መንግሥት ገቢ ከሚሰበሰብባቸው ምንጮች መካከል የቴምብር ቀረጥ አንዱ ነው፡፡ የቴምብር ቀረጥ ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ ሲሆን፣ የሚሰበሰበውም በተወሰኑ ሰነዶች ላይ እንዲለጠፍ ወይም እንዲከፈል በማድረግ ነው፡፡ በአገራችን የቴምብር ቀረጥ የተጣለው ስለ ቴምብር ቀረጥ አከፋፈል በወጣው አዋጅ ቁጥር 110/90 መሠረት ነው፡፡ የዚህ አዋጅ አፈጻጸም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ያለው አሠራር ተመሳሳይ አይደለም፡፡ በተግባር በሰነዶች የተለያዩ ግብይቶች (Transactions) የሚፈጸሙ ሰዎች፣ የአገር ውስጥ ገቢ ሠራተኞች፣ ባንኮች፣ ፍርድ ቤቶች ወዘተ የየራሳቸው የአዋጁ አረዳድ አላቸው፡፡ የልዩነቱ ምንጭ አዋጁን ካለማወቅ፣ ከአዋጁ ድንጋጌዎች ይልቅ በልማድ መሥራት፣ እንዲሁም የአዋጁን ክፍተት የሚሟሉ መመርያዎችን አለማወቅ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ የአዋጁ አፈጻጸም የሕግ አውጪውን መንፈስ እንዲከተል ማስቻል የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

የቴምብር ቀረጥ የሚከፈልባቸው ሰነዶች

የቴምብር ቀረጥ በሰነዶች ላይ የሚጣል ታክስ ቢሆንም፣ ሁሉም ሰነዶች ላይ የሚጣል አይደለም፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 3/12 የተለያዩ ሰነዶችን በመዘርዘር የሚከፈሉበትን ጊዜ፣ ሁኔታና መጠን በግልጽ አመልክቷል፡፡ የአዋጁ ዝርዝር ምሉዕ (Exhaustive) በመሆኑ በማመሳሰል ሌሎች ያልተጠቀሱ (ያልተዘረዘሩ) ሰነዶች ላይ የቴምብር ቀረጥ እንዲለጠፍ ወይም እንዲከፈል መጠየቅ አይቻልም፡፡ የቀረጥ ቴምብር የሚከፈለው በመመሥረቻና መተዳደሪያ ደንብ፣ የግልግል ሰነድ፣ ማገቻ፣ የዕቃ ማከማቻ ማረጋገጫ ሰነድ፣ ውል፣ ስምምነትና የእነዚህ መግለጫ፣ የመያዣ ሰነዶች፣ የኅብረት ስምምነት፣ የሥራ (ቅጥር) ውል፣ የኪራይ፣ የተከራይ አከራይና መሰል መብት የማስተላለፊያ ሰነዶች፣ ማረጋገጫ፣ የውክልና ሥልጣንና የንብረት ባለቤትነትን ማስመዝገቢያ ሰነድ ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰነዶች ውጭ ባሉ ሰነዶች ላይ የቴምብር ቀረጥ አይከፈልም፡፡

በተግባር በፍርድ ቤቶች አካባቢ ሬጅስትራሮች ለፍርድ ቤት በሚቀርቡ ማናቸውም ዓይነት ሰነዶች ላይ የቴምብር ቀረጥ እንዲለጠፍ (እንዲከፈል) ይጠይቃሉ፡፡ ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ የባለቤትነት የምስክር ወረቀት፣ ማስጠንቀቂያ፣ ተራ ደብዳቤ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ ወዘተ ላይ ባለጉዳዮች የቴምብር ቀረጥ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡ ይህ አሠራር ሕጉን ያልተከተለ ስለመሆኑ በአዋጁ የቴምብር ቀረጥ የሚከፈልባቸውን ሰነዶች በመመልከት ብቻ መረዳት ይቻላል፡፡ ሕግ አውጭው ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ሰነድ ሁሉ የቴምብር ቀረጥ እንዲከፈልበት ቢፈልግ ኖሮ ይህን የሚፈቅድ አጠቃላይ ድንጋጌ ባስቀመጠ ነበር፡፡

በአዋጁ የተዘረዘሩትን ሰነዶችንም በተመለከተ የአተረጓጐም ልዩነት ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ በመያዣ ሰነዶች ላይ የሚከፈለው የቀረጥ ቴምብር ተጠቃሽ ነው፡፡ አዋጁ የመያዣ ሰነድ ማለት ‹‹ተበዳሪው ወይም ዋሱ ለአበዳሪ በሙሉ ወይም በከፊል ንብረቱን በመያዣነት የሚሰጥበት ሰነድ ነው፤›› በሚል ትርጓሜ ቢሰጥም፣ አተረጓጎሙ ልዩነት ይታይበታል፡፡ በመያዣ ላይ የሚከፈለውን የቴምብር ቀረጥ በተመለከተ በተግባር የሚታየው ክፍተት አብዛኛዎቹ የፋይናንስ ተቋማት የቴምብር ቀረጥ የሚያስከፍሉት በመዝጋቢ አካል የሚመዘገቡ ሕንፃ (ቤት)፣ ተሽከርካሪ፣ የንግድ ተቋማትና ማሽነሪዎች በመያዣነት ሲቀርቡ ብቻ ነው፡፡ ተሰብሳቢ ገንዘብ (Receivables)፣ አክሲዮን፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ሸቀጥ (Merchandise) እና የመሳሰሉትን ንብረቶች በዋስትናነት ሲይዙ የቀረጥ ቴምብር አያስከፍሉም፡፡ አዋጁን በጥሞና ለመረመረው ግን ይህ ልማድ በሕጉ አይደገፍም፡፡ በአዋጁ ለመያዣ ሰነድ የተሰጠው ትርጉም ማንኛውም ‹‹ንብረት በመያዣነት›› ሲሰጥ የቀረጥ ቴምብር እንደሚከፈልበት ስለሚገልጽና ‹‹ንብረት›› የሚለው ቃል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1126 እና 1128 መሠረት ‹‹ግዙፍነት ያላቸው ንብረቶች ሁሉ ተንቀሳቃሽ የሆኑና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም የገንዘብና ሌሎችም ግዙፍነት የሌላቸው ነገሮችን›› ስለሚጨምር መያዣ ለሁሉም የንብረት ዓይነት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሠረት ተሰብሳቢ ገንዘብ፣ አክሲዮን፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ሸቀጥና መሰል ንብረቶች በመያዣ ሲሰጡ በውሉ ላይ የቀረጥ ቴምብር ሊከፈል ይገባል፡፡

ከንብረት ውጭ የሆኑ ዋስትናዎችን በተመለከተ የቴምብር ቀረጥ አዋጁ ግልጽ ድንጋጌ የለውም፡፡ ለምሳሌ የሰው ዋስትና (Surety) የንብረት ዋስትና ባለመሆኑ የመያዣ ሰነድ የሚለው ትርጉም ውስጥ አይወድቅም፡፡ አንዳንዶች የሰው ዋስትና ማገቻ (Bond) በሚለው ትርጉም ውስጥ እንደሚወድቅ በመግለጽ በዋስትና ሙሉ በተጠቀሰው የዋስትና መጠን አንድ በመቶ የቴምብር ቀረጥ ሊከፈልበት እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 2 (1) ‹‹ማገቻ›› ማለት የተወሰነ ነገር በመፈጸሙ ወይም ባለመፈጸሙ ምክንያት የሚቀር ሆኖ አንድ ሰው ለሌላው ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ማናቸውንም ሰነድ ወይም በምስክር የተረጋገጠ ሆኖ፣ ነገር ግን በትዕዛዝም ሆነ ለአምጭው የማይከፈልበት አንድ ሰው ለሌላው ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበትን ማንኛውንም ሰነድ ይጨምራል በሚል ለማገቻ ትርጉም ስለሚሰጥ የዋስትና ውል (ሰነድ) ማገቻ በሚለው ጽንሰ ሐሳብ እንደሚወድቅ ማሰብ ቅቡል (Valid) ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 40187 ማገቻ፣ የዋስትና ውል ነው ሲል የሰጠው ገዥ ፍርድም ይህንኑ አቋም ይደግፋል፡፡ ከዚህ አቋም በተቃራኒው የሰው ዋስትና በቴምብር ቀረጥ አዋጅ በመያዣነት ትርጉም ውስጥ የሰው ዋስትና ስለማይካተት የቴምብር ቀረጥ ሊከፈልበት አይገባም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

ሌላው የአክሲዮን ዝውውር (Share Transfer) የቴምብር ቀረጥ ሊከፈልበት ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአክሲዮን ዝውውር ስምምነት ለመፈራረም አንዳንድ ሰዎች ውልና ማስረጃ ሲሄዱ በተላለፈው የአክሲዮን ዋጋ ላይ ሁለት በመቶ የቴምብር ቀረጥ ክፈሉ እንደሚባሉ፣ እንዳንዶችም እንደከፈሉ ታውቋል፡፡ የዚህ አቋም መነሻ የአዋጁ አንቀጽ 3 (12) የንብረት ባለቤትነት ማስመዝገቢያ ሰነድ የቴምብር ቀረጥ እንደሚከፈልበት መግለጹ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአዋጁ አንቀጽ 11 (6) ‹‹የአክሲዮን ድርሻ የምስክር ወረቀት ሲመዘገብ የቴምብር ቀረጥ አይከፈልም፤›› በሚል በግልጽ በመደንገጉ የአዋጁ አንቀጽ 3 (12) ለአክሲዮን ዝውውር ተፈጻሚ የሚሆን አይመስልም፡፡ በሌላ በኩል ግን በአንድ የግል ባንክ ጥናት ውስጥ እንደተመለከተው አንቀጽ 3 (12) አፈጻጸምን በሚመለከት በአንድ ወቅት በፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲና በአገር ውስጥ ገቢ ባለሥልጣን መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ፤ ጉዳዩን የዳኘው የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽሕፈት ቤት ‹‹… በንብረት ባለቤትነት ማስተላለፊያ ሰነድ ላይ የሚከፈለው የቴምብር ቀረጥ ሕንፃዎችና ተሽከርካሪዎችን ብቻ ይመለከታል፤›› በሚል የአክሲዮን ዝውውር የቴምብር ቀረጥ እንደማይከፈልበት አመላካች ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ከባንክ ብድር ጋር በተያያዘም የብድር ውል ሲሻሻል የመያዣው ውል እንደገና የቴምብር ቀረጥ ሊከፈልበት ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለው ነጥብም አከራካሪ ነው፡፡ የብድር ውሉ የቴምብር ቀረጥ እንደሚከፈልበት በአዋጁ በግልጽ ባይቀመጥም ‹‹ውል›› በሚለው የወል ስያሜ ስለሚሸፈን ብር አምስት የቴምብር ቀረጥ እንደሚከፈልበት አከራካሪ አይደለም፡፡ የሚያከራክረው ነጥብ የብድር ውሉ ገንዘብ ቢጨምር፣ ወይም የመክፈያው ጊዜ ቢራዘም ወይም ከአንድ የብድር ዓይነት ወደ ሌላ ቢለወጥ (ለምሳሌ ኦቨርድራፍት ብድር ወደ ተወሰነ ጊዜ የሚከፈል ብድር ቢለወጥ) በመያዣው ንብረት ላይ እንደገና የቴምብር ቀረጥ የመክፈል አለመክፈሉ ጉዳይ ነው፡፡ የብድር ወይም የመያዣ ውሎች በተለያዩ ምክንያቶች ሊሻሻሉ ወይም ሊታደሱ ይችላሉ፡፡ የቴምብር ቀረጥ አዋጁ ከብድር ወይም ከመያዣ ውል ጋር የተያያዙ ሰነዶች ማሻሻያን በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም፡፡ ለምሳሌ የኅብረት ስምምነትን በተመለከተ ሲመዘገብም ሆነ ሲሻሻል የተለያየ መጠን የቴምብር ቀረጥ እንደሚከፈልበት የአዋጁ የቴምብር ቀረጥ ታሪፍ ሰንጠረዥ ይደነግጋል፡፡ ለንግድ ማኅበርና ለኅብረት ሥራ ማኅበር መተዳደሪያ ደንብም ተመሳሳይ ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት የመያዣ ውል ሲሻሻል የብድሩ የገንዘብ መጠን ካልጨመረ በቀር ድጋሚ የቴምብር ቀረጥ ሊከፈልበት እንደማይገባ መረዳት ይቻላል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው ማብራሪያዎችም ይህንን አቋም አጠናክሯል፡፡ ተጨማሪ ብድር ሲፈቀድ ወይም የኦቨርድራፍት ወሰን (Limit) ከፍ ሲል አዲስ የብድርና የመያዣ ውል ስለሚፈጸም ለተጨማሪው ውል በገንዘብ ልዩነቱ የቴምብር ቀረጥ ሊከፈለበት ይገባል፡፡ የኦቨርድራፍት ብድርም ወደ ተወሰነ ጊዜ የሚከፈል ብድር ሲቀየር በውሉም ላይ የመያዣ ውሉ እንደሚተላለፍ እስከተገለጸ ድረስ ሊከፈል የሚገባው የቴምብር ቀረጥ በቁርጥ ብር አምስት ብቻ እንጂ በመያዣው ውል ላይ ተጨማሪ ክፍያ ሊከፈልበት አይገባም፡፡

የቴምብር ቀረጥ አከፋፈል ሁኔታ

አዋጁ የቴምብር ቀረጥ የሚከፈልባቸውን ሰነዶች ከመዘርዘር ባለፈ የቴምብር ቀረጥ አታማመን፣ የመክፈል ግዴታ ያለበትን ሰው እንዲሁም ቀረጡ የሚከፈልበትን ጊዜና ሁኔታ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በአዋጁ በተገለጹ በእያንዳንዱ ሰነድ ላይ መከፈል የሚገባው የቀረጥ መጠን በአዋጁ በሰንጠረዥ ተዘርዝሯል፡፡ አከፋፈሉ በቁርጥ ወይም በሰነዱ ዋጋ ይከፈላል፡፡ በቁርጥ ከሚከፈሉት ውስጥ የንግድ ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ ብር 350፣ የኅብረት ሥራ ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ ብር 35፣ ውሎች ብር አምስት፣ የኅብረት ስምምነት ብር 350፣ ማረጋገጫ ብር አምስት፣ የውክልና ሥልጣን ብር 35 እንደሚከፈልባቸው ተመልክቷል፡፡ በሰነዱ ዋጋ በመቶኛ የሚከፈልባቸው ደግሞ የሚተመን ግልግል አንድ በመቶ፣ ካልተተመነ ደግሞ በቁርጥ ብር 35፣ የመያዣ ሰነድ አንድ በመቶ፣ የቅጥር ውል የአንድ ወር ደመወዝ አንድ በመቶ፣ ኪራይ ውል አንድ በመቶና  የንብረት ባለቤትነት ስም ማስመዝገቢያ ሁለት በመቶ እንደሆነ ሰንጠረዡ ያመለክታል፡፡ ብዙ የተለያዩ ነገሮች የተጠቃለሉበት ሰነድ ከሆነ አከፋፈሉ በእያንዳንዱ ሰነድ ላይ የሚከፈለው ቀረጥ በመጠቃለል ተደምሮ ይከፈልበታል፡፡ 

የአከፋፈሉ ሁኔታ በተመለከተም አዋጁ ግልጽ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ የሚከፈለው የቴምብር ቀረጥ ከብር 50 በታች በሚሆንበት ጊዜ ክፍያው ተገቢውን ዋጋ የያዘውን ቴምብር በመለጠፍ ይፈጸማል፡፡ (አንቀጽ 7 (2) (ሀ))፤ በሌላ በኩል ቀረጡ ከብር 50 የበለጠ ሲሆን ወይም የሰነዱ ዓይነትና ሁኔታ ለየት ያለ አሠራርን ሲጠይቅ የፌዴራል መንግሥት የገቢዎች ቦርድ በሚያመጣው መመሪያ ቴምብር ከመለጠፍ በሌላ መንገድ ቀረጡ እንዲከፈል ሊያደርግ እንደሚችል አዋጁ በግልጽ ያሳያል፡፡ የቴምብር ቀረጥ የሚከፈልበትን ጊዜ አዋጁ እንደየሰነዱ ዓይነት ዘርዝሮ ገልጿል፡፡ ከአዋጁ አንቀጽ 7 (1) ለመረዳት እንደሚቻለው የቴምብር ቀረጥ በሁሉም ሰነዶች ላይ ሊከፈል የሚገባው ሰነዶቹ ከመፈረማቸው ወይም ከመመዝገባቸው በፊት ወይም በሚፈርሙበት ወይም በሚመዘገቡበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡ የቴምብር ቀረጥ የመክፈል ግዴታ እንደሰነዱ ዓይነት የሚለያይ ሲሆን ተከራይ፣ ተበዳሪ፣ የንብረት ባለቤትነት የሚመዘገብለት ሰውና አሠሪው የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ በውል፣ በግልግልና በኅብረት ስምምነት ደግሞ ሁለቱም ወገኖች በጋራና በነጠላ ኃላፊነት እንዳለባቸው አዋጁ ይደነግጋል፡፡

ከቴምብር ቀረጥ አከፋፈል ሁኔታ ጋር በተያያዘ የአዋጁን አፈጻጸም ስንመለከት የተወሰኑ ክፍተቶች እንዳሉበት እንረዳለን፡፡ የተወሰኑትን እንመልከት፡፡ የመጀመርያው የመያዣ ውል የቴምብር ቀረጥ የሚሰላው የብድር ውሉን መሠረት በማድረግ ነው ወይስ የመያዣ ንብረቱን ግምት የሚለው ነው? ሠንጠረዡ የመያዣ ሰነድ በዋጋው አንድ በመቶ ይከፈልበታል በሚል በደፈናው ስለሚደነግግ ጉዳዩን በአግባቡ አይገልጸውም፡፡ በተግባር በባንኮች አካባቢ ያለው ተሞክሮ ልዩነት ይታይበታል፡፡ አንዳንድ ባንኮች የመያዣ ሰነድ ዋጋ የብድሩን መጠን መሠረት በማድረግ ሲወስኑ ሌሎቹ ደግሞ የንብረቱን ግምት መሠረት ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ጭብጥ እልባት ለመስጠት ባንኮች በመያዣው ንብረት ላይ የሚጠይቁትን መብት ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2828 (1) እና 3045 (2) መሠረት ዋስትና የተሰጠበት ግዴታ የገንዘብ መጠኑን መግለጽ እንዳለበት ስለተደነገገ የመያዣ ውል ዋጋ በዚሁ መሠረት የሚገለጸው የገንዘብ መጠን መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በመያዣ ውሉ አስያዡ (ዋሱ) የሚገባው ግዴታ ተበዳሪው ብድሩን በሙሉ ወይም በከፊል ለመክፈል ያልቻለ እንደሆነ በተበዳሪው እግር ተተክቼ በመያዣ ሰነድ የተገለጸውን ገንዘብ እከፍላለሁ ወይም ያስያዝኩት ንብረት ተሽጦ በመያዣ ሰነዱ የተገለጸው ገንዘብ ለብድሩ ክፍያ ሊውል ይችላል የሚል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ‹‹የመያዣ ሰነዱ›› ዋጋ (Value) ሊባል የሚችለው የብድሩ ገንዘብ ወይም በመያዣነት የተሰጠው ንብረት ግምት ሳይሆን ዋሱ (አስያዡ) የሚገደድበትና በመያዣ ሰነዱ ላይ የተገለጠው ገንዘብ ነው፡፡

ሁለተኛው የቴምብር ቀረጥ አከፋፈል ላይ ያለው ክፍተት ነው፡፡ አዋጁ ከብር 50 በታች የሆነ የቴምብር ቀረጥ የመክፈል ግዴታ ሰነዱ ላይ በመለጠፍ ብቻ እንደሚከፈል ግልጽ አድርጓል፡፡ በፍርድ ቤቶች አካባቢ ግን ከብር 50  በታች የሆነ የቴምብር ቀረጥ አከፋፈል በአገር ውስጥ ገቢ ባለሥልጣን ካልተመሰከረ አይቀበሉም፡፡ ይህ የፍርድ ቤቶች አሠራር ወጥነት ይጎድለዋል፡፡ ቃለመሃላ (ማረጋገጫ) ላይ የሚለጠፍ ቴምብሮችን የሚቀበሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌሎች ማስረጃዎች ላይ የሚለጠፉትን በተመለከተ ግን ሬጅስትራርም እንዲለጠፍ አያደርግም፤ ባለጉዳዮቹም ለጥፈው ሲመጡ አይቀበሉም፡፡ ቴምብር የመለጠፍ አተገባበር በሌሎች ድርጅቶች ክፍተት አይታይበትም፡፡ ለምሳሌ ባንኮች በየዕለቱ የሚፈራረሟቸው ውሎች ላይ የቴምብር ቀረጥ በመለጠፍ ቀረጥ የሚከፈልበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ፡፡ የፍርድ ቤቶች ተሞክሮ ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ብዙ ባለጉዳይ ከፍርድ ቤት ወደ አገር ውስጥ ገቢ ቴምብር ለመለጠፍ ሲሯሯጥ ይስተዋላል፡፡ ይህ አሠራር ከአዋጁ ጋር እንዲጣጣም ባለጉዳዮች ቴምብር ለጥፈው ሲቀርቡ ሬጅስትራሩ በመሰረዝ መቀበል ይገባዋል፡፡ 

ሌላው ከባንኮች ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ነው፡፡ የፌዴራል አገር ውስጥ ገቢ ባለሥልጣን ከመያዣ የሚሰበሰቡ የቴምብር ቀረጦችን ባንኮች እንዲሰበስቡ ውክልና ሰጥቷቸዋል፡፡ ባንኮች በዚህ ውክልና የቴምብር ቀረጥ የሚሰበሰቡ ቢሆንም፣ በክልሎች አፈጻጸሙ ፈተና ሲገጥመው ይስተዋላል፡፡ ክልሎች ባንኮች ከመያዣ ሰነድ የሚሰበሰውን የቴምብር ቀረጥ ለክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ገቢ ካልተደረገ መያዣውን እንደማይመዘግቡ ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥ የመያዣ ውሉ የሚመሠረተው፣ የሚመዘገበውና የሚፈጸመው በክልሉ በመሆኑ የቴምብር ቀረጡ ገቢ ለክልሎች ቢገባ ፍትኃዊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ክልሎቹ የሚጠይቁበት የሕግ መሠረት በፌዴራሉ መንግሥት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 110/90 መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ደግሞ በአንቀጽ 8 (1) አዋጁን ማስፈጸምና በአዋጁ መሠረት የተወሰነውን ቀረጥ የመሰብሰብ ሥልጣን የፌዴራል አገር ውስጥ ገቢ ባለሥልጣን መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ባንኮች ክልሎች የሚያወጡት የቴምብር ቀረጥ አዋጅ በግልጽ ካልከለከላቸው በስተቀር የቴምብር ቀረጥን በውክልና ሰብስበው ገቢ ማድረግ ያለባቸው ለፌዴራል የአገር ውስጥ ገቢ ባለሥልጣን ነው፡፡

ሦስተኛው የቴምብር ቀረጥ ከሚከፈልበት ጊዜና የመክፈል ግዴታ ካለበት ሰው ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጉዳይ ነው፡፡ የቴምብር ቀረጥ የመክፈያ ጊዜ ሕጉና አተገባበሩ ልዩነት አለው፡፡ ሕጉ ቀረጡ ሰነዱ ከመፈረሙ (ከመመዝገቡ በፊት ወይም ሲፈረም) ሲመዘገብ ጊዜ እንዲከፈል ቢደነግግም፣ በተግባር ሰዎች የቴምብር ቀረጥ የሚከፍሉት ሰነዶቹን መሠረት በማድረግ በፍርድ ቤት መብታቸውን በሚጠይቁበት ወይም ክስ ቀርቦባቸው የመከላከያ መልስ ሲያቀርቡ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ ሰነዱ የሚፈጸምበት እንጂ የተፈረመበት ወይም የተመዘገበበት ጊዜ አይደለም፡፡ በአዋጁ የቴምብር ቀረጥ ያልተከፈለበት ሰነድ በፍርድ ቤት ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ስለዚህ መብት ጠያቂው ሕጉ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ የቴምብር ቀረጡን ለጥፎ ወይም ከፍሎ ካልቀረበ ፍርድ ቤት ክስ ሲያቀርብ ሊፈቀድለት ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ በኩል የሕግ አውጭው ሐሳብ ሰነዶች በሚፈርሙበት (በሚመዘገቡበት) ጊዜ ወይም ከዚያ በፊት የቴምብር ቀረጥ እንዲከፈልባቸው በመሆኑ ድንጋጌዎቹ ቸል ሊባሉ አይገባም፡፡ በሌላ በኩል ግን ግለሰቦች በፍርድ ቤት ለሚጠይቁት መብት የቴምብር ቀረጥ ባለመክፈላቸው ብቻ መብታቸውን ለማስረዳት መከልከላቸው ፍትኃዊ አይሆንም፡፡ የቴምብር ቀረጥ የመከፈል የመንግሥት መብትና ፍትሕ የማግኘት የዜጎች መብት ከተጋጩ የኋለኛው መብት ስለመቅደሙ መከራከር አሳማኝ ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለውል በተደነገገውም ክፍል የቴምብር ቀረጥ መክፈልን የመሰሉ ግዴታዎች አለመሟላታቸው የውሉን ቅቡልነት (Validity) እንደማያሳጣው ተገልጿል፡፡ የመዋዋል ነፃነት ያገኘው የሕግ ጥበቃ ፍትሕ የማግኘት መብት ላይም ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰነድ ሲፈረም የቴምብር ቀረጥ አለመከፈሉ፣ ሰነዱ በፍርድ ቤት ሲቀርብም የሚከፈልበት ከሆነ የመንግሥትን ገቢ አያሳጣም፡፡ የቴምብር ቀረጥ አዋጁም ሰነዱ ከተፈረመ (ከተመዘገበ) በኋላ ቀረጥ መክፈል የሚኖረውን ውጤት ባለማመልከቱ፤ በአዋጁ ከተጠቀሰውም ጊዜ በኋላ ቀረጡ ቢከፈል ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል፡፡ በተለይ በሰነዱ ላይ የቴምብር ቀረጥ የመክፈል ግዴታ ያለበት ወገን ግዴታውን ባለመወጣቱ ሌላው ባመብት ሊጎዳ አይገባም፡፡ አሠሪው ወይም ተበዳሪው ወይም ተከራዩ የቴምብር ቀረጥ ባለመክፈሉ የሠራተኛው፣ የአበዳሪው ወይም የአከራዩ ማስረጃ የማቅረብ መብቱ ሊጣበብ አይገባም፡፡ በእርግጥ በተግባር ዳኞች የቴምብር ቀረጥ ባለመለጠፉ ካልሆነ በቀር በሕጉ ከተቀመጠው ጊዜ በኋላ ተለጥፎ (ተከፍሎ) ሲቀርብ ሰነዱን ተቀብለው ስለሚያስተናግዱ ተግባራዊ ፋይዳው አነስተኛ ነው፡፡

ከቀረጡ ነፃ የመሆን መብት

የቴምብር ቀረጥ አዋጁ ከቀረጥ ነፃ የመሆን መብትን በአንቀጽ 11 ደንግጓል፡፡ ድንጋጌው የተወሰኑትን የነፃ መብት ተጠቃሚዎች የዘረዘረ ሲሆን፣ ሌሎቹን ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር በቂ ምክንያት ሲቀርብለት ከቴምብር ቀረጥ ነፃ ሊያደርግ እንደሚችል ገልጿል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የአስመጪነት የንግድ ሥራ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ለሽያጭ የሚያስመጡት ንብረት በአስመጪዎቹ ስም በሚመዘገቡበት ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተጠቃሚ የሆኑ፣ ተመሳሳይ መብት የሚሰጡ ኤምባሲዎችና የአክሲዮን ድርሻ የምስክር ወረቀት ሲመዘገብ የቴምብር ቀረጥ ነፃ መብት ይኖራቸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በመመሪያ ነፃ ካደረጋቸው ውስጥ ባንኮችና ኢንቨስተሮች ይገኙበታል፡፡ ባንኮች ለሦስተኛ ወገን በሚሰጧቸው ቦንዶች (Bid Bond, Performance Bond) ላይ የቴምብር ቀረጥ አይከፍሉም፡፡ ይህ በገንዘብ ሚኒስቴር በወጣ መመርያ የተደነገገ ሲሆን፣ የኢንቨስተሮች ልዩ መብት ደግሞ በገቢዎች ሚኒስቴር በወጣ መመርያ ነው፡፡

የፌዴራል የገቢዎች ሚኒስቴር በቁጥር 01/1/9/11/33/3፣ ጥቅምት 24 ቀን 1997 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ ‹‹ኢንቨስተር›› ተብለው የሚጠሩ ግለሰቦች ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ከባንኮች ብድር ሲወሰዱ የቀረጥ ቴምብር ሊከፍሉ እንደማይገባ ተደንግጓል፡፡ መመርያው ተፈጻሚ የሚሆነው ኢንቨስተር ተብሎ ለሚጠሩ ወገኖች እንጂ ለሌሎች አይደለም፡፡ በኢንቨስትመንት አዋጁ ‹‹ኢንቨስተር›› ወይም ‹‹ባለሀብት›› ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገ የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሀብት ሲሆን፣ ኢንቨስትመንቱ አዲስ ድርጅት ለማቋቋም ወይም ነባር ጅርጅቶችን ለማስፋፋት ወይም ለማሻሻል በባለሀብት የሚደረግ የካፒታል ወጪ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው አዲስ ፕሮጀክት አጥንቶ ለመተግበር የተዘጋጀም ሆነ ቀደም ሲል የነበረ ድርጅትን የሙሉ አቅም ምርት ወይም አገልግሎት ማሳደግ ‹‹ኢንቨስትመንት›› ሊባል ይችላል፡፡

የኢንቨስትመንት ማበረታቻን በተመለከተ የወጣው ደንብ ቁጥር 7/1988 ዓ.ም. ባለሀብቶች ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ የመሆን መብትንና በገቢ ግብር እንደ ኢንቨስትመንት መስኩ ለተወሰኑ ዓመታት ነፃ የመሆን መብትን አካትቷል፡፡ በገቢዎች ሚኒስቴር የወጣው መመርያ የደንብ ያህል የሕግ ደረጃ ባይኖረውም፣ ለባለሀብቶች የሚሰጠውን ማበረታቻ የሚያሰፋ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት አዋጅ አንቀጽ 9 የተጨማሪ ማበረታቻዎች ዓይነትና መጠን በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰን ቢደነግግም፣ በገቢዎች ሚኒስቴር የወጣው መመርያም በታክስ ሰብሳቢው የአስተዳደር አካል የወጣ በመሆኑ ተፈጻሚነቱን መቀበል ተግባራዊ (Pragmatic) ዕይታ ነው፡፡

ባለሀብቶችን ከቀረጥ ቴምብር ክፍያ ነፃ የሚያደርገው መመሪያ፡-

‹‹ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ሲባል በኢንቨስትመንት ሕጉ መሠረት ኢንቨስተር ተብለው ዕውቅና የተሰጣቸውን ባለሀብቶች ብቻ ለኢንቨስትመንት ከሚወሰዱት ብድር ጋር በተገናኘ በመያዣ ሰነድ ላይ ከሚከፈለው የቴምብር ቀረጥ ነፃ አንዲሆኑ ፈቅዷል፡፡››

በዚህ መመርያ መሠረት ባንኮች የቴምብር ቀረጥ ነፃ የሚሆኑ ተበዳሪዎችን ለመለየት ሁለት ነጥቦችን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመጀመርያው ባለሀብት (Investor) መሆናቸውን ሲሆን፣ ሁለተኛው የሚወስዱት ብድር ለኢንቨሰትመንት የሚያውሉት መሆን ይገባዋል፡፡ ኢንቨስተር የሚለውን ትርጉም ከላይ የተመለከትነው ቢሆንም ባንኮች ተበዳሪው ኢንቨስተር መሆኑን መለየት የሚችሉት በኢንቨስትመንት ፈቃዱ ብቻ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጠው ባለሀብት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱን ግንባታ አጠናቅቆ ማምረት ወይም አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ የንግድ ወይም የሥራ ፈቃድ እንዲያወጣ አይጠየቅም፡፡ ስለዚህ ባለሀብቱ የንግድ ፈቃድ ወይም የሥራ ፈቃድ ባይኖረው እንኳን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካለው ‹‹Investor›› ተብሎ የመብቱ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከኢንቨስትመንት አዋጁ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢንቨስተር የንግድ ሥራ ፈቃድ ሊኖረው እንደሚችል ነው፡፡

በተግባር አከራካሪ የሚሆነው ግን አንድ ባለሀብት የንግድ ሥራ ፈቃድ ቢኖረውና ባልታደሰ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የቴምብር ቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ እንደሆነ ቢጠይቅ ባንኮች ሊያስተናግዱት ይገባል ወይ የሚለው ነጥብ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ፈቃዱ ምርት ማምረት ወይም አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ በየዓመቱ መታደስ እንደሚገባው የኢንቨስትመንት አዋጁ በአንቀጽ 15/1/ ላይ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከቴምብር ቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ መሆን ያለበት ባለሀብት ምርት ማምረት ካልጀመረ ወይም አገልግሎት መስጠት ካልጀመረ የኢንቨስትመንት ፈቃዱን ሊያሳድስ ይገባል፡፡ ሆኖም የፕሮጀክት ትግበራ ተጠናቆ ማምረት ወይም አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የኢንቨስትመንት ፈቃዱ የአገልግሎት ጊዜ ዘላቂነት ያበቃል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባለሀብት የንግድ ሥራ ፈቃድ ሊኖረው ይገባል፡፡ የንግድ ሥራ ፈቃድ ከወጣ በኋላ ግን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ስለማይታደስ ለማንኛውም አገልግሎት የታደሰ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማቅረብ አይችልም፡፡ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በቁጥር ኢዲክ9/ኢጠ/1/662 ኀዳር 22 ቀን 1999 ዓ.ም. የጻፈው ማብራሪያ ይህንኑ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

ከኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አሠራር ለመረዳት እንደተቻለው ግን የፕሮጀክት ትግበራ አጠናቀው አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጁ ለሆኑ ባለሀብቶች ኤጀንሲው የንግድ ሥራ ፈቃድ (Business License) በውክልና ይሰጣል፡፡ ሆኖም በዚህ መመርያ መልስ ሊያገኝ የሚገባው አንድ ባለሀብት የንግድ ሥራ ፈቃድ ካወጣ በኋላስ በ‹‹Investor›› ስም ከቴምብር ቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ መሆን ይችላል ወይ የሚለው ነጥብ ነው፡፡

በኢንቨስትመንት አዋጁ አንቀጽ 2/1/ ለመረዳት እንደሚቻለው ነባር ድርጅትን ለማስፋፋት ወይም ለማሻሻል በባለሀብት የሚደረግ ወጪ ኢንቨስትመንት ሊሆን ስለሚችል፣ የንግድ ሥራ ፈቃድ ያለው ባለሀብትም ‹‹Investor›› ተብሎ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ አከራካሪ አይሆንም፡፡ ሆኖም የንግድ ፈቃድ ኖሮት የባለሀብት ማበረታቻ ተጠቃሚ መሆኑን ማስረዳት ያለበት ይሄው ሰው ነው፡፡

የቀረጥ ቴምብር ነፃ ማበረታቻ ከ‹‹ጉምሩክ ቀረጥ›› እና ‹‹ከገቢ ግብር›› ማበረታቻ የሚለየው በመመርያ የተሰጠ መብት መሆኑና ዝርዝር የመብቱ አጠቃቀም (መብቱ) የሚጀምርበትንና የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ባለማመልከቱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ባለሀብት የንግድ ሥራ ፈቃድ በማውጣቱ ብቻ ‹‹ባለሀብት›› አይደለም ብሎ ተጠቃሚ እንዳይሆን ከመከልከል የንግድ ሥራ ፈቃድ ኖሮትም ቢሆን የኢንቨስተር መብት ተጠቃሚ መሆኑን አንዲያስረዳ መጠየቁ አግባብነት ይኖረዋል፡፡

ከቴምብር ቀረጥ አዋጅ አፈጻጸም ጋር የሚነሱትን ተግባራዊ ክፍተቶች ከላይ ተመልክተናል፡፡ ሕጉና አተገባበሩ የተወሰነ ክፍተቶች አሉበት፡፡ የክፍተቶቹ ምንጭ ፍርድ ቤቶች በአዋጁ ላይ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ፣ ባንኮች የተለያየ ተሞክሮ መኖራቸው እንዲሁም ግብር ሰብሳቢው አካል ጉዳዩን በተመለከተ በጥናት ላይ የተመሠረተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አለመዘጋጀቱ ነው፡፡ እነዚህ ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ግዴታ ቢወጡ በሕጉና በአተገባበሩ መካከል ያለው ክፍተት እንደሚጠብ ጸሐፊው ያምናል፡፡