር የሚያውቅ ወይም ማወቅ የሚጠበቅበት ወይም የማያውቅ እና ማወቅ የማይጠበቅበት ሊሆን ይችላል፡፡

3. ውልን እንዲመዘግቡ ወይም ንብረትን እንዲመዘግቡ፤ የባለቤትነት ማስረጃን እንዲሰጡ ወይም ማስረጃን እንዲያረጋግጡ የተቋቋሙ መንግስታዊ ተቋማት በቅን ልቦና ወይም ያለቅን ልቦና የቀረቡትን ማስረጃዎች ሊያረጋግጡ ወይም ውልን ሊመዘግቡ ይችላሉ፡፡

4. እንዲሁም ንብረቱ የተላለፈለት ወይም መብቱ የተገደበለት ሰው፤ ንብረቱን ያስተላለፈለት ሰው ባለቤት ስላመሆኑ ወይም ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ የማያውቅና ማወቅ የማይጠበቅበት ወይም የሚያውቅ ወይም ማወቅ የሚጠበቅበት ሊሆን ይችላል፡፡

ጥያቄው ዘርዘር ሲደረግ

አሁን ታዲያ ጥያቄው በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ባለቤቱ ንብረቱን ለማስመለስ ወይም የተቋቋመውን የመብት ገደብ ማስነሳት ቢፈልግ በምን አይነት ሁኔታዎች እና ገደቦች ይቻለዋል የሚል ነው፡፡ ጥያቄው እነዚህን አስመልክቶ ያለው አግባብነት ያላቸው የ ኢትዮጵያ ሕጎች የትኞቹ ናቸው፤ ይዘታቸውስ ምንድን ነው? እንዲሁም በየትኞቹ ሁኔታዎች ነው ንብረቱን ለማስመለስ ወይም የመብት ገደቡን ለማስነሳት ለንበረቱ መተላለፍ ወይም በመብቱ መገደብ ምክኒያት/መሰረት የሆነውን ውል ማፍረስ የሚቻለው ወይም የሚገባው እና የማይቻለውና የማይገባው? ንብረትን ለማስመለስ ወይም የመብት ገደብን ለማስነሳት የሚቀርብ ክስን አስመልከቶ አግባብነት ያለው የይርጋ ዘመን የትኛው ነው? ንብረትን ለማስመለስ ወይም የመብት ገደብን ለማስነሳት የሚቀርብ ክስን አስመልከቶ ገዢው ሕግ የውል ሕግ ነው ወይስ የንብረት ሕግ ወይስ የውክልና ሕግ ወይስ አላግባብ የመበልጸግ ሕግ?

ጥያቄውን ያስነሳው የሰበር ውሳኔ

ይህን ቀላል የሚመስል ነገር ግን ብዙ አይነት ሴናሪዎችን ሊመለከት እና መልሱም እንደነገሩ ሁኔታ ሊለያይ የሚችልን ጥያቄ እንድናነሳና እንድንፈትሽ ያስገደደን በሰ/መ/ቁ.48094 በግንቦት 10 ቀን 2002 ዓ.ም በእነ ሙና እንድሪስ እና በ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጉዳይ የተላለፈው የሰበር ውሳኔ ስለሆነ ይህን ውሳኔ ከዚህ በታች ሙሉ ለሙሉ አስቀምጠነዋል፡፡

ይህ ጉዳይ የተጀመረዉ በፊዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት ሲሆን አመልካቾች በተጠሪና በሥር አንደኛ ተከሳሽ ላይ ባቀረቡት ክስ በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 6 ቀበሌ 13 ክልል ቁጥር 563 የሆነዉ ቤት ለከሳሾችና ለአንደኛ ተከሳሽ ከወላጆቻችን በዉርስ የተላለፈልን ንብረት ሲሆን አቶ ጅላል አብዱልመናን የተባሉ ግለሰብ ከሁለተኛ ተከሳሽ ገንዘብ ሲበደሩ አንደኛ ተከሳሽ አካለመጠን ባላደረሱት ወራሾች ላይ የተሰጠዉን የሞግዚትነት ሥልጣን መሠረት አድርጎ የጋራ የዉርስ ንብረት የሆነዉን ቤት በመያዣነት ሰጥቷል፡፡ በአንደኛ ተከሳሽ የተፈጸመዉ ተግባር ከፍ/ብ/ሕ/ቁ/300 እና 1266 አኳያ ሕገ-ወጥ ስለሆነ ሐምሌ 7 ቀን 1987 ዓ.ም እና ጥቅምት 16 ቀን 1987 ዓ.ም የፈረመዉ የመያዣ ዉል ፈራሽ ነዉ ተብሎ እንዲወሰንና  የቤቱንም   ካርታ   ሁለተኛ  ተከሳሽ   እንዲመልስ  ይወስንልን  በማለት ጠይቀዋል፡፡

የከሳሾች ክስና ማስረጃ ለተከሳሾች ደርሶ መልስ እንዲሰጡ ታዞ አንደኛ ተከሳሽ ተጠርቶ ባለመቅረቡ ጉዳዪ በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ (የአሁን ተጠሪ) ቀርቦ ለክሱ ምክንያት የሆነዉን ቤት በመያዣነት መያዙን አምኖ ይህንን ለማድረግ የቻለዉ አንደኛ ተከሳሽ በቤተዘመድ ጉባዬ ዓማካይነት በ24/1/87 ዓ.ም የሞግዚትነት ሥልጣን ተሰጥቶት ፍ/ቤትም ቀርቦ በመጽደቁ ምክንያት እንደሆነና የተሰጠዉም የሞግዚትነት ሥልጣን ሞግዚት በሆነላቸዉ ሰዎች ስም የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ  ንብረት  በዋስትና  ለመስጠት  እንደሚችል  በሰነዱ  ላይ  ስለተመለከተ በመሆኑ ለአንደኛ ተከሳሽ በተሰጠዉ የሞግዚትነት ሥልጣን ላይ ተመስርቶ የመያዣ ዉል መፈራረሙ  በአግባቡ  ስለሆነ  የመያዣ  ዉሉ  የሚፈርስበት  ምክኒያት  የለም  በማለት ተከላክሏል፡፡

የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤትም የመያዣ ዉሉ ሊፈርስ ይገባል ወይንስ አይገባም የሚለዉን ጭብጥ መስርቶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የቤተዘመድ ጉባኤ አንደኛ ተከሳሽን ሞግዚት አድርጎ የሾመዉ በ18/10/81 ዓ.ም ሲሆን ጥቅምት 11 ቀን 1987 ዓ.ም የሚግዚትነት ሥልጣኑ  ፍ/ቤት  ቀርቦ  ጸድቋል፡፡  በሞግዚትነት  ማጽደቅ  ዉሳኔዉም  ላይ  ከከሳሾች መካከል  አንደኛ  እና  ሁለተኛ  ከሳሾች  ከሞግዚት  አስተዳደር ነጻ የወጡ  መሆኑ ተመልክቷል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ሞግዚት በሆነላቸዉ ስም የተመዘገበ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት በመያዣ ወይም ዋስትና ለመስጠት የተፈቀደለት ቢሆንም የመያዣ ዉሉን በተፈራረሙ ጊዜ አንደኛ እና ሁለተኛ ከሳሾች ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥተዉ የነበረ  ስለሆነ  ያለእነሱ  ስምምነት  የመያዣ  ዉሉን  መፈራረሙ  የፍ/ቤ/ሕ/ቁ  1266ን የሚጻረር ነዉ፡፡

በመሆኑም በወረዳ 6 ክልል የቤ.ቁ 563 ተመዝግቦ የሚገኘዉ የከሳሾችና የአንደኛ ተከሳሽ የጋራ የዉርስ ሀብት ሆኖ እያለ አንደኛ እና ሁለተኛ ከሳሾች ስምምነታቸዉን ሳይሰጡ በአንደኛ ተከሳሽ በኩል ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር የመያዣ ዉል የተፈጸመዉ የሕጉን ድንጋጌ ባልተከተለ ሁኔታ ስለሆነ ጥቅምት 1987 ዓ.ም እና ሐምሌ 1987 ዓ.ም የተደረገ የመያዣ ዉል ፈራሽ ነዉ በማለት ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡

የሥር ሁለተኛ ተከሳሽ የአሁን አመልካች በዉሳኔዉ ቅሬታ አድሮበት የይግባኝ ቅሬታዉን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቦ ፍ/ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙን አከራክሮ አንድ ዉል እንዲፈርስ ተዋዋይ ወገን ያልሆኑ ሦስተኛ ወገኖች ማቅረብ የሚችሉት በፍ/ብ/ሕ/ቁ/ 1808(2)  እና  ተከታዮቹ  ድንጋጌዎች  መሠረት  ነዉ፡፡  ዉል  የማይረጋበት  ምክንያት ከቀረበት ጊዜ አንስቶ ከ2 ዓመት በኋላ የዉል ይሰረዝልኝ ክስ ሊቀርብ እንደማይችል ጉዳቱ የደረሰበት ሰዉ አካለመጠን የደረሰ ሰዉ ከሆነ ክሱን ማቅረብ የሚገባዉ ሙሉ በተደረገ በ2 ዓመት ጊዜ ዉስጥ እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810(1) ላይ ተደንግጓል፡፡ በተያዘዉ ጉዳይ ከተራ ቁጥር 1-3 የተጠቀሱት መ/ሰጭዎች ዉሉ ሲደረግ ለአቅመ አዳም የደረሱ መሆናቸዉ ከ4ኛ-7ኛ የተጠቀሱትም መ/ሰጭዎች ከ1995  ዓ.ም ጀምሮ ለአካለመጠን የደረሱ መሆናቸዉ በመ/ሰጭዎች ያልተካደ በመሆኑ የዉል ይሰረዝልኝ ክሱ 2 ዓመት ያለፈዉ መሆኑን ፍ/ቤቱ ተገንዝቧል፡፡ ስለሆነም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810(1) መሠረት የዉሉ ይሰረዝልኝ ክሱ በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት ዉሳኔ ሠጥቷል፡፡

የሥር ከሳሾች /የአሁን አመልካቾች/ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዉሳኔ ቅሬታ አድሮባቸዉ የይግባኝ ቅሬታቸዉን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረቡ ቢሆንም በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 337 መሠረት ፍ/ቤቱ ይግባኙን ሳይቀበለዉ ቀርቷል፡፡ የሰበር አቤቱታዉ የቀረበዉ ይህንኑ በመቃወም ሲሆን አቤቱታዉ ተመርምሮ የአመልካች የዉል ይፍረስልኝ ክስ በ2 ዓመት ይርጋ ቀሪ ሆኗል ተብሎ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት መወሰኑ ለሰበር ቀርቦ መጣራት የሚገባዉ ሆኖ በመገኘቱ ይህ ችሎት አቤቱታዉ ለሰበር እንዲቀርብ አድርጎ ተጠሪን በመጥራት ግራ ቀኙን አከራክሯል፡፡

በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን በበኩላቸወን አቤቱታዉ ለሰበር ያስቀርባል ከተባለበት ነጥብ አኳያ እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡

አንድ  ዉል  በሚመሰረትበት  ጊዜ  የችሎታ  ወይንም  የፈቃድ  ጉድለት  ያለበት  ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ችሎታ አልነበረኝም ወይንም ፈቃዴን በአግባቡ አልሰጠሁም በሚለዉ ተዋዋይ ወገን ጠያቂነት ዉሉ ሊፈርስ እንደሚችል እንደዚሁም ዉሉ የተደረገበት ጉዳይ ለሕግ  ወይንም  ለሞራ  ተቃራኒ  ሆኖ  በሚገኝበት  ጊዜና  የዉሉ  አጻጻፍ  ሥርዓትም ባልተጠበቀ ወቅት ከተዋዋዮች ወገኖች መካከል ወይንም በዉሉ ጥቅም አለኝ በሚል 3ኛ ወገን ዓማካይነት የዉል ይፍረስልኝ ጥያቄ ሲቀርብ ዉሉ ሊፈርስ እንደሚችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1808(1) እና (2) ላይ ተመልክቷል፡፡

የዉል ይፍረስልኝ ክስ ማቅረቢያ ጊዜዉን በተመከተም ዉሉ የማይረጋበት ምክኒያት ከቀረበት  ጊዜ  አንስቶ  በ2  ዓመት  ዉስጥ  ካልቀረበ  በይርጋ  ሊታገድ  እንደሚችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ/1810 ላይ ተመልክቷል፡፡ በተያዘዉ ጉዳይ በፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት ዉሉ ሊፈርስ ይገባል ተብሎ ዉሳኔ የተሰጠዉ የጋራ ባለንብረቶች የሆኑት አንደኛ እና ሁለተኛ ተጠሪዎች ፈቃዳቸዉን አልሰጡም በሚል ምክንያት ነዉ፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 ላይ የተመለከተዉ የ2 ዓመት ይርጋ ጊዜ ተፈጻሚነቱ ዉሉ የማይረጋበት ምክንያት ቀሪ በሚሆንበት ጊዜ ሲሆን ይህም የሚመለከተዉ ከአንደኛዉ ተዋዋይ ወገን ችሎታ ወይንም ፈቃድ ጉድለት ጋር የተያያዘ በሚሆንበት ጊዜ ነዉ፡፡ ዉሉ ከችሎታ ወይንም ከፈቃድ ጋር በተያያዘ ጉድለት አለበት በሚባልበት ጊዜ ይህንኑ መሠረት አድርጎ ክስ የሚያቀርበዉ ወገን በ2 ዓመት ክሱን ካላቀረበ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 መሠረት በይርጋ ቀሪ እንደሚሆን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ነገር  ግን  በተያዘዉ  ጉዳይ  ዉሉ  እንዲፈርስላቸዉ  የጠየቁት  አንደኛ  እና  ሁለተኛ አመልካቾች ለዉሉ መፍረስ በምክንያትነት የጠቀሱት የጋራ የሆነዉን የዉርስ ሀብት ለመሸጥም  ሆነ  በመያዣ  ለመስጠት  በፍ/ብ/ሕ/ቁ  1266  መሠረት  የጋራ  ባለሀብቶች ስምምነት አስፈላጊ ሆኖ ሳለ የሥር አንደኛ ተከሳሽ ያለ እኛ ስምምነት የጋራ የዉርስ ሀብት የሆነዉን ቤት ለሁለተኛ ተከሳሽ (ለአሁን ተጠሪ) በመያዣነት የሰጠ ስለሆነ ዉሉ ሊፈርስ ይገባል   በማለት  ነዉ፡፡  አንደኛ  እና  ሁለተኛ   አመልካቾች    ተዋዋይ   ወገን   ካልሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1808(1) መሠረት ዉሉ የችሎታ ወይንም የፈቃድ ጉድለት ያለበት ስለሆነ ሊፈርስ    ይገባል   በማለት    ሊጠይቁ  የማይችሉ  በመሆኑ   በፍ/ብ/ሕ/ቁ  1810   ላይ የተመለከተዉ የ2 ዓመት ይርጋ ጊዜ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት አይኖረዉም፡፡

በሌላ በኩልም በተሻሻለዉ የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 310 ላይ የተቀመጠዉን የይርጋ ጊዜ በተመለከተም አካለመጠን ያላደረሰ ልጅ በሞግዚቱ ላይ የሚያቀርበዉ ክስ አስመልከቶ ተፈጻሚ  የሚሆን  ሲሆን  በዚህ  ጉዳይ  ግን  ዉሉ  ፈራሽ  ነዉ  የተባለዉ  ከፍ  ብሎ እንደተጠቀሰዉ  ከሞግዚት አስተዳደር  ነጻ  ወጥተዋል  በተባሉት  አንደኛ  እና  ሁለተኛ አመልካቾችን አስመልክቶ ስለሆነ ድንጋጌዉ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለዉ አይደለም፡፡

እንግዲህ ተጠሪ ያነሳዉ የይርጋ ክርክር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 እና የቤተሰብ ሕጉ የሚሸፈን ባይሆንም የጋራ የሆነን ንብረት ለማስተላለፍ ወይንም በዋስትና ለመስጠት የሁሉንም የጋራ ባለንብረቶች ስምምነት ማግኘት እንዳለበት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1266 ላይ የተመለከተ ሲሆን ነገር ግን የጋራ ባለንብረት ከሆኑት መካከል አንደኛ እና ሁለተኛ ተጠሪዎች በመያዣ ዉሉ   ስምምነታቸዉን  ያልሰጡ  ስለሆነ  ይህም    ዉሉ   ሕግን   የሚጻረር   መሆኑን የሚያመለክት ነዉ፡፡ አንድ ዉል ሕግን የሚቃረን ነዉ በሚባልበት ጊዜ እንዲፈርስ ጥያቄ መቅረብ  ያለበት  በ10  ዓመት  ጊዜ  እንደሆነ  ከፍ/ብ/ሕ/ቁ  1845  መረዳት  ይቻላል፡፡

አመልካቾች ክሱን ቀረቡት ደግሞ በሕጉ ላይ የተቀመጠዉ የ10 ዓመት ጊዜ ከማለፉ በፊት ስለሆነ አቤቱታቸዉ በይርጋ የተጋደ አይደለም፡፡

ሲጠቃለልም የፌዴራል  ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመልካቾች ክስ በ2 (ሁለት) ዓመት ይርጋ ቀሪ ሆኗል ያለው ለጉዳዩ አግባብነት በሌለው ድንጋጌ ተመስርቶ በመሆኑ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝነዋል፡፡

እነ ሙና እንድሪስ እና ኢትዮጵያ ልማት ባንክ፡ የመጀመሪያ ደረጃ ግምገማ

የፍርድ ቤት ውሳኔ በሁለት ወገኖች መካከል ያለን ሙግት ማን እንዳሸነፈ ለማወጅ ብቻ ተብሎ የሚጻፍ አይደለም፡፡ እንደዛማ ቢሆን ኖሮ ሳንቲም ወደ ሰማይ ወርውረን ጎፈር ከሆነ ከሳሽ ዘውድ ከሆነ ደግሞ ተከሳሽ አሸንፏል በማለት መወሰን ይችል ነበር፡፡ ይህ ያልሆነበት በብዙ ምክኒያቶች ነው፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ ስለማይያያዝ በዚህ ጽሁፍ እነዚህን ምክንያቶች መዘርዘሩ አያስፈልግም፡፡ ቁም ነገሩ የፍርድ ቤት ውሳኔ ከሁለቱ ወገኖች መካከል ማን ምን እንዳገኘ/እንዳሸነፈ ከማስታወቅም በላይ ነው፡፡ በውሳኔው ፍርድ ቤቱ ተሸናፊውን ወገን በማሳመን የውሳኔውን ፍትሃዊነት እና ትክክለኛነት እንዲሁም የሕግ መሰረት የሚያስረዳበት ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ለተመልካችም ቢሆን የውሳኔውን ትክክለኛነት ምክንያቱን በማብራራት የሚያስረዳበትና ውሳኔው አግባብነት ባላቸው ሕጎችና በጉዳዮ ፍሬ ነገሮች የተደገፈ መሆኑን የሚያስረዳበት ነው፡፡ ከዘህ አንጻር የፍርድ ቤት ውሳኔ እንደ ትእዛዝ ሳይሆን መጻፍ ያለበት፤ አንባቢን ወይም ተመልካችን ለማሳመን ተብሎ ነው መጻፍ ያለበት፡፡ ውሳኔው የሰበር ሰሚ ውሳኔ ከሆነ ደግሞ ይህ አባባል የበለጠ ተቀባይነት ያገኛል፡፡

በእርግጥ የሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸው የሕግ ትርጎሞች በማንኛውም የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅ እንደሆነ የሚደነግግ አዋጅ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ድንጋጌ ብቻውን የሰበር ሰሚው የሚሰጣቸው የሕግ ትርጉሞች አስገዳጅ እንዲሆኑ አያስችልም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የአዋጅ ድንጋጌ የሚያስነሳው ጥያቄ፤ እንዴት ማስፈጸም ይቻላል የሚል ነው? አንድ ዳኛ ወይም ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠውን የሕግ ትርጉም ወደ ጎን በማለት ሌላ ትርጉም ቢሰጥ ይህ ቅጣትም ሆነ ሽልማትን ያልያዘን የአዋጅ ድንጋጌ እንዴት ነው ማስፈጸም የሚቻለው? በእርግጥ ዳኞችን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመሾም በሚደረገው ግምገማ፤ አንድ ዳኛ ምን ያህን የሰበር ውሳኔን ያከብራል የሚለው አንድ የግምገማ ነጥብ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህን የአዋጁ ማስፈጸሚያ መንገድ አድርጎ መውሰድ ያስቸግራል፡፡ ሁለተኛው የማስፈጸሚያ መንገድ ፍርድ ቤቱ ወይም ዳኛው ከዚህ በፊት በሰበር የተሰጠውን የሕግ ትርጉም ባለመከሉ የተነሳ ጥቅሙ የተነሳበት ወገን በሚያቀርበው ይግባኝ ወይም የሰበር አቤቱታ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ከሆነ ከዚህ በፊት ተቃራኒ ትርጉም የሰጠው ሰበር ችሎች ወይም ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ የበታች ፍርድ ቤት የሰጠውን የሕግ ትርጉም ውድቅ በማድረግ የቀደመውን የሕግ ትርጉም ሊከተለው ይችላል፡፡ ጥያቄው ታዲያ፤ ይህ የአዋጅ ድንጋጌ ባይኖም እንኳ በይግባኝ ወይም በሰበር አቤቱታ ይህ ሊስተካከል ከቻለ አዋጁ በግልጽ የሰበር የሕግ ትርጉሞች አስገዳጅ ናቸው ማለቱ የሚጨምረው አዲስ ነገር ምንድን ነው?

እንደ እኔ እምነት ሰበር ችሎቹ የሚሰጣቸው የሕግ ትርጉሞች ከሰበር በታች በሃገሪቱ ባሉ ችሎቶች ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የአዋጅ ድንጋጌ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ እንደውም የአዋጅ ድንጋጌም ላይስፈልግ ይችላል፡፡ የቀደምን የፍርድ ውሳኔን እንደ ሕግ ቆጥረው በሚከተሉ አገሮች ይህን እንዲያደደርጉ የሚያስገድድ የተጻፈ ድንጋጌ የለም፡፡ ሰበር ችሎቱ የሚሰጣቸው የሕግ ትርጎሞች አስገዳጅነታቸው የሚመነጨው መመንጨትም ያለበት ከውጭ (ከአዋጅ ድንጋጌ) ሳይሆን ከውስጥ ነው፡፡ ማለትም ከራሳቸው የሕግ ትርጉሞች ወይም የሰበር ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ውጫዊ ፋክተሮች አጋዥ ናቸው፡፡

የሰበር ሰሚ የሕግ ትርጉሞች አስገዳጅነታቸው የሚመነጨው ከራሳቸው ከውሳኔዎቹ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? እንደ እኔ እምነት ብዙ ነገር ለማለት ነው፡፡ አንደኛ ሰበር ችሎቱ ውሳኔውን ሲጽፍ እንዴት ነው የሚጽፈው የሚለው ይወስነዋል፡፡ ከሁለቱ ወገኖች ማን እንዳሸነፈ ለመናገር ብቻ ነው? ወይስ ሌሎች ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ የሕግ ትርጉም እንዲከተሉ ለማዘዝ ነው? ወይስ ሌሎች ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ የሕግ ትርጉም እንዲከተሉ ለማሳመን ነው? መልሱ አንድ እና ሁለት ከሆነ ከሰበር ውሳኔው የሚጠበቀው ይዘት ውስን ነው፡፡ ማን እንዳሸነፈ በግልጽ ካሳወቀና፤ ሌሎች ፍርድ ቤቶች እንዲከተሉ ማዘዝ የፈለገውን በግልጽ ካስቀመጠ በቂ ነው፡፡ ምክንያት ማቅረብም፤ ሆነ ለማሳመን ብዙ መጣር የለበትም፡፡ ነገር ግን አላማው ሌሎች ፍርድ ቤቶችን እንዲሁም የሕግ ባለሙያዎችን እና ዜጎችን ማሳመን ከሆነ ከሰበር ውሳኔው የሚጠበቀው ይዘትና የጥራት ደረጃም ከፍ ይላል፡፡

1.   የጉዳዩን ጭብጥ በግልጽና በትክክል ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

2. የጉዳዮን ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች በትክክልና በሙሉነት ማስቀመጥ አለበት፡፡ ከሰበር ችሎቱና ከተሟጋች ወገኖች ውጭ ያሉ አካላት የጉዳዩን ሙሉ መዝገብ የማየት እድል የላቸውም፡፡ ታትሞ የሚወጣው ውሳኔው እንጂ ሙሉ መዝገቡ አይደለም፡፡ በመሆኑም በውሳኔው ላይ ፍሬ ነገሮቹ በትክክልና በሙሉነት መመዝገብ አለባቸው፡፡

3. በተመሳሳይ ምክንያት የጉዳዩ አመጣጥ በግልጽ መቀመጥ አለበት፡፡ ጉዳዩ የት ተጀመረ፡፡ ምን አይነት መከራከሪያ ሃሳቦች ቀረቡ፡፡ ምን አይነት ውሳኔ በታች ባሉ ፍርድ ቤቶች ተሰጠ፡፡ ማን ይግባኝ አለ፡፡ ይግባኝ ለማለት የቀረበው ምክንያት ምን ነበር፡፡ በይግባኙ ላይ የተያዘው ጭብጥ ምን ነበር፡፡ ምን አይነት መከራከሪያዎች ቀረቡ፡፡ ምን አይነት ውሳኔ ተሰጠ፡፡

4. አሁንም በተመሳሳይ ምክንያት የሰበር አቤቱታውን ማን አቀረበ፡፡ በአቤቱታው ላይ የቀረቡት ምክንያቶች ምን ነበሩ፡፡ ለምን የሰበር አቤቱታው ተቀባይነት አገኘ፡፡

5. በሰበር ሂደቱ የተያዙት ጭብጦች ምንድን ናቸው፡፡ የቀረቡትን መከራከሪያዎች ምንድን ናቸው፡፡ እነዚህ መከራከሪያዎች በታማኝነት በትክክልና ሙሉ ለሙሉ ሊመዘገቡ ይገባል፡፡ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ እና የሚያቀርባቸው ምክኒያችና አሳማኝነታቸው በከፊል የሚገመገመው ተሟጋች ወገኖች ካቀረቧቸው መከራከሪያዎች አንጸር ነው፡፡

6. የሰበር ውሳኔው ችሎቱ የተለያዩ የታች ፍርድ ቤቶች ከሰጧቸው የሕግ ትርጎሞች የተለየ ከተጠቀመ ለምን የታች ፍርድ ቤቶች የሰጧቸው የሕግ ትርጉሞች ትክክል እንዳልሆኑ ማሳየት አለበት፡፡ እንዲሁም ሰበር ችሎቱ በተሟጋች ወገኖች የቀረቡትን መከራከሪያዎች እያንዳንዳቸውን ለምን እንደተቀበላቸውና እንዳልተቀበላቸው በሚገባ ማስረዳት አለበት፡፡

7. የሰበር ችሎቱ የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ የሚቀይር ከሆነ፤ የተለየ ትርጉም የሚሰጥ ከሆነ ለምን የተለየ ትርጉም መስጠት እንዳስፈለገ ማስረዳት አለበት፡፡ እንደሚታወቀው የሰበር አቤቱታ ተጨማሪ የይግባኝ መብት ወይም አማራጭ አይደለም፡፡ የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ማስተካከያ አማራጭ ነው፡፡ የሕግ ስህተት ሳይሆን መሰረታዊ የሕግ ስህተት ማሰተካከያ ነው፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች የሰጧቸው የሕግ ትርጉሞች ስህተት መሆናቸውን ማሳየት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ መሰረታዊ መሆናቸውንም ማስረገጥ አለበት፡፡

8. በአዋጁ መሰረት አስገዳጅ የሆነው የሰበር ትእዛዙ ሳይሆን የሰበር ችሎቱ የሰጠው የሕግ ትርጉም ነው፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የተረጎመውን እና አስገዳጅ እንዲሆን ያሰበውን አንድ ወይም ከዛ በላይ የሕግ ትርጉም ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ አለበት፡፡

9. ከጉዳዩ ጋር የሚገኛኙ ከዚህ በፊት ውሳኔ የተሰጣቸው የሰበር ውሳኔዎች ካሉ እነሱን በውሳኔው ጠቅሶ ከጉዳዩ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰሉና እንደሚለያዩ፤ ያሁኑ የሕግ ትርጉም ከዚህ በፊት ከተሰጡት እንዴት እንደሚሄዱ ማስረዳት አለበት፡፡

10. የውሳኔው የተለያዩ ክፍሎች እርስ በርሳቸው የማይጋጩ፤ በግልጽ ቋንቋ የተጻፉ መሆን አለባቸው፡፡

11. ሰበር ሰሚው በውሳኔው የሚጠቀምባቸውን ሕጎችና ይዘታቸውን እንዲሁም ትርጉማቸውን በሚገባና በትክክል ማስቀመጥ አለበት፡፡ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አርማለው በሚል እጅግ ቀላልና ግልጽ ስህተት ሕግን በመለየትና በመተርጎም የሚሰራ ከሆነ ታማኝነቱን ይሸረሽረዋል፡፡

12. ሰበር ሰሚው በውሳኔው ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት መሰራቱን ለማስረዳት ወይም አንድ ሕግ እንዴት መተርጎም እንዳበት ለማሳየት የተለያዩ አማራጭ ትርጉሞች የሚኖራቸውን የወደፊት አንድምታና መዘዝ፤ እንዲሁም የተከተለው ትርጉም ከሕጉ አላማ ጋር አብሮ የሚሄድ ስለመሆኑ ማስረዳት አለበት፡፡ ሕግን ለመተርጎም የቋንቋን እና የሎጂክ መመሪያዎችን ብቻ የሚከተል ከሆነ ሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዴት ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተለየ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

13. ሰበር ችሎቱ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን በሚገባ ሲወጣ የሚያስተላልፈው መልእክት ውሳኔዬን በሚገባ አይቼ፤ በጣሙን አምኜበት፤ ብዙ ነገሮችን መዝኜ፤ ነው የሚል ነው፡፡ ማለትም ጉዳዩን በሚገባ ከመርመሬ የተነሳ፤ ተመሳሳይ ጉዳይ ወደፊት ቢመጣልኝም እንኳ ተመሳሳይ ውሳኔ እና ትርጉም እከተላለው የሚል መልእክት ነው እያስተላለፈ ያለው፡፡ እነዚህን ነገሮች በሚገባ ካልተወጣ ግን የሚያስተላልፈው መልእክት ተመሳሳይ ጉዳይ ወደ ፊት ቢመጣም በተመሳሳይ መንገድ ላላየው እችላለው የሚል ነው፡፡ ታዲያ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ እንዴት ይቀበለዋል፡፡

ከላይ በግልጽ ለማስቀመጥ እነዚህ ጉዳዮች የአንድ ሰበር ሰሚ ውሳኔ እኔ በውሳኔው የተካተተው የሕግ ትርጉም የሚኖረውን የአስገዳጅነት ደረጃ የሚወስኑ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያሉ ውጫዊና አጠቃላይ የሕግ አመለካከቶች የሕግ ትርጉሙን አስገዳጅነት ሊያጠናክሩት ወይም ሊሽሩት ይችላል፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንጸር ሰበር ሰሚ ችሎቱ በእነ ሙና እንድሪስ እና የ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ መዝገብ የሰጠው ውሳኔ የሚከተሉት ቅርጻዊ ጉድለቶች ታይተውበታል፡፡

1.       የሰበር አመልካቾች ብዙ ለመሆናቸው እነ ሙና እንድሪስ የሚለው አነጋገር ቢያመለክትም ስንት ስለመሆናቸው የውሳኔ መስመር ቁጥር 43 እና 44 እስኪደረስ ድረስ ግልጽ አይደለም፡፡

2.      የቀን አጻጻፍ ዘይቤው ለምሳሌ በውሳኔ መስመር ቁጥር 23 ላይ ብቻ እንኳን ወጥነት ይጎድለዋል፡፡

3.     መስመር 36 ላይ የስር ሁለተኛ ተከሳሽ የአሁን አመልካች ይላል፡፡ ነገር ግን የስር ሁለተኛ ተከሳሽ የአሁን መልስ ሰጪ እንጂ አመልካች አይደለም፡፡

4.     ለምን ሰበር ችሎቹ የሰበር አቤቱታውን ለመቀበል እንደወሰነ ግልጽ አላደረገም፡፡ በደፈናው ለሰበር ቀርቦ መጣራት የሚገባው ሆኖ በመገኘቱ ነው የሚለን፡፡

5.     በሁለቱም ወገኖች በሰበር ሂደቱ ያቀረቧቸው ክርክሮች ምን እንደሆኑ ግልጽ አይደለም፡፡ መስመር 55 ላይ በአጠቃላይ የክርክር ይዞታ ከላይ የተመለከተው ነው ይለናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ መስመር በፊት ያሉት የውሳኔው ክፍሎች መከራከሪያ ነጥቦቹን አያስቀምጡም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የሰበር ችሎቱን ውሳኔ እና የሕግ ትርጉም አግባብነት መገምገም አይቻልም፡፡

6.     በመስመር 55 እና 56 አቤቱታው ለሰበር ያስቀርባል ከተባለበት ነጥብ አኳያ መርምረናል ይላል ውሳኔው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ መስመሮች በፊት ያሉት የውሳኔው ክፍሎች የተባለውን ነጥብ አያስቀምጡም፡፡

7.     ከመስመር 70 እስከ 75 ባሉት በቁጥር 1810 ያለው የሁለት አመት የይርጋ ጊዜ ተፈጸሚ የሚሆነው ለውሉ ፈራሽ የሚሆነው ለውሉ መፍረስ ምክንያቱ የችሎታ ወይም ፈቃድ ጉድለት ሲኖር ብቻ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ለዚህ ትርጉም የተሰጠ ምክንያት የለም፡፡

8.     ከመስመር 85 እስከ 89 ባሉት ውሳኔው ስለአዲሱ የቤተሰብ ሕግ ይመለከታል፡፡ ነገር ግን ይህ ድንገተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያሉት የውሳኔው ክፍሎች ለምን የቤተሰብ ሕግን መጠቀም እንዳስፈለገ ግልጽ አያደርጉም፡፡

9.     በመስመር 95 እና 96 ሰበር ችሎቱ አንድ ውል ሕግን የሚቃረን ነው በሚባልበት ጊዜ እንዲፈርስ ጥያቄ መቅረብ ያለበት በ10 ዓመት ጊዜ እንደሆነ ከቁጥር 1845 መረዳት ይቻላል ይለናል፡፡ እንዴት/ለምን ለሚለው ምክንያት የለውም፡፡

10.    ከመስመር 99 እስከ 101 ባሉት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የተጠቀመው ድንጋጌ ለጉዳዩ አግባብነት ስለሌለው መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተስርቷል ይላል፡፡ ይህ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሕግ ስህተት እንደሰራ እንጂ ይህ ስህተት መሰረታዊ ስለመሆኑ የሚያስቀምጠው ምክኒያት የለም፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሱት አስር ቅርጻዊ ውስንነቶችና እና ጉድለቶች ብቻ የሰበር ችሎቱ በእነ ሙና እንድሪስ እና የ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሰጠው የሕግ ትርጉም አስገዳጅነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ከላይ በግልጽ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት የሰበር የሕግ ትርጉም አስገዳጅነት የሚመነጨው በአብዛኛው ከራሱ ከውሳኔው ነው፡፡

ይህ የሰበር ውሳኔ ግልጽ አለመሆኑ እና ምክንያት አለማስቀመጡ ብቻ ሳይሆን ጉድለቱ እንደ እኔ እምነት ብዙ የሕግ ስህተቶችን ፈጽሟል፡፡ እንደ እኔ እምነት ሰበር ችሎቱ የፈጸማቸው ስህተቶች መሰረታዊ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሉ ባሉት ክፍሎች እነዚህን ስህተቶች ለመለየትና ለማብራራት ይሞከራል፡፡ እንዲሁም ይህን ውሳኔ እንደ መነሻ በጽሑፍ ርዕስ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ይሞከራል፡፡

Find the PDF version

(ይቀጥላል)