Print this page

የኢትዮጵያ ብር እና የውጭ ሀገር ገንዘብን ይዞ መገኘት/ማዘዋወር ያለው የሕግ ተጠያቂነት

Jun 24 2022

 

 

1. መግቢያ

ሀገራችን አንደሌሎች ሀገራት ገንዘብ የኢኮኖሚዋ መሠረት ሆኖ የሚያገለግልና ይህንን ውስን የሀገር ሀብት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል አስፈላጊ የሆኑ የቁጥጥር እርምጃዎችን ለመውሰድ  ገንዘብ የሚያዝበትና የሚተዳደርበትን አግባብ በተመለከተ በተለያዩ ሕግጋቶች ደንግጋ እናገኛለን፡፡ ይህንን አላማ ለማሳካት አስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነትን እንደማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጋ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ አካታ እየተገበረች በመሆኑ በቀጥታ ከወንጀል ጋር ያለውን ቁርኝት ጽሑፉ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡ ጽሑፉ በቅድሚያ አጠቃላይ መንደርደሪያ ሀሳቦችን ለማንሳት የሚሞክር ሲሆን የገንዘብ ትርጉምን፣ የውጭ ምንዛሬ ምንነትንና ሊታዩ የሚገባቸውን የሕግ ማዕቀፎችን መነሻ አድርጎ ያትታል፡፡ በመቀጠልም የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ገንዘብን በጥሬ ገንዘብ ለመያዝና ለማዘዋወር የሚፈቀድባቸው አግባቦች ከተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች አንፃር ለማንሳት ይሞክሯል፡፡ የተለየ ትኩረትም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ሊታዩ የሚገቡ ነጥቦችን አንስቶ የሚሞግትና የሚያስገነዝብ አፃፃፍን ተከትሏል፡፡ ጽሑፉ በሕግ ከተቀመጠው አግባብ ውጭ ገንዘብ መያዝና ማስተላለፍ የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነትን አጉልቶ በማንሳት የሚስተዋሉ የአረዳድና የአተረጓጎም ክፍተቶችን ሽፋን ሰጥቶ ካነሳ በኋላ ሊያዝ የሚገባውን ተገቢ አረዳድና አተረጓጎማቸውን አንስቶ ይሞግታል፡፡ በመጨረሻም ጽሑፉ ማጠቃለያ ሃሳቦችን ጨምቆ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡

2. የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ገንዘብ የሕግ ትርጉም

ገንዘብ በቀን ለቀን የኑሮ ዑደት ውስጥ ያለው እሴትና ትርጉም ከሕግ ከመነጫ መረዳት የዳበረ ብቻ ሳይሆን በማህበሩ ግኑኝነት ውስጥ ተፀንሶ የተወለደ ብሎም ያደገ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ትርጓሜውም ይሁን እሴቱ ታዲያ በመደበኛው የእውቀት የሽግግር ሂደት ተንከባሎ የመጣ አለመሆኑንና ባልተፃፈ ዕውቀት እንዲሁም መረዳት በማህበረሰብ ዘንድ ከመገኘቱም አልፎ ማህበረሰቡ በቀላሉ የሚግባባም ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ አይነት መረዳት በራሱ የሚነቀፍና የሚጠላ ሳይሆን የሚፈለግና ለሕግ ሰፈርም መነሻ ሊሆን እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ሆኖም ግን አሁን ባለንበት የማህበረሰቡ መረዳትና በሀገራችን ስለገንዘብ ከሚደነግጉ ድንጋጌዎች አኳያ አንድ አይነት ትርጓሜ ያዘሉ ሳይሆኑ ለየቅላቸው ተርጉመው የሚጓዙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ምንም እንኳን በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤና መረዳት ማየቱ አስፈላጊ ቢሆንም በራሱ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅና ከፀሃፊውም የሙያ ከባቢ ዘልሎ ማህበረሰባዊ ባለሙያነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ፀሀፊው ከዚህ ጉዳይ ይልቅ በህጉ ሙያ ላይ አትኩሮቱን ለማድረግ ሞክሯል፡፡ ታዲያ በህጋችን ውስጥ ስለገንዘብ የተሰጠውን ትርጉም ከማየታችን አስቀድሞ በተለያዩ አግባብ የተሰጠውን ትርጉም ማስቀደሙ ለግንዛቤ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ታላቁ ፀሀፊና ሕግ አዋቂ ብላክስተን (Blackstone) ገንዘብ (money) የሚለውን ቃል ሲፈታ

‘The medium of commerce … a universal medium, or common standard, by comparison with which the value of all merchandise may be ascertained, or it is a sign which represents the respective values of all commodities’.  በማለት ያስቀምጣል፡፡

የሕግ መዝገበ ቃላት የሆነው ብላክስሎው (Black’sLaw Dictionary) ገንዘብ (money) ለሚለው ቃል ትርጉም ሲሰጥ “medium of exchange authorized or adopted by a government as part of its
currency” በማለት ነው፡፡

ወደ ሀገራችን ሕግጋት ስንመጣ ገንዘብ ለሚለው ቃል ትርጓሚ የተሰጠው ሳይሆን ገንዘብ-አከል ንብረት በሚል ትርጉም የተሰጠው ሲሆን እጅግ ሰፊና ብዙ ፍሬ ነገሮችን የያዘ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ /እንደተሻሻለ/ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 2(9) መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ የሕግ ትርጉም መካከል ለርዕሰ ጉዳያችን ቀጥተኛ ግኝነት ያለው የጥሬ ገንዘብ ጉዳይ በመሆኑ የዚህ ጽሑፍ አተኩሮት በሌሎች ገንዘብ-አከል ንብረቶችን በሚመለከት ሳይሆን በጥሬ ገንዘቡ ላይ ይሆናል፡፡ በተለየም ጥሬ ገንዘብን ከመያዝ፣ ከማስተዳደር፣ ከመቆጣጠር እና ከወንጀል ተጠያቂነት ጋር በተያያዘ ያሉ የሕግ ድንጋጌዎችንና አተርጓጎማቸውን በስፋት ለማየት የሚሞክር ጽሑፍ ነው፡፡

ለዚህ ጽሑፍ አላማና አካሔድ ግልፅነት ጥሬ ገንዘብ የሚለውን የሕግ ፍሬ ነገር በሁለት አይነት እይታ በአጠቃላይ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ጥሬ ገንዘብ (ብር) በሚል እና ሁለተኛው ደግሞ የውጭ ሀገር ገንዘብ በሚል ለሁለት ከፍሎ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከውጭ ሀገር ገንዘብ ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ በሕግ ደንግጋ ስታስተዳድርና ገደብም ጥላ ከኢትዮጵያ ብር ይልቅ የቆየች በመሆኑ ከውጭ ሀገር ገንዘብ ጋር በተያያዘ ያሉ የሕግ ድንጋጌዎችን እና አተረጓጎማቸውን ለማየት ተሞክሯል፡፡ የውጭ ሀገር ገንዘብ የሚለው ቃል እራሱ ምን ማለት እንሆነ በቅድሚያ መመልከቱ የተሻለ ይሆናል፡፡

3.  የውጭ ሀገር ገንዘብ ምንነትና ከውጭ ምንዛሪ ጋር ያለው ተዛምዶ

3.1. የውጭ ሀገር ገንዘብ ምንነት

ስለውጭ ሀገር ገንዘብ አስተዳደር ከመሄዳችን በፊ በቅድሚያ የውጭ ሀገር ገንዘብ ምን እንደሆነና ከውጭ ምንዛሪ ጋር አንድ አይነት ስለመሆን አለመሆናቸው በዝርዝር ማየቱ ተገቢውን የሕግ አረዳድና አተረጓጎም ላይ እንድንደርስ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ የውጭ አገር ገንዘብ ምን ማለት እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ /እንደተሻሻለ/ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 2(5) በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ከድንጋጌው መረዳት እንደሚቻለው ሶስት መሰረታዊና በጣምራ (Cumulative) ሊነበቡና ሊሟሉ የሚገባቸው ፍሬ-ነገሮች አሉ፡፡

 1. ከኢትዮጵያ ገንዘብ በስተቀር፡- ይህ ፍሬ-ነገር ቀዳሚው መሟላት ያለበት ሀረግ ሲሆን ምናልባትም ግልፅና ብዙ ማብራሪያ የማይፈልግ በራሱ ገላጭ የሆነ (Self-explanatory) ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተገለገለችበት ያለው የገንዘብ መደብ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 17/1ና 2/ መሠረት ብር እና ሳንቲሞች እንደሆኑ የተመለከተ ሲሆን ከእነዚህ የገንዘብ መደቦች ውጭ ያሉትን የተመለከተ ፍሬ ሃሳብ መሆኑን መረዳት ይቻለል፡፡
 2. ከኢትዮጵያ ውጭ በማናቸውም ሃገር ሕጋዊ ገንዘብ የሆነ፡- ሌላኛው በጣምራ መሟላት ያለበት ፍሬ-ነገር ይኽው ሲሆን ከዚህ ፍሬ-ጉዳይ ላይ በትንሹ ሁለት መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን መረዳት ያቻላል፡፡ ቀዳሚው መሰረታዊ ፍሬ-ጉዳይ የውጭ ሀገር ገንዘብ ለማለት የውጭው ሀገር ላይ ወይም የገንዘቡ ባለቤት የተባለው ሀገር ላይ ሕጋዊ ገንዘብ መሆን እንዳለበት በጥብቅ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህ ማለት የገንዘቡ ባለቤት የሆነው ሀገር ገንዘብ በሀሰት ተመሳስሎ የተሰራ መሆን እንደሌለበት ከማስገንዘቡም በላይ በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ያለ መሆን የሚገባውን የሚያመለክትና አሁን ስራ ላይ ባለው የሌላ ሀገር ገንዘብ የተተካውን የቀድሞ ገንዘብ የሚመለከት እንዳልሆነ ልብ ሊባል የሚገባው ነው፡፡

ሁለተኛው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ድርጅቶች እየተዘዋወረ ያለው የክሪፕቶከረሲ (Crypto currency) ጉዳይ ጋር ያለው ሁኔታ ነው፡፡ የክሪፕቶከረሲ (Crypto currency) ዋናው ፅንሰ ሃሳብ በመንግስት የማይዘወርና የማይተዳደር ነገር ግን ድርጅቶች በኮምፒውተር በሚሰጥ ልዩ መለያ ቁጥር በመያዝ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱት አዲስ የሆነ የገንዘብ አይነት ነው፡፡ ይህ አይነት ገንዘብ ይህ ጽሑፍ እስከተፃፈበት ቀን ድረስ በአለማችን ላይ ያሉ ሀገራት እንደ ህጋዊ ገንዘብ ያልመዘገቡት ሲሆን ይህን አይነት ገንዘብ በሌሎች ሀገራት ህጋዊነቱ ባልፀናበት ሁኔታ እንደ ውጭ ሀገር ገንዘብ ሊቆጠር እንደማይችል በሁለተኛ ነጥብ የተመለከተው ፍሬ-ነገር ያስገነዝባል፡፡ በየትኛውም አገር ሕጋዊ ገንዘብ ተብሎ ያልተሰጠው እስከሆነ ድረስ የውጭ ሀገር ገንዘብ ተብሎ ሊወሰድ አይችልም ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን አንድ አገር ይህንን አዲስ ዘመን አመጣሽ ግኝት እንደህጋዊ ገንዘብ የተቀበለው እንደሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ በማናቸውም ሃገር ሕጋዊ ገንዘብ የሆነ የሚለውን ፍሬ-ነገር የሚያሟላ መሆኑን መገንዘቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም የክሪፕቶከረሲ (Crypto currency) ጉዳይን በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ ግንቦት 29 ቀን 2014 በወሰነው ውሳኔ መሠረት ማንኛውም አካል ሊጠቀመው እንደይማችል አስገንዝቧል፡፡

 1. በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረግ ክፍያ ተቀባይነት እንዳለው ብሔራዊ ባንክ ያሳወቀው ማናቸውም ገንዘብ፡- ሶስተኛውና የመጨረሻው በጣምራ ሊሟላ የሚገባው ፍሬ-ነገር መሰረታዊ የሚባልና አትኩሮት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ምንም እንኳ ከላይ የተመለከትናቸው ሁለት ፍሬ-ነገሮች የተሟሉ ቢሆኑ እንኳ የሶስተኛው ፍሬ-ነገር መሟላት አስፈላጊና የማይነጠል ነው፡፡ የዚህ መመዘኛ ዋናው ሃሳብ ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው የሚያወጣው ተቀባይት ያላቸው የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ዝርዝር ሲሆን ይህም እንደየጊዜውና እንደየሁኔታው ባንኩ የሚያወጣ በመሆኑ ጊዜውን የዋጀ መረጃ የሚያስፈልገው ነው፡፡ በአንጻሩ በተገላቢጦሽ አነባበብ ባንኩ በኢትዮጵያ ሀገር ውስጥ ተቀባይት ያላቸው ገንዘቦች በሚል ከገለፃቸው ውጭ ያሉ የውጭ ሀገር ገንዘቦች ሊቆጠሩና ሊካተቱ የሚገባ አለመሆኑን መረዳት ያቻላል፡፡ ይህ አይነት አረዳድ ህጋዊና ተገቢ ቢሆንም የራሱ የሆነ ክፍተቶች እንዳሉበት ማየት ይቻላል፡፡ በተለይ ብሔራዊ ባንክ ያላሳወቃቸውን ውጭ ሀገር ገንዘቦችን በጥቁር ገበያ ውስጥ የሚዘዋወር ከመሆኑ አኳያ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊጎዳ የሚቸል ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ የእነዚህ ሶስት መሰረታዊ ፍሬ-ነገሮች በጣምራ ሊነበቡና ሊወሰዱ የሚገባቸው ሲሆን ከሶስቱ ፍሬ ነገሮች አንዱ እኳን ያልተሟላ እንደሆነ የውጭ አገር ገንዘብ የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ አይሆንም፡፡ በመሆኑም የውጭ አገር ገንዘብ የሚለውን ህጋዊ ትርጉም ለመያዝም ሆነ ለመተግበር በቅድሚያ ከላይ የተመለከቱትን ሶስት ፍሬ-ነገሮች መሟላቱን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡

3.2. የውጭ ምንዛሬና የውጭ ሀገር ገንዘብ አንድነትና ልዩነት

ከዚህ ቀድሞ ባለው ምዕራፍ ውስጥ የውጭ አገር ገንዘብ የሚለውን ትርጉም በስፋት ያየን ሲሆን ከውጭ ሀገር ምንዛሪ ጋር ያለው ልዩነት እና ተዘማዶ ምን እንደሆነ በዚህኛው ክፍል ውስጥ በአግባቡ ማየቱ የጠራ አረዳድ፣ አተገባበር እና አተረጓጎም እንዲያዝ የሚያስችል በመሆኑ ሀሳቡን በመጠኑ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ለማቋቋም በወጣው /ማሻሻያ/ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 2(5) እና 2(6) ላይ የውጭ ሀገር ገንዘብና የውጭ ምንዛሪ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ በተሰጠው ትርጉም መሠረት የውጭ ምንዛሪ ትርጉም ሰፊና የውጭ ሀገር ገንዘብን እንደሚያካትት መረዳት ይቻለል፡፡ ድንጋጌው በብሔራዊ ባንክ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ገንዘቦችና በውጭ ሀገር ገንዘብ የተዘጋጁ የክፍያ ማዘዣዎች፣ የሐዋላ ሰነዶች፣ የተስፋ ሰነዶች፣ ድራፍቶች፣ ሴኪይሪቲዎች፣ እንደዚሁም ሌሎች የሚተላለፍ ሰነዶችና በውጭ ሀገር ገንዘብ የተያዙ የባንክ ሂሳቦች ወይም የሚከፈሉ ወይም በውጭ ሀገር ሂሳብ ወይም የማቻቻል አሠራር የሚደረግባቸው ንብረቶች እንደሆኑ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው የውጭ ሀገር ገንዘብን አጠቃሎና የተለያዩ የመገበያያ መንገዶችን ጨምሮ ሰፋ ባለመልኩ የተተረጎመ እንደሆነ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በብሔራዊ ባንክ ተቀባይነት ያገኘ ሁሉም የውጭ ሀገር ገንዘብ የውጭ ምንዛሬ ሊባል የሚችል ሲሆን ሁሉም የውጭ ምንዛሬ ግን የውጭ ሀገር ገንዘብ ሊባል አይችልም፡፡ በመሆኑም የሁለቱ ተዛማዶ አንዱ የሌላኛው አካል የሚሆኑበት ሁኔታ ያለ መሆኑን ልብ ይለዋል፡፡

4. ስለገንዘብ የሚደነግጉ አስፈላጊ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎች

የውጭ ሀገራትን ገንዘብንም ሆነ የኢትዮጵያ ብርን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚኖራቸው ተቀባይነት፣ ገደብ፣ ሁኔታ፣ ተጠያቂነት እና ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በተመለከተ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደነግጉ የሕግ ማዕቀፎች አሉ፡፡ እነዚህን የሕግ ማዕቀፎችን ለይቶ ማስቀመጡና አጭር የሆነ ማብራሪያ ማቅረቡ ለቀጣዩ ሰፊ ሀተታ ማጣቀሻ እንዲሁም በቀላሉ ግንዛቤ ለመጨበጥ የሚረዳ በመሆኑ እንደሚከለተው ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

 1. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/200፡- አዋጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ለማቋቋምና ስልጣንና ተግባሩን ለመደንገግ ወጣ አዋጅ ሲሆን በኢትዮጵያ ፈጣንና የተረጋጋ የዋጋ፣ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔና ጤናማ የፋይናንስ ስርዓትን ለማሳለጥ ዓላመው አድርጎ የወጣ ሕግ ነው፡፡
 2. አዲስ የታተሙ የኢትዮጵያ የብር ኖቶችን ስራ ላይ ለማዋል የወጣ መመሪያ ቁጥር ከማዳ/2/2013፡- ኢትዮጵያ በ2013 ዓ/ም መጀመሪያ ወር ላይ የብር ኖቶችን የቀየረች መሆኑን ተከትሎ የወጣ መመሪያ ሲሆን ይህ መመሪያ ግለሰቦችና ድርጅቶች ምን ያህል ኢትዮጵያ ብር በጥሬ ገንዘብ ሊይዙ እንደሚችሉ ጭምር የሚደነግግ መመሪያ ነው፡፡
 3. ሕጋዊ ገንዘብ ጥበቃ መመሪያ (Legal Tender protection directive) CMD 1/2020:- መመሪያው የኢትዮጵያ ሕጋዊ ገንዘብን ለመጠበቅ የወጣ ሕግ ሲሆን ብርን በማስቀመጥ ሊበላሽና ጉዳት ሊደርስበት የሚችልበትን ሁኔታዎችን ለመከለከል የወጣ መመሪያ ነው፡፡
 4. ሕጋዊ ገንዘብ ጥበቃ መመሪያ (ማሻሻያ) (Legal Tender protection (Amendment) directive) CMD 2/2021:- መመሪያው ገንዘብን አከማችቶ ከማስቀመጥ ጋር በተያያዘ ገደብን ለመጣል አልሞና ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የወጣ ሕግ ነው፡፡
 5. ገንዘብ የማውጣት ገደብ መመሪያ ኤፍአይኤስ/03/2020፡- መመሪያው ብሔራዊ ባንክን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሠረት የወጣ መመሪያ ሲሆን ግለሰቦችና ድርጅቶች በቀን እና በወር ውስጥ ምን ያህል የኢትዮጵያ ብር ከገንዘብ ተቋማት ማውጣት እንደሚችሉ የሚደነግግ መመሪያ ነው፡፡
 6. በኢትዮጵያ ውስጥ በብር እና በውጭ ምንዛሬ መያዝ ላይ የተጣለ ገደብ (መመሪያ ቁጥር ኤፍ.ኤክስ.ዲ/49/2017፡- ይህ መመሪያ የውጭ ምንዛሬና የኢትጵያን ብርን የሚያዝበትን አግባብና ወደ ውጭ ሀገር ይዞ መውጣት የሚቻልበትን እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ይዞ መግባት የሚቻልበትን ሁኔታዎችን እና ገደቦችን ለመደንገግ ታስቦ የወጣ መመሪያ ነው፡፡
 7. የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥረዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012፡- በሀገራችን ውስጥ የአስተዳደር ስነ-ስረዓት አዋጅ በተሟላ መንገድ ሲደነገግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን አዋጁ ከዚህ ቀደም የወጡ መመሪያዎች መመዘገብ እንዳለባቸውና አዲስ መመሪያዎችም በሚወጡበት ወቅት ሊከተሉት ስለሚገባቸው ስነ-ስረዓቶች የሚያስገድድ መመሪያ በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ ባወጣቸው መመሪያዎች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደሚኖር ልብ ማለት ይገባል፡፡
 8. የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ፡- የወንጀል ሕግ ሰዎችን ወንጀል እንዳይፈፅሙ ለማስተማር፣ ለማስጠንቀቅ፣ ወንጀል ከመፈፀም ለመከልከል እንዲሁም ፈፃሚዎችን ለማረም ታስቦ የተቀረፀ ሕግ ነው፡፡ ይህንን አላማ ለማሳካትም የወንጀል ድንጋጌዎች የሚመሩበትን የወንጀል መርሆችንና አጠቃላይ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ስለሚፈፀም ተግባር ወንጀል የሚሆንበትን አግባብ የሚያቋቁምበትን ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡
 9. የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006፡- የጉምሩክ አዋጅ ሌላው ቀጥተኛ ግኑኝነት ያለው ሕግ ሲሆን የውጭ ሀገር ገንዘብም ሆነ የኢትዮጵያ ብር ከሀገር ውጭ ይዘው የሚወጡ ወይም ይዘው የሚገቡ አልያም በሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬን ይዘው የሚገኙ ሰዎችን የሚቀጣ ድንጋጌን ያዘለ ነው፡፡

5. የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ገንዘብ በጥሬ ገንዘብ ለመያዝና ለማዘዋወር የሚፈቀድባቸው አግባቦች

ከዚህ ቀደም ባለው ምዕራፍ የኢትዮጵያ ብር እና የውጭ ሀገር ገንዘብ የሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፎችን አጠር ባለ መልኩ ለማቅረብ የተሞከረ ሲሆን በዚህኝ ምዕራፍ የተለያዩ የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ገንዘቦችን መያዝ ስለሚቻልበትና ስለተጣለባቸው ገደቦች በሰፊው ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

5.1. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማቋቋሚያ አዋጅ ስለኢትዮጵያ ገንዘብና ስለውጭ ሀገር ገንዘብ ሰፋ ባለ ሁኔታ የሚተነትንና እንደ እናት ሕግ ሆኖ የሚያገለግል አዋጅ ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት የሀገሪቱ ህጋዊ ገንዘብ ብር ተብሎ የሚጠራ ስለመሆኑና የገንዘብ መደቡም ሳንቲም ተብሎ የሚጠቀስ መሆኑን በግልፅ የሚደነግግ ነው፡፡ በገንዘብ ኖቶች ላይ የሚጻፈው ጽሁፍ፣ የኖቶቹ ስፋት፣ ቅርጽና መደባቸው እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ሁኔታዎች በብሔራዊ ባንክ የሚወሰን መሆኑን የደነገገ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ወይም ከኢትዮጵያ የሚወጣ ማንኛውም ሰው በባንኩ ከተወሰነው ወይም ከተፈቀደው በላይ የኢትዮጵያን ገንዘብ ይዞ  ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ወይም ለመውጣት እንደማይቻል በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስለውጭ ሀገር ገንዘብ አስተዳደር አዋጁ በሰፊው የሚያትት ሲሆን የውጭ ሀገር ገንዘብ ግብይት ስለሚፈፀምበት፣ መያዝ ስለሚቻልበት፣ ክፍያ ስለሚፈፀምበት ሁኔታዎችንና ገደቦችን በተመለከተ ሽፍን ሰጥቶታል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ  26 ላይ ተለያዩ ቅጣቶችን በተመለከተ የሚደነግግ ሲሆን ከውጭ ሀገር ገንዘብ እና ከሀገር ገንዘብ ጋር በተያየዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በቀላል እስራት አልያም ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት ድረስ እንዲሁም በገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

5.2. የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥረዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012

በሀገራችን በቅርቡ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥረዓት አዋጅ አፅድቃ በስራ ላይ ማዋሏ የሚታወስ ነው፡፡ አዋጁ ካስተዋወቃቸው ፅንሰ ሃሳቦች መካከል መመሪያ የማውጣት ስልጣን ያላቸው አካላት መመሪያውን በሚያወጡበት ጊዜ ሊከተሉት ስለሚገባ ሥነ-ሥረዓትና አዋጁ ከመውጣቱ በፊት መመሪያዎች ስላላቸው ውጤት የሚደነግግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ብሔራዊ ባንክ ከገንዘብ ጋር የተያያዙትን ጨምሮ ያወጣቸው ልዩ ልዩ መመሪያዎች በሥነ-ሥረዓት አዋጁ መሠረት ለጠቅላይ ዐ/ሕግ ቀርበው ሊመዘገቡና ለህዝብ ይፋ ሊደረጉ የሚገባቸው መሆናቸን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት ለጠቅላይ ዐ/ሕግ ቀርበው ያልተመዘገቡና ለህዝብ ይፋ ያልሆኑ መመሪያዎች በአዋጁ አንቀፅ 18 መሠረት እንደ ሕግ ሆነው የሚያገለግሉ አለመሆኑን በግልፅ ደንግጎ እናገኛለን፡፡ በዚህም መሠረት ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት በብሄራዊ ባንክ የወጡ መመሪያዎች በጠቅላይ ዐ/ሕግ ቀርበው የተመዘገቡ ስለመሆናቸውና የመመሪያ ቁጥርም የተሰጣቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡

5.3. አዲስ የታተሙ የኢትዮጵያ የብር ኖቶችን ስራ ላይ ለማዋል የወጣ መመሪያ ቁጥር ከማዳ/2/2013

ኢትዮጵያ በወርሃ መስከረም 2013 ዓ/ም አዲስ የብር ኖቶችን ያስተዋወቀችና የቀየረች መሆኑን ተከትሎ ይህንኑ ለማሳፈፀም ይረዳ ዘንድ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 5/1፣ 18/1 እና 27/2 መሠረት መመሪያ ወጥቷል፡፡ ከሀሰተኛ ገንዘብ ህትመትና ስርጭት ጋር በተያያዘ፣ የገንዘቡን የጥራት ደረጃ ከፍ ለማድግ በማቀድ፣ አዲስ የ200 ብር ኖት ለማስተዋወቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱና በወቅቱ በስራ ላይ የነበረውን ገንዘብ ከገበያው ላይ ለመሰብብ አስፈላጊ መሆኑን ተከትሎ መመሪያው ፀድቆ በስራ ላይ የዋለ ሲሆን አስፍላጊ የሆኑ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ በተለይም በመመሪያው አንቀጽ 6 ላይ ከተያዘው ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ ግኑኝነት ያለው ድንጋጌ የያዘ ሲሆን ከብር 5,000 በላይ ያለው የገንዘብ ቅያሪ በቀያሪው ስም በተከፈተ የሂሳብ ቁጥር መሆን እንዳለበት በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከብር 100,000 በላይ ያለ ገንዘብ በ30 ቀናት ውስጥ መቀየር እንዳለበት (መደበኛ የመቀየሪያ ጊዜ 60 ቀናት እንደሆነ ልብ ይለዋል) እንዲሁም ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማንም ሰው አከማችቶ የተገኘ እንደሆነ የሚወረስ ስለመሆኑ መመሪያው ተመልክቷል:: ከ1.5 ሚሊዮን ብር አከማችቶ የተገኘ ግሰለብ ገንዘቡ የሚወረስበት የሕግ አግባብ ምን ያህል አሳማኝና ህጋዊ ነው የሚለው ጥያቄ እዚህ ላይ ይነሳል፡፡ በተለይ የድንጋጌ ዝርዝር አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ ገንዘቡ ሊወረስ እንደሚችል የሚያስቀምጥ ከመሆኑ አኳያና በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ይህን አይነት የውርስ አተገባበር ያልደነገገ በመሆኑ ህጋዊነቱ እና አፈፃፀሙ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል፡፡ በአዋጁ መሠረት ገንዘብም ሆነ ንብረት ሊወረስ የሚቻልበት አግባብ በወንጀል ክስ ቀርቦ ፍ/ቤት በሚወስንበት ጊዜ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

5.4. ሕጋዊ ገንዘብ ጥበቃ መመሪያ (Legal Tender protection directive) CMD 1/2020 እና ሕጋዊ ገንዘብ ጥበቃ መመሪያ (ማሻሻያ) (Legal Tender protection (Amendment) directive) CMD 2/2021

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመመሪያ ቁጥር CMD1/2020 ገንዘብ አከማችቶ ሊያዝ የሚቻልበትን ሁኔታ በግልፅ የደነገገ ሲሆን ባንኩን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ላይ ይህን አይነት ገደቦችና ሁኔታዎች (ወደ ውጭ ሀገር እና ወደ ሀገር ውስጥ የኢትዮጵያን ብር ይዞ የመግባትን ሁኔታ ከመደንገጉ ውጭ) ካለመኖራቸውም በላይ ለብሔራዊ ባንክም ይህን ጉዳይ አስመልክቶ መመሪያ እንዲያወጣ ፈቃጅ ሕግ የተሰጠው ስለመሆኑ በግልፅ የተመለከተ ድንጋጌ የለም፡፡ ባንኩ መመሪያውን በሚያወጣበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁር 591/2000 አንቀፅ 27(2) መሠረት አድርጎ ቢሆንም ድንጋጌው በመሰረታዊ ደረጃ በአዋጁ የሰፈሩትን ድንጋጌዎች ለማስፈፀም እንጂ በአዋጁ ያልተካተቱ ሀሳቦችን በአዲስ መልክ ለመደንገግ እንዳልሆነ ሊታወቅ የሚገባው ነው፡፡ ሆኖም በአዋጁ ውስጥ ብርን ስለመያዝና ስለማከማቸት የሚመለከቱ ቀጥተኛ ድንጋጌዎች ባይኖሩም በአዋጁ አንቀፅ 5(19) ላይ ባንኩ ዓላማዎቹን ለማስፈፀም ማዕከላዊ ባንኮች በተለምዶ የሚኖራቸውን ሌሎች ሥልጣኖችን መጠቀምና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን እንደሚችል ከማስቀመጡ አኳያ በተዘዋዋሪ መልኩ ተመልክቷል የሚባልበት አግባብ እንዳለ መመልከቱ የሚቻል ይሆናል፡፡ መመሪያ ቁጥር CMD1/2020 ከሚከለክላቸው ተግባራት መካከል በህጋዊ ብር ላይም ሆነ በሳንቲሞች ላይ መልካቸውን በማንኛውም አግባብ መቀየር እንደማይቻል በግለፅ ያስቀምጣል፡፡

መመሪያው ከዚህ በተጨማሪ ገንዘቦቹን ማተም እንደማይቻልና ለማስተዋወቂያ አልያም ለማሳያ እንዲወል በማሰብ የሚደረግ የህትመት ስራ ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ሌሎች አካላት ፈቃድ መተየቅና ማግኘት እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛም ሰው በስራ-ቦታው፣ በቤቱ ወይም በማንኛቸውም ቦታ አስቦም ሆነ ቸልተኛ ሆኖ መደበኛ የገንዘብ ዝውውርን ሊገድበ በሚችል ሁኔታ ወይም በገንዘብ ላይ ገዳት ሊያደርስ በሚችልበት አኳኋን ከተፈቀደው መጠን በላይ ማከማቸት የተከለከ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ግለሰብ እስከ 100,000 (መቶ ሺህ) ብር ድስ በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል ሲሆን በሕግ ሰውነት የተሰጠው አካል ደግሞ እስከ 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) ብር ድረስ መያዝ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ቀድሞ ከነበር የ1 500 000 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ዝቅ የተደረገ በመሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ በሕግ ሰውነት ተሰጣቸው አካላት ማሻሻያ መመሪያው ከወጣ ቀን ጀምሮ በሶስት ቀናት ውስጥ በእጃቸው ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ ማስገባት እንዳለባቸው በአንቀፅ 5 ላይ ተመልከቷል፡፡

5.5. ገንዘብ የማውጣት ገደብ መመሪያ ኤፍአይኤስ/03/2020

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ከገንዘብ ተቋማት ገንዘብ ማውጣት ስለሚቻልበት ሁኔታና ገደብ በመመሪያ ኤፍአይኤስ/03/2020 ደንግጓል፡፡ የመመሪየው መውጣት አስፍላጊ የሆነበት መሰረታዊ ጭብጥ በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ ክፍያዎችን ለመተካት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም ቀልጣፍ የሆነ ስርዓት ለመዘርጋት በማቀድ በተጨማሪም የተለያዩ ወንጀሎችን ለመቀነስ በማቀድ፣ የገንዘብ ክምችትን ማሳደግ እና ገንዘብን ለማተም የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እንደሆነ ያትታል፡፡ በመመሪየው መሠረትም እስከ ብር 200,000 ድረስ በቀን እንዲሁም እስከ ብር 1,000,000 ድረስ በወር የተፈጥሮ ሰው ለማውጣት የተፈቀደለት ሲሆን የሕግ ሰውነት ያለው ተቋም ደግሞ በቀን እስከ ብር 300,000 እና በወር እስከ ብር 2,500,000 ድረስ ከአንድ የገንዘብ ተቋም ማውጣት እንደሚቻል ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በልዩ ሁኔታ እንዲፈቀድላቸው ለገንዘብ ተቋማት የሚያመለክቱ ሰዎች ስለሚፈቀድበት አግባብ በመመሪያው ተቀምጧል፡፡

5.6. በኢትዮጵያ ውስጥ በብር እና በውጭ ምንዛሬ መያዝ ላይ የተጣለ ገደብ (መመሪያ ቁጥር ኤፍ.ኤክስ.ዲ/49/2017

ሌላኛውና ምናልባትም ከሌሎች ላቅ ባለ ሁኔታ ስለገንዘብ መያዝ ሁኔታና ገደብ በሰፊው ደንግጎ የምናገኘው መመሪያ እ.ኤ.አ. በ2017 የወጣው ሕግ ነው፡፡ ህጉ አላማ አድርጎ በአጠቃላይ ያስቀመጠው በኢትዮጵያ ሀገር ውስጥ ነዋሪ የሆኑና ያልሆኑ ግለሰቦች ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅትና ከኢትዮጵያ ሀገር ወደ ውጭ ሀገር የሚወጡ ግለሰቦች መያዝ የሚችሉትን የኢትዮጵያ ብር እና የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ ሁኔታዎችንና ገደቦችን ለመደንገግ አላማው አድርጎ እንደሆነ ከመመሪየው መግቢያ ላይ መገንዘብ መቻል ነው፡፡ መመሪያው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑና ያልሆኑ ሰዎች በሚል ከፍሎ ገንዘብን የሚያዝበት ሁኔታና ገደብ ደንግጎ ይገኛል፡፡

5.6.1. በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ያላቸው መብትና ግዴታ

በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎችም ሆኑ ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም ሆነ ከኢትዮጵያ ሲሄዱ በሚያደርጉት እያንዳንዱ ጉዞ እስከ ብር 1,000 (አንድ ሺህ) ድረስ መያዝ እንደሚችሉ የሚደነግግ ሲሆን ወደ ጅቡቲ ሀገር የሚሄዱ ሰዎች ግን እስከ ብር 4,000 (አራት ሺህ) ድረስ ይዘው መሄድ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡

የውጭ ሀገር ገንዘብን በተመለከተ መመሪያው በግልፅ ያሰፈረ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት ከ1,000 ዶላር ወይም በሌላ ሀገር ገንዘብ ተመጣጣኙ በላይ በሚሆንበት ጊዜ አሳውቆና አስመዝገቦ /ዴክሌር አድርጎ/ መግባት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ሲሆን ወደ ውጭ ሀገር ይዞ መውጣት የሚችልበት አግባብ ደግሞ የባንክ ፈቃድ ያለው እንደሆነ ወይም የጉምሩክ ዴክላራሲዮን ያለው እና ማስረጃዎቹ 30 ቀናት ያልሞሉ ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንደሚገባ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በባንክ የተፈቀደላቸውን መጠን ወይም ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት ይዘውት የመጡትንና በጉምሩክ ዴክላራሲዮን ሰነድ ላይ ያስመዘገቡትን ገንዘብ ከያዙበት ቀን እና/ወይም በጉምሩክ ካስመዘገቡበት ቀን አንስቶ እስከ 30 ቀናት ድረስ መመንዘር እንደሚጠበቅባቸው ያስቀምጣል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባውና በአብዛኛው ስህተት እየተፈፀመበት ያለው የ30 ቀኑ አቋጣጠር ከያዘበት ጊዜ አንስቶ (From the date of acquisition) የሚለውን ሀረግ መሠረት አድርጎ ሲሆን አረዳዱ በማንኛውም አግባብ ማንኛውም ሰው የውጭ ሀገር ገንዘብን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ መረዳቱ አለ፡፡ ይህ አይነት አረዳድ ለትርጉም የተጋለጠ ቢሆንም ከሌሎች ተጓዳኝ ሕግጋቶችና ከህጉ አላማ አንፃር ሲመዘን ተገቢውን ጣዕም የሚሰጥ አይሆንም፡፡ በተለይም የመመሪያው እናት ሕግ የሆነው ብሔራዊ ባንክን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 20 ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ ማየት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

በአዋጁ አንቀፅ 20(1) መሠረት ማንኛውም ሰው ከባንኮች ወይም ፈቃድ ከተሰጣቸው መንዛሪዎች ጋር ካልሆነ ወይም ከብሔራዊ ባንክ የተለየ ፈቃድ ካላገኘ በቀር በውጭ ምንዛሪ ግብይት መሰማራት እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ እዚህ ጋር በውጭ ምንዛሪ ስለሚፈፀም ግብይት በአዋጁ ትርጉም የተሰጠው ሲሆን በአንቀፅ 2(13) መሠረት የውጭ ምንዛሬን መቀበልን እንደሚጨምር ያስቀምጣል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ማንኛውም ሰው የውጭ ምንዛሪ መቀበል የሚችል ሳይሆን ባንክ፣ ፈቃድ የተሰጣቸው መንዛሪዎች ወይም ብሔራዊ ባንክ በመመሪያ ቁጥር ኤፍኤክስዲ/56/2018 ባወጣው መሠረት ሆቴሎች፣ ማረፍያ ቤቶችና መመሪያው የተመለከታቸው አካላት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ የሚቻል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከያዘበት ጊዜ አንስቶ (From the date of acquisition) የሚለው ሃረግ በህጋዊ አግባብ የውጭ ምንዛሬ የተያዘበትን አግባብ ለማሳየት እንጂ ማንኛውም ሰው በማንኛውም አግባብ የያዘበትን ሁኔታ የሚመለከት አይሆንም፡፡ ሌላው ይህንኑ አረዳድ የሚያጠናክርልን በአዋጁ አንቀፅ 20(2) መሠረት የውጭ ምንዛሪ የሚያዝበትንና የሚጠቀምበትን ሁኔታና ገደብ በተመለከተ በመመሪያ እንደሚወሰን ማንሳቱ ሲታይ በመርህ ደረጃ የማይፈቀድ መሆኑን ደንግጎ በልዩ ሁኔታ ግን የሚቀድበትን አግባብ በመመሪያ ያወጣ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም አግባብ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሰው የውጭ ምንዛሪ ሊይዝና ሊገለገል የማይችል ሲሆን በልዩ ሁኔታ ብቻ በመመሪያ ቁጥር FXD/49/2017 ብቻ የተፈቀደ መሆኑን መገንዘቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ማንኛውም ሰው በየትኛውም አግባብ የውጭ ምንዛሬን ሊይዝና ሊገለገልበት ይችላል ብሎ ግምት መውሰዱ ህጋዊ አካሄድ የሚያደርገው አይሆንም፡፡

በተጨማሪም የሕግጋቶቹን አላማ የሚያሳካ አረዳድ ስለመሆኑ ሊነሳ የሚገባው ጭብጥ ይሆናል፡፡ በተለይም ማንኛውም ሰው ከያዘበት ጊዜ አንስቶ (From the date of acquisition) የሚለው ሀረግ ማንኛውም ሰው በማንኛውም አግባብ የውጭ ምንዛሬን ለ30 ቀናት መያዝ ይችላል የሚል ትርጉም የሚሰጠው ከሆነ የውጭ ምንዛሬን ለመቆጣጠር ሚያስችል አይሆንም፡፡ በተለይ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ጫና ውስጥ ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ማንንም ግለሰብ በሕግ ለመጠየቅ ቢሞከር የ30 ቀናት ጊዜ አልሞላም በሚል ምክንያት ከተጠያቂነት የሚሸሽና የውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያው ላይ በእጅጉ እንዲዘዋወር የሚጋብዝ ይሆናል፡፡ በዚህ አረዳድም ሳቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪና ነዋሪ ያልሆነ የሚለው በመመሪያው ላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎችና በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ እንዲቀበሉ የተፈቀደላቸውን አካላት ለመደንገግ የወጣው መመሪያ ትርጉም የሚያጣ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የህጉን ዋና አላማ የሚያስት መሆኑ ሲታይ ተገቢ የሆነ አረዳድ እንዳልሆነ መረዳት የሚቻል ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ህጉ ለመደንገግ የፈለገው ዋነኛው አላማ የውጭ ምንዛሬ በማንኛውም ሰውና በማንኛውም አግባብ ሊያዝ እንደማይችልና በልዩ ሁኔታ ብቻ የተፈቀደ መሆኑን ለማስገንዘብ እንደሆነ ነው፡፡

5.6.2. በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ያላቸው መብትና ግዴታ

በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች የኢትዮጵያን ብር ይዘው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበትና ከሀገር ውጭ ይዘው የሚወጡበትን ሁኔታና ገደብ በተመለከተ ከዚህ ቀድሞ ባለው ንዑስ-ክፍል ላይ የተገለፀ በመሆኑ እዚሁ ላይ በድጋሚ መግለፁ ድግግሞሽ ስለሚሆን ሳይገለፅ ታልፏል፡፡

የውጭ ሀገር ገንዘብን በተመለከተ መመሪየው ያሰፈረ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት ከ3,000 ዶላር ወይም በሌላ ሀገር ገንዘብ ከተመጣጣኙ በላይ በሚሆንበት ጊዜ አሳውቀውና አስመዝግበው /ዴክሌር አድርገው/ መግባት እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሲሆን ወደ ውጭ ሀገር ይዞ መውጣት ሚቻልበት አግባብ ደግሞ ከ3,000 ዶላር ወይም በሌላ ሀገር ገንዘብ ከተመጣጣኙ በላይ ከሆነ የባንክ ፈቃድ ወይም የጉምሩክ ዴክላራሲዮን ሰነድ ሊኖር እንደሚገባ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በህጋዊ አግባብ የተያዘውን የውጭ ምንዛሪ እስከ ቪዛ ማብቂያ ጊዜ ድረስ ይዘው መቆት የሚችሉ ስለመሆኑ መመሪያው በግልፅ ይደነግጋል፡፡

5.6.3. በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የሚችሉ ሰዎች ያላቸው መብትና ግዴታ

መመሪያው በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ስለሚችሉ ሰዎች የሚደነግግ ሲሆን የኢምባሲ ሰራተኞችን፣ በውጭ ድርጅቶች ውስጥ ጊዜያዊ ሰራተኛ ሆነው የሚሰሩትን፣ የወርክሾፕ ተሳታፊዎችን ወይም አሰልጣኞችን የሚመለከት ድንጋጌ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ከ3,000 የአሜሪካን ዶላር ወይም በሌላ ሀገር ገንዘብ ከተመጣጣኙ በላይ መያዝ እንደሚችሉ የሚያስቀምጥ ሲሆን ለዚህም ማስረጃ የባንክ ፈቃድ፣ የቀጣሪው ደብዳቤ፣ ከወርክሾፕ አስተባባሪ የድጋፍ ደብዳቤ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪው በህጋዊ አግባብ የተገኘ መሆኑን ማስረዳት እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡

6. በሕግ ከተቀመጠው አግባብ ውጭ ገንዘብ መያዝና ማስተላለፍ የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት

ከላይ በተመለከቱት ምዕራፎች በአጠቃላዩ ስለገንዘብ መያዝና ማንቀሳቀስ ስለሚፈቀድባቸው ሁኔታዎች የሚደነግጉትን የሕግ ማዕቀፎች በዝርዝር ለማየት የተሞከረ ሲሆን በዚህኛው ክፍል ደግሞ እነዚህን የሕግ ማዕቀፎች ተፈፃሚ ለማድረግ ያሉ የማስፈፀሚያ ድንጋጌዎችን ለማየት ተሞክሯል፡፡ እነዚህ ማስፈፀሚያዎች በዋናነት አስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ የሕግ ድንጋጌዎች ሲሆኑ የወንጀል ተጠያቂነት የሚቋቋምባቸውን ሁኔታዎች በጥልቀት ለማየት ተሞክሯል፡፡

6.1. የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ

የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ ሌላው አስፍላጊ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑ ካለው ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች አንፃር ማየት የሚቻል ነው፡፡ ከሕግ ማዕቀፉ ስያሜው መረዳት እንደሚቻለው ወንጀል በሆኑ ጉዳዮች ላይ በአንድም ይሁን በሌላ በኩል የሚጠቀስና የሚተገበር ማዕቀፍ ነው፡፡ ህጉን ከመግቢያ ጀምሮ እስከ ሶስተኛ ታላቅ ክፍል የደንብ መተላለፍ ሕግ ያለውን ፋይዳ መዳሰስ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ከተያዘው ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ ግኑኝነት ያለውን ክፍል ማየቱ የተሻለና ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህም ሲባል በማዕቀፉ ውስጥ የተካተቱት ሌሎች ድንጋጌዎችም ሆኑ ሀተታዎች ቀጥተኛ ግኑኝነት የላቸውም ለማለት ሳይሆን ከተያዘው ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መታየት አለበት የሚባሉ የተመረጡ ጉዳዮችን እንደሆነ መረዳቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የወንጀል ህጉ መግቢያ እና ጠቅላላ ድንጋጌዎች ቀጥተኛ ግኑኝነት ያላቸው ቢሆንም ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በልዩ ሁኔታ በድንጋጌ የተመለከቱትን ጉዳዮች ብቻ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

በዚህም መሠረት በሶስተኛ መጽሐፍ በርዕስ አራት እንዲሁም በርዕስ አምስት ስር የተመለከቱ የወንጀል ድንጋጌዎችን ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በሶስተኛ መጽሐፍ ርዕስ አራት ምዕራፍ አንድ ከአንቀፅ 343 እስከ አንቀፅ 345 ድረስ ያሉ ድንጋጌዎች ጠቅላላ ድንጋጌዎች ሲሆኑ ለርዕሱ በጠቅላላ መርህ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 343 ልዩ ህጎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የተመለከተ ሲሆን ስልጣን ባለው የመንግስት አካል በአገር የገንዘብ ወይም የኢኮኖሚ ጥቅም ላይ የሚፈፀም ማናቸውንም ጉዳት ለመቆጣጠር ወይም ለመከላከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ወይም በክልል መንግስታት የሕግ ጋዜጣ ላይ የሚወጣን ሕግ በመጣስ ወንጀል የተፈፀመ እንደሆነ ቅጣቱ በወንጀል ሕግ በተመለከቱት መርሆች መሠረት እንደሆነና በደንብ መተላለፍ የተደነገጉትን ወይም በዚህ ዓይነት ያልተመለከቱ የደንብ መተላለፍ ጠባይ ያላቸውን የሚያዙ ወይም የሚከለኩሉ ድንጋጌዎችን በመጣስ ወንጀል በሚፈፀምበት በማናቸውም ጊዜ የወንጀሉ መፈፀም ያስከተለው ጉዳት ከአስር ሺህ ብር ያልበለጠ እንደሆነ የሚወሰነው ቅጣት ስለደንብ መተላለፍ በተደነገጉት አንቀጾች መሠረት እንደሆነ በግልፅ ይደነግጋል፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 344 ላይ ደግሞ ስለወንጀል ቅጣቶች ዓይነታቸውና መጠናቸው ያስቀመጠ ሲሆን ጉዳዩን የሚመለከቱት ሕጎች በዚህ የወንጀል ሕግ ወደተደነገገ ወንጀል በግልፅ የማይመሩ ሆነው በተገኙ ጊዜ ፍርድ ቤቱ በዚህ የወንጀል ሕግ ጠቅላላ ድንጋጌዎችና መደበኛ የቅጣት ወሰን መሠረት ቀላል እስራት ወይም መቀጮ እንደሚወሰን፤ ጥፋቱ ከባድ ሆኖ ወንጀሉም የተፈፀመው በብዙ ገንዘብ ወይም ከፍ ያለ ግምት ባለው ዕቃ ላይ እንደሆነ ወይም ወንጀለኛው ወንጀሉን እንደዋና ሥራው አድርጎ የሚጠቀምበት ሆኖ ሲገኝ ፍርድ ቤቱ በወንጀሉ ሥራ የተገኘው ጥቅም አንዲወረስ ከማድረግ በተጨማሪ ጥፋተኛው ከአንድ መቶ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ እንዲከፍል ለመወሰን እንደሚቻል ያስቀምጣል፡፡

በርዕስ አራት ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ስለ ወንጀል ድንጋጌዎች የተመለከተ ሲሆን በተለይ በአንቀጽ 346 ለዚህ ጽሁፍ እጅጉን ጠቃሚ ድንጋጌ ነው፡፡ ድንጋጌው ማንም ሰው በገንዘብ ላይ ጥፋት የሚፈፅመውን ወንጀለኛ ስለመቅጣት በወንጀል ሕጉ ድንጋጌ /በወንጀል ህጉ አምስተኛ ርዕስ/ ላይ ከተመለከተው ውጭ በአንድ በተወሰነ ሁኔታ፣ በገደብ፣ በቁጥጥር ወይም በልዩ ጥበቃ፣ ንግድ ወይም የምንዛሪ ስራ የሚካሄድበትንና የአገር ወይም የውጭ አገር ሀብት የሆነውን ወርቅ ወይም ማናቸውንም ውጭ አገር ገንዘብ፣ ፈቃድ ሳይኖረው ወይም ሕግን በመጣስ የገዛ፣ ከውጭ አገር ያስመጣ ወይም ወደ ውጭ አገር የላከ፣ በአደራ አስቀማጭነት የተቀበለ፣ ያስቀመጠ፣ የመነዘረ፣ የሸጠ ወይም ለሽያጭ ያቀረበ እንደሆነ ይህን ወንጀል የፈፀመበትን ሀብት የመውረስ ደንብ የሚጸና መሆኑ ሳይቀር እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት እና ሃምሳ ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ያስቀምጣል፡፡

በርዕስ አምስት ምዕራፍ አንድ አንቀፅ 356 እና ተከታዮቹ ደግሞ ስለሀሰተኛ ገንዘብ መስራት፣መለወጥ፣ ዋጋውን ዝቅ ማድረግ፣ ወደ አገር ማስገባት፣ ከአገር ማስወጣት፣ መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማቅረብ እና ማዘዋወርን በመተለከተ በሰፊው ደንግጎ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ድንጋጌዎች በተጨማሪ በሦስተኛ ታላቅ ክፍል ስለደንብ መተላለፍ ሕግ የተደነገጉ ድንጋጌዎች እንደየአግባብነታቸው ጥቅም ላይ የሚውሉበት አግባብ ያለ ሲሆን በተለይም በመርህ ደረጃ የተቀመጡ ድንጋጌዎች አስፈላጊና ሊተገበሩ የሚችሉበት አግባብ የሚኖር ይሆናል፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 785 ደግሞ በወርቅ፣ በጥሬ ገንዘብ እና በውጭ አገር ምንዛሪ ህገወጥ ሥራ መሥራትን አስመልክቶ የወጣ ሕግን መጣስ በሚል ርዕስ የተደነገገ ሲሆን ማንም ሰው በወንጀል ህጉ በአንቀፅ 346 ከተመለከተው ሁኔታ ውጭ፣ በተወሰነ ሁኔታ፣ በገደብ፣በቁጥጥር ወይም በልዩ ጥበቃ፣ ንግድ ወይም የምንዛሬ ስራ የሚካሄድበትን የአገር ወይም የውጭ አገር ሀብት የሆነውን ወርቅ ወይም ማናቸውንም ዓይነት ጥሬ ገንዘብ አስመልከቶ የወጣውን ሕግ፣ ደንብ ወይም መመሪያ የጣሰ እንሆነ ከሶስት መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከሶስት ወር በማይበልጥ የማረፊያ ቤት አስራት እንደሚቀጣ አስቀምጧል፡፡

6.2. የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006

የጉምሩክ አዋጅ አላማ አድርጎ ከተነሳበት መካከል አንዱ ኮንትሮባንድንና ሌሎች የንግድ ማጭበርበር ወንጀሎች በሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ፣ በሕዝብ ደህንነት፣ በመንግስት ገቢና በሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶች ላይ የሚያስከትሉትንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የተጠናከረ የሕግ ማስከበሪያ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በአዋጁ መግቢያ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህን አዋጅ ለማሻሻል የወጣው የጉምሩክ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1160/2011 አንቀፅ 44 በቀድሞ የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀፅ 168(1) አሻሽሎ የደነገገ ሲሆን ማንኛውም ሰው እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የጉምሩክ ህጎችን በመተላለፍ የተከለከለ፣ ገደብ የተደረገበት ወይም የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት ያልተፈፀመበት ዕቃ ወደ ጉምሩክ ክልል ያስገባ ወይም ከጉምሩክ ክልል ያስወጣ ወይም ለማስወጣት ወይም ለማስገባት የሞከረ እንደሆነ የዕቃው መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአምስት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 50 ሺህ በማያንስና ከብር 200 ሺህ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጫ እንደሚቀጣ ያስቀመጠ ሲሆን በህገወጥ መንገድ የተገኙ ዕቃዎች መሆናቸውን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ዕቃዎችን ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የያዘ፣ ለሽያጭ ያቀረበ ወይም የገዛ ማንኛውም ሰው ከሶስት ዓመት በማያንስና ከአምስት አመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከብር 50 ሺህ የማያንስና ከብር 100 ሺህ በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

በድንጋጌው ውስጥ ዕቃ የሚል ቃል የሚገኝ ከመሆኑ አንፃር ከርዕሰ ጉዳያችን ማለትም ከገንዘብ ጋር የሚያያዝበትን አግባብ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በተለይ ዕቃ ለሚለው ቃል ትርጉም የተሰጠው በመሆኑ ይህንኑ ትርጓሜ ከጉምሩክ አዋጅ በማየት የሚያያዝበትን መንገድ መረዳት የሚቻል ይሆናል፡፡ ከዚህም አኳያ በጉምሩክ አዋጁ መሠረት ዕቃ ማለት ማናቸውንም ተንቀሳቃሽ ንብረት ማለት ሲሆን ገንዘብንም እንደሚጨምር በግልፅ ደንግጎ እናገኛለን፡፡ በዚህም መሠረት ገደብ ከተደረገበት የገንዘብ መጠን በላይ ይዞ የገባ ወይም ይዞ የወጣ አልያም ለመግባትም ሆነ ለመውጣት የሞከረ ማንኛውም ሰው ሊጠየቅ የሚችልበት የሕግ አግባብ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይም ገደቡን ጥሶ በሀገር ውስጥ ገንዘብ ይዞ የተገኘ ግለሰብ በወንጀል ሊጠየቅ የሚችልበት አግባብ እንዳለም መረዳት የሚቻል ይሆናል፡፡

6.3. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000

የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ስለገንዘብ መሰረታዊ የሆኑ ድንጋጌዎችን ያዘለ ብቻ ሳይሆን የወንጀል ጉዳዮችንም በውስጡ አቅፎ የደነገገ መሆኑን ከአዋጁ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአዋጁ ውስጥ የተደነገጉትን ፍሬ-ጉዳዮች ተፈፃሚ እንዲሆኑም የወንጀል ድንጋጌዎችን አይነተኛ መሳሪያ አድርጎ እንደወሰደም ልብ ማለቱም እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 26 ላይ በርከት ያሉ ወንጀልን የሚያቋቁሙ የወንጀል ድንጋጌዎችን ያዘለ ሲሆን አዋጁ ከወንጀል ህጋችን ጋር ሊታይ የሚገባውም ይሆናል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 26(1/ከሀ-መ) ድረስ ያሉ ድንጋጌዎች የተለያዩ የወንጀል ፍሬ ጉዳዮችን ያዘሉ ሲሆን ቅጣታቸውን በተመለከተ ግን በወንጀል ሕግ መሠረት ቅጣት እንደሚጣል ያስገነዝባል፡፡

አንቀፁ በአዋጁ ላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣ አዋጁን ተከትለው የወጡ ድንቦችና መመሪያዎች በመተላለፍ በውጭ ምንዛሪ ግብይት የተሳተፈ ወይም የውጭ ምንዛሪ ሲያገኝ ወይም ለማግኘት መብት እንዳለው ሲያውቅ ለባንክ ወይም ፈቃድ ለተሰጠው መንዛሪ ያላሳወቀ እንደሆነ፤ የውጭ ምንዛሪ የተቀበለ ወይም በውጭ ምንዛሪ ክፍያ የፈፀመ እንደሆነ፤ የውጭ ምንዛሪ የሚቀበልበትን ጊዜ ያዘገየ ወይም የመቀበል መብቱን የተወ እንደሆነ፤ በብሔራዊ ባንክ ከተወሰነው ወይም ከተፈቀደው መጠን በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ ይዞ ከኢትዮጵያ የወጣ ወይም ለመውጣት የሞከረ ወይም የገባ ወይም ለመግባት የሞከረ እንደሆነ፤ ወይም በብሔራዊ ባንክ ከተወሰነው ወይም ከተፈቀደው መጠን በላይ የውጭ ምንዛሪ ይዞ የተገኘ እንደሆነ በወንጀል ሕግ እንደሚጠየቅ ያስገነዝባል፡፡ በተጨማሪም አዋጁ ወይም አዋጁን ተከትለው የወጡት ሕግጋቶች ተፈፃሚ እንዳይሆኑ ወይም አተገባበራቸውን ለማዛባት በማሰብ ማናቸውንም ሰነድ ያጠፋ፣ የቀደደ፣ ይዘቱን የቀየረ፣ የደለዘ ወይም የደበቀ ወይም ሀሰተኛ ማስረጃ ያቀረበ ወይም ሀሰተኛ መግለጫ የሰጠ እንደሆነ፤ በአዋጁ አንቀፅ 22 የተደነገገውን (መረጃ ስለመሰብሰብና ስለመስጠት የተመለከተውን ድንጋጌ) በመተላለፍ ማናቸውንም መረጃ ለማይገባቸው ሰዎች የሰጠ እንደሆነ ወይም አዋጁን፣ ደንቡንና መመሪያዎችን በማናቸውም ሌላ መንገድ የተላለፈ ወይም አተገባበራቸውን ያሰናከለ እንደሆነ ወንጀል የሰራበት ሃብት መወረሱ እንዳለ ሆኖ በወንጀል ሕግ እንደሚጠየቅ ያስቀምጣል፡፡

በአዋጁ አንቀፅ 26/2 ደግሞ የማክበጃ ምክንያቶችን መሠረት አድርጎ የደነገገ ሲሆን የቅጣት ማክበጃዎቹን ከዘረዘረ በኋላ ከ15 ዓመት በማይበልጥ እስራት እና ከብር 50 ሺ እስከ 100 ሺህ ወይም ወንጀል የተፈፀመበት ንብረት ዋጋ እስከ ሶስት እጥፍ በድርጅት የተፈጸመ እንደሆነ ደግሞ እስከ ስድስት ዕጥፍ ሊደርስ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ሌላው ከዚህ ጽሑፍ አላማ ጋር ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ድንጋጌው የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት የሚፈፅማቸው ወንጀሎች ሲሆን የድርጅቱ ስራ-አስኪያጅ ከድርጅቱ ጋር በጋራ የሚጠየቅና ከሰባት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር ሃምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ድረስ ቅጣት ሊጣል እንደሚችል የሚያስቀምጥ ሲሆን ከተጠያቂነት ነፃ የሚሆነው ወንጀል መፈፀሙን ያላወቀና በበቂ ጥረትም ሊያውቅም እንደማይችል ማስረዳት እንደሚጠበቅበት በግልፅ ያስቀምጣል፡፡

7. የወንጀል ተጠያቂነት ላይ የሚነሱ የሕግ ክፍተቶችና አተረጓጎማቸው

የሕግ አተረጓጎም በሚነሳበት ወቅት በሕግ አረዳድ ላይ ያሉ ክፍተቶች ስለመኖራቸው እርግጥ መሆኑን ማየት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ህጉ በቀጥታ ሲታይ ክፍተት ያለበት እንደሆነ፣ ግልፅነት የሚጎድለው እና አሻሚ የሆነ ትርጉም ያዘለ እንደሆነ ሊተረጎም የሚገባ መሆኑን በሕግ ፍልስፍና ውስጥ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ ከገንዘብ ማንቀሳቀስ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅድሚያ ለይቶ በማቅረብና ትርጉም ሊሰጥባቸው የሚገባበትን አግባብ አንድ በአንድ ለይቶ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

7.1. የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ ይዞ የተገኘ ሰው ሊጠየቅ ስለሚችልበት አግባብ

ቀደም ተብሎ በዝርዝር በተገለፀው የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ከተቀመጠው የሕግ አግባብ ውጭ ይዞ የተገኘ ሰው በሕግ ሊጠየቅ የሚገባው ስለመሆኑ ለማየት ተሞክሯል፡፡ በተደጋጋሚ የሚነሳውና ጉራማይሌ በሆነ መንገድም በፖሊስና ዐ/ሕግ ሲሰራበት የቆየው ጉዳይ የውጭ ምንዛሬ በሀገር ውስጥ ይዞ የተገኘ ግለሰብ የሚጠየቅበት የሕግ መሠረት ነው፡፡ ይህ ሲባል በአንድ በኩል የወንጀል ህጉን አንቀፅ 346 መሠረት አድርጎ ውሳኔ ሲሰጥ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 26/1/ሀ/5 መሠረት ውሳኔ ይሰጣል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀፅ 168/2 መሠረት ውሳኔ የሚሰጥበትም አግባብ አለ፡፡ እያንዳንዱ ድንጋጌዎች የራሳቸው የሆነ መልክ ያላቸው ሲሆን በተለያየ መንገድም ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለም መዘንጋት የለበትም፡፡

በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀፅ 26/1 መሠረት ወንጀልን ሊያቋቁሙ የሚችሉ ፍሬ-ጉዳዮች እስከ ተሟሉ ድረስ ወንጀል የሰራበት ሀብት መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል ሕግ እንደሚቀጣ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ክስ ማቅረብ በአንድ በኩል የሚቻል ሲሆን የወንጀል ቅጣትን በተመለከተ ግን ወደ ወንጀል ሕጉ የመራ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ በአብዛኛው የወንጀል ክስ የሚቀርበው በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 346 መሠረት ሲሆን ከአስር አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከሃምሳ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ እንዲሁም ወንጀል የፈፀመበት ሀብት የሚወረስበት አግባብ እንዳለ ያስቀምጣል፡፡ ይህ አይነት ልምድ ምን ያህል ተገቢነት ያለው አካሄድ ነው የሚለው ጭብጥ አከራካሪ ነው፡፡ በተለይ የብሔራዊ ባንከ አዋጁ ወደ ወንጀል ሕጉ እየጠቆመ ያለው የወንጀል ቅጣቱን ብቻ እንጂ የወንጀል ፍሬ ጉዳዮችን በተመለከተ እንዳልሆነ ከአዋጁ ድንጋጌ መረዳት የሚቻል ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ስለወንጀል ቅጣት የተመለከተ ድንጋጌ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 344 ላይ የተመለከተውን መርህ በአግባቡ ማየት የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ በድንጋጌው መሠረት ጉዳዩን የሚመለከቱት ሕጎች (በመንግስት የኢኮኖሚና የገንዘብ ጥቅሞች ጋር በተያያዘ እንደሆነ ልብ ይሏል) በዚህ የወንጀል ሕግ ወደ ተደነገገ ወንጀል በግልፅ የማይመሩ ሆነው በተገኙ ጊዜ ፍርድ ቤቱ በዚህ የወንጀል ሕግ ጠቅላላ ድንጋጌዎችና መደበኛ የቅጣት ወሰን መሠረት ቀላል እስራት ወይም መቀጮ ይወስናል በማለት አስፍሯል፡፡

በዚህም መሠረት የብሔራዊ ባንክ አዋጅ አንቀፅ 26(1) ቅጣትን በተመለከተ በግልፅ ወደ አንድ ድንጋጌ የሚመራ ሳይሆን በጠቅላላው የሚመራ ከመሆኑ አኳያ ቅጣቱ ቀላል እስራት ወይም መቀጮ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም በተግባር ያለው ልምድ የብሔራዊ ባንክ አዋጅን መሠረት አድርጎ የሚቀርቡ ክሶች ወይም የሕግ ውሳኔዎች በአብዛኛው ያሉ ሳይሆኑ የወንጀል ህጉን አንቀፅ 346ን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ የወንጀል ህጉን አንቀፅ 346 የመጠቀሙ መነሻ ብዙ ምክንያቶች ከጀርባው ያዘሉ ሲሆን ቀዳሚው ምክንያት የብሔራዊ ባንክ አዋጅና የወንጀል ህጉን መስተጋብር በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በወንጀል ህጉ የተቀመጠው የቀላል እስራት ወይም የመቀጮ ሁኔታ አነስተኛና የወንጀል ህጉን አላማ የሚያሳካ አለመሆኑን በመረዳት የወንጀል ህጉን አንቀፅ 346 በቀጥታ የመጠቀሙ ሁኔታ ነው፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 346 አሁንም በስራ ላይ እንደዋለ ሊታሰብ ይገባል ወይስ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሽሯል (Implicit repealment) የሚለው መከራከሪያም አልፎ አልፎ እንደሚነሳ ማየት ይቻላል፡፡ በወንጀል ህጉ እና በብሔራዊ ባንክ አዋጅ ያሉት የድንጋጌዎቹ ይዘት ተመሳሳይ የሆኑ እንደሆነ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 346 ተሽሯል ለማለት የሚያስደፍር ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ድንጋጌው የያዛቸው ፍሬ-ነገሮች የሚወራረሱበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ በከፊል የተሻረ ስለመሆኑ መገንዘብ የሚቻል ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት የወንል ህጉን አንቀፅ 346 መሠረት አድርጎ ውሳኔ መስጠት ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡

ለሕግ ውሳኔ መሠረት የሆነው ሌላው ድንጋጌ የጉምሩክ አዋጅ ሲሆን በአንቀፅ 168/2 መሠረት በአንቀፅ 168(1) (ይህ ንዑስ አንቀፅ በአዋጅ ቁጥር 1160/2011 አንቀፅ 2(44) መሻሻሉን ልብ ይሏል) በህገ-ወጥ መንገድ የተገኙ ዕቃዎች መሆናቸውን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ዕቃዎቹን ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የያዘ፣ ለሽያጭ ያቀረበ ወይም የገዛ ማንኛውም ሰው ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና ከብር 50ሺህ በማያንስና ከብር 100ሺህ በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ዕቃ ለሚለው ቃል አዋጁ ትርጉም የሰጠው ሲሆን ገንዘብንንም እንደሚጨምር በአንቀፅ 2(1) ያስቀምጣል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የሕግ ውሳኔ መስጠቱ የራሱ አንደምታ ያለው ሲሆን በቅድሚያ በህገወጥ የተገኘው ንብረት በፍርድ ቤት ክርክር ሳይደረግበት በአስተዳደራዊ መንገድ የሚወረስበትን አግባብ እንዳለ መረዳት የሚገባ ይሆናል፡፡ ከዚህ ባሻገር አዋጁ ከገቢ እና ከወጪ ዕቃዎች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ከመሆኑ አኳያ ምንም እንኳ ጉዳዩ በአዋጁ ሊሸፈን የሚችል ቢሆንም በሕግ ትርጉም አሰጣጥ መርህ መሠረት ልዩ አዋጅ (Specific Law) ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ከገንዘብ ጋር በተገናኘ የወጣው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ እና እንደ የአግባብነቱ ደግሞ የወንጀል ሕጉ የተመለከቱ ሆን ይገባዋል፡፡

7.2. በሕግ ሰውነት የተሰጠው አካል ሊጠየቅ ስለሚችልበት የሕግ አግባብ

የሕግ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪን በመያዝ ሊያስከትልባቸው የሚችለው የሕግ ተጠያቂነት አለ ወይ የሚለው አከራካሪ ሆኖ ይነሳል፡፡ ምንም እንኳ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀፅ 26/4 መሠረት የሕግ ሰውነት የተሰጣቸው አካላት እንደሚጠየቁ በግልፅ ቢያስቀምጥም የውጭ ምንዛሪ የሚያዝበትን አግባብ በተመለከተ በብሔራዊ ባንክ የወጣው መመሪያ ቁጥር FXD/49/2017 በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ለሆኑ እና ላልሆኑ ሰዎች ገደብን ያስቀመጠ ከመሆኑ አኳያና የሕግ ሰውነት ያላቸው አካላትን በተመለከተ ያስቀመጠው ገደብ የሌለ በመሆኑ የሚጠየቁበት የሕግ መሠረት እንደሌለ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ሆኖም በፀሀፊው እሳቤ ይህ ሀሳብ ከህጉ አንፃር ተገቢነት የሌለው ሲሆን ሊታይ የሚገባው መሰረታዊ ጭብጥ በመመሪያ ላይ የተመለከቱት ጉዳዮች ሳይሆኑ የመመሪያው እናት ሕግ የሆነው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ይሆናል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 20 መሠረት የውጭ ሀገር ገንዘብ ግብይት ስለሚፈፀምበት፣ መያዝ ስለሚቻልበት፣ ክፍያ ስለሚፈፀምበት ሁኔታዎችንና ገደቦችን በተመለከተ በመመሪያ እንደሚደነግግ የማስቀመጡ ሁኔታ በአንክሮ ሲታይ ድንጋጌው ከመነሻውም ማንኛውም ሰው የውጭ ምንዛሪ መያዝም ሆነ መገበያየት የማይችል መሆኑን ከደነገገ በኋላ ስለሚፈቀድበት ሁኔታዎችና ገደቦቸን በተመለከተ ብቻ በመመሪያ እንዲወሰን ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህም ማለት ማንኛውም ሰው (በሕግ ሰውነት የተሰጠው አካል) ከመነሻውም የውጭ ምንዛሪ መያዝም ሆነ መገበያየት እንደማይችል አወጁ ያስቀመጠ ሲሆን በመመሪያ ላይ ድርጅቶች ያልተካተቱ እንደሆነ ምንም አይነት ፈቃድ ከመነሻውም አልተሰጣቸውም ማለት እንደሆነ መገንዘቡ የሚገባ ይሆናል፡፡ በተለይ በአዋጁ የትርጉም ክፍል በውጭ ምንዛሪ የሚፈፀም ግብይት ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጉም ሲታይ መቀበልን የሚይዝ ከመሆኑ አኳያ ድርጅቶች በመመሪያ ቁጥር ኤፍኤክስዲ/56/2018 መሠረት መቀበል የሚችሉበት አግባብ እና በሌሎች ሕግጋት ውስጥ የተመለከቱት ካልሆኑ በስተቀረ ከመነሻውም የውጭ ምንዛሪ መያዝ የማይቻል በመሆኑ የወንጀል ተጠያቂነትን ማቋቋም የሚቻል ይሆናል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነትም ሲቋቋም በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 34 መሠረት ድርጅቶች በግልፅ እንደሚጠየቁ መመላከት እንዳለበት ከማስቀመጡ አኳያ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ሊጠየቅ የሚችልበት አግባብ እንዳለ ማንሳቱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

7.3. ከአንድ ቦታ በላይ ነዋሪ የሆነ ሰው ያለው ተጠያቂነት

ግለሰቦች ስላላቸው መብትና ግዴታ እንዲሁም ሀላፊነት ከላይ በሰፊው ለመዳሰስ የተሞከረ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑና በተመሳሳይ ደግሞ በሌላ ሀገር ውስጥም ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ከሕግ ተጠያቂነት አንፃር እንዴት ይታያሉ የሚለው ሌላው የሚነሳ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ የውጭ ሀገር ዜግነት ኖሯቸው የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የላቸው ግለሰቦች ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 270/1994 አንቀፅ 5 መሠረት የፀና የኢትዮጵያ መታወቂያ ካርድ ያለው ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ ወደ ኢትየጵያ ለመግባትና ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየትም ሆነ ለመኖር የመግቢያ ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲኖረው እንደማይጠየቅ ያስቀምጣል፡፡ የውጭ ምንዛሬን ለመደንገግ የወጣው መመሪያ ደግሞ የውጭ ሀገር ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጣበት ጊዜ በህጉ አግባብ ይዞት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እስከ ቪዛ ማብቂያው ጊዜ ድረስ ብቻ ሊይዝ እንደሚገባው ደንግጓል፡፡

በውጭ ሀገር ነዋሪ የሆኑ የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የያዙ ግለሰቦች እስከመቼ ድረስ የውጭ ምንዛሪ ሊይዙ እንደሚገባቸው በግልፅ የተደነገገ ድንጋጌ የለም፡፡ ከዚህ አኳያ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ግሰለቦች አዋጅ ቁጥር 270/1994 ሊሰጣቸው የፈለገው መብት ያለምንም ቪዛ በሀገር ውስጥ እንዳለ ኢትዮጵያዊ እንዲታዩና እንዲጠቀሙ፣ ለሀገራቸው እድገትና ኑሮ መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲወጡ ለማስቻል አልሞ የወጣ ሕግ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖረው ነዋሪ የተሻለን መብት ለማጎናፀፍ እንዳይደለ ከህጉ መግቢያና ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻል ይሆናል፡፡ አዋጁ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ግለሰቦች ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባትም ሆነ ለመቆየት እንደሌሎች የውጭ ሀገር ዜጎች ተጨማሪ እርምጃ ላለመጣል አስቦ በመሆኑ እነዚህ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ እንደሆኑና በነዋሪነታቸውም የሚገኙትን ጥቅም አስጠብቆ በሌላው ጎኑ ደግሞ የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ አይደሉም በማለት የሚጣልባቸውን ተያያዥ ግዴታዎችን ማንሳትና ተፈፃሚ አለማድረግ እርስ በእርሱ የሚጋጭ እንዲሁም ፍትሐዊነት የሚጎድለው የሕግ አተረጓጎም የሚያደርገው ይሆናል፡፡

ሌላው ከላይ በሰፊው የተገለፀውን አረዳድ የሚያጠናክረው የመመሪያው አንቀጽ 1.1 በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ተብለው ከሚጠቀሱ ሰዎች መካከል የውጪ ዜጎች ሆነው በኢምግሬሽን እና የስደተኞች ጉዳይ መ/ቤት ተመዝግበው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ቋሚ ወይም ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ የተሰጣቸው ዜጎችን የተመለከተው ትርጉም ይሆናል፡፡ በኢሚግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995 አንቀጽ 13 እና 15 መሠረት ጊዜያዊ ወይም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ማውጣት የሚጠበቅባቸው ከዘጠና ቀናት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት በቪዛ የሚገቡ ግለሰቦች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ይህም የሚያሳየው ግለሰቦቹ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያወጡ የሚገደዱት ሌላ የመኖሪያ ቦታ አይኖራቸውም በሚል ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆዩበት የጊዜ ርዝማኔ ታይቶ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመመሪያው ቋሚ ወይም ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው የውጭ ሀገር ዜጎችን በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ብሎ ሲቀበላቸው ከአንድ በላይ የመኖሪያ ቦታ ሊኖራቸው እንደሚችል ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንም ለመረዳት ይቻላል፡፡

ስለሆነም የሕግ አውጪውን መንፈስ ስንረዳው ከአንድ በላይ የመኖሪያ ቦታ ሊኖር እንደሚችል ግምት የሚወሰድበት ሆኖ አዋጁ እና መመሪያው የወጣበትን አላማ ለማሳካት ሲባል በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ተጠያቂ ማድረግ የሚገባ ይሆናል፡፡ ይህ አይነት አተረጓጎም የራሱ አንደምታ ያለው ሲሆን እኚህ ግለሰቦች ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት ከ1,000 ዶላር በላይ ለጉምሩክ ኮሚሽን አሳውቆ መግባት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ ያላቸው ግለሰቦች ያላቸውን መብት ለመንጠቅ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ በመሆን የሚገኝ መብትን ለትውልደ ኢትጵያዊ መታወቂያ ላላቸው ለማጎናፀፍ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር በፀሀፊው እምነት መሠረት ወደ ሀገር ውስጥ እኚህ ግለሰቦች ይዘው በሚመጡበት ወቅት ከ3,000 ዶላር በላይ በሚሆንበት ወቅት ለጉምሩክ ኮሚሽን የማሳወቅ ሀላፊነት የሚጥል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የፀና የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የያዙ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሬን ወደ ሀገር ውስጥ ይዘው የገቡ እንደሆነ የውጭ ምንዛሬን ለመደንገግ በወጣው መመሪያ አንቀፅ 4.2 መሠረት በ30 ቀናት ውስጥ በህጋዊ አግባብ መመንዘር የሚገባቸው እንደሆነ በግልፅ ከተቀመጠው ድንጋጌ መረዳት የሚቻል ይሆናል፡፡

7.4. በኤግዚቢትነት የተያዘ የውጭ ምንዛሪ ስለሚመለስበት ሁኔታ

ቀደም ባሉት ክፍሎች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ የሚያዝበትን አግባብና በወንጀል ተጠያቂ ስለሚደረጉባቸው ሁኔታዎች በሰፊው ለማየት ተሞክሯል፡፡ በወንጀል ተጠያቂነት ውስጥ የውጭ-ምንዛሪ የሚያዝበትና በፍ/ቤትም ሆነ በአስተዳደራዊ መንገድ የሚወረስበት አግባብ እንዳለም ለማስፈር ተሞክሯል፡፡ ሆኖም የወንጀል ምርመራ ከተደረገ በኋላ ጉዳዩ የሚያስጠይቅ አይደለም ወይም ወንጀል አይደለም የሚባል እንደሆነ የተያዘው የውጭ ሀገር ገንዘብ እጣ ፈንታው ምን መሆን አለበት የሚለው ሊታይ ይገባዋል፡፡ በተለይም ምርመራውን ባደረገው አካል በአብዛኛው ጊዜ የሚታየው የውጭ ሀገር ገንዘብን በሚመልስበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ብር ቀይሮ የሚመልስ መሆኑ አግባብነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል፡፡

ኤግዚቢት ማለት ወንጀል የተፈፀመበት መሳሪያ ወይም ወንጀሉን ሊያስረዳ ይችላል የሚባሉ ቁሳዊ ማሳያዎች እንደመሆናቸው መጠን ሊለወጡም ሆነ ሊቀየሩ የሚቻሉ እንዳይደሉ መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የውጭ ሀገር ገንዘብ እንደኤግዚቢት የሚመዘገብ እንደሆነ ለፍ/ቤት ወይም ለዐ/ሕግ ውሳኔ እስከሚቀርብ ድረስ ባለበት ሊቆይና ሊያዝ የሚገባው እንደሆነ መገንዘቡ አስፈላጊ ነው፡፡ አንደ ኤግዚቢት የተያዘ ንብረት ላይ ለማስረጃነት የሚያስፈልግ አይደለም አልያም ሊወረስ አይገባም የሚባል ውሳኔ ካለ ንብረቱ ባለበት ለባለቤቱ ሊመለስ የሚገባ ይሆናል እንጂ ተቀይሮ የሚመለስበት ህጋዊ መሠረት የለም፡፡ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 33(3) ላይ የተያዘው ኤግዚቢት ለክሱ መሰማት አስፈላጊ ካልሆነ ግን ለተወሰደበት ሰው ተመላሽ መደረግ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ከመሆኑ አንፃርና ኤግዚቢት በባህሪው ሊለወጥ የማይገባው ከመሆኑም በተጨማሪም ህጋዊ ነው ተብሎ በተሰጠ ወሳኔ ላይ ግለሰቦች ንብረታቸውን ሊያጡ ወይም ሊቀየርባቸው አልያም ሊኖራቸው የሚገባውን ጥቅም ማሳጣቱ የማይገባ በመሆኑ የውጭ ሀገር ገንዘብ ባለበት ሁኔታ ሊመለስ የሚገባ ይሆናል፡፡

7.5. አነስተኛ የውጭ ሀገር ገንዘብ መያዝ ያለው የወንጀል ተጠያቂነት

በመርህ ደረጃ ማንኛውም ግለሰብ የውጭ ሀገር ገንዘብ ሊይዝ የማይችል ሲሆን በልዩ ሁኔታ ግን የውጭ ምንዛሪ የሚያዝበት አግባብ እንዳለ በተለያዩ ህጎች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ከመርህ አኳያ በሀገሪቱ በተጨባጭ የሚስተዋለው አነስተኛ የውጭ ሀገር ገንዘብ የሚያዝበት አግባብ ያለ በመሆኑ ምንም እንኳ ይህ አይነቱ ድርጊት በሕግ የሚያስጠይቅ ቢሆንም የተፈፀመው ወንጀል አነስተኛ ገንዘብ ከመሆኑ አኳያና መንግስት ከሚያወጣው የጊዜ፣ የገንዘብ እና ሌሎች ግብዓቶች አዋጭነቱ ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚያዝበት አግባብ ህጋዊ አይባል እንጂ ቀን ተቀን ባለው የህይወት ዑደት ውስጥ የሚስተዋሉ ጉዳዩች እንዳሉ መካድ አይቻልም፡፡ ከዘመድ አዝማድ ተገኘ ውጭ ሀገር ገንዘብ፣ በሆቴሎች እና በአስጎብኚ ድርጅቶች ውስጥ ለአስተናጋጆች፣ ለሹፌሮች እና ለተለያዩ ግለሰቦች በውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በትውልደ ኢትዮጵያዊያን አማካኝነት የሚሰጡ ጉርሻዎች እንዲሁም ለማስታወሻነት የሚያዙ አነስተኛ የውጭ ሀገር ገንዘብ እንደሚኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡

አነስተኛ የውጭ ሀገር ገንዘብ መያዝ በራሱ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገሪቷ ካላት ውስን ሃብት አንፃር እንዴት መታየት እንደሚኖርበት ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ በቅድሚያ አነስተኛ የውጭ ሀገር ገንዘብ ማለት በራሱ ስንት ነው? ለዚህ መልስ ማግኘት እጅጉን አስቸጋሪ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚንስቴር በመጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ/ም የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዘው በሚገኙ ግለሰቦች ላይ የሚቀርብ ክስን በተመለከተ መሪ ትዕዛዝ ሲሰጥ አነስተኛ የሆኑ የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዘው በሚገኙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረቡ የዐ/ሕግንም ሆነ የፍ/ቤትን ጊዜንና ሀብትን የሚያባክን መሆኑን አስረድቶ ከ100 የአሜሪካን ዶላር ወይም አቻ ምንዛሬ ካላቸው የውጭ አገር ገንዘብ ኖቶችን ይዘው የሚገኙ ሰዎች ላይ ገንዘብን መውረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ የወንጀል ክስ ማቅረቡ ቀሪ እንዲሆን ትዕዛዝ ከመስጠቱ አኳያ ከ100 የአሜሪካን ዶላር በታች ያለው መጠን አነስተኛ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ የተሰጠው ትዕዛዝ መነሻ እሳቤው ተገቢነት ያለውና የመንግስትን አላስፈላጊ ወጪ በተገቢ መንገድ ለታለመለት አላማ እንዲውል ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ይህን አላማና እሳቤ ለማሳካት የተወሰደበት አማራጭ ግን ከሕግ እኳያ ሊያከራክር የሚችል መሆኑ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም በቅድሚያ የ100 የአሜሪካን ዶላር መለያ ገንዘብ የተቀመጠበት አግባብ ከወንጀል ህጋችን አንፃር የተጣጣሞ ያልተመለከተ መሆኑና ሕግን የማውጣት ውጤት ያለው በመሆኑ ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ያሆናል፡፡

በተጨማሪም ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በታች የሚመወረስበት አግባብ እንዳለ የተመላከተ ከመሆኑ አኳያ በምን ስልጣን ማስፈፀም እንደሚቻል የሕግ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ምናልባት ይህንን ጉዳይ ከወንጀል ህጋችን አንቀፅ 343/2 አንፃር ታይቶ ማረምና ማስተካከል የሚቻልበት አግባብ አለ፡፡ ድንጋጌው በደንብ መተላለፍ የተደነገጉትን ወይም በዚህ አይነት ያልተመለከቱ ደንብ መተላለፍ ጠባይ ያላቸውን የሚያዙ ወይም የሚከለክሉ ድንጋጌዎችን በመጣስ ወንጀል በሚፈፀምበት በማናቸውም ጊዜ የወንጀሉ መፈፀም ያስከተለው ጉዳት ከአስር ሺህ ብር ያልበለጠ እንሆነ የሚወሰነው ቅጣት ስለደንብ መተላለፍ በተደነገጉት አንቀጾች መሠረት እንደሚሆን ይገልፃል፡፡ ከዚህ አኳያ አነስተኛ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ገንዘብ አስር ሺህ ብር የሚለውን ወስዶ በሀገሪቱ ውስጥ ባለው የውጭ ምንዛሬ ምጣኔ መሠረት ስሌቱን በማስላት የሚሰጠው የውጭ ሀገር ገንዘብ ውጤት ከተመለከተው ገንዘብ በታች መሆን አለመሆኑን መመዘንና ከዚሁ በታች የሆነ አንደሆነ የተያዘው የውጭ ሀገር ገንዘብ ተወርሶ ክስ መመስረቱ ቢቀር የተሻለ ይሆናል፡፡ ሆኖም ይህ አይነት መመሪያ በበላይ አመራሩ ሊታሰብበትና እንደአሰራር ሊዘረጋ የሚገባው ነው እንጂ እንዲሁ በደፈናው ስራ ላይ የሚውልበት ህጋዊ አግባብ አይኖርም፡፡ ሆኖም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 343/2 ላይ የተመለከተው ድንጋጌ ከተያዘው ጉዳይ ጋር እጅግ በጣም ቁርኝት ያለው መሆኑን መገንዘብ ያሻላል፡፡ ድንጋጌው በመንግስት የኢኮኖሚና የገንዘብ ጥቅሞች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ በመርህ ደረጃ ገዢ ሆኖ የተቀመጠ መሆኑ ሲታይ ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ በድንጋጌው መሠረት በደንብ መተላለፍ የተደነገጉትን ወይም የደንብ መተላለፍ ጠባይ ድንጋጌዎችን በመጣስ ወንጀል ተፈፅሞ ያስከተለው ጉዳት ከአስር ሺ ብር ያልበለጠ እንደሆነ የሚወሰነው ቅጣት ስለደንብ መተላለፍ በተደነገጉት አንቀፆች መሠረት እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡

ከዚህ አኳያ የውጭ ሀገር ገንዘብ መያዘን መሠረት በማድረግ የሚቀርብ የሕግ ውሳኔ እንዳለ ሆኖ ከዚህ አግባብ ውጭ የሚፈፀሙ ጉዳዮችን በተመለከተ በደንብ መተላለፍ ክፍል ውስጥ በአንቀፅ 785 ላይ የተደነገገ በመሆኑ በወንጀል ህጉ አነቀፅ 343 ላይ የተመለከተው ቀዳሚው መስፈርት የተሟላ መሆኑ ያሳያል፡፡ ሁለተኛው መስፈርት በአማራጭ የተቀመጠውና የደንብ መተላለፍ ፀባይ ያለው አይነት የሆነ እንደሆነ በማለት ያስቀመጠውን የሕግ ፍሬነገር በተመለከተም በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የውጭ ሀገር ገንዘብ መያዝ ወንጀልነታቸው የተመለከቱ ሆነው በወንጀል ህጉ አንቀፅ 735 መሠረት የደንብ መተላለፍ የሚለውን ትርጉም ሲያሟሉ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ በአንዳንድ ባለሙያዎች የሚነሳው ክርክር ከአስር ሺህ በታች ጉዳት ያደረሰ የትኛውም ድርጊት የደንብ መተላለፍ ባህሪያ ያለው ስለመሆን አለመሆኑ ታይቶ በደንብ መተላለፍ በቀጥታ ቅጣት እንዲበየንበት ማድረግ እንደሚቻል ያነሳሉ፡፡ ይህ አይነት አረዳድ በፀሃፊው እምነት የደንብ መተላለፍ ትርጉምን የሚለጥጥና በደንብ መተላለፍ ክፍል ውስጥ ካሉ ድንጋጌዎች ውጪ እያቋቋሙና ተጠያቂም እያደረጉ መሄድ ነው የሚል እምነት አለው፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት መሰረታዊ ድንጋጌ የወንጀል ህጉን አንቀፅ 3 እና 784 ሲሆን ድንጋጌዎቹ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በቀር የነገሩን ዓይነት እንዲሁም የሕጉን መንፈስና ግብ በመመልከት የወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል መሰረታዊ መርሆችና ደንቦች በደንብ መተላለፍ ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ያስገነዝባሉ፡፡

በዚህ መርህ መሠረት የወንጀል ህጉ ጠቅላላ ክፍል ላይ የተመለከተው መሰረታዊ መርህ በአንቀፅ 2 ላይ የሚገኘው የህጋዊነት መርህ ሲሆን በመርሁ መሠረት ሕገወጥነቱ በሕግ ያልተደነገገ ድርጊት ወይም ግድፈት እንደወንጀል ሊቆጥረው እና ቅጣት ሊወሰንበት እንደማይችልና በግልፅ ባልተደነገገበት ሁኔታ ከተደነገጉት ወንጀሎች ጋር በማመሳሰል ማቋቋም እንደማይቻል ያስቀምጣል፡፡ ይኽው መርህ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት (Mutatis-Mutandis) ለደንብ መተላለፍ በእኩል ደረጃ የሚሰራ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት በልዩ ሕግጋቶች ውስጥ በግልፅ በደንብ መተላለፍ የሚያስጠይቅ መሆኑ ያልተደነገገ እንደሆነ የደንብ መተላለፍ ባህሪ አለው በማለት ብቻ ማቋቋም የሚቻል አይሆንም፡፡ ይህን አይነት አተረጓጎም የሚደግፈው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ገንዘብ ጋር በተገናኙ ያሉ ድንጋጌዎች እንደ ግብር አለመክፈልና ኬላ መስበር (ኮንትሮባንድ) የመሳሰሉ ወንጀሎች በውስጡ ያካተተ ቢሆንም በደንብ መተላለፍ ክፍል ውስጥ ግን የማይገኝ ከመሆኑ አኳያ የተፈፀመው ድርጊት ከአስር ሺህ ብር በታች ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ወደ ደንብ መተላለፍ በመውሰድ ቅጣት እንዲጣል የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በተለይ አሁን ከግብር መሰብሰብ ጋር በተያያዘ ከአስር ሺህ ብር በታች ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች በርካታ ከመሆናቸው አንፃር ምንም እንኳ በግልፅ የደንብ መተላለፍ ድንጋጌ ባይኖርም የደንብ መተላለፍ ባህሪን በማየት ማቋቋም ይቻላል ማለቱ የወንጀል ህጉ ከወጣበት መንፈስና ግብ ጋር የማይጣጣም ይሆናል፡፡

ስለዚህ ይህን አይነቱን የሕግ አተረጓጎም መከተሉ ተገቢነት የሌለው ሲሆን ከላይ በተመለከተው አግባብ አነስተኛ ውጭ ሀገር ገንዘብ በሚገኝበት ጊዜ በደንብ መተላለፍ ቅጣት እንዲሰጥ ማድረግ የሚቻልበት አግባብ እንዳለ መረዳት ይቻላል፡፡ ሶስተኛውና የመጨረሻው ፍሬ-ነገር የደረሰው ጉዳት ከአስር ሺህ ብር ሊበልጥ የማይችችል ወይም የማይገባ እንደሆነ የተመለከተው ሀሳብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የውጭ ምንዛሬ በየቀኑ የሚለዋወጥና ተገቢውን ስሌት ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም በህጉ መሠረት አስር ሺህ ብር የሚለው መለኪያ የተቀመጠና ይህንኑ ድንጋጌ በተገቢው ሁኔታ ማስፈፀም የሚገባ በመሆኑ ወንጀል የተፈፀመበት የውጭ ሀገር ገንዘብን ብሔራዊ ባንክ ወንጀሉ በተፈፀመበት ወቅት ያወጣውን የምንዛሪ ምጣኔ መሠረት አድርጎና ተገቢውን ስሌት አከናውኖ የአስር ሺህ ብር መጠኑን አልፏል ወይስ አላለፈም የሚለውን በማየት እንደየአግባብነቱ በደንብ መተላለፍ አልያም በወንጀል መጠየቅ የሚቻልበት አግባብ እንዳለ መረዳት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይም የውጭ ምንዛሬ የሚያዝበት አግባብ እጅግ ብዙ ከመሆኑ አኳያና ጥቃቅን የሚባሉትን ጉዳዮችን ለማስተናገድ የሚቻልበትን አግባብ ከወንጅል ህጉ መርሆች አንፃር አይቶ በደንብ መተላለፍ ለመቅጣት የአስር ሺህ ብሩን ተመን አድርጎ መውሰድ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ መረዳት ይቻላል፡፡

8. ማጠቃለያ

ሀገራችን አንደሌሎች ሀገራት ገንዘብ የኢኮኖሚዋ መሠረት ሆኖ የሚያገለግልና ይህንን ውስን የሀገር ሀብት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል አስፈላጊ የሆኑ የቁጥጥር እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ በመሆኑ ገንዘብ የሚያዝበትና የሚተዳደርበትን አግባብ በተመለከተ በተለያዩ ሕግጋቶች ደንግጋ እናገኛለን፡፡ ገንዘብ የሚለው ቃል በራሱ በአለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት ላይ የተደረሰ ትርጉም ባይኖረውም ተቀራራቢ የሆኑ ትርጉሞች ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ በሀገራችን ገንዘብ ለሚለው ቃል ሳይሆን ገንዘብ-አከል ንብረቶች በሚል ሰፊ ትርጉም ተሰጥቶች እናገኛለን፡፡ ከጽሑፉ አላማ አንፃር ከጥሬ ገንዘብ ጋር የተመለከተውን ብቻ ለማየት የተሞከረ ሲሆን ጥሬ ገንዘብ የሚለውን የሕግ ፍሬ ነገር በሁለት አይነት እይታ በአጠቃላይ ከፍሎ ማየት ተችሏል፡፡ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ጥሬ ገንዘብ (ብር) በሚል እና ሁለተኛው ደግሞ የውጭ ሀገር ገንዘብ በሚል ለሁለት ከፍሎ ለማየት ተሞክሯል፡፡ የውጭ አገር ገንዘብ ማለት ከኢትዮጵያ ገንዘብ በስተቀር ከኢትዮጵያ ውጭ በማናቸውም ሀገር ሕጋዊ ገንዘብ የሆነና በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረግ ክፍያ ተቀባይነት እንዳለው ብሔራዊ ባንክ ያሳወቀው ማናቸውም ገንዘብ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ /እንደተሻሻለ/ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 2(5) ይደነግጋል፡፡

በአንፃሩ የውጭ ምንዛሬ ትርጉም ሰፊና የውጭ ሀገር ገንዘብን እንደሚያካትት አዋጁ ከሰጠው ትርጉም መረዳት የሚቻል ነው፡፡ አዋጁ ስለኢትዮጵያ ገንዘብና ስለውጭ ሀገር ገንዘብ ሰፋ ባለ ሁኔታ የሚተነትንና እንደ እናት ሕግ ሆኖ የሚያገለግል አዋጅ እንደሆነም መገንዘብ ይቻላል፡፡ አዲስ የታተሙ የኢትዮጵያ የብር ኖቶችን ስራ ላይ ለማዋል የወጣ መመሪያ አንዱ መመሪያ ሲሆን ገንዘብ የማውጣት ገደብ መመሪያ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ በብር እና በውጭ ምንዛሬ መያዝ ላይ የተጣለ ገደብ መመሪያ አዋጁን መሠረት አድርገው የወጡ መመሪያዎች ናቸው፡፡ በሕግ አግባብ ከተቀመጠው አግባብ ውጪ የሚከናወኑ ድርጊቶች የአስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ሲሆኑ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያቋቁሙት ድንጋጌዎች በወንጀል ህጉ፣ በጉምሩክ አዋጅ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ የሚገኙ ናቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ ይዞ የተገኘ ሰው ሊጠየቅ ስለሚችልበት ድንጋጌ በተደጋጋሚ የሚነሳና ጉራማይሌ በሆነ መንገድ ውሳኔ ሲሰጥበት ቆይቷል፡፡ በአንድ በኩል የወንጀል ህጉን አንቀፅ 346 መሠረት አድርጎ ውሳኔ ሲሰጥ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀፅ 26/1/ሀ/5 መሠረት ውሳኔ ይሰጣል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀፅ 168/2 መሠረት ውሳኔ የሚሰጥበትም አግባብ አለ፡፡ ሆኖም ተገቢ የሆነ አተረጓጎም ለመከተል የወንጀሉ ክብደት፣ የአዋጆቹ አንደምታ እና የሕግ አውጪውን አላማ መሠረት በማድረግ ተገቢውን ድንጋጌ እንደሁኔታው መጠቀም የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ ሌላው የሕግ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪን በመያዝ ሊያስከትልባቸው የሚችል የሕግ ተጠያቂነት አለ ወይስ የለም የሚለው የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

ማንኛውም ሰው (በሕግ ሰውነት የተሰጠው አካል) ከመነሻውም የውጭ ምንዛሪ መያዝም ሆነ መገበያየት እንደማይችል አወጁ ያስቀመጠ ሲሆን በመመሪያ ላይ ድርጅቶች ያልተካተቱ እንደሆነ ምንም አይነት ፈቃድ ከመነሻውም አልተሰጣቸውም ማለት እንደሆነ ግንዘቤ መውሰድ የሚገባ ነው፡፡ ከአንድ ቦታ በላይ ነዋሪ የሆነ ሰው ያለው የሕግ ተጠያቂነት በተመለከተ ሌላው ሊታይ የሚገባው አከራካሪ ጉዳይ ሲሆን የፀና የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የያዙ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሬን ወደ ሀገር ውስጥ ይዘው የገቡ እንደሆነ የውጭ ምንዛሬን ለመደንገግ በወጣው መመሪያ መሠረት በ30 ቀናት ውስጥ በህጋዊ አግባብ መመንዘር የሚገባቸው እንደሆነ በግልፅ ከተቀመጠው ድንጋጌ መረዳት የሚቻል ይሆናል፡፡ በኤግዚቢትነት የተያዘ የውጭ ምንዛሪ ስለሚመለስበት ሁኔታ በተመለከተም የተያዘው ኤግዚቢት ለክሱ መሰማት አስፈላጊ እስካልሆነ ድረስ ለተወሰደበት ሰው ተመላሽ መደረግ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ከመሆኑ አንፃርና ኤግዚቢት በባህሪው ሊለወጥ የማይገባ ከመሆኑም በተጨማሪ ህጋዊ ነው ተብሎ በተሰጠ ወሳኔ ላይ ግለሰቦች ንብረታቸውን ሊያጡ ወይም ሊቀየርባቸው የማይገባ በመሆኑ የውጭ ሀገር ገንዘብ ባለበት ሁኔታ ሊመለስ የሚገባ ይሆናል፡፡ አነስተኛ የውጭ ሀገር ገንዘብ መያዝ ያለውን የወንጀል ተጠያቂነት በተመለከተም አነስተኛ የሚለውን መጠን ከወንጀል ህጉ አንፃር በአግባቡ በመተርጎም በደንብ መተላለፍ መጠየቅ የሚቻልበት አግባብ እንዳለ በስተመጨረሻም ማንሳቱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

Download this article with full citation

Read 2368 times Last modified on Jun 24 2022
Gemechis Demissie

ጸሐፊው በ2004 ዓ.ም ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪውን (LLB) ያጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪውን በሕግ (LLM) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ/ም አግኝቷል፡፡ ጸሐፊው በፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በዐቃቤ ሕግ ሙያ የሠራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በፍትሕ ሚነስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ዐቃቤ ሕግ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

The writer earned his first law degree (LLB) in 2012 with distinction from Haramaya University and his second degree (LLM) from Addis Ababa University in 2020. The writer has worked as a public prosecutor in Federal Ethics and Anti-Corruption Commission and is currently a public prosecutor in the Federal Ministry of Justice, the Office of Attorney General. The blogger can be reached at lawbuffet@gmail.com