የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በሰበር ችሎት ዉሳኔዎች ቅጽ 14 መግቢያ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፤ “ለተመሣሣይ ጉዳዮች በጣም የተራራቁ ዉሣኔዎችን በመስጠት ይታይ የነበረዉን ችግር በመቅረፍና የዉሣኔዎችን ተገማችነት በማረጋገጥ ረገድ የሰበር ዉሣኔዎች አስገዳጅ መሆን ከፍተኛ ዉጤት አስገኝቷል ማለት ይቻላል፡፡ አልፎ አልፎ በዉሣኔዎች ጥራትና ስርጭት ሊታዩ የሚችሉ ችግሮች ሥርዓቱ እየተጠናከረ ሲሄድ የሚፈቱ ሲሆን አነዚህን ችግሮች ለማቃለል እኛም ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ጥረታችን ሊሳካ የሚችለዉ በዉሣኔዎቹ ላይ በሕግ ምሁራንና ባለሙያዎች ገንቢ የሆኑ ትችቶችና አስተያየቶች ሲቀርቡ ነዉ”፡፡ እኔም ይህን ግብዣ በመቀበል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት ሕዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጠዉ ዉሳኔ ላይ ትችቴን ከዚህ በመቀጠል አቀርባለሁ፡፡ ዉሳኔዉ የተሰጠዉ በማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ እና ታዬ አበራ መካከል ባለዉ ክርክር በሰበር መዝገብ ቁጥር 72341 ነዉ፡፡ በዚህ መዝገብ ከተነሱት ዋነኛ ጉዳዮች ዉስጥ፤ አላግባብ የተከፈለ ጡረታን ለማስመለስ የሚቀርብ ክስ በይርጋ ይታገዳል ወይ፤ ከታገደስ የይርጋ ዘመኑ ምን ያህል ነዉ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የጉዳዩ መነሻ

አቶ ታዬ አበራ ከግንቦት 01 ቀን 1984 ዓ.ም. ጀምሮ በየወሩ የጡረታ አበል ይወስዱ ነበር፡፡ ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረዉ ደመዎዝ ተከፍሏቸዋል፡፡ አቶ ታዬ የጡረታ አበላቸዉን መዉሰዳቸዉንም እንደቀጠሉበት ነዉ፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 209/1955 አንቀጽ 30(2) እና በመንግስት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀጽ 46(1) መሰረት፡ የአገልግሎት የጡረታ አበል በመቀበል ላይ ያለ ባለመብት እንደገና በመንግስት መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ ደመዎዝ ማግኘት ከጀመረ አበሉ ይቋረጣል፡፡ በመሆኑም በማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የተጠየቀዉ ዳኝነት እነዚህን ያጠቃልላል፡፡ 1) ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1995 ዓ.ም. ድረስ በየወሩ ብር 105.00 የወሰዱት ለሰባ አምስት ወራት ያህል ተባዝቶ የሚመጣዉን ዉጤት ብር 7575.00፤ 2) ከሐምሌ 01 ቀን 1996 ዓ.ም. እስከ ሀምሌ 01 ቀን 1998 ድረስ በየወሩ ብር 115.50 የወሰዱት ታስቦ የሚመጣዉን ድምር ብር 4045.50፤ 3) ወጪና ኪሳራ እንዲሁም ከሕጋዊ ወለዱ ጋር እንዲከፍሉ፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ክስ የተመሰረተዉ በጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም. ነዉ፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዉሳኔ

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተዉ ፍርድ ቤት፤ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክስ አቶ ታዬ በተቀጠሩበትና የጡረታ አበል መቋረጥ ከሚገባበት ጊዜ (ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም) ጀምሮ ሲታሰብ ከአስራ ሁለት አመታት በላይ ቆይቶ የቀረበና ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677 እና 1845 ድንጋጌዎች አኳያ ሲታይ ተገቢነት የሌለዉ መሆኑን ጠቅሶ ክሱን ዉድቅ አድርጎታል፡፡ ይህ ዉሳኔ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡

አንደኛዉ አጠቃላይ የዉል ሕግ የሚያስቀምጠዉን የአስር አመት የይርጋ ዘመን አላግባብ የተከፈለን የጡረታ አበልን ለማስመለስ የቀረበን ክስ ይመለከታል የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህ አባባል አላግባብ የተከፈለን የጡረታ አበል በተመለከተ እላይ የተጠቀሱት ሁለቱ አዋጆች የሚያስቀምጡት የጊዜ ገደብ አለመኖሩንና፤ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677 የሚለዉን እንደማጠናከሪያ ይጠቀማል፡፡ በቁጥር 1677 መሰረት ግዴታዎቹ ከዉል የተገኙ ባይሆኑም የዚህ አንቀጽ (ስለ ዉሎች በጠቅላላዉ) ደንቦች ይፈጸሙባቸዋል፤የአንዳንድ ግዴታዎችን ከስር አመጣጣቸዉን ወይም ዐይነታቸዉን በመመልከት ከዚህ ደንብ የተለዩት ድንጋጌዎች የተጠበቁ ናቸዉ፡፡

ሁለተኛዉ ደግሞ የአስር አመት አቆጣጠርን ይመለከታል፡፡ አቶ ታዬ ከተቀጠሩበት ቀን ጀምሮ (ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም) ተቆጥሮ ከአስር አመት በላይ ስላለፈዉ ክሱ በይርጋ ይታገዳል የሚል ነዉ፡፡ ምንም እንኳ ልዩነቱ ትንሽ ቢሆንምና በዚህ ጉዳይ ደግሞ የተለየ ለዉጥ ባያመጣም፤ ጊዜዉ መቆጠር ያለበት አቶ ታዬ እንደገና በመንግስት ሰራተኛነት ከተቀጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን፤ ከቅጥሩ በኋላ የጡረታዉን አበል ከተቀበለበት ጊዜ ጀምሮ ነዉ፡፡ ይሄ ደግሞ ከሀምሌ 1 ቀን 1989 ዓ.ም. ጀምሮ ነዉ፡፡ ምክኒያቱም መልስ የሚል ጥያቄ ሊቀርብ የሚችለዉ የጡረታዉን አበል ሲወስድ ነዉ፡፡ ሌላዉ የመጀመሪያዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔን በተመለከት ትኩረት የሚገባዉ ነገር የጡረታ አበሉ በየወሩ የሚከፈል ሆኖ ሳለ ግን ሁሉንም በአስር አመት ይርጋ ታግዷል የሚለዉ አባባል ነዉ፡፡ ይርጋዉ መቆጠር በሚጀምርበት (ማለትም ከሀምሌ 01 ቀን 1989 ዓ.ም) ጊዜ በማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ሊጠየቅ የሚችለዉ የአንድ ወር የጡረታ አበል ማለትም 100 ብር አካባቢ የሚሆነዉ ነዉ፡፡ ይህ ማለትም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተሰልቶ አስር አመት ካለፈዉ ይህን 100 ብር የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መጠየቅ አይችልም፡፡ ይሄ አቶ ታዬ ድጋሚ እንደ መንግስት ሰራተኛነት ተቀጥረዉ የተቀበሉትን የመጀመሪያ ወር የጡረታ አበል ይመለከታል፡፡ የሁለተኛዉን፤ የሶስተኛዉን፤….የጡረታ አበል በተመለከተም እንደዚሁ መሰላት አለበት፡፡ ማለትም እያንዳንዱን መመለስ ያለበት ወርሃዊ የጡረታ አበልን በተመለከተ የይርጋ ጊዜዉ መሰላት ያለበት ለየብቻ ነዉ፡፡ ወይም ሰበር ቸሎቱ እንዳደረገዉ ክሱ የተመሰረተበትን ቀን (ጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም.) መነሻ አድርገን ወደ ኋላ አስር አመት እንቆጥራለን፡፡ ይህ ማለት ጥቅምት 18 ቀን 1993 ዓ.ም በፊት የተከፈሉ የጡረታ አበሎች በይርጋ ሲታገዱ፤ ከዚህ በኋላ ያሉት ግን አይታገዱም፡፡ ልብ ይበሉ-እስከአሁን ድረስ እያሰብን ያለነዉ የይርጋ ዘመኑ አስር አመት ነዉ በሚል ነዉ፡፡

የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሳኔ

ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተዉ የኦሮሚያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ ከመጀመሪዉ ፍርድ ቤት በተለየ መልኩ የይርጋ ዘመኑ ሁለት አመት ነዉ በሚል ወስኗል፡፡ ምክኒያቱም፤ ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዳኝነት እየጠየቀ ያለዉ ያለአግባብ የተከፈለዉና ተጠሪ የበለጸጉበትን ገንዘብ ነዉ፡፡ በመሆኑም (እንደ ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ) ለጉዳዩ አግባብነት ያለዉ የይርጋ ዘመን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143(1) ስር የተመለከተዉ ሁለት አመት ነዉ፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳዉ ጥያቄ፤ ያለአግባብ መበልጸግን መሰረት ተደርጎ የሚቀርብ ክስን የሚመለከተዉ የይርጋ ዘመን በቁጥር 2143 የተለመለከተዉ ሁለት አመት ነዉ ወይ? ከሆነስ እንዴት ነዉ ይህ የይርጋ ዘመን በማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ እና በአቶ ታዬ መካከል ያለዉን ሙግት የሚመለከተዉ?

የሰበር አቤቱታዉ

ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካጸናዉ በኋላ፤ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የሰበር አቤቱታዉን ለፊዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ ዋናዉ ምክኒያትም እላይ የተጠቀሱት አዋጆች አላግባብ የተከፈለን የጡረታን አበል አስመልክቶ ያስቀመጡት የይርጋ ዘመን ሰለሌለ ክሱ በይርጋ አይታገድም የሚል ነዉ፡፡ እንዲሁም አቶ ታዬ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረዉ ደመወዝ እየተቀበሉ ባሉበት ጊዜ የተቀበሉትን የጡረታ አበል ሊመልሱ አይገባም ተብሎ መወሰኑ የአዋጅ ቁጥር 209/1955 አንቀጽ 30(2) እና አዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀጽ 46(1) ድንጋጌዎችን ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ ዉሳኔዉ ሊታረም ይገባል የሚል ነዉ፡፡

የሰበር ዉሳኔዉ

የፊዴራል ሰበር ችሎት ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የሰጠዉን ዉሳኔ ሙሉ ለሙሉ ከዚህ በታች የተቀመጠዉ ነዉ፤

በእርግጥ የአዋጅ ቁጥር 209/1955 እና አዋጅ ቁጥር 345/1995 ስር ሉት ድንጋጌዎች ከሕግ ዉጪ የተከፈለ የጡረታ ገንዘብ ይመለስ ጥያቄ መቅረብ ያለበትን የጊዜ ገደብ አላስቀምጡም፡፡ ይህ ማለት ግን ጥያቄዉ የሚቀርብበት ጊዜ ገደብ የለዉም ወደሚለዉ ድምዳሜ የማያደርስ ስለመሆኑ ከይርጋ ጽንሰ ሃሳብ የምንገነዘበዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለዉ ሕግ ስለ ይርጋ የጊዜ ገደብ በግልጽ ያስቀመጠዉ ድንጋጌ ከሌለ በአገራችን የሕግ ስርአት የተዘረጋዉ መፍትሔ በዉል ሕጉ የተመለከቱት ደንቦች የሚፈጸሙ መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677(1) እና 1845 ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡

ያላግባብ መበልጸግን በተመለከተ የሚደነግጉ ድንጋጌዎቸ የይርጋ ደንብ የይርጋ ጊዜን በተመለከተ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለዉ ሕግ ያስቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ከሌለ ተፈጻሚ የሚሆንበትን አግባብ የሚያሳይ ድንጋጌ የለም፡፡

በመሆኑም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ክፍያዉ ያላግባብ ተወስዷል…በሚል ምክኒያት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143(1) ድንጋጌን ለጉዳዩ ተፈጻሚነት አለዉ በማለት የስር ፍርድ ቤት ያስቀመጠዉን ድንጋጌ መለወጡ የሕግ መሰረት ያለዉ ሆኖ አልተገኘም፡፡

የስር ፍርድ ቤት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677 እና 1845 ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ በአስር አመት የይርጋ ጊዜ ጉዳዩ መታየት እንዳአለበት የሰጠዉ ምክኒያት ተገቢ ሁኖ የተገኘ ቢሆንም የስር ፍርድ ቤት ይርጋዉ መቆጠር የሚጀመርበትን ጊዜ በተመለከተ ግን ተጠሪ ከተቀጠሩበት ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም. ጀምሮ ነዉ በማለት የወሰደዉ ተገቢ ሁኖ አልተገኘም፡፡ ምክኒያቱም  ተጠሪ የጡረታ አበሉንና በቅጥር የሚያገኙትን ደመዎዝ በአንድ ላይ መቀበሉን በተከታታይ ሲፈጽሙበት ቆይተዉ ገንዘቡን ከሕግ ዉጪ ሲቀበሉ የቆዩ መሆኑን አመልካች በማረጋገጥ የጡረታ አበሉን ለተጠሪ መክፈል ያቆመዉ ከነሀሴ 30 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን ተጠሪ ከሕግ ዉጪ የወሰዱትን የጡረታ አበል እንዲመልሱ ክስ ያቀረበዉ ጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም. ነዉ፡፡ ስለሆነም የይርጋ ጊዜዉ መቆጠር ያለበት ክሱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኋላ ሲቆጠር አስር አመት ያላለፈበት የጡረታ ገንዘብ ክፍያ ለአመልካች ሊመለስ የሚገባዉ ይሆናል፡፡ አመልካች ይርጋዉ መቆጠር ያለበት በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1847 መሰረት ነዉ በማለት ያቀረበዉ ክርክር በየጊዜዉ የሚከፈለዉን ገንዘብ የሚቀበል ሰዉ ክፍያዌ ሲቋረጥ ምብቱን ለማስከበር የሚችልበትን የይርጋ ጊዜ ለመቁጠር የሚያስችለዉን አግባብ የሚያሳይ በመሆኑ በተያዘዉ ጉዳይ ላይ አመልካች ክፍያ ተቀባይ ሳይሆን ከሕግ ዉጪ የከፈለዉን ገንዘብ እንዲመለስለት የሚጠይቅ በመሆኑ ቀጥተኛ አግባብነት ያለዉ ሁኖ አላገኘነዉም….

ከዚህ መገንዘብ የሚቻለዉ ከጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኋላ አስር አመት ሲቆጠር አስር አመት የማያልፍበት የጡረታ አበል ክፍያ ከጥቅምት 19 ቀን 1993 ዓ.ም. ወዲህ ያለዉ ነዉ፡፡ በመሆኑም ከጥቅምት 18 ቀን 1993 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኋላ ያለዉ ማለትም ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 18 ቀን 1993 ዓ.ም ድረስ ያለዉ የጡረታ አበል አስር አመት ያለፈበት በመሆኑ የአመልካች ጥያቄ ዉድቅ ሊሆን የሚገባዉ ሁኖ አግኝተናል፡፡

የእኔ አስተያየት

እንደኔ አመለካከት የሰበር ሰሚዉ ዉሳኔ ሕግን የተከተለ አይደለም፡፡ የሕግን ጠቅላላ አወቃቀር ግምት ዉስጥ ያላስገባ ነዉ፡፡ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ በደንብ ያልተብራራ ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እላይ የተጠቀሱት አዋጆች ላይ የተቀመጡና በጠቅላላዉ ከጡረታ አበል ጋር የተያያዙ አንዳንድ ክሶችን አስመልክቶ የተቀመጡትን የይርጋ ዘመኖች በፍጹም ግምት ዉስጥ ያላስገባና ተያያዥነት ያላቸዉ ክሶች እጅግ የተለያየ የይርጋ ዘመን እንዲኖራቸዉ ያደረገ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ይህን አስተያያት ከዚህ በታች አብራራዋለዉ፡፡

እላይ እንደተገለጸዉ ሁለቱም አዋጆች አላግባብ የተከፈለን የጡረታ አበልን ለማስመለስ የሚቀርብ ክስን በተመለከተ የይርጋ ዘመን አያስቀምጡም፡፡ ይህም መሰረት አድርጎ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ እንደዚህ አይነት ክሶች ይርጋ የላቸዉም ማለት ነዉ በሚል ተከራክሯል፡፡ ሰበር ችሎቱ ይህ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክርክር ከይርጋ ጽንሰ ሃሳብ ጋር የሚጣጣም ስላልሆነ አልተቀበዉም፡፡ ይህ ዉሳኔ ምን ችግር አለዉ? ምንም እንኳ እኔም የማህበራዊ ኤጀንሲን ክርክር ባልቀበለዉም ምክኒያቴ ግን የይርጋ ጽንሰ ሃሳብ አይደለም፡፡ ሰበር ችሎቱ የይርጋ ጽንሰ ሃሳብ ሲል ምን ለማለት እንደፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡ ደሞም እንዴት ነዉ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክርክር ከይርጋ ጽንሰ ሃሳብ ጋር የማይጣጣመዉ? ይሄም አልተብራራም፡፡ የኔ ምክኒያት ይህ ነዉ፤ ማንኛዉንም ግዴታ (ከህግ ወይም ከዉል የሚመነጭ) መሰረት አድርጎ የሚቀርብ ክስ በሌላ ሕግ የተለየ የይርጋ ጊዜ ካልተቀመጠለት በቀር በአስር አመት የይርጋ ጊዜ ሊታገድ እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁጥሮች 1677 እና 1845 ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም አንድ የተለየ ሕግ ስለይርጋ ያስቀመጠዉ ነገር የለም በሚል ጉዳዩ በይርጋ አይታገድም የሚል ክርክር ተቀባይነት የለዉም፡፡ በይርጋ የማይታገድ አይነት ክስ ከሆነ ሕጉ በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ምክኒያት ሕጉን መሰረት ያደረገ ነዉ እንጂ የይርጋን ጽንሰ ሃሳብን (ያዉም ያልተብራራን) መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ ስለዚህ ማንኛዉም የፍትሐ ብሔር ክስ (በተለየ ሕግ የተለየ የይርጋ ዘመን ካልተቀመጠለት በስተቀር) በአስር አመት የይርጋ ዘመን ይታገዳል፡፡ ልብ በሉ፤ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክስ በአስር አመት የይርጋ ዘመን ይታገዳል እያልኩ አይደለም፡፡

ሰበር ችሎቱ እንዲህ ሲል ያክላል፤ “ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለዉ ሕግ ስለ ይርጋ የጊዜ ገደብ በግልጽ ያስቀመጠዉ ድንጋጌ ከሌለ በአገራችን የሕግ ስርአት የተዘረጋዉ መፍትሔ በዉል ሕጉ የተመለከቱት ደንቦች የሚፈጸሙ መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677(1) እና 1845 ድንጋጌዎች ያሳያሉ”፡፡ በዚህ አባባል እስማማለዉ፡፡ የማልስማማዉ ይህ አባባል ታሳቢ ያደረገዉ ግምትን በተመለከተ ነዉ፡፡ የሰበር ችሎቱ እምነት በተያዘዉ ጉዳይ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለዉ ሕግ እላይ የተጠቀሱት አዋጆች ናቸዉ፡፡

እንደኔ እምነት ግን እላይ የተጠቀሱት አዋጆች አቶ ታዬ እንደገና በመንግስት መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ ደመዎዝ ማግኘት ከጀመረ የጡረታ አበሉ እንደሚቋረጥ ከመናገር ዉጪ፤ በስህተት ከተከፈለዉ ግን መመለስ እንዳለበት የሚናገረዉ ነገር የለም፡፡ ለማስመለስም የሚቀርበዉ ክስ በምን ያህል የይርጋ ዘመን ይገዛል የሚለዉም እንዲሁ፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያዉ ጥያቄ መሆን ያለበት የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የተከፈለ የጡረታን አበል ለማስመለስ የሚከፍተዉ ክስ የሕግ መሰረቱ ምንድን ነዉ የሚለዉን ማየት ተገቢ ነዉ፡፡

እንደ እኔ እና እንደ ኦሮሚያ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እምነት የዚህ ክስ መሰረቱ አላግባብ መበልጸግ ነዉ፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2162 ያላግባብ ስለ መበልጸግ እንዲህ ይላል፤ በሌላ ሰዉ የሥራ ደካም ወይም የሌላ ሰዉ ሀብት በሆነ ነገር በመገልገል በቂ ባልሆነ ምክንያት ጥቅም ያገኘ ሰዉ አላግባብ ጥቅም ባገኘበት መጠንና ለባለሀብቱ ወይም ጉልበቱ ለደከመዉ ሰዉ ይህ አድራጎት በደረሰበት ጉዳት መጠን ለባለሀብቱ ወይም ጉልበቱ ለደከመዉ ሰዉ ኪሣራ መክፈል አለበት፡፡ ይህ ጠቅላላ ድንጋጌ እንዳለ ሆኖ ቁጥር 2164 ሊከፍል የማይገባዉን ነገር የከፈለ ሰዉ እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት እንዳለዉ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ በሰበር ችሎቱ ዉሳኔ በግልጽ ባይቀመጥም የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክስ እንዲህ የሚል ነዉ፤ ልንከፍል የማይገባንን ነገር በስህተት ስለከፈልን ይመለስልን የሚል ነዉ፡፡ እላይ የተጠቀሱት ሁለቱ አዋጆች የሚጠቅሙት ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የከፈለዉ የጡረታ አበል መክፈል የማይገባዉን እንደሆነ ለማሳየት ነዉ፡፡ ይህ ከተረጋገጠ በኋላ ግን ይህን የተከፈለን የጡረታ አበል ለማስመለስ የሚቀርብ ክስ የሕግ መሰረት አላግባብ አለመበልጸግን (በተለይ ደግሞ የማይገባዉን ስለመክፈል) የሚመለከተዉ የፍትሐ-ብሔር ሕግ አካል ነዉ፡፡

የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክስ የሕግ መሰረቱ አላግባብ መበልጸግን የሚመለከተዉ የፍትሐ ብሔር ሕግ ክፍል ከሆነ ለእንደዚህ አይነት ክስ የሚያገለግለዉ የይርጋ ድንጋጌ የቱ ነዉ? በቁጥር 2143 መሰረት ከዉል ዉጪ የሚመነጭ ሃላፊነትን (ያለአግባብ መበልጸግን ጨምሮ) የሚቀርብ ክስ የተቀመጠለት የይርጋ ዘመን ሁለት አመት ነዉ፡፡ በመሆኑም የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክስ በሁለት አመት ይርጋ ሊገዛ ይገባል፡፡ አስር አመቱ የይርጋ ዘመን የሚያገለግለዉ በልዩ ሁኔታ በሕግ የይርጋ ዘመን ካልተቀመጠ ነዉ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሙግት ቀጥተኛ አግባብ ያለዉና ያላግባብ መበልጸግን የሚመለከተዉ የሕግ ክፍል ልዩ የይርጋ ዘመን አስቀምጧል፡፡ ሰበር ችሎቱ እንዲህ ይላል፤ ያላግባብ መበልጸግን በተመለከተ የሚደነግጉ ድንጋጌዎቸ የይርጋ ደንብ የይርጋ ጊዜን በተመለከተ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለዉ ሕግ ያስቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ከሌለ ተፈጻሚ የሚሆንበትን አግባብ የሚያሳይ ድንጋጌ የለም፡፡ እኔም እስማማለዉ፡፡ ከዉል ዉጭ የሚመነጭ ሃላፊነትን በተመለከተ የተቀመጠዉ ይርጋ ለሌሎች ጉዳዮች አያገለግልም፡፡ ቸግሩ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ክስ ሌላ ጉዳይ ሳይሆን ከዉል ዉጭ የሚመነጭ ሃላፊነትን መሰረት አድርጎ የቀረበ ነዉ፡፡

አቆጣጠሩን አስመልክቶ ግን እላይ ከመጀመሪያዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ ጋር አያይዤ ያየዉት ነዉ፡፡ ሰበር ችሎቱም በሚገባ አብራርቶታል፡፡ በዚህ መሰረት ከተሄደ አንድም የተከፈለ የጡረታ አበል ሊመለስ አይችልም ማለት ነዉ፡፡

የሰበር ሰሚ ዉሳኔ ሌላዉ ችግር እላይ እንደጠቀስኩት በሁለቱ አዋጆች ላይ የተቀመጡና ከጡረታ አበል ጋር የተያያዙ አንዳንድ ክሶችን አስመልክቶ የተቀመጡትን የይርጋ ዘመኖች በፍጹም ግምት ዉስጥ ያላስገባና ተያያዥነት ያላቸዉ ክሶች እጅግ የተለያየ የይርጋ ዘመን እንዲኖራቸዉ ያደረገ ዉሳኔ ነዉ፡፡ አንቀጽ 43 እንዲህ የሚሉ ድንጋጌዎች አሉት፤ 1) ማንኛዉም ዉዝፍ የጡረታ አበል ክፍያ ጥያቄ ከአንድ ዓመት በኋላ በይርጋ ይታገዳል፤ 2) ማንኛዉም የዳረጎት ክፍያ ጥያቄ ከሁለት ዓመት በኋላ በይርጋ ይታገዳል፤ 3) የይርጋ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረዉ በመብቱ መጠቀም ከሚቻልበት ቀጥሎ ካለዉ ቀን አንስቶ ነዉ፡፡ ዉዝፍ የጡረታ አበል ክፍያ ጥያቄ ከአንድ ዓመት በኋላ በይርጋ የሚታገድ ከሆነ፤ አላግባብ የተከፈለ የጡረታ አበልን ለማስመለስ የሚቀርብ ክስ እስከ አስር አመት ድርስ እንዲቀርብ መፍቀድ ከፍተኛ ልዩነትን መፍጠር ነዉ፡፡

በአጭሩ፤ አላግባብ/በስህተት የተከፈለን የጡረታ አበል ለማስመለስ የሚቀርብ ክስን የሚያስቀረዉ የይርጋ ዘመን ሁለት አመት በሚል በርእሱ ያነሳዉትን ጥያቄ እመልሳለዉ፡፡