ይህ አጭር ጽሁፍ በቅርብ ጊዜ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር መዝገብ ቁጥር 76248 ላይ፤ በኦሮሚያ ጠቅላይና በአዳማ ልዮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተሰርቷል ማለት አይቻልም በሚል፤ በሶስት ዳኞች ጥቅምት 6 2005 የተዘጋን ጉዳይ መሰረት አደርጎ የቀረበ ነዉ፡፡ የምንዳስሰዉ ጥያቄ በጽሁፉ ርእስ ላይ የተመለከተዉን ነዉ፤ ያለዉክልና የሌላን ሰዉ እዳ መክፈል ይርጋን ያቋርጣል? ለጽሁፉ አላማ የተከራካሪ ወገኖችን ስም መጥቀስ አስፈላጊ ስላልሆነ አበዳሪ፤ ከሳሽ፤ ተበዳሪ፤ እና የተበዳሪ ልጅ የሚሉትን እንጠቀማለን፡፡ በአጭሩ ፍርድ ቤቶቹ የወሰኑት ባለእዳዉ ሳይሆን ሌላ ሰዉ (የጽሁፍ ዉክልና ሳይሰጠዉ በፊት) በባለእዳዉ ስም ያደረገዉ የእዳ አከፋፈል እንዳልተደረገ ስለሚቆጠር ይርጋን አያቋርጥም በማለት ወስነዋል፡፡

የጉዳዩ መነሻ

ተበዳሪዋ ከኢትዮጲያ ንግድ ባንክ አዳማ ቅርንጫፍ ለንግድ ማስፋፊያ በሚልና ንብረት በማስያዝ በየወሩ ተከፍሎ በአንድ አመት ዉስጥ የሚያልቅ ብድር ወስደዋል፡፡ ነገር ግን አንድም ወር የተስማሙትን ወርሀዊ ክፍያ ሳይፈጽሙ በብድር ዉሉ ላይ የተጠቀሰዉ የእዳ መክፈያ ጊዜ ያልፋል፡፡ የብድር ዉሉ የተፈረመዉ በ25/11/1987 ሲሆን በ24/11/1988 ተከፍሎ ማለቅ ነበረበት፡፡ የተበዳሪዋ ልጅ የመጀመሪያዉን የ28000 ብር ክፍያ በተበዳሪዋ ስም የፈጸሙት በ24/11/1989 ነበር፡፡ ከዛ በመቀጠል በ15/8/1994 በዚሁ ልጅ በተዳሪዋ ስም የ2000 ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ክሱ በቀረበበት ወቅት ከመጀመያዉ ክፍያ ጀምሮ ሲሰላ ከአስር አመት በላይ አልፎታል፡፡ ነገር ግን ከሁለተኛዉ ክፍያ ጀምሮ ከተሰላ አስር አመት አልሞላም፡፡

ተበዳሪዋ ለቀረበባቸዉ ክስ የይርጋ መቃወሚያ አንስተዋል፤ ክሱ በአስር አመት የይርጋ ጊዜ ዉስጥ ስላልቀረበ ይታገዳል በሚል፡፡ ሁለተኛዉን ክፍያ በተመለከተ፤ አልከፈልኩም በክፍያ ሰነዱም ላይ ያለዉ ፊርማ የኔ ፊርማ አይደለም ብለዋል፡፡ ይህንን እኔ ያልከፈልኩትን የሁለተኛ ክፍያ ሰነድ ያቀረበዉ ከሳሽ በይርጋ ቀሪ የሆነዉን የብድር ገንዘብ በፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ለማስመለስ እንዲያመቸዉ ነዉ የሚል ነዉ፡፡  

ከሳሽ ባንክ በበኩሉ በዉላቸዉ ክፍያ የሚፈፅመዉ ተበዳሪ ወይም በተበዳሪ የተወከለ ሰዉ ብቻ ነዉ የሚል ቃል የለም፤ እንዲሁም ልጃቸዉ ከ1996 ጀምሮ የዉክልና ማስረጃ ተስጥቶታል፡፡ ከዛ በፊትም ቢሆን ዉክልና ነበረዉ፤ ምንም እንኳ በጽሁፍ ባይሆንም ብሏል፡፡

የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሳኔ

የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱ በአስር አመት ይርጋ ታግዷል በሚል ወስኗል፡፡ አንድ ስምምነት የብድር ስምምነትን ጨምሮ መፈጸም በሚገባዉ ጊዜ ዉስጥ ባለመፈጸሙ ምክኒያት የሚቀርብ ክስ በአስር አመት ጊዜ ዉስጥ ያልቀረበ ከሆነ ክሱ በይርጋ ዉድቅ እንደሚሆን በፍ/ብ/ሕ ቁጥር 1845 ስር ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሰረት፤ አለ ፍርድ ቤቱ፤ ተከሳሽ የመጀመሪያ ክፍያ የከፈሉበት ጊዜ በ9/11/1989 ጀምሮ ይህ ክስ እስከሚቀርብበት ጊዜ ድርስ ሲታሰብ ጊዜዉ 10 አመት አልፏል፡፡ ስለሆነም ይህ የቀረበዉ ክስ በዚህ አማካይነት በይርጋ ዉድቅ የሚሆን ነዉ፡፡

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሁለተኛ ክፍያዉን በተመለከተ እንዲህ ሲል አክሏል፤ ተከሳሽ በተወካይዋ አማካይነት የመጨረሻዉን ክፍያ 15/8/94 በተጻፈ ደረሰኝ ከፍለዋል ተብሎ በከሳሽ በኩል የተነሳዉ ክርክር አስመልክቶ በእዉነት የተከሳሽ ተወካይ የተከፈለ ለመሆኑና የዉክልና ማስረጃዉም ሆነ እዉነት መሆኑን የሚያረጋግጥ የቀረበ ሌላ ማስረጃ የለም፤ ስለሆነም በዚህ ጭብጥ ላይ በከሳሽ በኩል የተነሳዉ ክርክር ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ለመከታተል ግልጽ ለማድረግ ለሁለተኛዉ ክፍያ የተቆረጠዉ ደረሰኝ እዉነት በተበዳሪ ልጅ የተፈረመ ለመሆኑ ሳይሆን ጥያቄዉ፤ ይኸዉ ልጅ ክፍያዉን ለመፈጸም ዉክልና ስለመኖሩ ከሳሽ አላስረዳም የሚል ነዉ፡፡

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዉሳኔ

የኦሮሚያ ፍርድ ቤት ደግሞ በበኩሉ የተበዳሪዋ ልጅ ዉክልና ሳይኖረዉ የከፈለና ይህ ክፍያ ደግሞ በተበዳሪዋ የተፈጸመ ክፍያ ነዉ ተብሎ ስለማይታሰብ የስር ፍርድ ቤት ዉሳኔ አግባብ ነዉ በማለት ዉሳኔዉን አጽንቷል፡፡

በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተካሄደዉ ክርክር ተበዳሪዋ ልጇ ከፍሏል የሚባለዉ ክፍያ አላዉቅም፤ እንዲከፍል የሰጠዉት ዉክልና የለም፤ ራሱን ችሎ የሚተዳደር ነዉ፤ ከፍሏል ብለዉ እኔን ለመጉዳት ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተበዳሪዋ ልጅ የከፈለዉ 2000 ብር ይርጋን ያቋርጣል ወይ የሚል ጭብጥ ይዟል፡፡ ማለትም እላይ እንደተጠቀሰዉ የተበዳሪዋ ልጅ የመጨረሻዉን ክፍያ እንደከፈለ ልዩነት የለም፤ ልዩነቱ ክፍያዉን በፈጸመበት ወቅት ዉክልና አለዉ ወይስ የለዉም በሚለዉ ላይ ነዉ፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ሲል ዉሳኔዉን ያብራራል፤ ዉክልናዉ የተሰጠዉ በ18/04/1996፤ ከፈለ የተባለዉ በ15/08/94፤ አንድ ሰዉ ደግሞ በሰዉ ምትክ መክፈል የሚችለዉ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1740 መሰረት ከባለእዳዉ ዉክልና ከተሰጠዉ ወይም ዉክልና ሳይኖር ባለእዳዉ መክፈሉን ከተቀበለ ነዉ፤ ሆኖም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1740 ስር በተደነገገዉ መሰረት ዉክልና ሳይቀበል ክፍያ ከፈጸመ እና ክርክሩ የባለእዳዉን መብት የሚጎዳ ከሆነ ባለእዳ ከፍያለሁ ወይም ተወካዩ ከፍሏል የሚያስብል አይደለም፡፡ ስለዚህ፤ አለ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፤ በተወካይ ስለመከፈሉ የሚያሳይ ማስረጃ ስለሌለ የተበዳሪዋ ልጅ ዉክልና ሳይኖረዉ የተከፈለዉ ክፍያ ተበዳሪዋ እስካልተቀበለችዉ የይርጋ ጊዜ አያቋርጥም፡፡

የፊዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ በኦሮሚያ ጠቅላይና በአዳማ ልዮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተሰርቷል ማለት አይቻልም በሚል በሶስት ዳኞች ጥቅምት 6 2005 መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

የኔ አስተያየት

የተበዳሪዋ ልጅ የ2000 ብሩን ክፍያ እንደፈጸመ ልዩነት ያልፈጠረ ጉዳይ ነዉ፡፡ ልዩነቱ ክፍያዉን በፈጸመበት ወቅት ዉክልና ነበረዉ ወይ በሚለዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ የሚገርመዉ የመጀመሪያዉንም ክፍያ የፈጸመዉ እሱ ራሱ የተበዳሪዋ ልጅ ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቶቹ እንዳሉት ለልጁ የጽሁፍና በፍትህ ቢሮ የተመዘገበ ዉክልና የተሰጠዉ በ18/04/1996 አ.ም ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ አጨቃጫቂዉ ክፍያ ከተፈጸመ ከሁለት አመት በኋላ ነዉ፡፡ ይህ ማለት ግን ከዛ በፊት ዉክልና አልነበረዉም ማለት አይደለም፡፡

እንደ አበዳሪዉ ገለጻ ብድሩ በሚመቻችበት ወቅት እየመጣ በእናቱ ስም የሚከታተለዉ እሱ ከፋዩ/ልጇ ነበር፡፡ የመጀመሪያዉንም ክፍያ የፈጸመዉ እሱ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ በድርጊት ወይም በዝምታ የተቋቋመ ዉክልና (implied agency) እንዳለ ነዉ የሚያሳየዉ፤ ይላል አበዳሪዉ፡፡

ምንም እንኳ የተበዳሪዋ ልጅ በወቅቱ ምንም ዉክልና የለዉም ቢባልም እንኳ፤ በአበዳሪዉ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በዉክልና ሕግ የአምሳለ-ስልጣንን ድንጋጌዎች (apparent authority) ይመለከታል፡፡ በኢትዮጲያ ሕግ አግባብ አንድ ሰዉ በሌላ ሰዉ ስም የሰራዉ ስራ ያኛዉ ሰዉ ላይ የሕግ ዉጤት እንዲኖረዉ ከተፈለገ ስራዉን በግልጽ ወይም ግልጽ ባልሆነ ስልጣን መሰረት ያከናወነዉ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን በቅን ልቦና ያለ ለሶስተኛ ወገን ሰዉየዉ ስልጣን ያለዉ ከመሰለዉና ወካዩ የተባለዉም ሶስተኛ ወገን ይህን እምነት እንዲያሳድር ካደረገ ሁለቱም የሚጠየቁበት አግባብ በሕጋችን ተቀምጧል፡፡

ከላይ ማየት እንደሚቻለዉ ሁለቱንም ነጥቦች ሁለቱም ፍርድ ቤቶች አላዩዋቸዉም፡፡ እኔ በዚህ ጽሁፍ ማንሳት የምፈልገዉ በድርጊት ወይም በዝምታ ስለተቋቋመ ዉክልና ወይም ስለ አምሳለ-ስልጣን አይደለም፡፡ ይህንን በሌላ ክፍል እመለስበታለሁ፡፡ ለዚህ ጽሁፍ አላማ፤ ልጁ ምንም አይነት እዉነተኛም ሆነ እዉነት-የሚመስል ስልጣን የለዉም እንበል፡፡ በእንደዚህ ሁኔታ የተከፈለ ክፍያ በተበዳሪዋ (በእናቱ) እንደተደረገ የሚቆጠርበት እድል አለ ወይ የሚለዉን እንመለከታን፡፡

ማነዉ መክፈል የሚችል

መክፈል የሚለዉ ቃል በዉል ሕግ አግባብ ገንዘብን ብቻ አይመለከትም፡፡ መክፈል  በዉል የተቋቋሙና በሕግ የተቀመጡ ግዴታዎችን ይመለከታል፡፡ እነዚህ ግዴታዎች አንድን የተወሰነን ድርጊት የማድረግ ያለማድረግ፤ አንድን እቃ ወይም ንብረት መስጠትን ይጨምራል፡፡ እንደዉም የፍትሐ ብሔር ሕጋችን የዉልን ግዴታ ስለመፈጸም በሚል ነዉ የተቀመጠዉ፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1740 እንዲህ ይነበባል፤

ከዉሉ አይነት የተነሳ ለባለገንዘቡ ጥቅም ግዴታዉን ባለእዳዉ እንዲፈጽመዉ የሆነ እንደ ሆነ ወይም በዚህ አይነት እንዲደረግ ግልጽ የሆነ ስምምነት እንዳለ ባለእዳዉ የዚህን ግዴታ እርሱ ራሱ መፈጸም አለበት፡፡

በሌላዉ ጊዜ ሁሉ ግዴታዉን እንዲፈጽምለት ከባለእዳዉ ስልጣን የተቀበለ ወይም ስለ ባለእዳዉ ሆኖ ግዴታዎችን እንዲፈጽም በፍርድ ወይም በሕግ የተፈቀደለት ሌላ ሶስተኛ ወገን የተባለዉን ግዴታ ሊፈጽም ይችላል፡፡

ከላይ ማየት እንደሚቻለዉ፤ ዉልን በሁለት መንገድ መፈጸም ይቻላል፡፡ አንደኛ፤ ራሱ ባለእዳዉ ሲፈጽም ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ሶስተኛ ወገን ስለባለእዳዉ ብሎ ሲፈጽም ነዉ፡፡

ያኛዉ ወገን የለም ባለእዳዉ ራሱ መፈጸም አለበት ብሎ ሊከራከር የሚችለዉ በሁለት ሁኔታዎች ብቻ ነዉ፡፡ አንደኛዉ ዉሉ ዉስጥ ግዴታዉን ራሱ ባለእዳዉ ብቻ ነዉ መፈጸም ያለበት የሚል ቃል ካለ ነዉ፡፡ ወይም ምንም እንኳ እንዲህ አይነት ስምምነት ባይኖርም፤ ከዉሉ አይነት ተነስተን የባለገንዘቡ ጥቅምን ለማስከበር ሲባል ባለእዳዉ ራሱ ግዴታዉን እንዲፈጽመዉ የሚያስፈልግ ከሆነ ነዉ፡፡ አንዳንድ ዉሎች፤ በተለይ ባለእዳዉ ላይ የአቅሙን ያህል ጥረት እንዲያደርግ ግዴታ የሚጥሉ ከሆነ ወይም የዉሉ ዉጤት በባለእዳዉ ማንነት የሚወሰን ከሆነ፤ ባለገንዘቡ ጥቅሜ ይነካል እና የግድ ራሱ ባለእዳዉ ግዴታዉን ይወጣ ማለት ይችላል፡፡

ከዚህ ዉጭ በሆኑ ሁኔታዎች ወይም ባለገንዘቡ እስከፈቀደ ድረስ፤ የባለእዳዉን ግዴታ ሌላ ሶስተኛ ወገን ሊወጣዉ ይችላል፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ማንኛዉም ሶስተኛ ወገን ይህን ማድረግ እንዲችል ቢፍቅዱም እንኳ የኢትዮጲያ ሕግ ግን ይህ ሶስተኛ ወገን በባለእዳዉ ስም ሆኖ ዉልን እንዲፈጽም፤ ባለእዳዉ፤ ሕግ፤ ወይም ፍርድ ቤት ሊፈቅድለት ይገባል ይላል፡፡

በእርግጥ አሁን በያዝነዉ ጉዳይ ስንነሳ ባለእዳዉ አልፈቀደለትም ብለናል፡፡ ከፍርድ ቤትም አስቀድሞ ፍቃድ አላገኘም፡፡ አሁን ጥያቄዉ ሕግ ይፈቅድለታል ወይ ነዉ? ይህን ከማየታችን በፊት ግን የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለዉን እንመልከት፡፡

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1740 ስር በተደነገገዉ መሰረት ዉክልና ሳይቀበል ክፍያ ከፈጸመ እና ክርክሩ የባለእዳዉን መብት የሚጎዳ ከሆነ ባለእዳ ከፍያለሁ ወይም ተወካዩ ከፍሏል የሚያስብል አይደለም ይላል፡፡ የተሰመረበት ሀረግ ከየት እንደተወሰደ ግልጽ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነት አሳብ በ1740 አልተቀመጠም፡፡

እንደኔ አመለካከት፤ ምንም እንኳ የተበዳሪዋ ልጅ፤ ክፍያዉን በሚፈጽምበት ጊዜ በእናቱ (በባለእዳዉ) ዉክልና/ፈቃድ ባይኖረዉም፤ ለመክፈል ግን ሕጉ ይፈቅድለታል የሚል ነዉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የራሱን ብር ተጠቅሞ ነዉ የከፈለዉና ከከፈለ በኋላ ብሩን ማስመለስ ፈለገ እንበል፡፡ እናትየዉ እምቢ ማለት ትችላለች? ከእናትየዉ አስቀድሞ ዉክልና/ፈቃድ ስላላገኘና ያለስልጣን የተደረገዉን ስራ ለማጽደቅ እንቢ ስላለች ጉዳዩን ማየት ያለብን ያለስልጣን ስለተደረጉ ስራዎች ከሚያወራዉ ክፍል ነዉ፡፡

ያለስልጣን የተደረጉ ስራዎችን የሚመለከተዉ የፍትሐ ብሔር ሕግ ክፍል ስለ ስራ አመራር ይሰኛል፡፡ ስለ ስራ አመራር ያሉት ድንጋጌዎች የሚመለከቱት ጉዳይን ሕጉ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል፤ አንድ ሰዉ የነገሩን ሁኔታ እየተገነዘበ ይህን እንዲፈጽም ሳይገደድ የወኪልነትም ስልጣን ሳይሰጠዉ የሌላዉን ሰዉ ጉዳይ በመምራት ስራ ዉስጥ ገብቶ ጉዳዩን ያካሄደ እንደ ሆነ፡፡

የተበዳሪዋ ልጅ ያደረገዉን ክፍያ የወኪልነት ስልጣን ሳይሰጠዉ የእናቱን ጉዳይ በመምራት ስራ ዉስጥ ገብቷል ያስብላል፡፡ የልጁ ድርጊት (እዳን መክፈል) ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2004 መሰረት የመምራት ስራ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ነገር ግን ለባለንብረቱ ጥቅም በማይሰጥ ሁኔታና ከፈቃዱ ዉጪ የተፈጸመ ከሆነ አላግባብ መበልጸግና ከዉል ዉጪ ሃላፊነትን የሚመለከቱት የፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች ስራ ላይ እንደሚዉሉ ሕጉ ይናገራል፡፡

ነገር ግን ክፍያዉ በተፈጸመበት ወቅትና ሁኔታ ከእናቱ ፈቃድ ዉጪና የእናቱን ጥቅም አያስከብርም ማለት አይቻልም፡፡ እንደዉም የእናቱን እዳ መቀነሱ እናቱን የሚጠቅም ነዉ፡፡ በእርግጥ ብዙ አመት ካለፈ በኋል ባይከፍል ኖሮ በይርጋ ይታገድ ነበር ማለት ቀላል ነዉ፡፡ ነገር ግን የክፍያዉ ጠቃሚነት መመዘን ያለበት ክፍያዉ በተፈጸመበት ወቅት ነዉ፡፡

በቁጥር 2264 መሰረት ደግሞ የስራዉ አመራር እንዲወጠንና በስራ መሪዉ እንዲካሄድ የባለቤቱ ጥቅም የሚያስገድድ ሆኖ የተገኘ እንደ ሆነ ስራ መሪዉ በስሙ የተወጠነዉን የስራ ተግባር ባለንብረቱ ሊያጸድቅለት ይገባል፡፡ በመሆኑም እናቱ የልጇን ስራ የማጽደቅ ግዴታ አለባት፡፡ ይህ ማለት ድርጊቱ መጀመሪዉንም በስልጣን እንደተደረገ ይቆጠራል፤ ክፍያዉ በተበዳሪዋ እንደተደረገ ይቆጠራል ማለት ነዉ፡፡

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክሩ የባለእዳዉን መብት የሚጎዳ ከሆነ ባለእዳ ከፍያለሁ ወይም ተወካዩ ከፍሏል የሚያስብል አይደለም የሚል ቃል አስቀምጦ አልፏል፡፡ ይህ አባባል ስለ ስራ አመራር ሕጉ ካስቀመጠዉ ጋር ግንኙነት አለዉ፡፡ ስህተቱ የተሰራዉ ይህን አባባል ፍርድ ቤቱ የተጠቀመዉ ከ1740 ጋር አያይዞ ነዉ፡፡ ሌላዉ ስህተት የባለእዳዉን ጥቅም ሲገመግም ክሱ የቀረበበት ጊዜ ላይ ሆኖ ነዉ፡፡ ባለቤቱ ይጠቀማል ወይ የሚለዉ መገምገም ያለበት ክፍያዉ በተፈጸመበት/ስራዉ የተከናወነበት ወቅትንና ሁኔታን ግምት ዉስጥ አስገብተን ነዉ፡፡

በመሆኑም በእኔ እምነት ከተወሰነ አመት በኋላ ባይከፍል ኖሮ በይርጋ ይታገድ ነበር፤ ስለዚህ ያለስልጣኑ ስለከፈለ እንዳልከፈለ ይቆጠራል የሚለዉ መከራከሪያ ዉድቅ መደረግ ነበረበት፡፡ በወቅቱ ክፍያዉ መፈጸሙ እዳዋን አቅሎላታል፤ ስለዚህ ጠቅሟታል፡፡ በወቅቱ ልጇ የከፈለዉን ብር እንድትመልስለት ቢጠይቅ ኖሮ እናት መከራከሪያ አይኖራትም ነበር፡፡ በአጭሩ የልጇን ስራ እንድታጸድቅና ስልጣን እንዳለዉ ሕጉ (ከላይ የተጠቀሱት) ስለሚቆጥር በ1740 መሰረትም ቢሆን ክፍያዉ ሕጋዊ ነዉ፡፡

የኦሮሚያ ጠቅላይና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዉሳኔ የሕጉን ሙሉ አቋምና ይዘት ያላገናዘበና እንዲሁም የባንክን አሰራር ግምት ዉስጥ ያላስገባና የሚያወሳስብ ነዉ፡፡ ባንኮች አንድ ሰዉ የእከሌን እዳ ልከፍል ነዉ ሲል፤ ዉክልና እንዳለዉና እንደሌለዉ እንዲያረጋግጡ መጠየቅ ተገቢም አይደለም፡፡ እዳን ለመክፈል የዉክልና ማስረጃ የሚያስፈልግ ከሆነ ባለእዳዉንም ተጨማሪ ወጪና ኪሳራ የሚያጋልጥ አሰራር ነዉ፡፡

ከክርክሩ መሀል ተበዳሪ፤ ይሄ የ2000 ብር ክፍያ ይርጋን ለማቋረጥ የተደረገና በልጇም እንዳልተፈጸመ ጠቆም አድርጋ አልፋለች፡፡ ነገሩን አሰገራሚ የሚያደርገዉ ተበዳሪ በጠበቃ ነዉ የተከራከረችዉ፤ ጠበቃዉን ደግሞ የቀጠረዉ ልጇ በ1996 የተሰጠዉን ዉክልና መሰረት አድርጎ ነዉ፡፡ ለነገሩ ፍርድ ቤቱ እንደ ጭብጥ የያዘዉ ልጇ ከፍሏል ወይ የሚለዉን ሳይሆን ዉክልና አለዉ ወይ የሚለዉን ነዉ፡፡ ግን ክፍያዉን የፈጸመዉ እሱ ባይሆንስ?

እላይ እንደጠቀስኩት ለአስተያየቱ መነሻ የሆነዉ ልጁ ስልጣን የለዉም የሚል ነዉ፡፡ነገር ግን ጉዳዩ በድርጊት ወይም በዝምታ ስለተሰጠ ዉክልና፤ እና ስለ አምሳለ-ስልጣን የሚያነሳቸዉ የሕግ ጥያቁዎችን በሌላ ጽሁፍ እንመለከታለን፡፡

አቶ አስቻለዉ ቱጂ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ መረጃ ስለሰጡኝ፤ ሀሳብ ለመለዋወጥ ጊዜያቸዉን ስለሰዉ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ነገር ግን የቀረበዉ አስተያየትና ክርክር ድክመት ቢገኝበት ሃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ፡፡