Print this page

ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል፣ የሕግ ማዕቀፋ እና አተገባበሩ

Jun 22 2022

አታላይነትና ማጭበርበር፡ ጠቅላላ መግቢያ

አታላይነት (ከባዱም ቀላሉም)፣ የማጭበርበር ወንጀል አንድ አካል ሲሆን ማጭበርበር በይዘቱ ሰፊ ነው፡፡ ዓለም ላይ የተለያዩ የማጭበርበር ወንጀሎች ሲፈጸሙ ማየት የእለት ተእለት እንቅስቃሴና የተለመደ ክስተት ነው፡፡ የማጭበርበር ወንጀል በዓይነቱ ብዙ፣ የተለያየ መልክ ያለው፣ ውስብስብ፣ ምስጢራዊ፣ ከባድና ሙያን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም ነው።

ማጭበርበር ሰፊ ጽንሰ ሀሳብ በመሆኑም ምክንያት ወጥና ሁሉንም የሚያስማማ ትርጉም መስጠት አይቻልም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጉዳዩ ላይ ለሚኖረን ግንዛቤ የተሻለ እንዲሆን፣ ማጭበርበርን አስመልከቶ የተሰጡ የተወሰኑ ትርጉሞችን እንመለከታለን።

ኦክስፎርድ ኢንግሊሽ ዲክሽነሪ፣ ማጭበርበርን እንደሚከተለው ይተረጉማል።

“The using of false representations to obtain an unjust advantage or to injure the rights or interests of another.”

ወደ አማርኛ ሲመለስ፤

“ለራስ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም የሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅምን ለመጉዳት የሀሰት መረጃ ወይም መግለጫ ማቅረብ ማለት ነው።” (ትርጉም የጸሐፊው)

Legal Dictionary በበኩሉ ማጭበርበርን እንደሚከተለው ይተረጉሟል።

“A false representation of a matter of fact whether by words or by conduct, by false or misleading allegations, by concealment of what should have been disclosed-that deceives and is intended to deceive another so that the individual will act upon it to her or his legal injury.”

“በድርጊት ወይም በንግግር መገለጽ የነበረበትን አንድ ፍሬ ነገር በመደበቅ፣ ሀሰትን እውነት አስመስሎ በማቅረብ፣ በማታለል፣ የተታለለው ሰውም የተነገረውን የሀሰት ፍሬ ነገር እውነት ነው ብሎ በመቀበሉ ምክንያት በሕጋዊ መብቱ ላይ ጉዳት ሲደርስበት ማጭበርበር ይባላል።” (ትርጉም የጸሐፊው)

ከላይ በተመለከቱት ገለጻዎች መሰረት፣ የማጭበርበር ወንጀል ታስቦ ወይም ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የማታለል ዘዴ ሲሆን በመሰረታዊነት የሚከተሉት አምስት ፍሬ ነገሮችን በጣምራ ሲሟሉ ቃሉ ሙሉ ትርጉም ይኖሯል፡፡

ስለአንድ ግዙፋዊ ነገር የሀሰት መግለጫ መሥጠት፤

አጭበርባሪው አንድን ግዙፍ እውነት የሀሰት ካባን አልብሶ ያቀርቧል። አጭበርባሪው አንድን ግዙፋዊ እውነት ሀሰት አስመስሎ ሲያቀርብ ብልህ መሆኑን ቢያውቅም ራሱን እንደ ብልህ ሳይሆን እንደ ሞኝና ምንም የማያውቅ ተራ ሰው አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይህ የሁሉም አጭበርባሪዎች መሰረታዊ መገለጫና ባህሪይ ነው።

አጭበርባሪው የሚሰጠውን መግለጫ ሐቅ አለመሆኑን ያውቃል፤

አጭበርባሪው አንድን ፍሬ ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ ሲያቀርብ ሀሰት መሆኑን በሚገባ ያውቃል፡፡ ሀሰት መሆኑን ስለሚያውቅም ሀሰት እየተናገረ ስለመሆኑ እንዳይነቃበት የተለያዩ የማታሊያ ዘዴዎችን ይፈበርካል፤ ይተገብራል።

አጭበርባሪው ተጎጂውን የሚያታልለው ሆነ ብሎ ነው፤

የማጭበርበር ወንጀል በአጋጣሚ ወይም በድንገት የሚፈጠር ክስተት ሳይሆን ታስቦበትና ሆነ ተብሎ (Calculated and deliberately) የሚፈጸም ነው፡፡

 ተጎጂው በሚሰጠው ወይም በሚገለጽለት መግለጫ መሰረት “እውነት ነው” የሚል እምነት ያሳድራል፤

አጭበርባሪው በሚናገረው ወይም በሚሰጠው ሀሰተኛ መግለጫ መሰረት ተጎጂው መግለጫው እውነት ነው ብሎ ያምናል፣ ይቀበላል፤ ተቀብሎም ወደ ተግባር ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ተጎጂው የአጭበርባሪው ሀሰተኛ መግለጫ ተቀብሎ ወይም እምነት አድሮበት ወደ ተግባር ካልገባ ወይም ካልተቀበለው በስተቀር የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሟል ሊባል አይችልም።

…በተበዳይ ላይ ጉዳት ይደርሳል፤

ተጎጂው በአጭበርባሪው ላይ ባሳደረው እምነት መሰረት የመብት ወይም የጥቅም ጉዳት ሊደርስበት ወይም ሊሞከርበት ይገባል፡፡ በተጎጂው ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት ከሌለ አጭበርባሪው ሆነ ብሎ ቢያታልለውም የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሟል ሊባል አይችልም።

ስለዚህም ማጭበርበር (Fraud) መረጃን ማዛባት፣ የተሳሳተ እምነት ማሳደር፣ ገንዘብ ለማግኘት የተዛባ ኢንፎርሜሽን ወይም መረጃ መሥጠት፣ በዚሁ በተዛባ መረጃ ምክንያትም ገንዘብ ማግኘት በሚል አግባብ ሊገለጽ ይችላል። ወንጀሉ እምነትን በመብላት፣ በመካድ፣ በመስረቅ፣ በመመዝበር፣ የፋይናንስ መረጃን በማዛባት፣ የአንድ የቢዝነስ ተቋም ገንዘብ የራስ አስመስሎ በመውሰድ ወይም በመዝረፍ ወዘተ… ሊፈጸም ይችላል።

ማጭበርበር የሚፈጸመው ገንዘብን ለማግኘት ነው፤ ሌላ ዓላማ የለውም፡፡ “ገንዘብ የዲያብሎስ ዓይን ነው” (Money is the devil’s eye) ፣ የሚል የፈረንጆች አባባል አለ። ይህ አባባል ገንዘብ በሰዎች ሕይወት ላይ ምን ያህል ተጽእኖ መፍጠር የሚችል ስልጣንና ጉልበት እንዳለው የሚያሳይ ነው። የማጭበርበር ወንጀል ውስጥ በቀጥታም በተዘዋዋሪም፤ ሐቅ፣ ፍትሕ፣ የሌሎች ሰዎች ጥቅምና መብት የሚሉ ቁልፍ ሞራላዊ ቃላት እናገኛለን፡፡ እነዚህ የማጭበርበር ቁልፍ ቃላት ናቸው፤ መሰረታዊ ናቸው።

የማጭበርበር ወንጀል ሕገ ወጥ ብቻ አይደለም። ኢ_ስነ ምግባራዊና ኢ_ሞራላዊም ጭምር ነው፡፡ የፍትሕ፣ የሐቅ፣ እንዲሁም የሕዝብና የዜጎች ጥቅምና መብት ጸርም ነው፡፡ የማጭበርበር ወንጀል የማታለል፣ የመዋሸት፣ የመስረቅ፣ እምነትን የመብላት ወይም የማጉደል ተግባራትን አጠቃልሎ የያዘ ነው።

በዚሁ አጭር ጽሑፍ ከባድ የማጭበርበር ወንጀል አካል ተደርጎ የሚወሰደው ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል በዋናነት፤ መንግሥታዊ ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶች አስመስሎ በማዘጋጀት፤ ወደ ሀሰት በመለወጥ ወይም ሐሰተኛ ሰነድ በመገልገል የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ደግሞ በተወሰነ መልኩ የሕግ ማእቀፋቸውንና አተገባበራቸውን እንዳስሳለን።

 

ከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል በኢትዮጵያ ሕግ

የማታለል ወንጀል በተለያዩ ሕጎች ላይ በወንጀልነት ተደንግጎ ይገኛል። ለምሳሌ በኢፌድረ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 692፣ እና 696፣ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32፣ እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ ሕጎች ደንቦች እና መመሪያዎች ላይ ተደንግጎ ይገኛል። ይሁን እንጂ የዚህ ጽሑፍ መሰረታዊ ዓላማ በሌሎች ሕጎች ላይ የተመለከተውን የማታለል ወንጀል በጠቅላላ ለመዳሰስ ሳይሆን ከሙስና ወንጀል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ሕጎች ስለ ከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል አስመልክቶ የሚደነግጉትንና የሚሉትን ላይ ወፍ በረር ዳሰሳ ለማድረግ ነው፡፡

ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰዉ ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር፣ የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም፣ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ ሌላውን ሰው ማታለል በሕግ የሚያስቀጣ ነዉ፡፡የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 ላይ እንደተመለከተው፤

“ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር፣ የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም፣ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ ሌላውን ሰው በማታለል የተታለለው ሰው የራሱን ወይም የሌላውን ሰው የንብረት ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገው እንደሆነ ከሦስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሦስት ሺህ ብር እስከ ሰላሳ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡”

በዚሁ ንኡስ ድንጋጌ መሰረት አንድ ሰው የማታለል ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የሚጠየቀው የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው።

አታላዩ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ወይም ከዚሁ ሰው ጋር በዋና እና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን የሚሳተፍ ሰው መሆን አለበት፡፡

አታላዩ የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ድርጊቱን መፈፀም ይኖርበታል፡፡ በሌላ አገላለፅ አታላዩ ተበዳዩን ለመጉዳት ወይም ለራሱ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን በቅን ልቡና ለመርዳትና ለማገዝ ያደረገው ከሆነ ወይም በቸልተኝነት ያደረገው እና በዚሁ አጋጣሚም በተበዳዩ ላይ ጉዳት የደረሰ እንደሆነ አድራጊው በሙስና ወንጀል ሊጠየቅ አይገባም፡፡

አታላዩ አሳሳች የሆኑ ነገሮች በመናገር፣ የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለጽ የሚገባውን ነገር መደበቅ ይኖርበታል፡፡ አታላዩ እውነትን ደብቆ ሀሰትን አጋንኖ፣ ያልሆነው ነገር ነኝ በማለት፣ ራሱን፣ ስራውን፣ ተግባሩን፣ ማንነቱን እና ሌሎች ጉዳዮችን በመደበቅ ተበዳይን እንዲሳሳት፣ ተሳስቶ እንዲያምነው፣ አምኖትም እንዲቀበለው በማሰብ ወይም ምንም አይነት ጥያቄ እንዳይነሳበት፣ ጥርጣሬ እንዳይድርበት በማድረግ ንብረቱን የወሰደበት መሆን አለበት፡፡

አታላዩ በድርጊቱ ወይም በንግግሩ ምክንያት ተበዳዩ የተሳሳተ እምነት ያደረበት ወይም የተታለለ መሆን አለበት፡፡ በሌላ አገላለፅ የግል ተበዳዩ ተታልሎ ወይም የተሳሳተ ግምት አድሮበት የንብረት ጥቅሙን አሳልፎ መስጠት አለበት፡፡ በተቃራኒው የተነገረውን ነገር ከጅምሩ ስህተት መሆኑን እያወቀ የአጥፊ ሀሳብ ተቀብሎ ወይም የውጤቱም ተካፋይ ለመሆን አስቀድሞ ተስማምቶ የራሱን ንብረት ወይም የሌላ ሰው የንብረት ጥቅምን አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ የማታለል ወንጀል ተፈፅሞበታል ሊባል አይችልም፡፡

ተበዳዩ በመታለሉ ምክንያት የራሱ ወይም የሌላ ሰው ንብረት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ሊደርስበት ይገባል፡፡ አንድ ሰው ቢታለልም በንብረቱ ወይም በሌላ ሰው ንብረት ላይ በዚሁ ምክንያት የደረሰበት ጉዳት ከሌለ የማታለል ወንጀል ተፈፅሞበታል ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም፣ ከፍ ሲል እንደተገለጸው፣ የማታለል ወንጀል የሚፈጸመው የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት በመሆኑ ነው።

ስለሆነም ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ከላይ የተጠቀሱት ፍሬ ነገሮችን ባጠቃለለ ሁኔታ ፈፅሞ ከተገኘ በከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ይጠየቃል፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ሰው የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 በከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል መሰረት ተጠያቂ የሚሆነው በመርሕ ደረጃ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ሆኖ ከላይ የተገለፁት መሰረታዊ የወንጀሉ ማቋቋሚያ በአንድነትና በጣምራ ተሟልተው ሲገኙ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም አስገዳጅ ትርጉም የሰጠ ሲሆን በዚሁም መሰረት አንድ የማታለል ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት አንደኛ አጥፊው ሆን ብሎ አሳሳች ነገሮችን በመናገር የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም፣ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ መግለፅ ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ ተበዳዩ መታለል ይኖርበታል ወይም አምኖ ሊቀበል ይገባል፡፡ ተበዳዩ በሀሰት ተገለፀለትን በማመን ያደረገው ወይም የፈፀመው ተግባር ሊኖር ይገባል፡፡ ሶስተኛ የግል ተበዳዩ በመታለሉ ምክንያት ያጣውን የገንዘብ ጥቅም ሊኖር ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ከላይ የተመለከተውን የማታለል ወንጀል መፈጸሙን ተከትሎ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም በመንግሥት፣ ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ወይም በሕዝብ ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት፣ የወንጀል አድራጊው የሥልጣን ደረጃ የወንጀሉን አፈጻፀም ከባድ አድርጎት እንደሆነ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት እና ከአሥር ሺህ ብር እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

በዚሁ ድንጋጌ መሰረት ሊጠየቅ የሚችለው “ማንኛውም ሰው” ሳይሆን የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ የማታለል ወንጀሉን የሚፈጽመው ግለሰብ ወንጀሉን የሚፈጽምበት ተጎጂ አካል የመንግሥት ወይም የሕዝብ ድርጅት ጭምር ሊሆን እንደሚችል ከዚሁ አንቀጽ ንኡስ ድንጋጌዎች (1) እና (2) ላይ መገንዘብ ይቻላል። ስለዚህ በአንቀጽ 32(1) እና (2) መሰረት የማታለል ወንጀሉን የሚፈጽመው የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ማታለሉን የሚፈጽመው በግለሰቦች፣ በሕዝባዊ ድርጅቶች፣ በመንግሥታዊ ተቋማትና አስተዳደራዊ አካላት ላይ ሊሆን ይችላል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወንጀሉ የተፈፀመው በሕዝብ አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ የሆነ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በአንቀጽ 32 ንዑስ አንቀፆች (1) ወይም (2) በአንዱ መሰረት እንደሚቀጣ የዚሁ አዋጅ አንቀፅ፣ ንኡስ ቁጥር ሦስት ይደነግጋል፡፡ ይሁንና ይህ ንኡስ ድንጋጌ ግልጽነት የሚጎድለው ይመስላል፡፡ ምክንያቱም በዚሁ ንኡስ ድንጋጌ ላይ ወንጀሉ የተፈፀመው በሕዝብ አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት እንደሆነ ይገልፃል እንጂ የወንጀሉ ፈጻሚ ማንነት ግን ለይቶ አላስቀመጠም፡፡ በሌላ አነጋገር የወንጀሉ ፈፃሚ ማንኛውም ሰው ነው? ወይስ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ብቻ ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ በሚመልስ አግባብ ግልፅ ሆኖ የተቀረጸ ድንጋጌ አይደለም፡፡

ከዚህ አከራካሪ ድንጋጌ በመነሳትም በዳኞችና ዓቃቤያነ ሕግ መካከል ሁለት ጎራ የለየ የጦፈ ክርክር ሲደረግበት የተለመደ ከመሆኑ በላይ ከድንጋጌው የአተረጓጎም ልዩነት በመነሳትም ወጥነት የሌላቸውና እርስ በእርስ የሚቃረኑ የተለያዩ ውሳኔዎችና ፍርዶች ሲሰጡ ይታያል፡፡

አንድ አንድ ዓቃቤያነ ሕግና ዳኞች አንቀፅ 32(3) ን ሲተረጉምት የወንጀሉ መሰረታዊ ማቋቋሚያ፣ በሕዝባዊ አስተዳደር ወይም በሕዝባዊ አገልግሎት ላይ የሚፈፀም የሚል እንደመሆኑ መጠን፣ ወንጀል አድራጊው “ማንኛውም ሰው” የሚመለከት ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ በድንጋጌው መሰረትም ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ያልሆነ ግለሰብ በመንግሥት ተቋማት ወይም የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የአስተዳደር ተቋማት በመሄድ የማታለል ወንጀል የፈፀመ እንደሆነ በዚሁ ድንጋጌ መሰረት ሊጠየቅ ይገባል በማለት ይከራከራሉ፡፡

በተቃራኒው የሚከራከሩ ዓቃቤያነ ሕግ እና ዳኞች ደግሞ ይህ ድንጋጌ ከመንግሥት ወይም ከሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ውጪ ያለውን ሰው ለመጥቀስ ቢፈልግ ኖሮ፤ ድንጋጌው በግልጽ “ማንኛውም ሰው” የሚል አጠቃቀም ይመርጥ ነበር፤ ይሁንና ይህን አልመረጠም፡፡ በማመሳሰል ተርጉመን ሰዎች በሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ ማድረግ ደግሞ ጠቅላላ የወንጀል ሕጎች መሰረታዊ የአተረጓጎም መርሆዎችን የሚጥስ ነው፡፡ ሕጎች አከራካሪ፣ ግልጽነት የሚጎድልባቸው፣ ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ናቸው ተብለው ቢወሰዱ እንኳን መተርጎም ያለባቸው ተጠርጣሪን ወይም ተከሳሽን በሚጠቅም አግባብ መሆን እንዳለበት በወንጀል ሕግ ፍልስፍና እና በሕጋዊነት መሰረተ ሀሳብ መሰረት ቅቡልነት ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡

ስለሆነም የወንጀሉ ተጠቂ አካል ብቻ በመግለጽ የወንጀል ፈፃሚው ማንነት “ማንኛውም ሰው” ነው፣ የሚል የዘፈቀደ ትርጉም ከማስቀደም ይልቅ ንኡስ ድንጋጌው ከንኡስ ድንጋጌ (1) እና (2) ጋር በማያያዝና በማስተሳሰር ፈፃሚው “የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ” እንደሆነ ግምት መውሰድ የሚቀል ይሆናል እንጂ “ማንኛውም ሰው” ነው የሚል ግምት መውሰድ አደገኛ አተረጓጎም ነው በማለት አበክረው ይከራከራሉ፡፡ በዳኞች በኩል ያለው አተረጓጎምም ወጥነት ያለው ነው ለማለት የሚከብድ ቢሆንም በአብዛኛው ግን ይህን ክርክር መሰረት በማድረግ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ያልሆነን “ማንኛውም ሰው” በመንግሥታዊ አስተዳደር ወይም በሕዝባዊ አገልግሎት ላይ የማታለል ወንጀል የፈፀመ እንደሆነ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32(3) ሳይሆን በኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 696(ሐ) መሰረት እንዲጠየቅና እንዲቀጣ ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አተረጓጎምና አተገባበር ፀኃፊው አያምንበትም፤ አያራምደውም፡፡

ጉዳዩን የበለጠ ግልፅ እንዲሆንልን፣ አንድ የመንግሥት ሰራተኛ የሚሰራበትን የመንግሥት ተቋም አታልሎ የገንዘብ ጉዳት ሊያደርስበት ይችላል ብለን አንድ ጉዳይ ይዘን እንነሳ፡፡ ለምሳሌ፡- በኢፌድሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ተቀጥሮ የሚሰራ አቶ ጫላ የተባለው ዓቃቤ ሕግ የደረጃና የእርከን እድገት ለማግኘት ሲል ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ ተቋሙን አታልሎ ያልተገባ የደረጃና የእርከን እድገት ማግኘቱን ተከትሎ ሕገ ወጥ የደመውዝና የጥቅማ ጥቅም ጭማሬ ያገኘ እንደሆነ በሀሰተኛ ሰነዶች መገልገል ወንጀል መከሰሱን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ክስም ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ይሁንና ይህ ዓቃቤ ሕግ በማታለል ወንጀል መከሰሱን የማይቀር ቢሆንም በየትኛውም ንኡስ ድንጋጌ ነው ሊጠየቅ የሚችለው? የሚለውን ጉዳዩ ግን በአግባቡና በጥንቃቄ መመርመር የጉዳዩ አከራካሪነት የሚገድለው ይመስለኛል፡፡

ይህ ዓቃቤ ሕግ ሀሰተኛ ሰነዶችን ተገልግሎ ያገኘው ጥቅም ወይም ያደረሰው ጉዳት አነስተኛ ከሆነ በአንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ (1)፣ ያገኘው ጥቅም ወይም ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከሆነ ደግሞ በንዑስ አንቀጽ (2) መሰረት ይከሰሳል፤ ይቀጣል። ይሁንና ይህ ዓቃቤ ሕግ ያታለለው የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ አስተዳደር ተቋም መሆኑን ግልጽ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የአዋጁ አንቀፅ 32 (1) እና (2) ድንጋጌዎች፣ የወንጀሉ ፈፃሚ ማንነት እነማን እንደሆኑ በመግለፅ የወንጀሉ ተጠቂ አካል ግን “ሌላውን ሰው” በሚል አግባብ አስቀምጦት እናገኘዋለን፡፡ ድንጋጌው በትኩረት ስንመለከተው፡-

….ሌላውን ሰው በማታለል ፣የተታለለው ሰው የራሱን ወይም የሌላውን ሰው የንብረት ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገው…..እንደሆነ በማለት ተደንግጓል፡፡

የወንጀሉ ሰለባ “ሌላ ሰው” የሚል በመሆኑ ይህ ሰው ደግሞ ‘የተፈጥሮ ሰው’ ወይም ’ግለሰብ’ ወይም ‘ሕግ ወለድ ተቋም’ እና ‘ድርጅት’ ሊሆን ይችላል፡፡ ከላይ እንደ ምሳሌ የተመለከተንው ዓቃቤ ሕግም የሚሰራበትን ሕግ ወለድ ተቋም የሆነውን የፍትሕ ሚኒስቴር በማታለሉ ምክንያት ያደረሰው ጉዳት ወይም ያገኘው ጥቅም አነስተኛ ከሆነ በአንቀፅ 32(1) ፣ ከፍተኛ ከሆነም በንኡስ ድንጋጌ (2) መሰረት የሚቀጣ ይሆናል የተባለበት መሰረታዊ ምክንያት ከዚሁ በሚመነጭ ነው፡፡

ስለዚህም የአዋጁ አንቀፅ 32 ንኡስ ቁጥር (1) እና (2) … ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በመንግሥታዊ ተቋማትና በሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ ጨምሮ በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈፅመውን የማታለል ወንጀል ሲኖር… እንደ ወንጀሉ ቅለትና ክብደት እየታየ ለመቅጣት የተቀረጹ ንዑስ ድንጋጌዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይም በንዑስ ድንጋጌ (2) ላይ እንደተመለከተው፣ በንዑስ አንቀጽ (1) ላይ የተመለከተው ወንጀል የተፈጸመው የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም በመንግሥት ወይም በሕዝብ ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት፣ በወንጀል አድራጊው የሥልጣን ደረጃ የወንጀሉን አፈጻጸም ከባድ አድርጎት እንደሆነ ቅጣቱ ከብዶ እንደሚወሰን ደንግጓል (ቅጣቱ ተቀምጧል)።

በዚሁ ድንጋጌ መሰረት በመንግሥትና በሕዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ በማለት የደነገገበት አግባብ ስናጤነውና በጥልቀት ስንመረምረው፣ በአንቀጽ 32፣ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) መሰረት የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛው የማታለል ወንጀሉን የሚፈጽመው በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በመንግሥትና በሕዝባዊ ድርጅቶች ጭምር እንደሆነ፤ ከዚሁ አንጻር ንኡስ ድንጋጌ (3) “ማንኛውም ሰው” በሕዝብ አስተዳደር ወይም የሕዝብ አገልግሎት ላይ ለሚፈጽምው የማታለል ወንጀል እንዲቀጣ የሚያደርግ ውጤት ከሌለው ድንጋጌው “ዋጋ አልባ ድንጋጌ” እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ፣ ድንጋጌው አላማ እና ውጤት ኑሮት ስራ ላይ ማዋል አንዱ ምርጫ ሲሆን፤ ድንጋጌው ትርጉም የለሽና የማይፈጸም ማድረግም ሌላ አማራጭ ነው፡፡ ምርጫው ለአንባቢው ይሁን።

ለክርክሩ ምክንያት እየሆነ ያለው፣ አንቀጽ 32 (3) የወንጀሉን ተጠቂ ወይም ሰለባ እንጂ የወንጀሉን ፈፃሚ ማንነት በግልጽና በማያሻማ መንገድ ስለማይገልጽ እንደሆነ ከፍ ሲል ተመልክተናል፡፡ የከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል መሰረታዊ ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮች በንኡስ ድንጋጌ (1) ላይ የተመለከቱ ሲሆን በንኡስ ድንጋጌ (2) ላይ የተመለከተው ግን የንኡስ ድንጋጌ (1) አክባጅ ምክንያት ነው፡፡

በአንቀጽ 32(3) ላይ የተመለከተው የማታለል ወንጀል ድንጋጌ ግን የንኡስ ድንጋጌዎች (1) እና (2) አክባጅ ምክንያት ሳይሆን ራሱን የቻለና አዲስ የማታለል ወንጀል ማቋቋሚያ ነው፡፡ ይህን ንኡስ ድንጋጌ ራሱ የቻለ አዲስ የወንጀል ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮችን በመያዝ የተደነገገበት መሰረታዊ አላማም በማንኛውም ሰው አማካኝነት በመንግሥት አስተዳደርና በሕዝባዊ አገልግሎት ላይ የሚፈፀም ማንኛውም አይነት የማታለል ወንጀል ለመቅጣት የወጣ መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በሌላ አነጋገር ይህ የማታለል ወንጀል “በማንኛውም ሰው” በመንግሥታዊ አስተዳደር ወይም በሕዝባዊ አገልግሎት ላይ የተፈጸመ ሲሆን ለመቅጣት የወጣ እንጂ “ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ” በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት የሚፈፅመው የማታለል ወንጀል ለመቅጣት ቢሆን’ማ ኖሮ በንኡስ ቁጥር (1) እና (2) ላይ ተደንግጎ ያደረ ጉዳይ በመሆኑ በድጋሜ መደንገጉ አስፈለጊ አልነበረም፡፡ በአንቀፅ 32(3) ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የሚፈፅመውን ወንጀል ለመቅጣት የወጣ ድንጋጌ ነው የሚባል ከሆነ፣ ድንጋጌው በንኡስ ድንጋጌ (1) እና (2) ላይ ተደንግጎ የሚገኘውን ጉዳይ እንደገና የሚደነግግ በመሆኑ ድግግሞሽና ትርጉም የለሽ (Redundancy and meaningless) ድንጋጌ ይሆናል፡፡

የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች የሚፈፅሙትን ማናቸውንም አይነት የማታለል ወንጀል ቀላል ከሆነ በንኡስ አንቀፅ አንድ፣ ከባድ ከሆነ በንኡስ አንቀጽ ሁለት መሰረት እንዲቀጡ ድንግጓልና እነዚህ ሰራተኞች በመንግሥት አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ ለሚፈፅሙት የማታለል ወንጀል ተብሎ ለብቻው ተነጥሎ መደንገግ አስፈላጊ አልነበረም፤ ለዛውም ለተመሳሳይ ቅጣት፡፡ አንቀፅ 32 ንኡስ ቁጥር (1) እና (2) ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በመንግሥታዊ ተቋማትና ሕዝባዊ ድርጅቶችን ጨምሮ በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈፅሟቸውን የማታለል ወንጀል ስለሚቀጡ በቂ ነበሩ፡፡

ስለዚህም አንቀጽ 32(3) የተደነገገው፣ ማንኛውም ሰው በመንግሥታዊ አስተዳደር ወይም በሕዝባዊ አገልገሎት ላይ የማታለል ወንጀል የፈጸመ እንደሆነ፤ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ሌላ ሰውን በማታለል የዚህ ሰው ወይም የሦስተኛ ወገን ጥቅም በመጉዳቱ ምክንያት ከሚቀጣው የቅጣት መጠን በእኩል እንደሚቀጣ የሚደነግግ ነው፡፡

በተጨማሪም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 36(1) ላይ እንደተመለከተው፣ በዚሁ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 696 ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በግልጽ ደንግጓል፡፡ በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 696(ሐ) ላይ ከባድ አታላይነት ወንጀል ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና እስከ ብር ሃምሳ ሺሕ በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣው….

() ወንጀሉ የተፈጸመው በሕዝብ አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ እንደሆነ ነው፤

በማለት የተደነገገውን ድንጋጌ የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007ም ቃል በቃል ቀድቶ በአንቀጽ 32(3) ላይ በማስቀመጡ (Copy paste) በማድረጉ፤ ማንኛውም ሰው በሕዝብ አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ የማታለል ወንጀል የፈጸመ እንደሆነ፣ በዚሁ ግለሰብ ላይ ክስ ለማቅረብ የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም ይህ ጉዳይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32(3) መሰረት የተሸፈነ በመሆኑ ነው።

በአጠቃላይ የአንቀፅ 32 ጠቅላላ ይዘትና አላማ አንድ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በሕግ ወለድ ተቋማት (Artificial Persons) ጨምሮ በማንኛውም ሰው ላይ የማታለል ወንጀል የፈጸመ እንደሆነ በንኡስ ቁጥር አንድ ላይ በተቀመጠው ቅጣት መሰረት እንደሚቀጣ፣ የፈጸመው የማታለል ወንጀል ተከትሎ ያገኘው ጥቅም ከፍተኛ ከሆነ ወይም በሕዝብ፣ በመንግሥት፣ በድርጅት ወይም በግለሰብ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነም በንኡስ ቁጥር ሁለት መሰረት ቅጣት እንደሚወሰንበት፤ እንዲሁም የማታለል ወንጀሉ የተፈፀመው በመንግሥታዊ ተቋማት ወይም ሕዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ድርጅቶች ላይ እንደሆነና የወንጀሉ ፈፃሚውም “ማንኛውም ሰው” እንደሆነ እንደተገኘው የጥቅም መጠን ወይም እንደደረሰው የጉዳት መጠን እየተመዘነ እንደየአግባብነቱ ክሱ በንኡስ አንቀጽ (1) ወይም (2) መሰረት ለመቅጣት የተደነገገ ድንጋጌ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዚሁም መሰረት የማታለል ወንጀሉ የተፈፀመዉ በሕዝብ አስተዳደር ወይም የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ድርጅቶች ላይ ከሆነ ከመንግሥት ወይም ከሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ዉጭ ያሉ ግለሰቦችም በሙስና ሊጠየቁ ይገባል እንጂ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ክሱ በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀፅ 696(ሐ) መሰረት መቅረብ አለበት የሚለውን ክርክር የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 ጠቅላላ ይዘትና አላማ በአግባቡ አለመገንዘብና ተግባር ላይ አለማዋል ነው፡፡

የማታለል ወንጀሉ የተፈጸመው በሀሰተኛ ሰነድ ከሆነ የክስ አቀራረብ ሥርዓቱ እንዴት ይሁን?

የማታለል ወንጀሉን የተፈጸመው ሀሰተኛ ሰነዶችን በመገልገል እንደሆነ የክስ አቀራረብ ሥርዓቱ እንዴት ሊታይ ይገባል? የሚለውን ሌላኛው መሰረታዊ ጭብጥ ማየት አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ አቶ አበበ የተባለው ተጠርጣሪ አቶ ከበደ በሚል ደንበኛ ስም ከአቢስንያ ባንክ የተሰጠ የሚመስል፣ 60 ሚሊዮን ብር የያዘ ሀሰተኛ ቼክ በመያዝ ለአቢስንያ ባንክ በማቅረብ ክፍያ እንዲፈጸምለት በማድረግ ገንዘቡን ይዞ ሊሰወር ሲል እጅ ከፍንጅ ተይዞ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ተደራጅቶበት፤ ለሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ ቢቀርብልህ/ሽ ውሳኔህ/ሽ ምን ሊሆን ይችላል?

ከዚሁ ጥያቄ በመነሳት፣ በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል እና መንግሥታዊ ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶች አስመስሎ ማዘጋጀት፤ ወደ ሀሰት መለወጥ ወይም በሐሰተኛ ሰነድ መገልገል በሚሉ ሁለት ተደራራቢ የሙስና ወንጀሎች ክስ ሊቀርብ ይችላል ወይ? የሚለውን ጉዳይ ማየት ያስፈልጋል።

ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ግን በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ ላይ ስለ ተደራራቢ ወንጀሎች የሚደነግጉ ድንጋጌዎች በአጭሩ መዳሰሱ ጠቃሚ ነው።

ተደራራቢ ወንጀሎች የሚባሉት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60 ላይ የተመለከቱት ግዙፋዊ ተደራራቢ ወንጀሎችና ተራ ተደራራቢ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ተደራራቢ ወንጀሎች (Concurrent offences) ማለት ሁለት ወይም ከሁለት የሚበልጡ አንድ አይነት ወይም የተለያዩ ማናቸውም አይነት ግዙፍ ወንጀሎች አከታትሎ መፈፀም ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ ወይም በአንድ ድርጊት ልዩ ልዩ ግዙፋዊ ውጤት የሚያስከትሉ ወንጀሎችን በመፈፀም ጣምራ ወንጀሎችን ያደረገ እንደሆነ፤ እንዲሁም በአንድ ወንጀል ማድረግ ሀሳብ ወይም ቸልተኝነት ያደረገው ድርጊት አንድን የሕግ ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ አንድ አይነት ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ተደራራቢ ወንጀሎች ፈፅሟል ይባላል፡፡ ተደራራቢ ወንጀል ለሦስት ይከፈላል፡፡ እነዚህም ግዙፋዊ ተደራራቢ ወንጀሎች (Material concurrence)፣ ሀሳባዊ ተደራራቢ ወንጀሎች (Notional concurrence)፣ እና የተበዳዮች ተደራራቢነት (Victim concurrence) ናቸው።

ግዙፋዊ ተደራራቢ ወንጀሎች ማለት ተመሳሳይ ወይም የተለያዩ ወንጀሎችን በመደጋገም መፈፀም ማለት ሲሆን ሀሳባዊ ተደራራቢ ወንጀሎች ማለት ደግሞ በአንድ ድርጊት ብቻ ከአንድ በላይ ወንጀሎችን የሚያስከትል ወይም የተለያዩ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ተግባር ተፈጽሞ ሲገኝ ነው፡፡ ስለሆነም ሀሳባዊ የወንጀሎች መደራረብ ከቁሳዊ ወይም ግዙፋዊ የወንጀሎች መደራረብ የሚለይበት መሰረታዊ ምክንያት በነጠላ ድርጊት የተለያዩ ድንጋጌዎችን ስለሚጥስ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ አይነት የወንጀል መደራረብ የድርጊት መደራረብን ሳይሆን በአንድ ድርጊት ምክንያት የተደራረቡ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ጥሰትን አስከትሎ ሲገኝ ነው፡፡ የተበዳዮች ተደራራቢነት ማለትም በአንድ ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ወይም ቸልተኝነት በተለያዩና በብዙ ሰዎች ሕጋዊ መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረስ ማለት ነው።

በሌላ በኩል በሕግ በተጠበቀ በአንድ መብት ላይ የሚደረጉ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ የተቀላቀሉ የወንጀል ድርጊቶች የተደረጉት በአንድ የወንጀል ማድረግ ሃሳብ ወይም ቸልተኛነት ሲሆን እና ድርጊቶቹ በሙሉ በአንድ ድንጋጌ ሥር የሚሸፈኑ ሲሆኑ አድራጊው ተመሳሳይ ባህሪ ባላቸው በሁለት ወይም ከሁለት በበለጡ ተደራራቢ የቅጣት ድንጋጌዎች እንደማይቀጣ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 61 (1) በልዩ ሁኔታ ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ አንድ የማታለል ወንጀል የተፈጸመው ሀሰተኛ ሰነዶችን በመገልገል እንደሆነ የተፈለገውን ግብና ውጤት ወይም የተሳካው ዓላማ አንድ ቢሆንም ክሶቹ ግን ሀሰተኛ ሰነዶችን መገልገል የሙስና ወንጀሎችና ከባድ አታላይነነት የሙስና ወንጀል በተደራራቢነት መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 699 ላይ በግልጽ ተመልክቶ የሚገኝ ልዩ መርሕ ሲሆን በዚሁም መሰረት ማንኛውም ዓይነት የማታለል ተግባር የተፈጸመው ወደ ሀሰተኛነት በተለወጠ ሰነድ አማካይነት ሲሆን አግባብ ያላቸው ድንጋጌዎች በተደራራቢነት ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ መሰረታዊ መርሆዎች ተደንግገው የሚገኙ ከአንቀጽ 1 እስከ 237፣ ስለ ተደራራቢ ወንጀሎች የክስ አቀራረብ ሂደትና የቅጣት አወሳሰን ሥርዓት በሚመለከትም ከአንቀጽ 60 እስከ 67 ድረስ ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ በመርሕ ደረጃ ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው ሲገኙ፣ ተደራራቢ ክስና ቅጣት እንደሚያስከትሉ በአንቀጽ 60 ላይ በግልጽ ተመልክቶ የሚገኝ ሲሆን ተደራራቢ ወንጀሎቹ የተፈጸሙት በአንድ ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ወይም ቸልተኝነት ከሆነ ግን የሚቀርበው ክስ በተደራራቢነት ሳይሆን በአንድ ነጠላ ክስ ይሆናል። ከዚሁ አንጻር በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 699 ላይ እንደተደነገገው፣ በሀሰተኛ ሰነዶች የሚፈጸሙ የማታለል ወንጀሎች በሚመለከት ሀሰተኛ ሰነዶችን መገልገል ወንጀል እና የማታለል ወንጀል በተደራራቢነት እንዲቀርቡ፣ ቅጣትም በዚሁ አግባብ እንዲወሰን ያስገድዳል።

ለምሳሌ አቶ ኑርሁሴን የተባለው ግለሰብ አንድ የግል ትምህርት ቤት ገብቶ የትምህርት ቤቱ አንድ ኮምፒዩተር አታልሎ ለመውሰድ በማሰብ በር ላይ የነበሩትን የጥበቃ ሰራተኞችን የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ነኝ፣ ኮምፒዩተሩ ስለተሰበረ አስጠግኜ እንደመልሰው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አዝዞኝ ነው በማለት ሀሰተኛ የተማሪነት መታወቂያና የኮምፒዩተሩ የማውጫ ምስክር ወረቀት ወይም ሰነድ አሳይቶ ኮምፒዩተሩን እንዲሰጡት በማድረግ ይዞ ከወጣ በኋላ ኮምፒዩተሩን ሽጦ ለግል ጥቅሙ ቢያውለው፤ የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 699 በሚደነግገው መርሆ መሰረት ተጠርጣሪው በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 692 እና በአንቀጽ 385 መሰረት በማታለል ወንጀልና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመገልገል ወንጀል በተደራራቢነት ሊከሰስ ይችላል፤ ይህ ግልጽ እና የማያከራክር ነው።

እዚሁ ላይ መሰረታዊ ጥያቄ ሆኖ የሚነሳው፣ ይህ መርሕ በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 699 ላይ ተደንግጎ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን፣ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ ለወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 ሊያገለግል ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለውን ነው፡፡

በ1997 ዓ.ም ከወጣው የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አዋጅ ቁጥር 414/1996 በተጨማሪ ወንጀሎችን የሚደነግጉ ሌሎች ደንቦችና ልዩ ሕጎች፣ የዚሁ የወንጀል ሕግ ክፍተቶችን የሚሸፍኑ መሟያ ሕጎች እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አዋጅ ቁጥር 414/1996፣ በጠቅላላ ክፍል ሆነ በልዩ ክፍል ተደንግገው የሚገኙ መርሆዎች ለሌሎች ልዩ ሕጎችና ደንቦችም ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው የሚያከራክር አይደለም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ በጠቅላላ ክፍል፣ አንቀጽ 3 ላይ ተከታዩን መሰረታዊ መርሆ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

ይህ የወንጀል ሕግ ቢኖርም ቅጣት የሚደነግጉ ደንቦችና ልዩ ሕጎች የተጠበቁ ናቸው። በእነዚህ ሕጎችና ደንቦች ላይ በተለየ አኳኋን ካልተደነገገ በቀር የዚህ ሕግ መርሆች ለእነርሱም ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

ይህ ድንጋጌ እየነገረን ያለው፣ በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ሆነ ልዩ ክፍል ላይ ተደንግገው የሚገኙ መርሆዎች፣ የወንጀል ሕጉን ክፍተት ለመሸፈን ወይም ለመሙላት የሚወጡ፣ እና ቅጣት በሚደነግጉ ደንቦችና ልዩ ሕጎች ላይም ተፈጻሚነት ይኖሯል የሚል ነው፡፡ የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 34፣ በወንጀል ሕጉ የመጀመሪያ ታላቅ ክፍል ከአንቀጽ 1 እስከ 237 ድረስ የተደነገጉት ድንጋጌዎች በዚህ አዋጅ ለተመለከቱት የሙስና ወንጀሎችም ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል በማለት በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ የደነገገ በመሆኑ የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 3 በዚሁ ታላቅ ክፍል ስር የሚገኝ ነው፡፡ ይህ በዚሁ ታላቅ ክፍል ስር የሚገኘው አንቀጽ 3 ደግሞ የወንጀል ሕግ መርሆዎች (በታላቅ ክፍሉ ሆነ በልዩ ክፍሉ የሚገኙ መርሆዎች) የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ ለማሟላትና ክፍተቱን ለመሸፈን በሚወጡ ልዩ ሕጎችና ደንቦች ላይም ተፈጻሚነት እንደሚኖረው በግልጽ የደነገገ በመሆኑ፣ የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 699፣ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 ላይም ተፈጻሚነት ይኖሯል ማለት ነው።

ስለዚህም በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 3 እና 699 ላይ የተመለከቱት ጠቅላላ እና ልዩ መርሆዎች እንዲሁም የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 34 ጣምራ ንባቦች መሰረት መንግሥታዊ ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶች አስመስሎ በማዘጋጀት፤ ወደ ሀሰት በመለወጥ ወይም ሐሰተኛ ሰነድን በመገልገል፣ ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ተፈጽሞ ከተገኘ ክሶቹን የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 እና 32 መሰረት በተደራራቢነት ሊቀርቡ ይገባል።

በዚሁም መሰረት ከፍ ሲል አቶ አበበ የተባለው ተጠርጣሪ አቶ ከበደ በሚል ደንበኛ ስም ከአቢስንያ ባንክ የተሰጠ የሚመስል፣ 60 ሚሊዮን ብር የያዘ ሀሰተኛ ቼክ በመያዝ ለአቢስንያ ባንክ በማቅረብ ክፍያ እንዲፈጸምለት በማድረግ ገንዘቡን ይዞ ሊሰወር ሲል እጅ ከፍንጅ ተይዞ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ተደራጅቶበት፤ ለሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ ቢቀርብልህ/ሽ ውሳኔህ/ሽ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ በምንችለበት አግባብ ተግባብተናል የሚል የጸሐፊው እምነት ሆኗል።

ቸር እንሰንበት!

Read 1476 times Last modified on Jun 22 2022
ገብረእግዚአብሔር ወልደገብርኤል

ጸሐፊው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዓቃቤ ሕግ ሲሆኑ በስልክ ቁጥር -0914505008, 0947931110 ወይም ኢ-ሜይል wgebregziher@gmail.com ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡