ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ የሚሰማበት ሥነ-ሥርዓት /Trial in absentia/

Jan 01 2020

 

መግቢያ

ክስ በሚሰማበት ሂደት ውስጥ ተከሳሽ የመኖር መብት እንዳለው ተግባራዊ መሆን የጀመረው በጥንታዊው የአንግሎሳክሶን ሕግ ነበር፡፡ በጥነታዊው የአንግሎሳክሶን ሀወግ የትኛውም ፍርድቤት ተከሳሽ በሌለበት ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም ነበር፡፡ (ST. JOHN'S LAW REVIEW volum 53 pp.722)

ስለሆነም የተከሳሽ የመሰማት መብት በጥንታዊው የሕግ ሥርዓትም ተግባራዊ ነበር ማልት ይቻላል፡፡ ባሁኑ የሕግ ሥርዓትም በመርህ ደረጃ ከክስ ጀምሮ እሰክ ቅጣት ውሳኔ ድረስ ያሉት ሂደቶች ተከሳሰሁ ባለበት መከናወን አለባቸው፡፡ ተከሳሽ ችሎት በመቅረብ የቀረበበትን ክስ የመረዳትና የመከላከል መብት አለው፡፡ ሥለሆነም ተከሳሽ ችሎት መገኘቱ ክሱን በበቂ ሁኔታ ለመከላከል እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች ሀገራት ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ የሚታይበትን ሥርዓት በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ህጋቸው አካተውት ይገኛሉ፡፡

ተከሳሽ በሌለበት ክስ የሚሰማበት ሥርዓት በኢትዮጵያ

በወንጀል ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተረድቶት የመሰማት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንሥግሥት አንቀጽ 20 ደንግጓል፡፡ የሕገመንግስቱ አንቀፅ 9(4) በደነገገው መሰረት ሌሎች ኢትዪጲያ ያፀደቀቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እነዚህ ውስጥ የሚካተቱ እና እንደ ኢትዬጲያ ሕግ እንደሚቆጠሩ ይደነግጋል፡፡

ልክ እነደ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ በኛ ሀገርም በመርህ ደረጃ ክስ መሠማት ያለበት ተከሳሽ ባለበት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የወንጀል ክስ ሁሉ ተከሳሽ ፍርድ ቤት ካልቀረበ ታይቶ አይወሰንም ማለት አይደለም፡፡

በሕግ ተለይተው በተመለከቱ ወንጀሎች ላይ ተከሳሽ በሌለበትም ክሱን መርምሮ መወሰን ይቻላል፡፡ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 160/2/ ሥር ነገሩ ሊሰማ በተቀጠረበት ቀን ተከሳሽ ካልቀረበ ወይም ለመቅረቱ በቂ ምክንያት የሚሰጥለት እንደራሴ ካልቀረበ እንዲያዝ ትዕዛዝ ፍ/ቤት እንደሚሰጥ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ትዕዛዝ መሠረት መፈፀም ካልተቻለ ተከሳሹ በሌለበት ነገሩን ለመስማት ፍ/ቤቱ እንደሚያስብበት የዚሁ ቁጥር 160/3/ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ይዘት መረዳት የሚቻለው ተከሳሹ መጥርያ ደረሰውም አልደረሰውም ክሱ እነዲሰማ በተቀጠረበት እለት ካልቀረበ ክሱ በሌለበት ሊሰማ እነደሚችል ነው፡፡

በተገቢው ሁኔታ የፍርድ ቤቱ መጥርያ ለተከሳሽ መድረስ አለመድረሱ ሳይረጋገጥ ጉዳዩን በሌለበት ለመስማት መዎሰን የተከሳሽን ክሱን የመከላከል መብት አያጠብም? በሕገመንግሰቱ አንቀጽ 20 ላይ የተዘረዘሩት ማስረጃ የማቅረብ፣ ምስክሮችን የመጠየቅ፣ የሀግ አማካሪ የማግኘት የመሳሰሉት መብቶች ተከሳሽ ከቀረበ ብቻ የሚያገኛቸው አይደሉም?

የኢፌደሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20/2 ተከሳሽ ክስ የቀረበበት መሆኑን እና የክሱን ዝርዝር ሁኔታም የመረዳት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ይህ ደግሞ ክሱ ከመሰማቱ በፊት ለከሳሽ መጥርያ ሊደርሰው እንደሚገባ መንግስት ላይ ግዴታ የሚጥል ነው፡፡ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣውና በልምድ የዳበረው ጉዳይ ፖሊስ ለተከሳሽ መጥርያ አለማድረሱን መጥርያ ያላደረሰበት ምክንያትም ተከሳሽ ባካባቢው የሌለ መሆኑን ከገለጸ ጉዳዩ በሌለበት እነደሚታይ ይወሰናል፡፡ ፖሊስ መጥርያ ስላላደረስሰ ወይም መጥርያ ማድረስ ስላልቻለ ጉዳዩ በሌለበት ይቀጥል ማለት ለተከሳሽ ከተሰጠ የመብት ጥበቃ ጋር አንጻር እንዴት ይታያል?

 ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ጉዳይ ተከሳሽ መጥርያ ደርሶት በመጀመርያው ቀጠሮ ፍርድቤት ከቀረበ በኋላ ቀጣይ ባሉት ቀጠሮዎች ሳይቀርብ ቢቀር ምን አይነት ሥነ-ሥርዓት ልንከተል ይገባል የሚለው ነው፡፡ ተከሳሽ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ወይም የዐቃቤ ሕግ ምስክር ተሰምቶ ለብይን በተቀጠረበት ቀን ወይም ተከላከል ተብሎ መከላከያ ማስረጃ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ባይቀርብ ልንከተለው የሚገባው ሥነ-ሥርዓት ምን ሊሆን ይችላል? ተከሳሽ ተከላከል ተብሎ የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት በተቀጠረበት መቅረብ ካልቻለ የ ወንጀል ሥነስርኣት ህጉ ድንጋጌዎች 160 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ተግባራዊ እንደማይሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚችሎት በአመልካች የአብክመ ፍትሕ ቢሮ እና በተጠሪ አቶ አንዷለም ገናነው መካከል የሰበር መዝገብ ቁጥር 127313 አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ የጠቅላይ ፍርድቤቱ ሰበር ሰሚችሎት ቡውሳኔው ላይ የሚከተለውን ተታ ሰጥቷል፡፡

…………… ተጠሪ ክሱ በሚሰማበትና የከሳሽ ዓ/ሕግ ምስክሮች በሚሰሙበት ጊዜ ችሎት ቀርቦ የተከራከረ በመሆኑ እና በተከሰሰበት የሕግ ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ አውቆ መከላከያ ማስረጃ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ በያዘበት ቀን ሳይገኝ መቅረቱ ጉዳዩ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ (4) በወንጀል የተከሰሰሰው የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ሲሰማ በመገኘት የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች የመጠየቅና የመመርመር መብቱን በአግባቡ ከተጠቀመና የመከላከያ ምስክሮችንና ማስረጃ እንዲያቀርብ የተሰጠውን መብት በራሱ ፍላጎት ካልተጠቀመ እና የመከላከል መብቱን ካልተጠቀመ ዳኞች የቀረበውን ክርክርና ማስረጃ በመመዘን ፍርድ ከመስጠት የሚገድባቸው ባለመሆኑ በህጉ ለተከሳሽ ከተሰጠው የመደመጥ መብት አንፃር ተከሳሹ መብቱ በራሱ ፍላጎት ባለመጠቀሙ ጉዳዩ ተከሳሹ በሌለበት እንደሚታይ ጉዳይ ሊታይ የሚችል ባለመሆኑ ፍርድ ቤቶች የቀረበውን ጉዳይ መርምረውና መዝነው ውሳኔ ከመስጠት የሚገድባቸው ጉዳይ አይሆንም፡፡ (የሰበር መዝገብ ቁጥር 127313 ቅጽ22)

ከዚህ ውሳኔ ለመረዳት የሚቻለው ተከሳሽ የዐቃቤሕግ ማስረጃዎችን ከሞገተ በኋላ ባይቀርብ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ህጉ ድንጋጌዎች 160 እና ተከታዮቹ/provisions governing default proceeding /ተግባራዊ መሆን እንደሌለባቸው ነው፡፡

ሆኖም ግን ተከሳሽ በመጀመርያው ቀጠሮ ቀን ቀርቦ በዋሰ ከወጣ በኋላ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ለመስማት ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ባይቀርብ ምን ሥነ-ሥርዓት እንከተላለን? የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን የመመርመርና የመጠየቅ መብቱን ስላልተጠቀመ ጉዳዩ በሌለበት የሚታይ አይደለም እንላለን?መብቱን በራሱ ግዜ ትቶታል በማለት በሌለበት ቀጥታ ጉዳዩን እናስቀጥላለን? ወይሰ የሥነስርት በህጉን 160 እና ተከታዮችን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ዕናደርጋለን?

ተከሳሽ መጥርያ ደርሶት ፍርድቤት ካልቀረበ መብቱን በራሱ ፈቃድ እንደተዎው በመቁጠር ተከሳሽ ሳይኖር ጉዳዩ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን በኛ ሀገር የሕግ ስርአት ተከሳሽ መጥርያ ደርሶት በራሱ ፈቃድ ፍርደቤት ሳይቀርብ ብቻ ሳይሆን መጥርያ ሳይደርሰውም ቢቀር ጉዳዩ በሌለበት የሚታይበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡

በኛ ሀገር ሁሉም ወንጀሎች ተከሳሽ በሌለበት ይታያሉ ማለት አይደለም፡፡ አንድን የወንጀል ክስ ተከሳሽ በሌለበት መስማትና መወሰን የሚቻለው በወንጀል ሥነስርአት ሕግ ቁጥር 161/2/ መሠረት ከ12 ዓመት በማያንስ ጽኑ እሥራት የሚያሳስር ወንጀል የሠራ ወይም በቀድሞ ወ/መ/ሕግ ቁ. 354-365 በአዲሱ የወንጀል ሕግ ቁ. 343 እስከ 354 ድረስ ያሉ ወንጀሎች ፈጽሞ ጽኑ እሥራት ወይም ከ5ዐዐዐ ብር በላይ በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን እንዲሁም በውጭ ሀገር ጥገኛ ሆኖ ጥገኛ ያደረገው ሀገር አሳልፎ ያልሰጠው እንደሆነ ነው፡፡

 ከ12 አመት በማያንስ ጽኑ እስራት ማለት ምን ማለት ነው? በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል የተደነገገው ወይም ተከሳሽ የተከሰሰበት ወንጀል ፍቅድ ስልጣን ውስጥ መነሻው 12 አመት መሆን አለበት? ወይስ የ12 አመት ቅጣቱ በፍቅድ ስልጣኑ ዝቅተኛውና ከፍተኛው ጣርያ መካከል መገኘት ለበት?

እነዚህ ጥያቄዎች በሕግ በለሙያዎች ዘንድ አከራካሪነታቸው እነደቀጠለ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ሁሉም የሕግ ባለሙያዎች የየራሳቸውን አቋም ሲያንጸባርቁ ማየት የተለመደ ነው፡፡

 የወንጀል ሕግ ሲተረጎም ማለትም ህጉ ግልጽነት የጎደለው እንደሆነና መተርጎሙ የግድ አስፈላጊ ከሆነ ተከሳሽን በሚጠቅም መልኩ መተርጎም አለበት፡፡ ይህ ደግሞ አለማቀፋዊ ተቀባይነት ያለው የሕግ አተረጓጎም መርህ ነው፡፡ ስለሆነም የወንጀል ሥነስረአት ሕግ ቁጥር 162/2 ሲተረጎም ተከሳሹን ሊጠቅም በሚችል መልኩ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲበል ተከሳሽ ፍርደቤት ቀርቦ ክሱን የመከላከል መብት እንዳለው በሕገመንግሰቱና በሰብዘዊ መብቶች ሰነዶች ላይ ጥበቃ ሰጥቶታል፡፡ ስለሆነም ይህ ሕግም ሲተረጎም ተከሳሽ መብቱን መጠቀም በሚያስችል መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ የሚታይበት ስርአት ልዩ ሕግ (exception) እንጅ መርህ አይደለም፡፡ የ12 አመት እስራት ቅጣት በከፍተኛው አና በዝቅተኛው ቅጣት መካከል ከተገኘ በሌለበት ለማለት በቂ ነው የሚባል ከሆነ እጅግ በርካታ ወንጀሎች ከደንብ መተላለፍ እና ቀላል ወንጀሎች በስተቀር ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ተከሳሽ በሌለበት መስማትን ልዩ ሕግ መሆኑ ቀርቶ መርህ የሚያደርግ ነው፡፡ ልዩ ሕግ ደግሞ መተርጎም ያለበት በጠባቡ ነው፡፡

ሌላው ሕግ ሲተረጎም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሚተረጎመው ሕግ አላማ /purpose of the law/ነው፡፡ ሕግ ሲተረጎም ህጉየቆመለትን አላማ ከግብ ለመምታት መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም በወንጀል ሥነስረአታችን ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ ሊታይ የሚችልበት ሥነስርአት ለምን የህጋቸን አካል እንደሆነ ማጤኑ ተገቢ ነው፡፡ የወንጀል ሥነስርአት ህጉን አንቀጽ 160 እና ተከታዮቹን ድንጋጌቸ ስንመለከት ተከሳሽ በሌለበት ክሱ የሚታየው ለከባድ ወንጀሎችና ተከሳሽም ሊጣልበት የሚችለውን ከባድ ቅጣት በመፍራት ከሕግ ለመሸሽ የሚደበቁ ተጠርጣሪዎችን የክስ ሂደት ከግብ ለማድረስና ተከሳሾችንም ተጠያቂ ለማድረግ የተቀመጠ ነው፡፡ ይህም ማለት በባህርያቸው ከባድ የሆኑ ወንጀሎች ላብነትም በከባድ ሁኔታ ሰው መግደል(የወንጀል ሕግ ቁጥር 539/1)፣ ህጻናት ላይ የግብረስጋ በደል መፈጸም( አንቀጽ627/1 )ተከሳሽ፣ ከ13 አመት በታች የሆኑ ህጻናት ላይ የሚፈጸም ግብረሰዶማዊነት( ወ/ህ/ቁ 631/1/ለ)፣ ጅምላ ጭፍጨፋ (የወ/ህ/ቁ 269) በሌለበት የሚታዩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ 12 ዝቅተኛው የቅጣት መጠን መሆኑ አስገዳጅ አይደለም፤ የ12 አመት እስራት ቅጣት በዝቅተኛውና በከፍተኛው ቅጣት መካከል የሚገን ከሆነ ተከሣሽ በሌለበት ጉዳዩን ማየት ይቻላል የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች የሚያቀርቡት የመከራከርያ ሃሳብ ተከሳሽወንጀል ፈጽም ከፍትሕ መሸሽና ማምለጥ የለበትም፤የህጉ አላማም ወንጀል ፈጽመው የሚደበቁ ግለሰቦች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኑ ማድረግ ኑው የሚል ነው፡፡

ከዚ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ክርክር ሙስና ወንጀል ዋስትና ክርክርን በተመለከተ አዋጅ ቁጥር 437/97 አንቀጽ 4/1ን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚችሎት በሰበር መዝገብ ቁጠር 63344 የሰጠው የሕግ ትርጉም ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 437/97 አንቀጽ 4/1 የሚደነግገው ከ 10 አመትና በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው ዋስትና የማግኘት መብት የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ይህንን የአዋጁን ድንጋጌ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት በሰጠው የሕግ ትርጉም ላይ ተከሳሽ የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ክስ ጣርያው ከ 10 አመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ በዋስትና ወረቀት ሊለቀቅ እንደማይችል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ (በሰበር መዝገብ ቁጠር 63344 ቅጽ12)

ስለሆነም ተከሳሽበሌለበት ሊታዩ የሚገባቸውን ጉዳዮችም በዚህ ውሳኔ መሰረት የ12 አመት ጣርያ መታየት አለበት? የሰበር ውሳኔ የሕግ ትርጉም አስገዳጅነት ለተመሳሳይ የሕግና የፍሬ ነገር ጉዳዮች ብቻ መሆነ የለበትም?

የሰበር ሰሚ ችሎቱ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች አስገዳጅ የሚሆኑት በተመሳሳይ የፍሬ ነገርና የሕግ ጉዳዮችነው፡፡ የሰበር ሰሚችሎቱ በሙስና ጉዳይ ላይ ለተነሳ የዋስትና ክርክር ላይ ለደረሰበት ድምዳሜ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስን ለማየት እንደ ምክንያት ሊወሰድ አይችልም፡፡

ሌላው መነሳት የሚገባው ነጥብ በሕገመንግስታችን አንቀጽ 20 ስር በዝርዝር እንደተመለከተው ማንኛውም የተከሰሰ ሰው የቀረበበትን ክስ የመከላከል መብት አለው፡፡ ይህ መብት በሕገመንግሰቱ ገደብ የተጣለበት አይደለም፡፡ ሌሎች የሕገመንግሰቱን ድንጋጌዎች ስንመለከት የራሳቸው የሆነ ገደብ/limitation clauses/ ያላቸው ሲሆን ስለተከሰሱ ሰዎች የሚደነግገው ድንጋጌ ግን ገደብ አልባ እንደሆነ ከድንጋጌው ለመረዳት ይቻላል፡፡

 በሕገመንግስቱ ገደብ ያልተጣለበትን መብት በሥነስርኣት ህጉ መገደብ ይቻላልን? በሕግ ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል ሕገመንግሰቱ ላይ ሊደነገግ አይገባም ነበር? በተራ አዋጅ ተፈጥሮአዊ እና ሕገመንግስታዊ የሆነውን መብት መገደብ ሕገመንግስታዊ ነውን? ምናልባትም ሕገመንግስቱ የጸደቀው ከወንጀል ሥነስረዓት ህጉ በኋላ ስለሆነ ነው ለማለት ይቻላልን?

 በረቂቅ ደረጃ ያለው የወንጀል ሥነስረዓት ሕግ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጥ በሚችል መልኩ የተረቀቀ ከሆነ ተፈጥሮዓዊ የሆነውን መብት ማስከበር ይቻል ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክሱን ማየት በሕግ የተከለከለ ባይሆንም ጉዳዩ እንዲቀጥል ፍርድቤቶች የሚወስኑ ከሆነ የተከሳሹን መብት በማያጣብብ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ተከሳሽ ስለመከሰሱ በማያውቅበት ሁኔታ ክሱን ማስቀጠል ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በተለይም በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ሰፊ ያልተማረ ህዝባ ባለበትና ጋዜጣ ማንበብ ባህሉም በሌለበት እንዲሁም ሰፊ የጋዜጣ ስርጭት ሳይኖር የጋዜጣ ጥሪ በማድረግ ብቻ ተከሳሽ ካልቀረበ ጉዳዩ በሌለበት እንዲቀጥል መወሰን ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አንጻር የፍትሕ ተቋማት የተከሳሽ መብት በክርክሩ ሂደት መከበሩን ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው፡፡

 

Read 6032 times Last modified on Jan 13 2020
 Abel Abebe

The blogger is currently working as a Public Prosecutor at Federal Attorney General. The blogger served as a Woreda court judge in Amhara region.