Font size: +
14 minutes reading time (2871 words)

በኢትዮጵያ ሕግ የግል የኮንስትራክሽን ውሎች ምንነት፣ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦች

“And they said, Go to, let us build us a city and a tower, whose top may reach unto heaven; let us make as a name, lest we be scattered abroad upon the face of the whole earth…Therefore is the name of is called Babel; because the Lord did there confound the language of all earth…” Genesis 11:4-9

መግቢያ

የኮንስትራክሽን ውል በጣም ውስብስብና ብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ውል ነው፡፡ በይዘትም ሆነ በጥልቀት በጣም ሠፊ ከመሆኑ የተነሳ ውቂያኖስ መሰል ውል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለምን ቢባል በተለያየ ዕውቀትና ሙያ ዘርፍ የሚሳተፋ ሰወች ከመኖራቸው አልፎ በየደረጃው ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች መኖራቸው፤ የተለያዩ ጊዜ ወሰድ የዲዛይን ለውጦችና ማሻሻያወች ስለሚስተዋሉበት ጭምር  ነው፡፡

ኮንስትራክሽን የሰው ልጅ ወደ ምድር ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የነበረ፤ ያለና የሚኖር እንቅስቃሴ ነው፡፡ የመጀመሪያው ግንባታ የሚባለውም በጥንታዊ ጋርዮሽ ሥርዓተ ማኅበር የሰው ልጅ ለመጠለያነት የተጠቀማቸው መጠለያ ጎጆወች ናቸው፡፡ በዓለም ታሪክም አንኳር የሚባሉ ግንባታወች ወስጥ ዋና የሚባሉት በጽሑፋ መግቢያ ላይ የተጠቆመው የባቢሎን ግንብ፤ ግብፅ (ምስር) ውስጥ በፈርዖኖች 2700-2500 . የተሰሩ ፒራሚዶች፤ በንጉስ ሽን ሁኣንግ ትዕዛዝ በጄኔራል ሜይንግ ቲን 220 . ገደማ የተሰራው ታላቁ የቻይና ግንብ እና የሮማዊያን የውሃ ማቆሪያ ግንባታወች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ወደ ሃገራችን ስናመራም የግንባታው ዘርፍ ረጅም ጊዜ ያሰቆጠረ ሲሆን የአክሱም ሃውልት፤ የላሊለባላ ቋጢኝ ዐቢያት ክርስቲያን ግንብ፤ ብሎም የፍሲለደስ ግንብ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ለኮንስትራክሽን ከፍተኛ ትኩረት የሰጠች አገር በመሀኗ በተለይ ለመሠረተ ልማት፣ ለኢንዱስትሪና ለውኃ ለማት ሥራዎች ግንባታ ከፍተኛ ምዋዕለ ንዋይ ይውላል:: ለእነዚህም ውሎች ማስፈፀሚያ በርካታ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ውሎች ይደረጋሉ፡፡

በኢትዮጵያም የኮንስትራክሽኑን ዘርፍ አስመልክቶ የፍትሐብሔር ሕግ፤ የፌዴራል መንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ . 649/2001 የሕንፃ አዋጅ 624/2001 የኮንስትራክሽን መሣሪያወች ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ . 177/1991 የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መመሪያ፤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ግዥ መመሪያወች እና የሲቪል ግንባታወች ወጥ የሆኑ ውሎች (standard contracts for construction of civil works) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ጸሐፊው አብይ ትኩረቱን ያደረገው በኢትዮጵያ ሕግ የግል የኮንስትራክሽን ውሎች ምንነት፤ የኮንስትራክሽን ውል ዓይነቶች እና የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ለመዳሰስ ብሎም አንዳንድ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለመጠቆም ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ውል ፅንሰ ሃሳብ

የኮንስትራከሽን ውል ምን ማለት ነው? የሚለውን ነጥብ ከማየታችን በፊት የኮንስትራክሽንን ትርጉም መልከት እናድርግ፤ ኮንስትራክሽን ጥሬ ቃሉ እንግሊዘኛ ሲሆን አመጣጡም ከላቲንኮንስትራክሽነምከሚለው ነው፡፡ ትርጉሙም ማሳባሰብና መገንባት እንደማለት ነው፡፡ ኮንስትራክሽን ማለት መሠረተ ልማት የመገንባት ሂደት ነው፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ፤ የዲዛይን ማህንዲስ፤ የግንባታ ማህንዲስ፤ አርክቲክት (ቀራፂ) ወጭ ተማኝ (quantity surveyor) እና ተቆጣጣሪወችን ጨምሮ ብዙ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ብላክስ ሎው መዝገበ-ቃላት ግንባታን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል፡- Construction is the act of building by combining or arranging parts or elements; the thing so built.

በሌላ በኩል 2006 . በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ኮንስትራክሽን የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡-

“Construction” means a provisions of combination of goods and services carried out under or over ground for the development, extension, installation, repair, maintenance, renewal, renovation, alteration, excavation, dismantling or demolition of a fixed asset including building and engineering infrastructure.”

ታዲያ! ኮንስትራክሽን ከግንባታ ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ ከሆነ የኮንስትራክሽን ውል ምንድን ነው? በነገራችን ላይ ከላይ የተቀመጠውን የኮንስትራክሽን ውል ትንታኔ ከማየታችን በፊት 1952 . የወጣው የፍትሐብሔር ሕግ የግል የኮንስትራክሽን ውሎችን በሁለት ክፍል ለመክፍል ሞክሯል፡፡ የመጀመሪያው ከአንቀጽ 2610-2631 ሌላኛው ደግሞ አንቀጽ 3019-3040 የተመለከተው ነው፡፡

ይኸው የፍትሐብሔር ሕግ የኮንስትራክሽን ውልን በተመለከተ ስለ ሥራ ውል በሚናገርበት ክፍል አንቀጽ 2610 ላይ የሚከተለውን ነጥብ አስቀምጧል፡-

የሥራ ማከናወኛ ውል ማለት አሠሪው በገባው ውለታ ለአንደኛው ወገን የሥራ ዋጋ ሊከፈለው ሥራ ተቋራጭም በኃላፊነት የተሰጠውን አንድ ሥራ በገባበት ውለታ ሊፈፅም በሁለት ወገነኖች መካከል የተደረገ ውል ነው፡፡ ’’

ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው በመጀመሪያ የዚህ ዓይነቱ ውል ተቋራጩ ያለ አሠሪው መሪነት በነፃነትና በራስ ኃላፊነት የሚገባው ውል ነው፡፡ ይህም በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ እንደተመለከተው አይደለም፡፡

ሌላው ተዋዋዮች የሚገቡት ውለታ ሰጥቶ በመቀበል (reciprocal obligation) መርህ ላይ የተመሠረተ ውል መሆኑ ነው፡፡ ለምን ቢባል በሁለቱም ወገኖች መካከል የሚፈጠረው ግዴታ ስላለ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍትሐብሔር ሕጉ ስለ ማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በሚናገርበት ክፍል ላይ እንዲህ የሚል ንባብ እናገኛለን፡-

አንዱ ወገን ተዋዋይ ለሌላው ወገን ተዋዋይ አንድ ቤት፤ አንድ የቤት ክፍል ወይም ገና የሌለ አንድ የሚሠራ ሕንፃ ለመስጠት ግዴታ የሚገባበት ውል አንድ ሕንፃ ሥራ ውል ይባላል እንጅ የሽያጭ ውል ሊባል አይችልም፡፡

የኮንስትራከሽን ውሎችን ምንነት በተመለከተ ሁድሰን የተባለ የዘርፋ ምሁር እንዲህ ይገልፃቸዋል construction contract as "an agreement under which a person, called variously the builder or contractor, undertakes for reward to carry out for another person, variously referred to as the building owner of employer, works of a building or civil engineering character."

በሌላ በኩል በቀድሞው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር በአሁኑ ጊዜ የከተማ ልማት፤ የቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተብሎ በሚጣራው አካል በተዘጋጀው የሲቪል ግንባታወች ወጥ የሆኑ ውሎች (standard contracts for construction of civil works) ላይ በግልፅ እንደሠፈረው የኮንስትራክሽን ውል የሚባለው Contracts means the conditions of contract, specifications, methods of measurement, drawings, priced bill of quantities, schedules of prices and rates, the letter of acceptance, the contract agreement, the addenda and other documents thereof.

ከላይ ሠነዱ የኮንስትራክሽን ውሎችን ምንነት ከመተርጎም ይልቅ ወሉ ሊይዛቸው የሚገቡ ነገሮችን ዘርዘር አድርጎ ለማስቀመጥ ይሞክራል፡፡

የኮንስትራክሽን ውሎች ምንነትን ስናነሳ ከተራ ውሎች የሚለዩበት ሌላው ነገር ቢኖር መደበኛ ውሎች የሁለትዮሽ ውሎች (bilateral undertakings) ሲሆኑ የኮንስትራክሽን ውሎች ግን ብዙ ወገኖች የሚሳተፋበት (multilateral contracts) ናቸው፡፡

ስለ ኮንስትራክሽን ውሎች ሲነሳ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ነገር ቢኖር የኮንስትራክሽን ውል ሠነድ በጣም ሰፊ በገፅ ብዛት ረገድም በትንሹ ከመቶ እስከ ሺህ ገፅ የሚደረስ ውል ነው፡፡ ለምን ቢባል በውስጣቸው ብዙ ጠቅላላና ልዩ መገለጫወች ያሉት ከመሁኑ የተነሳ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ውሉ አጅግ ከመብዛቱ የተነሳ ብዙ የሚጣረሱና የሚጋጩ ድንጋጌወች ሊኖሩ እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ውል ዓይነቶች

የኮንስትራክሽን ዘርፋ እያደገ የመጣ የኢኮኖሚ ዘርፍ ከመሆኑ ባሻገር ይህንን ዘርፍ በበቂ ሁኔታ ለመግዛትም በማሰብ የተለያዩ ሕግጋት ከወጡ ሠንበትበት ብለዋል፡፡

ከእንዚህ ሕጎች መብዛት ጋር ተያይዞ የኮንስትራክሽን ውሎች የሕግ ማዕቀፍም እንዲሁ የተለያየበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡

በዋናነት ግን ከፕሮጀክት ባለቤትነት አንፃር የኮንስትራክሽን ውሎች በሁለት ዘርፍ መፈረጅ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የመንግሥት የኮንስትራክሽን ውሎች (government/public construction contracts) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የግል የኮንስትራክሽ ውሎች (Civil construction contracts) ናቸው፡፡

ወደ መጀመሪያው ውል ዓይነት ስናመራ የግል የኮንስትራክሽን ውሎች የፕሮጀክት ባለቤት ግለሰቦች ወይም የግል ኩባንያወች ሲሆኑ ይህም በፍትሐብሔር ሕግ በተበታተነ ክፍል ተቀምጦ አናገኛለን፡፡

የግል የኮንስትራክሽን ውል አንዱ የውል ዓይነት እንደመሆኑ መጠን አጠቃላይ የውል ሕግ (አንቀጽ 1675-2026) በልዩ ክፍሉ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ በተለይም በፍትሐብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 2610-2631 የተቀመጡ ድንጋጌወች ስለ ሥራ ማከናወኛ ውል ቢናገሩም ቅሉ በዋናነት መሉ ትኩረታቸው ግን ስለ ግሉ ግንባታ ውሎች ነው፡፡ ነገር ግን የሥራ ማከናወኛ ውሎች ተፈፃሚነትና የሕጉም ወሰን በጣም የተገደበ ነው ለምን ቢባል የፍ//ቁ፣ 2610-2631 የሚፈፀሙት የግንባታ ወጪያቸው ከአምስት መቶ (500.00) የኢትዮጵያ ብር በማይበልጡ ሥራወች ላይ ነው፡፡

ሌላው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሥራ ማከናወኛ ውል በሚለው ከፍል (ከአንቀጽ 3019-3040) ውስጥም ከፍተኛ ሽፍን ተሰጥቶት ይገኛል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የመንግሥት የኮንስትራክሽን ውሎች የሚባሉት መንግሥት ለህዝብ ጥቅም ብሎ የሚገባቸው ውሎች ሲሆኑ በተለይም ደግሞ የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች የግንባታ ሥራ ለማካሄድ የሚገቧቸው ውሎች እና የግዥ ውሎች (Procurement contracts) ናቸው፡፡

ይህንንም ዘርፍ የሚመለከቱ ሕጎች የአስተዳደር ውሎች በጠቅላላው (የፍትሐብሔር አንቀጽ 3131-3206) የመንግሥት ተቋራጭነት ውል/contract of public works (የፍትሐብሔር አንቀጽ 3244-3296) የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የግዠና ንብረት አስተዳደር አዋጅ .649/2001 እንዲሁም በየክልሎች የወጡ የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ታዲያ የግል ኮንስትራክሽን ውሎችን ጉዳትንና ኃላፈነትን ከመቀበል አንፃር በሦስት መክፈል ይቻላል፡፡

) ጥቅል ውል (Lump sum contract)- የዚህ ዓይነቱ ውል በባህሪው ቀድሞ የተገለፀና የታወቀ ነው፡፡ ስለ ጥቅል ውሎች በተመለከተ ቲሆን ኬቲንግ የተባለ ጸሐፊ ህንጻ ተቋራጩ በተገለፀው ዋጋ መሠረት ሥራውን መፈጸም እንዳለበት ጭምር ይናገራል፡፡ የፍትሐብሔር ሕጋችንም ይህንን በተመለከተ በአንቀጽ 3023(1) ላይ የሚከተለውን ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡

የሥራ ተቋራጭ ለመፈጸም የተዋዋላቸው ሥራወች ዋጋ በጅምላ ሊሆን ይችላል፡፡ ’’

በሌላ በኩል አሠሪው ውሉን ያፈረሠ እንደሆነ ሥራ ተቋራጩ ስምምነት የተደረገበትን የጅምላ ዋጋ ለማግኘት መብት አለው፡፡

የዚህ ዓይነት ውሎች በመንግሥት የግንባታ ውሎች ላይም የታወቁ ናቸው፡፡ የጥቅል ውሎች ዋነኛ ችግር የሚባለው ተቋራጩ (contractor) ያልጠበቀው ጉዳት ሊደርስበት ይችላል፡፡ ለምን ቢባል ዋጋቸው አስቀድመው በውል ስለተወሰነ በገበያው የዋጋ ማስተካከያ ወይም ግሽበት ቢኖርም እንኳ በገባው ውል መሠረት ሥራውን አጠናቆ የተባለውን ዋጋ ሊወስድ ስለሚችል ነው፡፡

) እንደገና የሚለካ ውል (Re-measurement Contract)- እነዚህ ውሎች ደግሞ የጅምላ ወሎች ተቃራኒ ሲሆኑ ትኩረታቸውን ያደረጉትም የሥራውን ዝርዝር ሁኔታ በጥልቀት በማየት እንዲሁም በውሉ አባሪ በሆነው የዋጋ ሠንጠረዥ መሠረት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ውል ሌላኛው መገለጫቸው ውሉ በሚፈረምበት ጊዜ የሥራው መጠንና ወሰን የማይታወቅ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ይንን ጉዳይ በአንቀጽ 3023(3) ላይ እንዲህ በማለት ለመግለፅ ይሞክራል፡፡

ዋጋው በጅምላ ወይም አቅራቢያ ግምት ያልተወሰነ እንደሆነ የሥራው ዋጋ የሚገመተው ለሥራ በዋሉት ነገሮችና ለሥራው አፈጻጸም አስፈላጊ በሆነው ሥራ ግምት መሠረት ነው፡፡

የሥራ ዋጋ በመሣሪያዎቹ (materials) እና ሥራውን ለመፈጸም አስፈላጊ በሚሆነው ሥራ ዋጋ መሠረት የተወሰነ የሆነ እንደሆነ የውሉ መፍረስ ማስታወቂያ ለሱ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ ለተሰራባቸው መሣሪያዎችና ለተሠሩት ሥራዎች ተቋራጩ የዋጋ ግምት ለማግኘት መብት አለው፡፡

እንደገና የሚለኩ ውሎች በመንግሥት የግንባታ ውሎችም ይታወቃሉ፡፡ የእንዚህ ውሎች ችግር የሚባለው ደግሞ በሥራ ውሉ በግልጽ ያለተመለከቱ ማሻሻያ ሥራወች በሚሠሩበት ጊዜ ከዋጋ ክፋያ ጋር የሚነሱ አለመግባባቶች ይሰተዋላሉ፡፡

) ወጪ የሚሸፈንበት ውል (Cost-reimbursement contact)- ከስሙም ለመረዳት እንደምንችለው የዚህ ዓይነቱ ውል በመጀመሪያ ደረጃ ግምታዊ ዋጋ ይቀመጣል፤ ከዚያም የተቋራጩ ጠቅላላ ወጪ ከበለጠ አሠሪው ወጪ የሚሸፍንበትን ሁኔታ እናገኛለን፤ በሌላ በኩል የሥራው ወጪ ከተገመተው ካነሰም እንዲሁ ለአሠሪው ገንዘቡ ይመለስለታል፡፡

ይህም የበአብዛኛው የሚከሰት ጉዳይ ሲሆን መንስዔውም በአብዛኛው አንድም የግንባታ ለውጦች በመኖራቸው አሊያም ውል በሚመሠረትበት ጊዜና ሥራው አልቆ በሚረከብበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ልዩነት በመኖሩ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጋችን ለእንደዚህ ዓይነት ውሎች እውቅና የሠጠበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ በተለይም አንቀጽ 3032(1) ላይ አንደተቀመጠው ተቋራጩ ከሚሠራው ሥራ እንዲቀነስ በሥራ አሠሪው ተጠይቆ ከሠራና የሥራ ለውጡ የተቋራጩን ወጪ ከቀነሠለት በውሉ ተወስኖ ከነበረው ዋጋ ላይ እንዲቀነስለት አሠሪው ተቋራጩን ለመጠየቅ ይችላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሠሪው በጠየቀው የሥራ መለዋወጥ ምክንያት የሥራ ተቋራጩን ወጪ የሚያበዛ ወይም ተጨማሪ ሥራ የሚያስከትል ወይም አላፊነቱን የሚያከብድበት ከሆነ ለተጨማሪው ሥራ ዋጋውና የሚከፈለው አበል ተጨምሮ እንዲከፈለው አሠሪውን ለመጠየቅ ይችላል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 47526 በዛፍኮ ኃላ/የተ/የግል ማኅበር እና በብሔራዊ ማህንዲሶች ሥራ ተቋራጭ ድርጅት መካከል በነበረው ክርክር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የግንባታ ውሎች ውል በተደረገበት ፎርም አይሻሻሉም፤ በዚህ አግባብ የተደረጉ ወሎች የሚገዙት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 3019-3040 መሠረት በልዩ ሕግ የሚገዙ ከመሆናቸው ባሻገር ውሉም ተፈጸመ የሚባለው ተዋዋዮች ስለ ሚሰራው ሥራም ሆነ ስለ ክፍያ ከተስማሙ ጭምር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ብሎም አንደ ሥራ ተቋራጭ የሥራ ለውጥ (alterations) ካደረገ ተጨማሪ ክፍያ ይገባዋል፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1721 በጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም ለምን ቢባል ስለ ማይንቀሳቀስ ንብረት ውል የፍትሐብሔር ሕጋችን ልዩ ሕግ በማስቀመጡ ነው፡፡ ሲጠቃለልም እንደዚህ አይነት ውሎች ወጪ የሚሸፈንበት ውል (Cost-reimbursement contact) ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ እንችላለን፡፡

የሚስተዋሉ ችግሮች

በዚህ ክፍልም ጸሐፊው ሙሉ ትኩረቱን ያደረገው በግል የኮንስትራክሽን ውሎች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ማሳየትና መለየት ሲሆን ዋና ዋና የሚባሉትም የሚከተሉት ናቸው፡፡

. የውል አመሰራረት ችግር፡-

እንደሚታወቀው ውሎች በተዋዋዮች ላይ ግዴታ የሚጥሉ ሕጎች ናቸው፡፡ ውል ተመሠረት የሚባለውም በሕጉ መሠረት ችሎታ ያላቸው ተዋዋይ ወገኖች ወደውና ፈቅደው የሚገቡበትን ግዴታ አውቀው ሲፈፅሙና በሕጉ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታወች እንደ የውሉ ጉዳይ እንዲሁም የውል ቅርፅ/form/ ሲያሟሉ ጭምር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ወደ ያዝነው ጉዳይ ስናመራም የኮንስትራክሽን ውሎች በተለምዶው በጽሑፍ የሚደረጉ ውሥብስብ ውሎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ውል ሲመሠረት የተለያዩ ሠነዶች ከመፈረማቸው ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስለውል በጠቅላላው እንደተገለፀው ውል ተፈፀመ የሚባለው ተዋዋዮች በሚዋዋሉባቸው እያንዳንዱ ዝርዝር ሁኔታወች ሲስማሙ ነው፡፡

ሆኖም ግን በአብዛኛው የኮንስትራክሽን ውሎች የሚስተዋለው ችግር ውል በሚመሠረትበት ጊዜ በእያንዳንዱ የውል ነጥቦች ላይ መስማማት እጅግ በጣም አዳጋችና ውስብስብ መሆኑ ጭምር ነው፡፡ እንዲሁም የውል ሰነዶች በጣም ብዙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ግጭቶች መከሰታቸው እሙን ነው፡፡ ለማስረጃ ያህል በውል ስምምነቱ፤ የጨረታ እሽታ ደብደቤው፡ በጨረታ ሰነዱ፤ በጠቅላላና ዝርዝር መገለጫወችና ሌሎች ውሎች መካከል መጣረስና ግጭት ሲኖር እንዴት ይፈታል ሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው?

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የዓለም አቀፋ የአማከሪ ማሃንዲሶች ፌዴሬሽን (FIDIC 1999) ወይም ቀዩ መጽሐፍ ወጥ ውል አንቀጽ 1.5 ላይ የሚከተለውን አስቀምጧል፡፡

እንደየቅደም ተከተላቸው ትርጉሙ በሚያስፈልግበት ወቅት ሊሰጠው የሚገባ ቅደም ተከተል በመጀመሪያ ደረጃ የውል ስምምነት፤ በሁለተኛ የሚመጣው ጨረታ ተቀባይነት ማግኘቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ከዚያም ጨረታው፤ በመቀጠለም ልዩ የውል ሁኔታወች አለፍ ሲልም ጠቅላላ የውል ሁኔታወች፤ ከዚያም የሥራ ዝርዝር ሁኔታወች፤ ሁኔታው ከበድ ሲል ወደ ንድፎች እናመራለን በመጨረሻም የዋጋ ተመን መዘርዝሮችን በማየት መፍታት እንደሚቻል መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሌላው እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነገር አለመግባባቶች ሲፈጠሩ እንደነገሩ ሁኔታ ማሃንዲሱ አስፈላጊ ትእዛዝና ምክር ሊሰጥ እንደሚችል ነው፡፡ ይህም ሀሳብ 1994 በወጣው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የሲቪል ሥራወች ወጥ ውል ላይ በግልጽ ተመልክቷል፡፡

. ከንዑስ ተቋራጭነት ጋር የሚታዩ ክፍተቶች፡-

ንዑስ ተቋራጭ ማለት በኮንስትራክሽን ቋንቋ የተቋራጩን ሥራ በከፊል ወይም የተወሰነ ሥራ ለመሥራት ለሌላ ተቋራጭ የሚሰጥበት መንገድ ነው፡፡

ከንዑስ ተቋራጭነት አስፈላጊነት ጋር በተያያዘ ጆን መርዶክ የተባለ ጸሐፊ የሚከተለውን ነጥብ አስቀምጧል፡-

ንዑስ ተቋራጭ መኖሩ አንድ ኮንትራክተር ለሠራተኞቹ ከሥራ ጋር የተያያዙ ወጪወችን እንደ ስልጠና፤ የህክምና ክፍያ፤ የጡረታ ክፍያወችን ጨምሮ መሰል ክፍያወችን የሚያስቀር ከመሆኑ ባሻጋር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የተለያየ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ዘርፈ ብዙ መያተኞች መጠየቁ እንዲሁም የዋናውን ተቋራጭ ከማስተላለፍና ማስረከብ ጋር ተያያዙ ስጋቶችን/risks ይቀንስለታል፡፡

የፍትሐብሔር ሕጋችን ንዑስ ተቋራጭነትን በተመለከተ ስለ አስተዳደር ውሎች በሚናገረው ክፍል አንቀጽ 3201(2) ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡፡ በዚህም መሠረት ንዑስ ተቋራጭ ማለት ከዋናው ተቋራጭ የተስማማ ሁለተኛ ተቋራጭ የሚባለውም ከተዋዋዩ ውሉን በከፊል ለማስፈጸም ካንድ ሦስተኛ ወገን ከሆነ ሰው ጋር የሚደረግ ውል ነው፡፡

በግል የኮንስትራክሽን ዘርፍም የተለመደ ተገባር ቢሆንም የሕግ ማዕቀፋ ግን በጣም ጠበብ ያለ ይመስላል፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ የሲቪል የኮንስትራክሽን ውሎችን በሚገዛበት ክፍል የሚከተለውን ደንጋጌ አስቀምጧል፡፡

በአንድ የሕንጻ ሥራ ተቋራጭነት ውስጥ የሚሠሩ ሥራ ተቋራጮች የሠሩበትን ሥራ ክፍያ ዋጋ ለመጠየቅ ክሳቸውን ባቀረቡበት ጊዜ አሠሪው ለሥራ ተቋራጩ ሊከፍል በሚገባው ገንዘብ መጠን ባሠሪው ላይ ቀጥታ ገንዘባቸውን የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ በተግባር የሚገጥመው ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው  ተቋራጩ አሰሪው (ደንበኛው) ሳያውቅ ሌላ ንዑስ ተቋራጭ መቅጠሩ ወይም ሥራውን መስጠቱ ነው፡፡ ከዚህ ችግር በመነሳት ከሕጉ አንጻር የንዑስ ተቋራጭነት ውጤቱ ምንድን ነው? የሚለውን ነጥብ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የሲቪል ከንስትራክሽን ውሎችን የሚመለከተው የፍትሐብሔር ሕግ በዝርዝር ያስቀመጠው ነገር የለም ሆኖም ግን የሲቪል የኮንስትራክሽን ውሎችን ለሌላ ተቋራጭ መልቀቅ (assignment) በፍትሐብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 1962-1985 ባሉ ደንጋጌወች ይመራል፡፡

በሌላ በኩል አሠሪው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሲሆን እና ተቋራጩና ንዑስ ተቋራጩ የግል ሠራተኞች ወይም ድርጅቶች በሚሆኑበት ጊዜ የፍትሐብሔር ሕጉ የሚከተለውን ነጥብ አስቀምጧል፡-

ሳይፈቀድለት የተደረገው ውልን ለሌላ መልቀቅ ወይም ከዋናው ተቋራጭ የተስማማ ሁለተኛው ተቋራጭ አስተዳደር መሥሪያ ቤቱን መቃወሚያ ሊሆን አይችልም፡፡

እንዚህም ስለውል ጥፋት ተቆጥረው በተዋዋዩ ጉድለት ውሉን የሚያፈርሱ ይሆናል፡፡

ለነገሩ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚው ችሎትም ይህንን ጉዳይ በጨረፍታ አይቶት አልፏል፡፡ በዚህ ጸሐፊ እምነት ሰበር አስቀድሞ ሊያየው የሚገባ ነገር ኮንትራክተሩ ከአስተዳደር መሥሪያ ቤት ጋር በሚፈጽመው ውል ላይ ሌላ ተቋራጭ ሲተካ (assign) ሲያደርግ ፈቃድ ማግኘት የግድ ነው (Administrative authorization necessary አንቀጽ 3202) ይላል ታዲያ ይህን ዓይነት ፍጹም ክልከላ ካለ ወደ ተቋራጩና ንዑስ ተቋራጩ ስምምነት ሕግ አንቀጽ 1731 ማምራቱ ለምን አስፈለገ፡፡ ሌላው ነጥብ አሠሪው ይህንን ጉዳይ ካልተቃወመ ብቻ ነው ምናልባት ወደ ስምምነታቸው ሕጋዊነት የሚነሳውና ሌሎች የማጠራት ሥራ የሚሄደው፡፡ በነገራችን ላይ በተያዘው የሰበር ጉዳይ ግን ወደ // 1962 ተከታዮቹ ድንጋጌወች ማምራት ተገቢ አይደለም፡፡

. ከሥራ ርክክብ ጋር የሚታዩ ችግሮች፡-

እንዲህ ዓይነት እክሎች የሚስተዋሉት የኮንስትራክሽን ሥራ ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ  ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ የሕንጻ ግንባታው መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጉድለቶች ማየቱ አዲስ ነገር አይደለም፤ ለአብነት ያህልም የግንባታወች መሠነጣጠቅ፡ እቃወች በሠራተኞች መሰረቅ፤ እየገነቡ ሕንጻውን ሥራ ማስጀመር፤ ብሎም የሳኒቴሽን ችግሮች ከብዙ በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አሁን አሁን ሕንጻ ግንባታ ሲታሰብ መሠረቱ ወጥቶ በጊዚያዊነት ትነሽ እንዳለቀ ሕንጻው ወደ አገልግሎት የሚሄድበት ሆኔታ አለ፡፡ ታደያ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት በሕጋችን እንዴት ይታያል የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ በመሠረቱ FIDIC እስታንደዳርድ መሠረት ሥራው ሙሉ በሙሉ እንዳለቀ ይረከባል ይላል፡፡

በሌላ በኩል የፍትሐብሔር ሕጉ በግልፅ እንደደነገገው በከፊልም ሥራውን መቀበል እንደሚቻልም ጭምር ነው፡፡ ታዲያ ተቋራጩ ሥራውን ካስረከበ በኃላ ለሚደርሱ አንዳንድ ጉድለቶች ማለትም ከሥራ ጋር የተያያዙ ወይም በተሠራበት መሬት ዐይነት ምክንያት ለሚደርሱ ብልሽቶች ተጠያቂ ነው፡፡

ተቋራጩ በተባለው ቀን ባያስረክብስ ምን ዓይነት ኃላፊነት አለበት ቢባል አንድም ስለ ውል በጠቅላላው በተለይም ስለ መቀጮ በሚናገረው ክፍል ውስጥ በአንቀጽ 1889 መሠረት ሊጠየቅ ይችላል ወይም ለአሰሪው የተጣራ ኪሳራ (liquidated damages) የውሉን 1/1,000 ለዘገየበት ሊከፍል ይችላል፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ያለቁ ክፍሎችን ሥራ ማስጀመርና የገቢ ምንጭ ለመድረግ መሞከር አብዛኛው ባለቤት ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ ያለቀው ህንፃ ያላለቀውን አገልግሎ ይሥራ የሚለው አስተሳሰብ ነው፤ የጎንዮሽ ጉዳት አለው ዳሩግን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሥራ አይጀምሩ ባይባልም በተቻለ መጠን በደንብ በባለሙያ ተረጋግጠው ወደ ሥራ ቢገባ መልካም ነው፡፡

.የሕጉ አለመታወቅ እና የወጥ (ስታንዳርድ) ውሎች በየወቅቱ አለመከለስ፡-

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፋን የሚገዙ ሕጎች በተለያዩ አዋጆች፤ደንቦችና መመሪያወች ተበታትኖ ከመገኘቱም በላይ የሕጉ ይዘትና ምንነትም አለመለየቱሌላው ቀርቶ በሕግ ባለሙያዎች፤ ዳኞችና ጠበቆች ጭምር ይበልጥ አለመታወቁ ጉዳዩን  የበለጠ ውስብስብ ያደረገዋል፡፡

በተለየም ደግሞ የሲቪል ኮንስትራክሽን ሥራወችን የተመለከቱ የፍትሃ-ብሄር ድንጋጌዎች አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በበቂ ስለማይገዛ አሁን ከደረስንበት የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ እድገት አንጻር ተጣጥመው ቢሄዱ መልካም ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የኮንስትራክሽን ውሎች ከሌሎች ውሎች ለየት የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ ይህም ወጥ ውል (standard contract) መከተላቸው ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ውሎች ወቅቱን ጠብቀው መከለስ ይኖርባቸዋል፡፡ ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስናመራ ግን እኤአ 1994 ከወጣው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የሲቪል ሥራወች ወጥ ውሎች እስካሁን ድረስ ሥራ ላይ ያለና ያለተከለሰ ነው፡፡

. ከፈቃድና ምዝገባ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮች፡-

አብዛኛውን ጊዜ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ወይም ብሎም ግለሰቦች የግንባታ ሥራወች ከማከናወናቸው በፊት የንግድ ፈቃድና ምዝገባ ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡  በተለይ ደግሞ ፈቃድ ሲሠጥ የብቃት ማረጋገጫ ሳይቀርብ  መከናወኑ ብዙ ችግሮች ለመከሰቱ እንደ መንስኤ ይወሰዳል በተለይም አሁን አሁን የሚሰሩ ሕንጻወች የጥራት ጉድለት ብሎም የአገልግሎት ዘመን ማነስ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ይፈጥራል፡፡

ይህንን በተመለከተም 2006 . የተዘጋጀው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ የሚከተለውን ነጥብ አስቀመምጧል፡፡

ስለዚህ ምነጊዜም ቢሆን የኮንስትራክሽን ሥራ ውል ከመፈፀሙ በፊት አሠሪው ተቋራጩ አስፈላጊው የሚያ ብቃት መኖሩን ማረጋገጥ አለበት፡፡

ማጠቃለያ

የኮንስትራክሽን ውሎች በጣም ሰፊ ብሎም ብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ዘርፈ ብዙ ውል ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ውል አንዱ መገለጫው ብዙ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፉ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወጥ በሆነ መንገድ መዘጋጀታቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የሲቪል ኮንስትራክሽን ውሎችን በተመለከተ የፍትሃብሄር ሕግ በሁለት ክፍል ይቃኘዋል፡፡ በተለይም የግንባታ ወጪያቸው ከአምስት መቶ ብር በታች ለሆኑት ውልች ከአንቀጽ 2610 እስከ 2638 ሲያስቀምጥ በሌላ በኩል የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሥራ ውልን አስመልክቶም ከአንቀጽ 3019 እስከ 3040 ሥለ ሲቪል ኮንስትራክሽን ውሎች ይናገራል፡፡ እንዲሁም እኤአ 1994 በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የወጣው የሰቪል ሥራወች ወጥ ውልም ሌላኛው ተጠቃሽ ሕግ ነው፡፡

የመፍትሔ ሀሳቦች

የኮንስትራክሽን ውሎች እጂግ ውስብስብና ችግር የማይታጣበት ቢሆንም በሲቪል ግንባታ ዘርፍ ለሚታየው አንዳንድ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ጸሐፊው የሚከተለውን የመፍተሄ ሀሳብ ያቀርባል፡-

የሲቪል ሥራወች ንዑስ ተቋራጭነት በተመለከተ ሕጉ በግልፅ ባያስቀምጥም ልክ እንደ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የኮንትራክሽን ሥራ ተቋራጩ ለሌላ ተቋራጭ ሲያስተላልፍ አሰሪው እውቅና መሰጠትና መፍቀድ አለበት፡፡

በቅርብ የተዋቀረው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስለ ሲቪል የኮንስትራክሽን ውሎች የተመለከቱ የፍትሃ-ብሄር ድንጋጌወች ዝርዝር ጥንናት በማድረግ ቢያሻሽላቸውና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር እንዲሄዱ ቢደረግ፤

ተዋዋዩች በተቻለ መጠን የኮንስትራክሽን ውል ሰነዶችን በጥልቀት አንብበው ወደ ውል ቢገቡ፤

የሲቪል ግንባታ የሚያከናውኑ ሰወችና ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አግባብ ባለው አካል በተለይም አዲስ በተዋቀረው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ቢሰጥ መልካም ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ስለቀዳሚ ምርመራ (Preliminary Inquiry) ፍርድ ቤት ተልዕኮ፣ ሥልጣን...
የማይደፈረውን ፍርድ ቤት መድፈር

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024