መግቢያ

የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1724 እንዲህ ይነበባል፤ መንግስት ወይም ለሕዝብ አገልግሎት የቆሙ መስሪያ ቤቶች ግዴታ የሚዋዋሉባቸዉ ዉሎች ሁሉ በጽሁፍና በሚገባ አኳኋን በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ባንድ ባስተዳደር ክፍል መስሪያ ቤት መዝገብ ወይም ዉል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠዉ ሰዉ ፊት መሰራት አለባቸዉ፡፡ እንግሊዘኛዉ ደግሞ እንዲህ ይነበባል፤ Any contract binding the Government or a public administration shall be in writing and registered with a court, public administration or notary. የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የሚዋዋላቸዉ ዉሎች በዚህ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1724 የሚወድቁ ናቸዉ ወይ የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነዉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ.14285 በመጋቢት 15 1997 የሰጠዉ ዉሳኔ ነዉ፡፡

ጉዳዩ የተጀመረዉ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአንድ ግለሰብ ላይ በመሰረተዉ ክስ ዉዝፍ የቤት ኪራይ ባለመክፈላቸዉ እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ነዉ፡፡ ግለሰቡም ዉሉ ላይ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ሃላፊ ሆነ እራሱ አልፈረሙበትም፤፤ ኪራይ ክፈልበት በተባልኩበት ቤት ዉስጥም አልኖርኩም፤ የተከራየዉ ሌላ ቤት ሲሆን በዚያም የሚጠበቅበትን ክፍያ እንደፈጸመ በመግለጽ ተከራክሯል፡፡ 

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዉሳኔዉ ኪቤአድ የመንግስት መስሪያ ቤት ነዉ፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1724 መሰረት ደግሞ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዉል በጽሁፍ መሆን አለበት፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1727(1) እና (2) መሰረት ደግሞ በጽሁፍ የሚደረገዉ ዉል በሁለት ምስክሮች መረጋገጥ አለበት፤ ይህ ካልሆነ ዉሉ አይጸናም፡፡ ለጉዳዩ መነሻ የሆነዉ ዉል በሁለት ምስክሮች ያልተረጋገጠ በመሆኑ አይጸናም በሚል ወስኗል፡፡ ይህም ዉሳኔ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጽናቱ የሰበር አቤቱታ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የቀረበለትን አቤቱታ በተመለከተ እንዲህ ሲል ወስኗል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሉ በሁለት ምስክሮች ፊት ባለመረጋገጡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1724 እና 1727(2) መሰረት አይጸናም በሚል ነዉ የአመልካችን ይግባኝ ዉድቅ ያደረገዉ፡፡ በመሰረቱ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1724 የመንግስት አስተዳደር አካል ሆኖ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መስሪያ ቤትን የሚመለከት ነዉ፡፡ በመሆኑም አመልካች የተቋቋመበትን አዋጅ ቁ.59/83 ለማሻሻል የወጣዉ አዋጅ ቁ.133/91 አንቀጽ 2(1) አመልካች የራሱ የሕግ ሰዉነት ያለዉ ድርጅት ሆኖ እንደተቋቋመ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም የአመልካች ተግባርና ሃላፊነት የመንግስት አስተዳደር ስራን ማከናወን አለመሆኑን ከአዋጁ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ድርጅቱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.1724 መንፈስ የመንግስት አስተዳደር አካል እንዳልሆነ ያሳያል፡፤ በመሆኑም አመልካች ለመ/ሰጭ ጋር ያደረገዉ ዉል በተጠቀሰዉ ድንጋጌ የሚሸፈን አይደለም፡፡ በዚህም ይህ ችሎት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.348(1) መሰረት ሽሮታል፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በቀሩት ነጥቦች ላይ አከራክሮ የመሰለዉን እንዲወስን ጉዳዩ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.343(1) መሰረት ተመልሶለታል፡፡

 

በእርግጥ ይህ ዉሳኔ የተሰጠዉ የሰበር ሰሚ የሕግ ትርጉሞች በየትኛዉ ደረጃ በሀገሪቱ ባሉት ፍርድ ቤቶች ላይ ያለዉ አስገዳጅነት በሕግ ከመታወጁ በፊት ነዉ፡፡ ያም ቢሆን እንደ መጨረሻ የሀገራችን የዳኝነት አካል የሚሰጣቸዉን ዉሳኔዎች መተንተን እና መተቸት ለሕግ የበላይነት መጎልበትና ለሕግ ስርአቱ እድገት የሚኖረዉ ጥቅም ግልጽ ነዉ፡፡

ትንታኔ እና ትችት

ይህ ጉዳይ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1724ን ሲመለከት ይህን ድንጋጌ ተንትኖና ግልጽ አድርጎ ማለፍ ሲችልና ሲገባዉ ሰበር ችሎቱ ጉዳዩን አድበስብሶ በደንብ ያልተብራራ ዉሳኔ (የሕግ ትርጉም ማለት ያስቸግራል) ሰጥቶ አልፏል፡፡ “ይሄ ነዉ ብያለዉ ይሄ ነዉ” የሚል ነዉ የሚመስለዉ፡፡ ከዚህ በፊት የበላይ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸዉ ዉሳኔዎች ስለሚኖራቸዉ አስገዳጅነት የሚነካካ ጽሁፍ በእንግሊዘኛ በዚህ ዌብሳይት ላይ አቅርቤ ነበር፡፡ ጽሑፉን እዚህ ማግኘት ይችላሉ፡፡ የፍርድ ቤት ዉሳኔን (ማለትም የበላይ ፍርድ ቤት የሰጠዉን የሕግ ትርጉም) የታች ፍርድ ቤቶች እንዲቀበሏቸዉና እንዲተገብሯቸዉ ለማድረግ ሕግ ያለዉ ጥቅም እጅግ በጣም ትንሽ ነዉ፡፡ ማለቴ አዋጅ በማዉጣትና ከአሁን ከኋላ በሀገሪቱ ያሉ ዳኞች ሰበር ችሎት የሚሰጠዉን የሕግ ትርጉም ተከተሉ ብሎ በማወጅ ብዙ ዉጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ የሰበር ችሎት ዉሳኔዎችን ማሳተምና ማሰራጭት አንድ ጠቃሚ እርምጃ ነዉ፡፡ ዋናዉ ግን የዉሳኔ አሰጣጥና አጻጻፍ ስርአታችንን መፈተሸ አለብን፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ማወቅ ያለበት ነገር ምንም እንኳ አቤቱታዉ የቀረበዉ በአንደኛዉ ወገን ወይም በሁለቱም ተሟጋች ወገኖች ቢሆንም የሚሰጠዉ ዉሳኔ ግን ከተሟጋቾቹ ይዘላል፡፡ በመሆኑም ተሟጋቾቹ ከሚያነሱት መከራከሪያ ነጥቦች በላይ ማየት መቻል አለበት፡፡ የሚሰጠዉ ዉሳኔ የሁለቱን ሙግት ለመቋጨት ብቻ አይደለም፡፡ እሱ ብቻ ቢሆንማ ኖሮ ሳንቲም በመወርወር አንበሳ ላንተ ዘዉድ ለሱ ብለዉ በአጭሩ በፈቱት፡፡ የሰበር ችሎቱ ዉሳኔ ጉዳዩን መፍታት ብቻ ሳይሆን በፍትሕ ስርአቱና በጉዳዩ ላይ ድርሻ ያላቸዉን አካሎች ማሳመን መቻል ወይም መሞከር አለበት፡፡ ብያለዉ ብያለዉ፤ አይሰራም፡፡ ለምን እንዳለ፤ ለምን ይሄኛዉን መከራከሪያ ነጥብ እንዳልተቀበለዉ በበቂ ሁኔታ መተንተን መቻል አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር የሰበር ችሎቱ ዳኞች የአስተማሪነታቸዉን ሚና በሚገባ መጫወት አለባቸዉ፡፡ ምክኒያታቸዉን ሊያስረዱን ይገባል፡፡ ሕጉን በምን እንደዚህ አድርገዉ እንደተረጎሙት ስርተዉ ሊያሳዩን ይገባል፡፡ የመልካም አስተዳደር/አገዛዝ አንዱ መገለጫ ምክኒያታዊና ምክኒያቱ በደንብ የተዘረዘረ/የተገለጸ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ምሳሌ መሆን ይገባዋል፡፡ ስንት ቦታ አቆራርጠዉ ይመጣሉ ባለጉዳዩች፡፡ ጉዳዩን ስንት ፍርድ ቤት አልፎ እዛ በመምጣቱ የወጡ መጪዎችና ኪሳራዎችን እዉቅና በመስጠት የተነሱትን ጭብጦች በደንብ አጥንቶ፤ ምክኒያቱን ዘርዝሮ፤ ዉሳኔ መስጠት ይገባል፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ የታች ፍርድ ቤቶችም ለዉሳኔዉ የሚገባዉን ክብር ይሰጡታል፡፡

ወደተያዘዉ ጉዳይ ስመጣ፤ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1724 ራሱ ግልጽነት ይጎለዋል፡፡ በ1724 የሚገዙት ዉሎች በጽሁፍ መሆን እንዳለባቸዉና ዉል የማዋዋል ስልጣን በተሰጠዉ ፊት መደረግ እንዳለባቸዉ ይደነግጋል፡፡ ጥያቄዉ፤ በዚህ መልኩ መቋቋም ያለባቸዉ ዉሎች እነማን ናቸዉ የሚል ነዉ፡፡ መልሱ ይህ ነዉ፤ መንግስት ወይም ለሕዝብ አገልግሎት የቆሙ መስሪያ ቤቶች ላይ ግዴታ የሚጥሉ ዉሎች፡፡ መንግስት ላይ ግዴታ የሚጥሉ ወይም ለህዝብ አስተዳደር የቆሙ መስሪያ ቤቶች ላይ ግዴታ የሚጥሉ፡፡ ልብ ይበሉ፤ ወይም በሚል ነዉ የተገናኙት፡፡ አንድ መስሪያ ቤት (የመንግስትም ይሁን የሌላ) የሚሰራዉ ስራ ወይም የተቋቋመበት አላማ ለህዝብ አስተዳደር ከሆነ እሱ ላይ ግዴታ የሚጥል ዉል፤ ማለትም እሱ የሚዋዋለዉ ዉል በተባለዉ መልኩ/ፎርም መሆን አለበት፡፡ ይህ አንደኛዉ አይነት ነገር ነዉ፡፡ሁለተኛዉ ደግሞ ዉሉ መንግስት ላይ ግዴታ የሚጥል ከሆነ በዚህ ድንጋጌ መሰረት መቋቋም አለበት፡፡ ይህ ማለት መንግስት እንደተዋዋይ ወገን ሲዋዋል ነዉ፡፡ ሁለት ነገሮች ግልጽ መሆን አለባቸዉ፡፡ አንደኛዉ፤ መንግስት ምንድር ነዉ? አንድ ዉል መንግስት ላይ ግዴታ ይጥላል የሚባለዉ መቼ ነዉ? ሁለተኛ አንድ ድርጅት ለህዘብ አስተዳደር አላማ ነዉ የተቋቋመዉ የሚባለዉ መቼ ነዉ?

ስለዉል መቋቋምና የሕግ ዉጤት አስመልክቶ የኢትዮጲያን ሕግ በማብራራት ለረጅም ጊዜ እያገለገለ ያለን ጽሁፍ ያዘጋጀዉ ቺቺኖቪች ስለ 1724 የሰጠዉ ማብራሪያ በጣም አጭርና የያዝነዉን ጉዳይም የማይመለከት ሲሆን፤ እንደዉም ድንጋጌዉ ማብራሪያ የማያስፈልገዉና ግልጽ አድርጎ የተገነዘበዉ ይመስላል፡፡

‘Registered’ means filed with a public officer, whether judicial, administrative or notarial, empowered to and responsible for keeping special records to that end. In practice, he is often an official of the contracting administrative body itself. The implication that this body’s contracts do not bind before their registration is much clearer in the French master-version of this article.

 

የሰበር ችሎቱ የሰጠዉ ዉሳኔ ላይ ያነሳቸዉ ነጥቦች የሚከተሉት ሶስቱ ብቻ ናቸዉ፡፡ እነዚህም፤

1.  በመሰረቱ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1724 የመንግስት አስተዳደር አካል ሆኖ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መስሪያ ቤትን የሚመለከት ነዉ፡፡

2.  በመሆኑም አመልካች የተቋቋመበትን አዋጅ ቁ.59/83 ለማሻሻል የወጣዉ አዋጅ ቁ.133/91 አንቀጽ 2(1) አመልካች የራሱ የሕግ ሰዉነት ያለዉ ድርጅት ሆኖ እንደተቋቋመ ይገልጻል፡፡

3.  በተጨማሪም የአመልካች ተግባርና ሃላፊነት የመንግስት አስተዳደር ስራን ማከናወን አለመሆኑን ከአዋጁ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ድርጅቱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.1724 መንፈስ የመንግስት አስተዳደር አካል እንዳልሆነ ያሳያል

በመሰረቱ 1724 የሚመለከተዉ የመንግስት አስተዳደር አካል ሆኖ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መስሪያ ቤትን ነዉ

የሰበር ችሎቱ በመሰረቱ 1724 የሚመለከተዉ የመንግስት አስተዳደር አካል ሆኖ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መስሪያ ቤትን ነዉ ይላል፡፡ እላይ እንደገለጽኩት የአማርኛዉም ሆነ የእንግሊዘኛዉ ቅጂዎች እንዲህ አይሉም፡፡ 1724 እላይ እንደተገጸዉ የፎርም አይነትን (መጻፍና በባለስልጣን ፊት መደረግ እንዳበት) ይደነግጋል፡፡ ይህ ፎርም የተደነገገዉ ለሁለት አይነት ዉሎች ናቸዉ፡፡ አንደኛዉ አይነት መንግስት ላይ ግዴታ የሚጥሉ ዉሎች ናቸዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ለሕዝብ አስተዳደር አላማ የተቋቋሙ መስሪያ ቤቶች ላይ ግዴታ የሚጥሉ ዉሎች ናቸዉ፤ እነዚህ መስሪያ ቤቶች የመንግስት ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡እንደዉም የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ብቻ ቢመለከት ኖሮ ድንጋጌዉ መንግስት ላይ ግዴታ የሚጥሉ ዉሎች በማለት ብቻ ሊያልፍ ይችል ነበር፡፡

እናም ሰበር ችሎቱ 1724 በመሰረቱ የሚመለከተዉ የመንግስት አስተዳደር አካል ሆኖ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መስሪያ ቤትን ነዉ ሲል ከ1724 ይዘት ጋር አብሮ ስለማይሄድ፤ በተለይ ደግሞ ሁለቱን በወይም የተያያዙቱን በእና በማገናኘት የሰጠዉ ትርጉም ከምን ተነስቶ እንደሆነ እና ምክኒያቱ ምን እንደሆነ አላብራራም፡፡ ምክኒያት ያልተሰጠዉ/ያልተብራራ ትርጉም፡፡ ብያለዉ ብያለዉ አይነት፡፡

በመሆኑም አመልካች የተቋቋመበትን አዋጅ ቁ.59/83 ለማሻሻል የወጣዉ አዋጅ ቁ.133/91 አንቀጽ 2(1) አመልካች የራሱ የሕግ ሰዉነት ያለዉ ድርጅት ሆኖ እንደተቋቋመ ይገልጻል

እርግጥ ነዉ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የተቋቋመዉ በአዋጅ ቁ.59/83 ነዉ፡፡ ይህ አዋጅ በከፊል በሌላ አዋጅ (ማለትም በአዋጅ ቁ.133/91) ተሸሽሏል፡፡ ሰበር ችሎቱ እንዳለዉ በተደረገዉ ማሻሻያ መሰረት ድርጅቱ የሕግ ሰዉነት እንዳለዉ ተገልጧል፡፡ አንቀጽ 2(1) (የአዋጅ ቁጥር 133/91) እንዲህ ይላል፡

(2) ማሻሻያ

የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 59/1975 ለማሻሻል ወጥቶ የነበረዉ አዋጅ ቁጥር 31/1989 ተሸሮ የማቋቋሚያ አዋጁ እንደሚከተለዉ ተሸሽሏል፤

(1)አንቀጽ 3 ተሰርዞ በሚከተለዉ አዲስ አንቀጽ ተተክቷል፤

አንቀጽ 3 መቋቋም

1)  የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት (ከዚህ በኋላ ድርጅቱ እየተባለ የሚጠራ) የሕግ ሰዉነት ያለዉ ራሱን የቻለ የፌዴራ መንግስት መስሪያ ቤት ሆኖ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡

2)  የድርጅቱ ተጠሪነት ለስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ይሆናል”

 

የሕግ ሰዉነትስ ይኑረዉ ነገር ግን ይሄ ከተያዘዉ ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት አለዉ? ነዉ ወይስ የሕግ ሰዉነት የሌላቸዉን የመንግስት ድርጅቶች ነዉ የሚመለከተዉ? ጥያቄዉ መሆን የነበረበት፤ ይህ ድርጅት የሚዋዋለዉ ዉል መንግስት ላይ ግዴታ ይጥላል ወይም ደግሞ ይህ ድርጅት ለሕዝብ አገልግሎት አላማ ነዉ ወይ የተቋቋመዉ?

የኪራይ ቤቶች ተግባርና ሃላፊነት የመንግስት አስተዳደር ስራን ማከናወን አይደለም

በሶስተኛ ደረጃ ሰበር ችሎቱ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ተግባርና ሃላፊነት የመንግስት አስተዳደር ስራን ማከናዉን አይደለም፤ ይህን ደግሞ ከአዋጁ መረዳት ያቻላል፡፡ እንዴት ነዉ መረዳት የሚቻለዉ? የትኛዉ የአዋጁ ክፍል ነዉ ድርጅቱ የመንግስት አስተዳደር አካል እንዳልሆነ የሚያሳየዉ? የመንግስት አስተዳደር ስራስ ማለት ምንድን ነዉ? እነዚህም ጥያቄዎች ሳይመልሱ እንደዉ በደፈናዉ ከአዋጁ መረዳት ይቻላል፡፡ እንዲህ በቀላሉና በደፈናዉ ከአዋጁ መረዳት ቢቻልማ ጉዳዩም እዚህ ባልደረሰ  ኖሮ፡፡

መደምደሚያ

ሬኔ ዴቪድና ጥላሁን ተሾመ 1724ን አስመልክቶ የጻፉት ነገር ካለ በኋላ እጨምርበታለሁ፡፡ እንዲሁም ሰበር ችሎቱ ይህን ዉሳኔ ከሰጠ በኋላ ተመሳሳይ ጉዳይ አጋጥሞት ከነበር ጠቁሙኝ፤ ካገኘዉም አሁንም በጉዳዩ ላይ ማስታወሻ እጨምርበታለሁ፡፡ ከሁለቱ ጋር አያይዤም 1724 በምን መልኩ መተርጎም እንዳለበት የበኩሌን እላለዉ--በሚጨመር ማስታወሻ መልኩ፡፡ ጽሁፉ ሙሉ አይደለም፤ it is half-baked:: ሃሳባችሁን በማካፈል አበልጽጉት፡፡