የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ በተለያዩ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አተሰሳሰቦች የነበረ፤ ያለ እና የሚኖር መስተጋብር ነው፡፡ ታሪኩንም በወፍ በረር መለስ አድርገን ስንመለከት ከካፒታሊስታዊ ሥርዓተ ማኅበር በፊት በነበሩት ሥርዓቶች በተለይም በባሪያ አሳዳሪ /slave-owning/ ሥርዓተ ማኅበር እና በፊውዳል /feudal system/ ሥርዓተ ማኅበር ወቅት ይሰተዋል የነበረው ሠራተኛው እንደ ጪሰኛ የሚቆጠርበት ሥርዓት ነበር፤ የሚያገኘው ጥቅምም ከአሠሪው ምግብ እና መጠለያ እንጂ መደበኛ ደምወዝ አልነበረውም፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ብቅ ማለት የጀመረው በኢንዲስትሪ አብዮት ወቅት ሲሆን የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትም ከትናንሽ የጎጆ ኢንዱስትሪ ወደ ትላላቅ ፍብሪካዎች በተሸጋገረበት ጊዜ ነበር፡፡ በአንጻሩ አሠሪዎች ደግሞ በቀላሉ ሠረተኛ ቀጥረው ያሠሩ ነበር ለምን ቢባል በወቅቱ በጣም ርካሽ የሰው ኃይል ስለነበር ነው፡፡ በወቅቱም የሠራተኛች አንገብጋቢ ጥያቄ የነበረው የተሻለ የሥራ ሁኔታ /minimum working condition/ እንዲሁም ከሠራተኛ ማኅበር አባልነት ጋር የተያያዙ መብቶች ነበሩ፡፡

ከኢንዱስትሪ አብዮት ማግስትም በተለይ በእንግሊዝና በፈረንሳይ አካባቢ የሚኖሩ ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ለዚህም እንደማሳያ የሚቆጠረው ሠራተኞች ሃያ አራት (24) ሰዓት ደክመው የሚያገኙት ገቢ ከአንድ ፓውንድ ወይም ፍራንካ ያነሰ ነበር፡፡ የፋብሪካ ሥራ በተለይም የህጻናትን፤ የሴቶችን እንዲሁም ጎልማሶችን ህይወት በወል ስጋት ላይ የጣለ ነበር፡፡ (ጋልቢ፡1997)

አለም ዓቀሩ የሥራ ማኅበር (International labor organization) መሠረቱን ፈረንሳይ አድርጎ እኤአ 1919 ሲቋቋም ዋና ዓላማ አድርጎት የተነሳው ለሠራተኛው መደብ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠውና የሥራ ቦታም በሕግ እና ደንብ እንዲመራ የሦስትዮሽ (tripartite) ማለትም መንግስት፤ አሠሪ እና ሠራተኛ መር አወቃቀር ኢንዲኖር ያስቻለ ከመሆኑም ባሻገር በመንግሥት እና ሌሎች አካላት ግልጽና ነጻ ክርክር እንዲኖር የበኩሉን እያደረገ ነው፡፡

ወደ አገራችን ስናመራም ሥራን እና ሠራተኛን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕግ ያወጡት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እንደነበሩ ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ በወቅቱም ንጉሱ በጥር 17 ቀን 1900 ዓ.ም ባወጡት አዋጅ መሰረት ልክ አውሮጳ እንደሚደረገው ለሠራተኞች ተገቢው ክብር እና ጥበቃ እንዲሰጣቸው ጭምር ትእዛዛ እንደሰጡ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ (ተከለ ጻዲቅ፡ መኩሪያ፡1983፡591)

ከዚያም የሠራተኞች መብት እንዲሁም የሥራ ስንብት ክፍያን ጨምሮ በሰፊው ትኩረት የተሰጠው በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን እንደሆነ እና በተለይ በንጉሱ ዘመን ድንጋጌ ቁ. 49/1954 ከወጣ በኋላ የሥራ ውል በሚቋረጥበት ወቅት ለሠራተኞች የመጠባበቂያ ገንዘብ እንዲጠራቀም ሕጉ በአንቀጽ 49 ላይ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን የመጠባበቂያ ገንዘቡ ምን ያህል አንደሆነ ብሎም ከማን እንደሚዋጣ በግልጽ የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ (በላቸው፡ መኩሪያ፡166)

በደርግ ዘመን በወጣው የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 64/1968 መሠረት ሠራተኞች በማንኛውም ምክንያት ሥራ በሚያቆሙበት ጊዜ የሥራ ስንብት ከፍያ ሊያገኙ እንደሚችሉ ብሎም በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የጡረታ አገልግሎት ለማያገኙ ሠራተኞች በምትኩ የመጠባበቂያ ገንዘብ ይሠጥ እንደነበር ከአዋጁ መረዳት እንችላለን፤ ይህ የደርግ አዋጅም የሥራ ስንብትን አስመልክቶ ጥሩ ይዞታ እንደነበረው መረዳት እንችላለን፡፡

በዋናነት የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ዓላማ አድርጎት የተነሳው በጉልበታሙ አሠሪ እና በደካማው ሠራተኛ መካከል ያለውን ግንኙነት አስቀድሞ በተወሰኑ ሕግጋት መግዛት ነው፡፡

የዚህ ጹሑፍ ዋና ዓላማ የሥራ ስንብት ክፍያ ምንነት፤ የአከፋፈሉ ሁኔታ እና በምን ሁኔታዎች ሊከፈል እንደሚችል የሚዳስስ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን ተግዳሮት በትኩረት ከተመለከተ በኋላ የሌሎችን ሀገራት ልምድን ጠቆም ለማድረግ ይሞክራል፡፡

የሥራ ስንብት ክፍያ ምንነት፡-

የሥራ ስንብት ክፍያ አመጣጡ ከሦስት ታሪካዊ ምክንያቶች እንደሆነ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ (ሐውኪንስ፡1940) የመጀመሪያው ምክንያት ዘርዘር ያሉ የአሠሪና ሰተራተኛ ሕጎች /Labour codes/ መበራከት ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበረው አስከፊ ጊዜ በሺወች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው መልቀቅና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተካሄዱ ለውጦች መታየታቸው ነበር፤ የመጨረሻው ምክንያት ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጡ ለዜጎች የሚጨነቁ መንግሥታት መበራከት /welfare state expansion/ለጉዳዩ ትኩረት እንደሠጡት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሃገራት የተለያዩ የማኅበራዊ ዋስትና ፓኬጆችን መቅረጽ የጀመሩ ሲሆን በተለይም ሠራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሕግም እንደወጣ እንገነዘባለን፡፡

የሥራ ስንብት ክፍያ መከፈሉ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም ለሚለው ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ በተመለከት የሚከተሉት አንድምታወች በመላምትነት ይሰነዘራሉ፡፡ የመጀመሪያው አመክንዮ የሥራ ስንብት ክፍያ በጣም ረጀም ጊዜን ያስቆጠረ ማኅበራዊ መድህን መሆኑ እና ሥራ አጥነትን ብሎም ጥሮታን የሚያጠናክር በመሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ የሰው ሃብት አጠቃቀም በቃት ጋር ይያያዛል፡፡ ይህም ማለት ድርጅቱ ወይም ቀጣሪው አካል ከፍተኛ የሆነ የሠራተኛ ፈልሰት ስለሚያስቀርለት እና በአንጻሩ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ምርታማነትን መገኘቱ፡፡ ሌላኛው ምክንያት ድግሞ የሥራ ዋስትና /job security/ ከማረጋገጥ ጋር ይያያዛል፡፡

የሥራ ስንብት ክፍያ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ነጥብ ከማየታችን በፊት አንዳንድ ትርጓሜዎችን ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ Business law dictionary ገለጻ ከሆነ የሥራ ስንብት ክፍያ ማለት ‘Severance pay is money equivalent of one or two months’ salary that is offered by employers to employees who are laid off.’ይህም ወደ አማርኛ ቃል በቃል ስንመልሰው የሥራ ስንብት ክፍያ የሚባለው ለሠራተኛው በቅነሳ ወይም ከሥራ መገለል ወቅት የሚከፈለው የአንድ ወር ወይም ሁለት ወር ደምወዝ እንድሆነ ከላይ ከተሰጠው ትርጉም መረዳት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል Black’s Law dictionary 9th edition የሚከተለውን ትርጉም ይሰጠዋል፡-‘’severance Pay is Money (apart from back wages or salary) paid by an employer to a dismissed employee. Also termed as separation pay.’’ይህም ማለት ሠራተኛው ከሥራ ገበታ በሚለይበት ጊዜ የሚከፈለው ክፍያ መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡

በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የሥራ ስንብት ክፍያ የሚባለው በስንብት ወቅት ለሠራተኛው የሚሰጠው ካሳ መሰል ክፍያ መሆኑን እንረዳለን፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ.377/1996 የሥራ ስንብት ክፍያን ምንነት አስመልክቶ ትርጉም ከመስጠት ይልቅ የሥራ ስንብት ክፍያ የሚያስገኙ ጉዳዮችን መዘርዘር ይቀናዋል፡፡

በነገራችን ላይ በሌሎች ሀገራት የሕግ ሥርዓት እንደተመለከተው የሥራ ስንብት ክፍያ ሰፋ ያለ ይዞታ ሊኖረው እንደሚችል እንረዳለን፤ ለምሳሌ በአሜሪካ ለሠራተኛው አዲስ ሥራ እስኪያገኝ ድረስ የማፈላለጊያ የሚሆን እናመሰግናለን /"Thank you pay"/ ክፍያወችን ሁሉ ይጨምራል፡፡ በተለይም የዚህ ዓይነቱ ክፍያ አንድ ድርጅት ከሌላ ድርጅት ጋር በሚያደርገው ውህደት (merger) ወይም ጠቅልሎ መግዛት (take-over) ወቅት ሠራተኞች ሲሰናበቱ የሚሰጥ ክፍያ /"Golden-Parachute" የሚባለውንም ሊይዝ ይችላል፡፡

ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ ከግብር ጋር ተያይዞ ሲሆን የሥራ ስንብት ክፍያ ከግብር ነጻ ነውን? የሚለው ነጥብ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በአንዳንድ ሃገራት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ በሰጠው ውሳኔ (IRS V. US) የሥራ ስንብት ክፍያ ግብር የሚከፈልበት አርዕስት ሲሆን በአንዳንድ ሃገራት ላይ ደግሞ ከግብር ነጻ ያደርጉታል፤ በተለይም የፈረንሳይ ሕገ-መንግስታዊ ፍ/ቤት የሃገሪቱን የግብር ሕግ ጠቅሶ በሰጠው ብይንየሥራ ስንብት ክፍያ ከግብር ነጻ እንደሆን አስገዳጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በኢትዮጵያም ያለው የገቢ ግብር አዋጅም ጉዳዩን አስመልክቶ ግልጽ አቋም አልወሰደም፡፡ ነገር ግን አዋጅ ቁ.286/1994 አንቀጽ 13(ለ) ላይ "በቀጣሪወች የሚዋጣ ከሠራተኛ የወር ደምወዝ 15 ፐርሰንት ያልበለጠ የጡረታ መዋጮ፤ ፕሮቪደንት ፈንድ እና ማንኛውም ዓይነት የጡረታ ጥቅም" ከግብር ነጻ እንደሆነ አዋጁ በግልጽ ይናገራል፡፡ ታዲያ አዋጁ ፕሮቨደንት ፈንድን ጨምሮ ሌሎች መሰል ማኅበራዊ መድህኖችን ከግብር ነጻ ካደረገ የሥራ ስንብት ክፍያን በይበልጥ ደግሞ ከግብር ነጻ እንደሚያደርግ እሙን ነው፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ይዞታ፡-

የሥራ ስንብት ክፍያ በጹሁፋ መግቢያ ላይም እንደተመለከተው በኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ እንዳስቆጠረ መገንዘብ እንችላለን፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው አሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ. 377/1996 እንዲሁም ማሻሻያው አዋጅ ቁ. 494/1998 የሥራ ስንብት ክፍያ የሚያስገኙ ዘጠኝ የሚደርሱ ምክንያቶችን ሕጉ ሙሉ በሙሉ (Exhustively) ለመዘርዘር ይሞክራል፡፡ ለሁሉም ምክንያቶች ሕጉ በቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ ይህም የሙከራ ጊዜ ማጠናቀቅ/completing probation period/ እንደሆነ እና በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ.377/1996 አንቀጽ 11(3) መሠረት የአራባ አምስት(45) ቀን የሙከራ ጊዜን ማጠናቀቅ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቶችንም ወደ አራት ፈርጅ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ምድብ ከሕግ በሚመነጩ፤ በሠራተኛው አነሳሽነት፤ በአሠሪው አነሳሽነት እንዲሁም የተለያዩ አደጋበመድረሱ ምክንያት ብለን መፈረጅ እንችላለን፡፡

ሀ) ከሕግ ሚመነጩ ምክንያቶች፡-በዚህ ምድብ ውስጥ የሚመደቡት ሕጉ በራሱ የስንብት ክፍያ ያስገኛሉ ተብለው የተጠቀሱትን ሁኔታወች ተሟልተው ሲገኙ የሚስተናገዱ ጉዳዮችን ይይዛል፡፡ ይህም ማለት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ.377/1996 በአንቀጽ 24(4) ላይ የዘረዘራችው ጉዳዮች ተከስተው ሲገኙ ክፍያው ሊጠየቅ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምሳሌ ድርጅቱ በመክሰሩ (bankruptcy) ወይም በሌላ ምክንያት ቢዘጋ የሥራ ስንብት ክፍያ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ /የአዋጁ አንቀጽ 39(1)(ሀ) ይመለከተዋል፡፡ /በሌላ በኩል በማሻሻያ አዋጅ ቁ.494/1998 አንቀጽ "ሰ" እና "ሸ" ላይ የተመለከቱ ጉዳዮች በዚሁ ክፍል ይፈረጃሉ፡፡ አንድ ሰው የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፍን ተጠቃሚ ካልሆነ እንዲሁም የጡረታ እድሜው ደረሶ በጡረታ ሲገለል የጥሮታ ክፍያ ተጠቃሚ ካልሆነ የሥራ ስንብት ክፍያ ሊሰጥ እንደሚችል ህጉ በጥብቅ ያስቀምጣል፡፡

ሌላው ሕጉ እዛው ማሻሻያ አዋጅ ላይ በራሱ ያስተዋወቀው ነገር ቢኖር ቢያንስ አምስት አመት የሥራ አገልግሎት ያለው ሠራተኛ የሥራ ውሉን በህመም ወይም በሞት ምክንያት ቢያቋርጥ የሥራ ስንብት ክፍያ ሊያገኝ እንደሚችል ይናገራል፡፡

ለ) በሠራተኛው አነሳሽነት የሚመጡ ምክንያቶች፡-ይህ የሚሆንበት አንድም አሠሪው በሠራተኛዉ ላይ ሰብዓዊ ክብሩን እና ሞራሉን የሚነካ ጉዳይ በማድረጉ ወይም በወንጅል ሕግ መሠረት የሚያስጠይቅ አድራጎት በመፈጸሙምክንያት በሠራተኛው አነሳሽነት የሥራ ውሉ ቢቋረጥ የሥራ ስንብት ክፍያ መጠየቅ ይችላል፡፡ (አዋጁ አንቀጽ 39(1)(መ) ይመለከተዋል፡፡ )

ሌላው ደግሞ ከጥንቃቄ ርምጃ አለመውሰድ ጋር ይያያዛል፤ ይህም የሠራተኛውን ደኅንነት ወይም ጤንነት የሚያሰጋ አደጋ እንዳይደርስ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት እያለ አሠሪው እርምጃ ባለመውሰዱ ሠራተኛው የሥራ ውሉን ቢያቋርጥ የሥራ ሥንብት ክፍያ ያገኛል፡፡ (አዋጁ አንቀጽ 39(1)(ሠ) ይመለከተዋል፡፡ ይህም ጉዳይ በአዋጁ ምዕራፍ ሰባት ላይ የሥራ ቦታ ደኅንነት (occupational safety) ጋር የተያያዙ የአሠሪው ግዴታወችን ከመተላለፍ ጋር ይገናኛል፡፡

ሐ) በአሠሪው አነሳሽነት የሚመጡምክንያቶች፡-በዚህ ክፍል የሚመደበው የመጀመሪያው አድራጎት ከሕግ ውጪ በአሠሪው አነሳሽነት የሥራ ውል ሲቋረጥ የሥራ ስንብት ክፍያ ሊከፈል እንደሚችል አንቀጽ 39(1)(ለ) ላይ ተመልክቷል፡፡ የዚህ ድንጋጌ መኖር አንድምታው ከሕግ ውጪ ሠራተኛ እነዳይሠናበት የሚደረገው የሥራ ዋስትናን ለማረጋገጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአዋጁ አንቀጽ 28(2)(ሀ) እንዲሁም አንቀጽ 29 መሠረት ሠራተኛው በሚቀነስበት ጊዜ የሥራ ስንብት ክፍያ ሊከፈል እንደሚገባ ከአንቀጽ 39(1)(ሐ) ንባብ መረዳት እንችላልን፡፡ ይህንንም ጉዳይ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቅጽ 17 መዝገብ ቁ.105620 በእነ አቶ ሃብቴ ብርሃኑ(ስድስት ሰወች) እና አቶ ሙሉነህ ቡና ላኪ ትራንስፖርትና ትራንዚት የክስ መዝገብ ላይተመሳሳይ አቋም ወሰዷል፡፡

መ) ከአደጋ ጋር በተያያዘ፡- በዚህ ምድብ የሚመደቡት ምክንያቶች ደግሞ በሠራተኛው ላይ የተለያዩ ችግሮች፤ የማይድን በሽታ እና አደጋ በመጋረጣቸው የሚጠየቁ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በአዋጁ አንቀጽ 39(1)(ረ) መሠረት በሠራተኛው ላይ ሙሉ ወይም ከፊል የአካል ጉዳት በመደረሱ ሠራተኛው ሥራ ለመሥራት አለመቻሉ በህክምና ቦርድ ተረጋግጦ የሥራ ውሉ ሲቋረጥ የሥራ ሥንብት ክፍያ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በማሻሻያ አዋጁ አንቀጽ 2(ቀ) ላይ እንደተመለከተው በኤች አይ ቪ ኤድስ ህመም ምክንያት በሠራተኛው ጥያቄ ውሉ ቢቋረጥ የሥራ ስንብት ክፍያ ማግኘት ይችላል፡፡

ከላይ የተቀመጡት ምክንያቶች ብቻ ይዞ መብቱን የሚጠይቅ ሠራተኛ የሥራ ስንብት ያገኛል፡፡ ይህ ማለት ግን አሠሪው ለሠራተኛው የተሻለ መብት የሚስከብር ሌሎች የሥራ ውል ሊቋረጥባቸው የሚችሉ ምክንያቶችን አካቶ ሠራተኛውን የሥራ ስንብት ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን በሕብረት ሥምምነት/ Collective agreement/ ቢፈቅድ የሚበረታታ እንጂ የሚነቀፍ ተግብር አይደለም፡፡ /የአዋጁ አንቀጽ 134(2) ተመልክቷል፡፡

ይህ ሲሆን ግን መብቱ የሚጠየቅበት የጊዜ ገደብ እንዳለው ልብ ልንል ይገባል፡፡ ሕጉም በአንቀጽ 162(4) በግልጽ እንዳስቀመጠው በሥራ ውል መቋረጥ ምክንያት የሚጠየቁ ክፍያወች ማለትም የሥራ ስንብት ክፍያን ጨምሮ ውሉ በተቋረጠ በስድስት(6) ወር ውስጥ መቅረብ እንዳለባቸው እና ይህ ካልሁነ ግን በይርጋ ሊታገድ እንደሚችል በግልጽ ይደነግጋል፡፡

ይህንን አርዕስት ከመቋጨታችን በፊት የሥራ ስንብት ክፍያ መጠን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ የሥራ ስንብት ክፍያ መጠን ህጉ በግልጽ እንዳስቀመጠው ለመጀመሪያ የአንድ ዓመት አገልግሎት የሠራተኛው የመጨረሻ ሳምንት አማካይ የቀን ደምወዙ በ 30 ተባዝቶ የሚከፈል ሲሆን ከአንድ ዓመት በታች ያገለገለ ሠራተኛ እንዳገልግሎቱ ጊዜ እየተመዘነ ተመጣጣኝ ክፍያ ያገኛል፡፡ በአንጻሩ ግን የአገልግሎት ዓመቱ እያደገ በሄደ ቁጥር ለተጨማሪው የአገልግሎት ዓመት የአንድ ወር ደምወዙ አንድ ሶስተኛ እየታከለ ይከፈለዋል፡፡ ዳሩ ግን ጠቅላላ ክፍያ ከሠራተኛው የ12 ወራት ደምወዝ መብለጥ የለበትም፡፡ /የአዋጁ አንቀጽ 40 ይመለከቷል፡፡ /በአጭር ሂሳባዊ ቀመር ለመገንዘብ የሚከተለውን ሠንጠረዡን ይመልከቱ፡-

ሥሥ= ሀ+1/3xሀ(ለ-1) < 12ሀ

ይህም

ሥሥ= ሥራ ሥንብት ክፍያ

    ሀ=ወርሃዊ ደምወዝ

    ለ=የአገልግሎት አመት

ለምሳሌ አቶ ኩራባቸው 6,000 ብር ወርሃዊ ደምወዛቸው ቢሆን እና 11ዓመት ቢያገለግሉ የሥራ ስንብት ክፍያቸው የሚሆነው 6,000+1/3x6,000(11-1)< 12(6,000) ማለትም 6,000+20,000ይህም 26,000.00ብር ያገኛል ማለት ነው፡፡ የሚያገኘው ገቢም ከአመታዊደምወዙ(72,000) ያነሰ ነው፡፡

የሌሎች ሀገራት ልምድ፡-ጸሀፊው በዚህ ንዑስ ርዕስ ትኩረቱን ያደረገው የሥራ ስንብት ክፍያ በሌሎች አገራት ያለው ይዞታ እና ከሌሎች ልምድ የምንወሰደው ነገር ካለ ጠቆም ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ጸሀፊው የዳበረ እና የካበተ ልምድ ያላቸውን ሀገራት (Parent test approach of comparative study) በመጠቀም የቻይና፤ ደቡብ አፍሪቃ እና የታላቋ ብሪታኒያ ልምድ እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡

ሀ. ቻይና፡- በህዝባዊት ሪፖሊክ ቻይና የሥራ ውል ሕግ አንቀጽ 46 እና 47 እንዲሁም የሥራ ውል ማስፈጸሚያ ደንብ አንቀጽ 27 ላይ እንደተመለከተው የሥራ ውል በሚቋረጥበት ጊዜ ሠራተኛው ባገለገለበት ዓመት ልክ ተመሳሳይ የወር ደምወዙን ያገኛል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሠራተኛ አንድ ዓመት ካገለገለ የአንድ ወር ደምወዙን ክፍያ ያገኛል፡፡ በተመሳሳይ አሥራ አምስት ዓመት ከሠራ የአሥራ አምስት ወር ደምወዙን በስንብት ወቅት ተከፋይ ይሆናል፡፡

በአንጻሩም ለስደስት ወራት ካገለገለ ልክ አንድ ዓመት እንዳገለገለ ተቆጥሮ የአንድ ወር ደምወዝ በስንብት ወቅት ተከፋይ ይሆናል፡፡ ከስድስት ወር በታች የሠራ ከሆነም የግማሽ ወር ደምወዝ በክፍያ መልክ ያገኛል፡፡ በዚህም መሠራት የቻይና የሥራ ስንብት ክፍያ ሠራተኛውን የሚጠቅም ይመስላል፡፡

ለ. ደቡብ አፍሪቃ፡- በደቡብ አፍሪካ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ክፍል 41 በግልጽ እንደተመለከተው በሕግ ረገድ የተቀመጠ የሥራ ስንብት ክፍያ የለም፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ/አሠሪው በሚያደርገው ተቋማዊ ለውጥ፤ ቴክኖሎጂያዊ እድገት እና የውስጥ አሠራር ምክንያት የሚቀነሱ ሠራተኞች የሥንብት ክፍያ/redundancy pay/ ሊከፈል ይችላል፡፡ እዚህ ላይ redundancy pay የሚባለው ከቅነሳ ጋር የተያያዘ ክፍያ ስለሆነ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ከአንድ አመት በታች ያገለገሉ ሠራተኞች የክፍያው ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ ሆኖም ግን ከአንድ አመት በላይ ያገለገለ ሠራተኛ በአገለገለበት እኩል የሳምንት ክፍያ ያገኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ ዓመት ያገለገለ ሠራተኛ የአንድ ሳምንት ደምወዙን በስንብት ወቅት ተከፋይ ይሆናል፡፡ ሃያ አመት ያገለገለ ሠራተኛ የሃያ ሳምንት ደምወዙን ያገኛል ማለት ነው፡፡

ሐ.ታላቋ ብሪታኒያ፡- እኤአ በ1996 በወጣው የእንግሊዝ የሠራተኞች መብት ሕግ ክፍል 135 እና 155 እንደተገለጸው በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ለሚደረጉ ቅነሳወች ብቻ የሥራ ስንብት/redundancy pay/ ያገኛል ማለት ነው፡፡ በሕጉ መሰረትም ሠራተኞች የተባለውን መብት ለመጠየቅ ቢያንስ ሁለት አመት ለቀጣሪው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የእንግሊዝ የሠራተኞች መብት ሕግ ለየት የሚያደርገው ክፍያው በሚከፈልበት ወቅት የሠራተኛው እድሜ ከግምት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም መሠረት ከ22 ዓመት እድሜ በታች የሆነ ሠራተኛ 0.5 ወይም የግማሽ ሳምንት በእያንዳንዱ አመት አገልግሎት ተከፋይ ሲሆን ከ 22 ዓመት እስከ 40 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሠራተኛ በእያንዳንዱ የአገልግሎት አመት የአንድ ሙሉ ሳምንት ክፍያ በስንብት መልክ ያገኛል፡፡ እንዲሁም ሠራተኛው ከ 41 ዓመት እድሜ በላይ ከሆነው ለእያንዳንዱ ለሠራበት ዓመት አንድ ሳምንት ተኩል(1.5)ክፍያ ያገኛል ማለት ነው፡፡

የሚስተዋሉ ችግሮች፡-

ጸሐፊው በዚህ ረገድ የሚከተሉትን ችግሮች እንደ ክፍተት ተመልክቷል፡፡ የመጀመሪያው ክፍተት የሥራ ስንብት ክፍያ በማንኛውም የሥራ መቋረጥ ምክንያት የሚጠየቅ ክፍያ አድርጎ መገንዘብ ነው፡፡ በዚህም ችግር ሳቢያ ብዙ ሠራተኞች ስንብታቸው በአዋጁ አንቀጽ 39 ብሎም ማሻሻያው እንዲሁም በህብረት ስምምነት ላይ ከተቀመጡ ምክንያቶቸ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ሆኖም የሥራ ስንብት ክፍያን የሚጠይቁበት ሁኔታ አለ፡፡

ሌላው ጉዳይ ሕጉ የሠራተኛውን ልምድ፤ እድሜ፤ የሥራ ሁኔታ እና ሌሎች ምክንያቶችን ከግምት አለማሰገባቱ እንደክፈተት ይታያል፡፡

ሌላው ደግሞ የሥራ ስንብት የክፍያ መጠን እንደ ሀገሪቱ የምጣኔ ሃብት በየጊዜው ቢከለስ እና ለውጥ ማሻሻያ ቢደረግበት የሠራተኛውን ማህራዊ መድህን ሊያረጋግጥ የሚችል ቢሆን መልካም ነው፡፡

ማጠቃለያ፡- የሥራ ስንብት ክፍያ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ የሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትናን ሊያረጋግጥ የሚችል መንገድ ነው፡፡ የሥራ ስንብት ክፍያ የሚባለው በስንብት ወቅት ለሠራተኛው የሚሰጠው ካሳ መሰል ክፍያ ነው፡፡ የሥራ ስንብት ክፍያ ከሦስት ታሪካዊ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ እንደመጣ እንረዳለን፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ዘርዝር ያሉ የአሠሪና ሰተራተኛ ሕጎች /Labour codes/ መበራከት ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበረው አስከፊ ጊዜ በሺወች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው መልቀቅና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተካሄዱ ለውጦች መታየታቸው ሲሆን፤ የመጨረሻው ምክንያት ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጡ ለዜጎች የሚጨነቁ መንግስታት መበራከት /welfare state expansion/ ለጉዳዩ ትኩረት እንደሠጡት መገንዘብ ይቻላል፡፡ 

በመጨረሻም የኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ.377/1996 እንዲሁም ማሻሻያ አዋጅ 494/1998 የሥራ ስንብት ክፍያን በተመለከተ በሕጉ አስቀድመው በተወሠኑ ምክንያቶች ብቻ ሊከፈል እንደሚገባ በዝርዝር ይደነግጋል፡፡