የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ከሕገ መንግሥቱ ጋር ባለው ተቃርኖ ምክንያት ተፈፃሚ ሊሆን የማይችልና በወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች የሚሸፈን ስለመሆኑ

Dec 13 2019

 

 

1. መግቢያ

ኢትዮጵያ የጸረ ሽብር አዋጅ በማውጣት ወደ ስራ ከገባች የቆየች ሲሆን ይህ አዋጅ ከረቂቅነቱ ጀምሮ ከአለማቀፉ ማህበረሰብና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ከተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት እንዲሁም ከተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችና ምሁራን መንግሥት (ኢሕአዴግ) ለስልጣኔ ያሰጉኛል የሚላቸውን ተቃዋሚዎቹንና ተሰሚነት ያላቸውን ግለሰብ ተቺዎችንና ነፃ ፕሬሱን ለማፈንና ለማስወገድ አላግባብ ሊጠቀምበት ይችላል በሚል እሳቤ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዳይጸድቅ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ቢሆንም አዋጁ እንዲወጣ ተደርጎ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ በስራ ላይ ሲሆን መንግሥትም አዋጁን ተከትሎ ሲፈጸሙ የቆዩ ኢሰብአዊ ድርጊቶች መኖራቸውንና በፖለቲካ አመለካከታቸውና መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘራቸው ምክንያት በሽብር ስም ብዙ ንጹሃን ለእስርና ለእንግልት ከበድም ሲል ለአካል መጉደልና ለሥነ ልቦና ቀውስ መዳረጋቸውን በማመን የታሰሩትን ዜጎችን በይቅርታና በምህረት የለቀቀና እሰካሁንም ለተሰራው ስህተት ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ የአዋጁን ኢፍትሃዊነት አረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ የመንግሥት የማመንና ያለማመን ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን የሚቃረንና ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የጣሰ በመሆኑ አዋጁ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ነው፡፡ በሕግ አስፈፃሚው ከታመነና አዋጁ ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደማይገባ ከተገለጸ በኋላ እንኳን በዚሁ አዋጅ የተጠረጠሩና ጉዳያቸው በፍ/ቤት የተያዘ ግለሰቦች መኖራቸው ጥያቄ ማሥነሳቱ አልቀረም፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻ ዓላማም በአዋጁ ተፈፃሚነት ላይ እና በአዋጁ የተዘረዘሩት የወንጀል ድርጊቶች በወንጀለኛ ሕጉ የተሸፈኑ መሆን አለመሆናቸውን በሚመለከት ጸሐፊው የተሰማውን የግል ሙያዊ አስተያየቱን ለማስቀመጥ ያክል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጽሑፉ አዋጁ የሕገ-መንግሥቱን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥስ በመሆኑ መሻር ወይም በሌላ መተካት ሳያስፈልገው ቀሪ ማድረግ የሚቻልበት አግባብ መኖሩን የሚያብራራ ሲሆን በዋናነት በአዋጁ የተጣሱ ሕገመንግሥታዊ መብቶች ምን ምን እንደሆኑ ያትትና አዋጁ መፈጸም የለበትም ከተባለ አማራጪ ሕግ አለን የለንም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በወንጀል ሕጉ የሚሸፈን መሆን አለመሆኑን በአጭሩ በማብራራት ይጠናቀቃል፡፡ 

 

2. የጸረ-ሽብር አዋጁ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን በመሆኑ በሌላ ህግ መሻር ወይም መተካት ሳያስፈልገው ተግባራዊ ሊደረግ የማይገባውና ተፈፃሚነት የሌለው ነው

ለዚህም

                  የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(1) 

ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፡ ልማዳዊ አሰራር ፡ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡

በማለት ካስቀመጠው ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ የሚወጡም ይሁኑ ቀድሞ የወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና አሰራሮች እንዲሁም መመሪያዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃራኑ ከሆኑ ተፈፃሚነት የሌላቸውና ተግባራዊ ሊደረጉ የማይገቡ መሆናቸውን ነው፡፡ በዚሁ መሠረትም የጸረ ሽብሩ አዋጅ ቁጥር 652 / 2001 ከታች የተዘረዘሩትን ሕገ መንግሥቱ ያካተታቸው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጥስ በመሆኑ ተፈፃሚነት የለውም ማለት ነው ፡፡ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ተቃራኒ የሆኑ ሕጎች ሲወጡ እንደሌሎቹ አዋጆች (ሕጎች) ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የሚመለከተው አካል እንዲሻሩ/እንዲሻሻሉ የሚያደርጋቸው ሌላ አዋጅ በማውጣት ብቻ ሳይሆን ወይም ይህን ሂደት መከተል ሳይጠበቅበት ጥሰቱ ከተለየበት ወይም ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ተግባራዊ ባለማድረግም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) ላይ የገለጸው አዋጁ (ሕጉ) ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑን እንጂ እንደሚሻር / ሊሻሻል እንደሚገባና እስከዚያው ተግባራዊ መሆን እንዳለበት የሚያሳይ አይደለም፡፡ ተፈፃሚነት የለውም ያለበት ዓላማም ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ባለበት ሁኔታ መደበኛውን የሕግ የማውጣትና የመሻር/የማሻሻል ሂደት እንዲከተል ቢደረግ ግዜ ስለሚወስድና እስከዚያው ጥሰቱ እንዲቀጥል የማድረግ ውጤት ስለሚኖረው ይህን ለመከላከል እና የሕገ መንግሥት ጥሰት በተለይ ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ከመሆኑ አንፃር ሲታይ ግዜ የማይሰጠውና የአገር አለመረጋጋት፣ የሕዝብ ደህንነትና ሰላማዊ ኑሮና ህይወት ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የጸረ-ሽብር አዋጁ በግልጽ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ስለሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሠረት በሌላ ሕግ መሻር ወይም መሻሻል ባይደረግበትም (እንዲደረግ ሳይጠበቅ) ተግባራዊ ሊደረግና ተፈፃሚነት ሊኖረው አይችልም፡፡ የጸረ-ሽብር አዋጁ በአብዛሃኛው የያዛቸው ድንጋጌዎች ሕገ-መንግሥቱን የሚፃረሩ ቢሆንም እንደ ማሳያ የሚሆኑ ዋና ዋና ዎቹን በዚህ ጽሑፍ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡

3. የግል ህይወት የመከበርና የመጠበቅ እንዲሁም የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት የተጣሱበት ሁኔታ

        በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26(1) ላይ የማንኛውም ሰው የግል ሕይወት፣ ግላዊነ  የመከበር መብት ያለው መሆኑን የደነገገ ሲሆን  ይህ  መብቱ ደግሞ መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን የሚያካትት ነው፡፡ በተጨማሪም በንዑስ አንቀጽ (2) ላይ ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚጻጻፋቸው፣ በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች፣ እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች የተጠበቁለትና ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ጠያቂነት በነፃነት የመጠቀም መብት ያለው ሲሆን በምን ጉዳይ ላይ እና ከማን ጋር እንደሚገናኝና እንደሚፃፃፍ የትኛውም ግለሰብ ይሁን የመንግሥት አካል ወይም ሌላ ይመለከተኛል የሚል ቡድን / ድርጅት / ሊያውቅና ሊጠይቀው የማይችል መሆኑን እና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃና ከለላ ( ዋስትና ) የተደረገለት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህን ያስቀምጥ እንጂ የጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ 14 ላይ ለብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኤጄንሲ ከፍ/ቤት ፍቃድ በማውጣት በሽብርተኝነት ወንጀል ጠረጠርኩት የሚለውን ሰው የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬድዮ፣ የኢንተርኔት፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የፖስታና የመሳሰሉትን ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል እንዲሁም ጠለፋውን ለማስፈጸም ወደ ማናቸውም ቤት ውስጥ በሚስጥር ለመግባት፤ ወይም  ይህንኑ ለመፈጸም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማስቀመጥ ወይም ለማንሳት የሚያስችል ስልጣን ሰጥቶታል፡፡

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 26 አንድ ሰው በየትኛወም የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም የሚያደርጋቸው ግንኙነቶችና መልእክቶች የተጠበቀለት ሲሆን በአንቀት 29 ደግሞ እነዚህን የመገናኛ ዘዴ በመጠቀምም ይሁን በሌላ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ መንገድ የመሰለውንና ማንኛውንም አይነት መረጃ እና ሀሳብ የመያዝ፣ የመቀበል፣ የመሰብሰብ እና የማሰራጨት ነፃነቱ የተረጋገጠለት መብት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህ የመሰለውን የሀሳብና አመለካከት የመያዝና የመግለጽ ነፃነት መብት ያለገደብ የተሰጠና ማንም ጣልቃ በመግባት ይህን አመለካከት ያዝ አትያዝ ሊለው የማይችለው በነፃነት የማሰብ መብት ነው፡፡ እንዲሁም ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሲባል በጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀት 14 ላይ የተቀመጠውን በስውር ክትትልና ጠለፋ አይደረግበትም ማለትን ጪምር ነው፡፡

ሌላውና ከዚሁ ነጥብ ጋር መነሳት ያለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 (3) እና 29 (6) ላይ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸው ሁኔታዎች ሲሟሉ አጠቃቀማቸው ላይ ገደብ የሚያስቀምጡ ሕጎች ሊወጡ እንደሚችሉ ያስቀመጠውን ድንጋጌ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ነጥብ ማንሳት የፈለኩት የጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 14 ላይ ያስቀመጠው ድንጋጌ ከላይ የተቀመጡትን የሕገ-መንግሥቱን ንዑስ አንቀፆች በመከተል ነው እነዚህ ንዑስ አንቀፆች ደግሞ መብቶቹን ለመገደብ ሕግ ማውጣት እንደሚቻል ይደነግጋሉ የሚል ክርክር ሊነሳ ስለሚችል በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ንዑስ አንቀጽ 26(3) እና 29 (6) ላይ የተቀመጡት ገደቦች በጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ 14 ላይ ያስቀመጠውን ሁኔታ የሚያካትት አይደለም፡፡ በአንቀጽ 26(3) እና 29(6) በግልጽ ተቀምጦ እንደሚታየው መብቶቹ አጠቃቀም ላይ ሕግ በማውጣት ገደብ የሚጣለው አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ብሔራዊ ደህንነትን፣ የሕዝብ ሰላምን፣ ወንጀልን በመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብ የሞራል ሁኔታ በመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነፃነት በማስከበር ዓላማዎች ላይ በተመሰረቱ ዝርዝር ሕጎች፤ የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች ሲከሰቱ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት እነዚህ ገደቦች አጠቃቀሙ ላይ እና የአጠቃቀሙን ሁኔታ የሚገድቡ እንጂ በመንግሥት በስለላ መልክ ግለሰቦችና ቡድኖች ምን እየሰሩ ነው? በሚስጢር ከማን ጋር እየተገናኙ ነው ? እቅዳቸው ምንድን ነው ? የሚለውን የሚመለከተ ሳይሆን በግልጽ ግለሰቡ ወይም ቡድኑ የሚያደርቻውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የሚመጣ ገደብ ነው፡፡  ይህም የሚሆነው ችግሮች ከመከሰታቸው በፊትም ይሁን ከተከሰቱ በኋላ ግልጽ ሕግ በማውጣት ክልከላ / ገደብ / በማድረግ የሚፈጸም እንጂ የጸረ-ሽብር አዋጁ እንዳስቀመጠው አይነት በድብቅና በስውር የተለያየ ዘዴዎችን በመጠቀም ጠለፋንና መኖሪያ ቤት ውስጥ የመከታተያና መቅረጫ መሳሪያ በመቅበር አይደለም፡፡ 

 

4. የተያዙና የተከሰሱ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች የተጣሰበት ሁኔታ

 

  • ከክስና ከማስረጃ ማገኘትና ማወቅ ጋር የተያያዙ መብቶች የተጣሱበት ሁኔታ

አንድ ተከሳሽ /በፖሊስ የተያዘ ተጠርጣሪ/ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 20 መሠረት የተከሰሰበትን ክስ በቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገረውና በጽሑፍ የማገኘት መብት ያለው ሲሆን የቀረበበትን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከትና ምስክሮችን የመጠየቅ መብት ተሰጥቶታል፡፡ የጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ 32(1) ላይ ምስክሮች ስማቸውና አድራሻቸው እንዳይገለጽ የሚደነግግ ሲሆን ይህ ክልከላ በፍ/ቤቱ መዝገብ ላይም ይሁን በሚሰጣቸው ትእዛዞች ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ እንዳይገለጽ እስከማድረግ የሚደርስ ነው፡፡ በርግጥ በዚህ ነጥብ ላይ የፌደሬሽን ምክርቤት የሕገ-መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ተጠይቆ የምስክሮች ስምና አድራሻ እንዳይገለጽ መደረጉ ሕገ-መንግሥቱን አይጥስም በሚል ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ ነገር ግን ሕገ-መንግሥቱ ለተከሳሹ ክሱን በቂ በሆነ ዝርዝር በጽሑፍ እንዲደረሰው መደረግ እንዳለበት ሲደነግግ ክስ ማለት ወንጀሉን የሚዘረዝረው አቤቱታና ለክሱ ማስረጃ የሚሆኑ የማስረጃ ዝርዝርን ይጨምራል፡፡ የማስረጃ ዝርዝር ደግሞ የሰነድና የሰው ምስክሮች ሲሆን የምስክሮች ስምና አድራሻ ያለው መሆን አለበት፡፡ በሌላም በኩል ለተከሳሹ ማስረጃን የመመርመርና ምስክሮችን የመጠየቅ መብት የሰጠ ሲሆን ምርመራና መጠየቅ ደግሞ የምስክሩ ስም ማን እንደሆነ፣ ስራው ምን እንደሆነ፤ አድራሻው የት እንደሆነ፣ ወንጀሉ ሲፈጸም በቦታው ሊገኝ እንዴት እንደቻለ፣ በስራ ነው ወይስ በአጋጣሚ የሚሉት ጥያቄዎችን መጠየቅ ይችላል፡፡ ስማቸውን እና አድራሻቸውን እንዲሁም ስራቸውን ማወቅ የለብህም ማለት ሕገ-መንግሥቱን የሚፃረር ነው፡፡ ስማቸውን፤ አድራሻቸውንና ማንነታቸውን ማወቅ የሚጠቅመው ከወንጀሉ ጋር ምን ግንኙነት እንደላቸው፣ በግል ቂም የሚመሰክሩ ከሆነም ይህን ሁኔታ ለፍ/ቤቱ ለማስረዳት፣ የተባለው ወንጀል የተፈጸመበት ቦታ ሊገኙ የማይችሉም ከሆነ ሃሰተኛ መሆናቸውን ለማስረዳት የሚጠቅም ነው፡፡ ምስክሮች እንዳይለዩና እንዳይታወቁ መደረጉ ባልተሰራ ወንጀል ንጹሃንን ጥፋተኛ የሚያስብል ከመሆኑም በተጨማሪ ሃሰተኛ ምስክሮችን የሚያበረታታ ነው፡፡ በርግጥ አዋጁ የምስክሮች ማንነትና አድራሻ እንዳይገለጽ ያደረገበት ምክንያት የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅና ጥበቃ ለማድረግ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን የምስክሮች ደህንነት የሚጠበቀው ሌላውን መስዋእት በማድረግ መሆን የለበትም፡፡ ዜጎች ያለ ስጋትና ጥርጣሬ በአገራቸው የመኖርን ህልውና በሚያሳጣና እርስ በርስ አለመተማመን በሚፈጥር መልኩ እንዲሁም በሌላ ሰው ላይ ምስክር በመሆን ለሰጡት ምስክርነት ተጠያቂ እንዳይሆኑ ለመከላከል በሚያመች ሁኔታ ጥበቃ ማድረጉ አግባብነት የለውም፡፡ ጥበቃ ነው ከተባለም በዚህ አግባብ ሳይሆን በሌላ ሁኔታ ማድረግ ይቻላል ለምሳሌ ምስክሮቹንና ቤተሰባቸውን ተጠርጣሪው ሊያገኛቸው በማይችልበት ደህንነቱ በተረጋገጠለት ቦታ በማስቀመጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም እራሳቸውን የሚከላከሉበት መሳሪያ በመስጠት ካልሆነም ደግሞ ስጋቱ እስኪቀረፍ ድረስ በግልጽም ይሁን በስውር በመኖሪያ አካባያቸውና ቤታቸው እንዲሁም በስራ ቦታቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ማድረግም ለመንግሰት የሚከብድ አይደለም፡፡ 

  • የአካል ደህንነት የመጠበቅ መብት የተጣሰበት ሁኔታ

አንቀጽ19(5) ላይ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን አንቀጽ 16፣ 18 እና 21 ደግሞ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለውና ኢሰብዓዊ፣ ጭካኔ የተሞላበት፣ ክብርን የሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የተጠበቀና ድርጊቶቹም ክልክል መሆናቸውን የሚያስቀም ነው፡፡

ነገር ግን የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ከላይ በተገለጸው መልኩ የተያዙ ሰዎችን ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ቢያስቀምጥም የጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ 21 ላይ ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ በሚለው አርእስ ስር “ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረ ሰው የእጅ ጽሑፉን፣ የጣት አሻራውን፣ ፎቶ ግራፉን፣ የጸጉሩን፣ የድምጹን፣ የደሙን፣ የምራቁንና ሌሎች በሰውነቱ የሚገኙ ፈሳሽ ነገሮችን ናሙናዎች ለምርመራ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የህክና ምርመራ እንዲያደርግ ሊያዝ ይችላል ፡፡ ተጠርጣሪው ለምርመራው ፍቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል፡፡” በማለት ለፖሊስ ስልጣን ይሰጣል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ላይ ፖሊስ አስገድዶ ከተጠርጣሪው የሰውነት ክፍል ላይ ፈሳሽም ይሁን ሌላ ከሰውነቱ አካል ላይ ናሙና የመውሰድ መብት ተሰጥቶታል፡፡ ፖሊስ በማስገደድ ( ተመጣጣኝ እርምጃ የሚለው መመዘኛ የሌለው ከመሆኑም በላይ እርምጃው ተመጣጣኝ ነው አይደለም የሚለውን የሚያጣራው ማን እንደሆነና ተመጣጣኝ እርምጃ ካልሆነ በፖሊሱ ላይ የሚወሰደው እርምጃና የማስረጃውን ውጤት አይገልጽም፡፡ እንዲሁም ድንጋጌው ሕገ-መንግሥቱን እስከተፃረረ ድረስ ተመጣጣኝ መሆን አለመሆኑ ከግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡) የሚወስደው ናሙና በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 19 (5) መሠረት አስገድዶ የተገኘ ማስረጃ ስለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው የማይገባ መሆን ቢኖርበትም የጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ 23(1) “የመረጃውን ምንጪ ወይም መረጃው እንዴት እንደተገኘ…” መግለጽ የማይጠበቅበት መሆኑን በመደንገግ የፖሊስን ሃይል ተጠቅሞ ያገኘውን እና ሕገ-መንግሥቱን የሚቃን ማስረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝና ለፖሊስ ሕገ-ወጥ ድርጊት ከለላ ያደረገ ድንጋጌን አስቀምጧል፡፡

ፖሊስ ከተጠርጣሪው ላይ በማስገደድ ናሙና ሲወስድ አዋጁ ላይ እንደተቀመጠው ጸጉሩን ሊነቅል፣ ደሙን ሊወስድ፣ አፉን በማስከፈት ምራቁን ሊወስድ፣ ከሰውነቱ ፈሳሽ ሊወስድ እና የመሳሰሉትን ድርጊቶች መፈጸም እንደሚችል መብት የሰጠ ሲሆን ይህ ሁኔታ የሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 16፣18 እና 21 ላይ የተቀመጡትን የተያዙ ሰዎች ከኢሰብአዊ አያያዞች የመጠበቅና የአካል ደህንነቶችን መረጋገጥን መብት የሚጥሱ ናቸው፡፡

  • ከማስረጃ አግባብነትና ተአማኒነት አንፃር የተጣሰ መብት

የጸረ-ሽብር አዋጁ ካካተታቸው ነገሮች አንዱ ለሽብር ወንጀል ማስረጃ እንዴት እንደሚቀርብና እንዴት ማግኘት እንደሚቻል እንዲሁም ለሽብር ወንጀል በማስረጃነት ሊቀርቡ የሚችሉ የማስረጃ አይነቶችንና ያላቸውንም ተቀባይነት በተመለከተ አስቀምጧል፡፡ በዚህ የማስረጃ አግባብነትና ቅቡለነት ጋር በተያያዘ የተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች በሕገ-መንግሥቱ የተጠበቁላቸው ሰብአዊና ዲሞክሲያዊ መብቶች የተጣሱበትን ሁኔታና አግባብ ከታች እንደተመለከተው በሁለት ክፍል ለማሳየት ተሞክሯል፡፡

  • ማስረጃው የተገኘበት መንገድ አግባብነት

ለወንጀል ድርጊት አስረጂ ናቸው ተብለው የሚቀርቡ ማስረጃዎች ሁሉ ለተያዘው ጉዳይ አግባብነት አላቸው ማለት ተቀባይነት ወይም ተአማኒነት አላቸው ማለት አይደለም፡፡ አንድ ማስረጃ ለተያዘው ጉዳይ አግባብ ነው ወይም ነገሩን ማስረዳት ይችላል ማለት በፍ/ቤት ተቀባይነት አለው ማለት አይደለም፡፡ የቀረበው ማስረጃ ተጠርጣሪው የተጠረጠረበትን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ያስረዳ ቢሆንም እንኳን ማስረጃው የተገኘበት መንገድና ሁኔታ ሕግን ያልተከተለ ከሆነ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አንድ ማስረጃ በማስገደድ፣ በተንኮል፣ በማባበል፣ ተጠርጣሪው ላይ ዛቻና ማስፈራራት በማድረስ እንዲሁም ያልተገባ የተስፋ ቃል በመስጠት የመሳሰሉት የተጠርጣሪውን ሙሉ ነፃ ፍቃድ ሳይኖርበት የተገኘ ማስረጃ እውነትነት ቢኖረው እንኳን በሕግ እረገድ በማስረጃ ምዘና መርህ መሠረት ተቀባይነት የሌለውና ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡ ይህ የሆነት ምክንያት ንጹሃንን እራሳቸውን ከመወንጀል / self increamination /  ለመከላከል ሲባል ሲሆን አንድ ንጹህ ሰው ያለጥፋቱ ከሚቀጣ 100 ወንጀለኛ ቢያመልጥ ይቀላል የሚለውን መርህ መሠረት ያደረገ የማስረጃ ምዘና አተገባበር ነው፡፡ እንዲሁም በዜጎች ላይ በመንግሥት አካላት ማስረጃ ለማገኘት ሲባል የሚደርሰውን ሰብአዊ ጥሰቶችን ለመከላከልም ጪምር ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱም ይህን መርህ ሙሉ በሙሉ ግልጽ በሆነ ሁኔታ አካቶታል ለማለት ባያስደፍርም በአንቀጽ 19 (5) እና 20(3) ላይ የተያዙ ሰዎች የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም አንድን ማስረጃ እንዲያምኑ ወይም በራሳቸው ላይ ምስክርነት እንዲሰጡ የማይገደዱና በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ማስገደድ ሲባልም ከላይ የተገለጹ ሕጋዊ ያልሆኑና በነፃ ፍቃድ ተሰጥቷል የማያስብሉ ድርጊቶችን ማለት ነው፡፡ የጸረ-ሽብር አዋጁ ይህን የሕገ-መንግሥቱን አስገዳጅ ሁኔታ በመሻር በአንቀጽ 21 ላይ ፖሊስ ከተጠርጣሪ ላይ ናሙናዎችን ሃይልን በመጠቀም መውሰድ እንደሚችል መብት የሰጠ ሲሆን በአንቀጽ 23(1) ደግሞ በአንቀጽ 21 መሠረት የተገኘውን ናሙናም ይሁን ሌሎች በአዋጁ መሠረት የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ፖሊስ እንዴት እንዳገኘው መግለጽ የማይጠበቅበት መሆኑን በማስቀመጥ ሕግን ባልተከተለ መንገድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ፖሊስ ማስረጃውን እንዴትና በምን ሁኔታ እንዳገኘው ካልተጠየቀና ማስረጃውን ለማግኘት የተጠቀመበት ዘዴ ሕጋዊ ይሁን አይሁን ማስረጃውን በሚመዝነው አካል ተጣርቶ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ ማስረጃውን ውድቅ በማድረግና በፖሊስ አካሉ ላይ ተገቢውን ቅጣት ማስተላለፍ ካልተቻለ

  • የማስረጃው አይነት የሰሚ ሰሚ (Hearsay)

የጸረ የሽብር አዋጁ ተቀባይነት አላቸው ብሎ ያስቀመጣቸው ማስረጃዎችና የማስረጃ አይነቶች በአንቀጽ 23 ላይ የዘረዘራቸው ሲሆን በአንቀጹ የተዘረዘሩት ሌሎች የማስረጃ አይነቶች ከላይ ባለው ማብራሪያ የሚሸፈኑ በመሆናቸው የሰሚ ሰሚ ወይም በተዘዋዋሪ የተገኙ ማስረጃዎች አግባብነትን በተመለከተ በዚህ ክፍል ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ የሰሚ ሰሚ (hearsay) ማስረጃ ማለት ከቃሉ መረዳት እንደሚቻለው ከፍ/ቤት ወጪ ሌላ ሰው የተናገረውን የሰማ ሰው በፍ/ቤት ቀርቦ በመመስከር የሚሰጥ ማስረጃ ነው፡፡ የተናገረው ሰው አይቀርብም ሲናገር የሰማው ነው በችሎት የሚቀርበው፡፡ የተናገረው ሰው ስለሌለ ( ስለማይቀርብ ) ቃሉ እውነት ይሁን ውሸት ማረጋግጥ አይቻልም፡፡ ማስረጃውን የሚያቀርበውም ሰው ሌላው ሰው ሲናገር ሰምቻለሁ ከማለት ባለፈ እውነት ይሁን ሃሰት የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ ሶስት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው ዋናው ተናጋሪ መስቀለኛ ጥያቄ ስለማይቀርብለት ስለሆነ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የመጀመሪያው ተናጋሪ ሰው በሚናገርበት ሰአት  ቃለ መሃላ ስላልፈጸመ ወይም እንዲፈጽም ስላልተደረገ ነው፡፡ የመጨረሻውና ሶስተኛው ደግሞ እውነታውን የሚገነዘብበት ሁኔታ የተሳሳተ ሊሆን ስለሚችልና ሁለተኛው ሰውም የመስማት፣ የማስታወስ ሁኔታው እንደየ ሰው ስለሚለያይ የተባለውን በትክክል ላይገልጽ የሚችልበት እድል ሰፊ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ በልዩ ሁኔታዎች ማስረጃው ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል እነሱም ፡ በሞት ማጣጣር ላይ ያለ ሰው የሚናገረው፤ መደበኛና የተለመደ የስራ እንቅስቃሴ ላይ የሚደረጉ ንግግሮች እና አንድ ሰው የራሱን ጥቅም በሚቃረን ሁኔታ የገለጸው ሁኔታ እንዲሁም ስለአጠቃላይ መብት ወይም ባህል የተነገረ ቃል በሰሚ ሰሚ ማሰረጃ ተቀባይነት አላቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ባሉት ሁኔታዎች ተቀባይነት የለውም፡፡

የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ከላይ በተገለጸው መልኩና ሁኔታ የሚገለጽ ሲሆን ተቀባይነቱም በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር እንደ ማስረጃ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ነገር ግን የጸረ-ሽብር አዋጁ ያለ ልዩነት ሁሉንም የሰሚ ሰሚ ማስረጃዎች ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን አስቀምጧል፡፡ የተከሳሽ አንዱ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ ምስክሮቸሮችን መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ ነው፡፡ በሰሚ ሰሚ ማስረጃ ግን መጀመሪያ የተናገረውን ሰውየ መስቀለኛ ጥያቄ እንዲጠየቅና እንዲመልስ ማድረግ ስለማይቻል እንዲሁም በተናገረበት ሰአት ቃለ መሃላ የፈጸመ ባለመሆኑ እውነትነቱና ተአማኝነቱ የሚረጋገጥበትና የሚመረመርበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ ያለልዩነት የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው የጸረ-ሽብር አዋጁ መፍቀዱ ሕገ-መንግሥቱን የሚቃረንና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ነው፡፡

4. የመንግሥት አሰራርና ተጠያቂነት የተጣሰበት አግባብ

አንቀጽ 12(1) የመንግሥት አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ በማለት ማንኛውም የመንግሥት ስራ ለህዝብ በሚታይና በሚታወቅ ሁኔታ መከወን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ዓላማ መንግሥትና የመንግሥት አካላት ለሚሰሩት ስራ ለህዝቡ ተቀጠያቂነት ስላለባቸው ነው፡፡ መርጦ ያስቀመጣቸው ሕዝብ እስከሆነ ድረስ የሚሰሩት ስራ ህዝብን ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል፣ በድርጊታቸው ሕግ ከሚያዘው ውጪ የተጎዳ ወይም በተለየ የተጠቀመ አካል አለ የለም፣ በህዝብ ስልጣን ምን እየሰሩ እንደሆነ ማወቅ እንዲቻል እና ተጠያቂ ለማድረግ እንዲሁም ከጥፋትና ከጉዳት ለመከላከል ሲባል የወጣ ድንጋጌ ነው፡፡ የመንግሥት አሰራር የሚለው ህረግ ሲተረጎም ማንኛውም የመንግሥት አካል በተሰጠው ስልጣን የሚሰራውን ስራ ሲሆን ፖሊስን፣ ፍ/ቤት ወይም ሌሎች የፍትህ አካላትን ይጨምራል፡፡ ሕገ-መንግሥቱ የመንግሥት አሰራር ግልጽ እንዲሆን ያስቀመጠ ቢሆንም የሽብር ሕጉ አንቀጽ 14 በስወር ስለሚደረግ ክትትል የሚፈቅድ ሲሆን አንቀጽ 17 ላይ ደግሞ ፖሊስ የድብቅ ብርበራ ማድረግ እንደሚችልና ፍ/ቤትም ለዚህ ድርጊት ተባባሪ በመሆን ፍቃድ መስጠት እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ፖሊስ በሽብር ወንጀል ጠረጠርኩትን ያለውን ሰው፣ ማንኛውንም መኖሪያ ቤት፣ የስራ ቦታ ወይም ድርጅት ወይም የተከለለ ቦታ ሲበረብር ተጠርጣሪው አካል ወይም የንብረቱ ባለቤት ወይም ሌላ ሶስተኛ ወገን እንዲያውቅ አይደረግም፡፡ የማን እንደሆነና ማን እንዳስቀመጠው ሳይጠይቅና በተጠርጣሪው ወይም በንብረቱ ባለቤት ሳይረጋገጥ እንዲሁም ንብረቱ ሲበረበርና በፖሊስ ሲወሰድ እማኞች እንዲኖሩ ሳይደረግ ለሽብር ዓላማ የተቀመጠ ንብረት ነው በማለት በድብቅ እንዲበረበር ይደረጋል ተጠርጣሪውም የማያውቀውም ይሁን የሚያውቀው ንብረት በምን ምክንያትና እንዴት እንደተገኘ ሳያውቅ በፍ/ቤት ማስረጃ ሁኖ እንዲቀርብበት ይደረጋል፡፡

5. የፍ/ቤት ነፃነትና ከፍርድ በፊት እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት የተጣሰበት ሁኔታ

የሽብር አዋጁ አንቀጽ 21(1) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥት አቅራቢነት አንድን ድርጅት በሽብርተኝነት የመሰየም እና የሽብርተኝነት ስያሜን የመሻር ስልጣን ይኖረዋል (ለራሱ ስልጣን የሰጠ የመጀመሪያው አምባገነን ፓርላማ ሳይሆን አይቀርም)፡፡ ይህ ስልጣን መሆን የነበረበት የፍ/ቤት ነው ፡፡ አንድ ወንጀል ተፈጽሟል አልተፈጸመም የተፈጸመው በተጠርጣሪው ነው አይደለም ተጠርጣሪው ወንጀለኛ ነው አይደለም ( ሽብርተኛ ነው አይደለም ) በማለት መወሰን የዳኝነት ስልጣንን የሚመለከት ሲሆን ሽብርተኛ ነው አይደለም የሚል ክርክር የሚነሳበት በመሆኑ በፍርድ የሚያልቅ ጉዳይ ነው፡፡ በፍርድ የሚያልቅ ጉዳይ ደግሞ መቅረብ ያለበት ለፍርድ ቤት ወይም የመዳኘት ስልጣን ለተሰጠው አካል መሆን እንዳለበት ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 37 ላይ አስቀምጧል፡፡ በአንቀጽ 55 ላይ ማየት እንደሚቻለወ የህዝብተወካዮች ምክርቤት የዳኝነት ስልጣን ያልተሰጠውና የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ለፍ/ቤት መሆኑን ከአንቀጽ 50(7)፣ 78(1)፣ 79(1) መረዳት ይቻላል፡፡

አንድን ድርጅትም ይሁን ግለሰብ ጥፋተኛ የማለት ስልጣን ያለው ፍ/ቤት ነው፡፡ ፍ/ቤት ጥፋተኛ እስካላለ ድረስ በማንኛውም ሰአት ንጹህ ሆኖ መታሰብ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 20(3) ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ አንድን ድርጅት ለፈለገው ዓላማ ሊቋቋም ይችላል የተቋቋመበት ዓላማና የሚሰራው ስራ ሕግን የሚቃረንና ለአገሪቱና ለህዝቦቿ አደጋ የሚጥል ከሆነ ይህን ሁኔታ አጣርቶ ጥፋተኛ የማለት ስልጣን የፍ/ቤት ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፍ/ቤት ጥፋተኛ ( ሽብርተኛ) ከማለቱ በፊት ድርጅቱን በሽብርተኝነት መሰየሙ የድርጅቱን እንደጠፋተኛ ያለመቆጠር መብቱን የሚጥስ ተግባር ነው፡፡ ከዳኝነት ነፃነት አኳያም ቢታይ ምክር ቤቱ ሽብርተኛ ብሎ የሰየመውን ድርጅት ከድርጅቱ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ክርክሮች እንዲሁም ከድርጅቱ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ለሚከሰሱ ሰዎችን ጉዳይ በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ አይደሉም በሚል በነፃነትና በገለልተኝነት ይወስናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስልጣንና ተግባር የሚያስቀምጠው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 55 ላይ ድርጅትን ወንጀለኛ (ጥፋተኛ-ሽብርተኛ) ብሎ የሚሰይምበት ስልጣን ለም/ቤቱ አልተሰጠውም ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78(1)፣ 79(1)፣ 50(7) ላይ በግልጽ ተደንግጎ እንደሚታየው ነፃ የዳኝነት አካል የተቋቋመ መሆኑንና የዳኝነት ስልጣን የፍ/ቤት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ የጸረ-ሽብር አዋጁ ለተወካዮች ምክርቤት የሰጠው ስልጣን ሕገ-መንግሥቱን የሚቃረ ነው ፦ 1. የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እራሱ ባወጣው ሕግ ላይ የስልጣን ባለቤት የሆነ ሲሆን በሕገ-መንግሥቱ ያልተሰጠው ስልጣን ነው  2. የፍ/ቤት ስልጣንና ስራን ስለወሰደ የፍ/ቤት ነፃነትን ተጋፍቷል 3. ከፍርድ በፊት እንደጠፋተኛ ያለመቆጠር ሕገ መንግሥታዊ መብትን ጥሷል፤

ም/ቤቱ በሚዋቀርበት ሰአት አብዛኻኛው የም/ቤቱ አባል የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊና አባል የመሆናቸው እድል ሰፊ በመሆኑ ወይም አብዛሃኛውን የፓርላማውን ወንበር የያዘው ወይም አሸናፊው የፖለቲካ ድርጅት ተቃዋሚን ለማስወገድ እንደመሳሪያ ሊጠቀምበት ፡፡

6. የመደራጀትና የመምረጥና የመመረጥ መብት የተጣሰበት ሁኔታ

በሽብር አዋጁ አንቀጽ 21(1) የተጣሰው የሕገ-መንግሥት ድንጋጌ አንቀጽ 31 ላይ የተቀመጠው የመደራጀት መብት ሲሆን ማንኛውም ሰው ለፈለገው ዓላማ በማህበር መደራጀት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ የጸረ-ሽብር አዋጁ ደግሞ አንድን ድርጅት ሽብርተኛ በሚል የመሰየም ስልጣን ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሰጥቷል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ በሚል የፈረጀው ድርጅት ሕጋዊ ሰውነት ስለማይኖረው በዚህ ሽብርተኛ በተባለ ድርጅት አባል መሆንና መሳተፍ ያስጠይቃል ወንጀልም ተደርጎ ብዙ ንጹሃን ዜጎች ለእስርና ለእንግልት ከመዳረጋቸውም ባለፈ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውና ክብራቸው ተጥሷል፣ አካላቸው ጎሏል፣ ቅስማቸውም ተሰብሯል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ የተረጋገጠው የመደራጀት መብት የተጣሰ ሲሆን በርግጥ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ለሕገ ወጥ ዓላማ ሲባል መደራጀት የተከለከለ መሆኑን የሚያስቀምጥ ሲሆን የተደራጀበት ዓላማ ወይም ግብ ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው አይደለም ወይም ለሽብር ድርጊት ነው አይደለም ድርጊታቸውስ ሽብርተኝነት ነው አይደለም የሚለውን መወሰን ያለበትና መፍረስም ካለበት ማፍረስ የሚችለው ፍ/ቤት እንጂ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አይደለም፡፡

የጸረ-ሽብር አዋጁ ለም/ቤቱ ይህን በሽብርተኝነት የመሰየም ስልጣን በመስጠቱ ም/ቤቱ በሚዋቀርበት ሰአት አብዛኻኛው የም/ቤቱ አባል የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊና አባል የመሆናቸው እድል ሰፊ በመሆኑ ወይም የአስፈፃሚውን የመንግሥት ስልጣን የሚይዘው አብዛሃኛውን የፓርላማውን ወንበር የያዘው ወይም አሸናፊው የፖለቲካ ድርጅት በመሆኑ ይህ አካል የመንግሥት ስልጣን ከያዘ ተቃዋሚን የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ አመራሮችንና አባላቱን፣ መንግሥትን የሚተቹ ግለሰቦችንና የሰብአዊ ተሟጋቾችን ለማስወገድና ለማፈን የጸረ ሽብር አዋጁን እንደመሳሪያ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡

7. የጸረ-ሽብሩ አዋጅ በወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች የሚሸፈኑ ስለመሆናቸው

የጸረ-ሽብር አዋጁ ሽብርተኛንና የሽብርተኝነት ወንጀልን በተመለከተ የወንጀሉ አይነትና ምንነትን ከአንቀጽ 3 እስከ 12 ባሉት ድንጋጌዎች ያስቀመጠ ሲሆን እነዚህ ድንጋጌዎች ያሉት የወንጀል ድርጊቶችና አይነቶች በሙሉ በሚባል ደረጃ በ1996 ዓ.ም. በወጣው የወንጀል ሕግ ውስጥ ሽብርተኛ፣ አሸባሪ፣ ሽብርተኝነት ከሚለው ቃል ከመጠቀም ውጪ በስፋትና በዝርዝር የተካተቱ ናቸው ፡፡ በጸረ ሽብር አዋጁ እና በወንጀል ሕጉ ያሉት ድንጋጌዎች በመካከላቸው ያለው ልዩነት የሽብር ወንጀል በማለት በቃላት አጠቃቀማቸውና የቅጣት መጠናቸው የተለያየ መሆኑ ነው፡፡

የወንጀል ሕግ አንቀጽ ፡ 238- 242፣ 246-251፣ 254-270፣ 274፣ 276፣ 335፣ 422-424፣ 438፣ 440-445፣ 477-483፣ 485-488፣ 494(2)-497፣ 499-500፣ 503፣ 505-513 525፣ 585-587፣ 590፣ 595፣ 599 እና 682 በመሳሰሉት ድንጋጌዎች የጸረ-ሽብር  አዋጁ ከአንቀጽ 3 እስከ 12 ባሉት ያካተታቸውና የተሸፈኑ ናቸው፡፡

ስለዚህ የጸረ-ሽብሩ አዋጅ በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመግለጽና ለማብራራት እንደተሞከረው የሕገ-መንግሥቱን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥስ በመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሠረት ተፈፃሚነት የሌለው በመሆኑ መሻር ሳያስፈልገው ወድቅ ሊደረግ የሚገባውና ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችም ካሉ የወንጀል ሕጉ ባስቀመጣቸው ድንጋጌዎች መሠረት የሚዳኙ መሆን እንዳለባቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡

8. ማጠቃለያ

         ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በስራ ላይ ያለው የጸረ ሽብር አዋጁ የሕገ መንግሥቱን  አንቀጽ 12፣ 16፣ 18፣ 19፣ 20፣ 21፣ 26፣ 29፣ 31፣ 37፣ 50(7)፣ 55፣ 78(1) እና 79(1) የሚጥስ በመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሠረት ተፈፃሚነት የሌለውና ተግባራዊ ሊደረግ የማይገባው ሲሆን በአንቀጽ 13 መሠረት ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ፈፃሚው አካል እንዲሁም በተለይ ሕገ-መንግሥቱን ለመተርጎም ስልጣን የተሰጠው የፌደሬሽን ም/ቤት አንዱና ዋና ሃላፊነቱ የሆነውን የሚወጡ ሕጎችና ደንቦች ሕግ-መንግሥቱን የማይቃረኑ መሆን አለመሆናቸውን ማጣራትና የመከታተል ሃላፊነቱን የተወጣበት ሁኔታ አለመኖሩን ያሳየ አዋጅ ነው፡፡ የጸረ-ሽብር አዋጁ የአገሪቱ የሁሉም ሕግ በላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት በሚቃረን ሁኔታ እንዲወጣና እንዲተገበር ሲደረግ ሕግ አውጪው ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሕግ አውጪው የህዝብ ተወካይ ነው እስከተባለ ድረስ ሕግ ሲወጣ የህዝቡን ጥቅምና መብት የሚያስጠብቅ፣ የሕገ መንግሥቱንና አለማቀፍ ጥበቃ የተሰጣቸውን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በጠበቀ መሆኑን የማረጋገጥ ሃላፊነትና ግዴታ እንዲሁም ተጠያቂነት አለበት፡፡ እንደሚታወቀው በ2012 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ ይደረጋል የምንመርጣቸውና የምንወክላቸው ሰዎች ( ፓርቲ ) ምብትና ጥቅማችንን የሚያስከብር፣ የሥርዓቱን እድሜ ለማራዘምና ዜጎችን ለማፈን የሚወጡ ሕግና ደንቦችን እንዳይወጡ የሚታገሉና የሚከላከሉ፣ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በእኩልነት የሚታዩባት ሰላምና ፍትህ የሰፈነባት ሃገር ለመገንባት የሚያስችል በቂ እውቀትና ችሎታ ያላቸው መሆን እንዳለባቸው የጸረ-ሽብር አዋጁ በቂ ማሳያ ነው፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

Read 5863 times Last modified on Dec 16 2019
 Solomon Tesfaye Dejene

ጸሐፊው በፌዴራልና በአማራ ክልል በማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ናቸው፡፡