የወጣቶች የወንጀል ፍትሕ - ወፍ በረር እይታ

Oct 25 2019

 

 

1. መግቢያ

እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች በሕግ የተለየ ጥበቃ ይደርግላቸዋል። ይህ ጥበቃ በሕገመንግሥት፣ በቤተሰብ ሕግ፣ በውርስ ሕግ፣ በውል ሕግ፣ በወንጀል ሕግ፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ፣ በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ፣ በአለም ዓቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎችም በርካታ የይዘት ሕጎች ተደንግጎ የሚገኝ ነው። እነዚህ ሕጎች ከሞላ ጎደል የሚጋሩት ጉዳይ ከ18 ዓመት በታች ለሆኑት ሰዎች ይበልጥ በሚጠቅም መርህ የያዙ መሆናቸው ነው። በወንጀል የፍትሕ ሥርዓት ለወጣቶች (እንዲሁም ለሕፃናት) የሚደረገው ጥበቃ በወንጀል ሕጉ እና በሥነ-ሥርዓት ሕጉ የተዘረጋውን ሥርዓት የሚያጠቃልል ነው። የወንጀል ሕጉ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችን/ሕፃናትን በሦስት የእድሜ ክልሎች (ከ9 በታች፣ ከ9-15፣ ከ15-18) በመመደብ በተለይዩ የሕግ ማዕቀፎች እንዲገዙ አድርጓል። ወጣቶችን የሚመለከተው የሥነ-ሥርዓት ሂደት እንደዚሁ ከመደበኛው በይዘት የተለየ፣ ከሌሎች ታሳቢዎች የሚንደረደርና በሌሎች መርሆች የሚመራ ነው። ይህ ልዩነት ከሞላጎደል በሁሉም የሂደቱ ደረጃዎች የሚንፀባረቅ ነው። ስለሆነም ምርመራው፣ ክሱ፣ የመስማት ሂደቱና የማረም ሥርዓቱ የራሱ ገፅታዎች ያሉት ነው።

የወንጀል ፍትሕ ሂደት የሚመራው በዋናነት በወንጀል የሥነ-ሥርዓት  ሕግ  ነው። የሥነ-ሥርዓት ሕጉ የወንጀል ጉዳዮችን በማስመልከት ሦስት የተለያዩ ሀዲዶችን አስቀምጧል፤ አንድ መደበኛና ሁለት ልዩ ሥነ-ሥርዓቶችን። ሁለቱ ልዩ ሥነ-ሥርዓቶች የደንብ መተላለፍንና  (አንቀጽ 167-180)  የወጣቶችን ጉዳይ (አንቀጽ 171-180) የሚመለከቱ ሲሆን ሦስተኛው ከነዚህ ውጭ ያሉትን ሁሉንም የወንጀል ጉዳዮች የሚሸፍነው መደበኛው ሥነ-ሥርዓት ነው። እነዚህ ሦስት ሥርዓቶች የተለያየ መነሻ ያላቸው፣ በተለያዩ መርሆች የሚመሩ፣ በሂደት፣ ይዘትና ዓላማ የሚለያዩና ለተዋናዮች የተለያየ ሚና የሚሰጡ ናቸው። የእያንዳንዱ ሂደት ባህርይ ከሌሎቹ የተለየ በመሆኑ የሂደቶቹ መምታታት የሕጉን ዓላማ በማሳካት ረገድ አሉታዊ እንደምታ እንደሚኖረው የሚታመን ነው።

በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ልዩ ሂደት ከተበጀላቸው ጉዳዮች አንደኛው በወንጀል ጉዳይ ገብተው የተገኙ ወጣቶችን የሚመለከተው ነው (አንቀጽ 171—180)። ከዚህ በታች በዝርዝር እንደሚቀርበው በመደበኛውና በወጣቶች ጉዳይ መካከል ያለው ልዩነት በተሟጋችና (adversarial) በአጣሪ ሥርዓቶች (inquisitorial) መካከል ያለውን የአስተሳሰብና የአሠራር ልዩነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።  ሆኖም በተግባር ልዩነቱ ተድበስብሶ በአጣሪ አስተሳሰብ የተቃኘው የወጣቶች የወንጀል የፍትሕ ዓዋቂዎች በሚዳኙበት የተሟጋች ሥርዓት ተተክቷል። የወጣቶች ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘረጋው ማስረጃ የመሰብሰብ (gathering of evidence)፣ የማቅረብ (presentation)፣ ክስ የመስማት (trial) እና የማረም ሂደት (review of judgments) መና ቀርቷል። በወጣቶች ጉዳይ ዋናው ተዋናይ ፍርድቤት እንዲሆን ታስቦ የተዘረጋው ሥርዓት በፖሊስ ተዋናይነት ተተክቶ ሀዲዱን እንዲስት ተደርጓል። በአጠቃላይ ወጣቶችን በሚመለከት ያለው አሠራር ሕጉ ከሚለው አፈንግጧል። ይህ ሁኔታ በወጣቶቹ መብትና ጥቅም ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሕግ ያፈነገጠ አሠራር በመሆኑ የሕግ የበላይነትንም የሚፈታተን ነው። የወጣቶችን ጉዳይ በሚመለከት ገዥው መርህ የሕፃናትን ጥቅም ያስቀደመ (best interest of the child) አሠራር መከተል ነው።  የወጣቶችን ጥቅም ማስቀደምና ማስከበር የሚቻለው ዝርዝር ድንጋጌዎችን በማውጣት፣ አሰራሮችን በመዘርጋትና በማስፈፀም ነው። በሕጉ የተቀመጠው ሥርዓት መሻሻል ይኖርበታል አይኖርበትም በሚል ነጥብ የተለያዩ ሀሳቦች ሊቀርቡ እንደሚችሉ ይገመታል። ሆኖም ሥልጣን ባለው አካል ማሻሻያ እስኪደረግበት ድረስ ያለውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።

ይህ ጽሑፍ በሕጉና በአፈፃፀሙ መካከል ያለው ልዩነት በማሳየት ለመፍትሄው መጠነኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል በሚል እምነት የተዘጋጀ ነው። ልምዱ ከሕጉ የሚለየው በከፊል ሕግ ባስቀመጠው ስርዐት ላይ በቂ ግንዛቤ አለመፈጠሩ እንደሆነ ፀሀፊው ያምናል። ይህን ችግር ለመፍታት ያለው አማራጭ በጉይዩ ላይ መግባባት ሊፈጥሩ የሚችሉ የውይይት አጋጣሚዎችን መጠቀምና በሂደት የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በመሆኑም ይህ ጽሑፍ ለውይይትና ክርክር መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ያቀርባል። ዓላማውን ለማሳካትም በመደበኛውና ወጣቶችን በሚመለከተው የወንጀል የፍትሕ ሂደት መካከል ያለውን ልዩነት ለማመላከት ይጥራል። የጽሑፉ ዋና ትኩረት ወጣቶች በወንጀል ጉዳይ ገብተው ሲገኙ ተፈፃሚነት የሚኖረው የሥነ-ሥርዓት ሕግ ነው። የወንጀል ሕጉ በወጣቶች/ሕፃናት ጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት ያላቸው የይዘት ድንጋጌዎች የያዘ ቢሆንም ይህ ጽሑፍ እነሱን በተመለከተ እምብዛም የሚለው ነገር አይኖርም። የጽሑፉ ጭብጥ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ እንዲመች ከምርመራ እስከ እርምት ድረስ ባሉ ዋና ዋና ክንውኖች ላይ ትኩረት ይደረጋል።


2. ምርመራ

የወንጀል የፍትሕ ሥርዓት ዓላማ (የፍትሐ ብሔርም ጭምር) እውነት ላይ በመድረስ ትክክለኛ ፍርድ መሰጠት እንደሆነ ከሞላጎደል ሁለም ሥርዓቶች ይተማመኑበታል። ሆኖም እውነት እንዴት ይገኛል፣ ሊያገኘውስ የሚገባው ማን ነው፣ በምንስ መንገድ? በሚሉና በመሳሰሉ ነጥቦች ሰፊ ልዩነቶች ይታያሉ። እውነት የማግኘት አቅም የፍትሕ ተቋማት በግብዓትነት ከሚወስዱት መረጃ ብዛትና ጥራት ጋር ግኑኝነት አለው። ስለዚህ በወንጀል ጉዳዮች መረጃ የመሰብሰብ ሃላፊነት የማንነው፣ መረጃ የሚሰበሰበው በምን ዓይነት ሥርዓት ነው፣ ለዳኝነት አካላት የሚቀርበውስ እንዴት ነው፣ ድርሻቸውስ ምንድ ነው? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ የተለያዩ የአሰተሳሰብ፣ የአሠራር የአደረጃጀትና የአቋም አማራጮች ይታያሉ። የተሟጋች ሥርዓት የመረጡ አገሮች እውነት የሚነጥረው ተፃራሪ ጥቅም ያላቸው ተሟጋቾች (ከሳሽና ተከሳሽ) የየራሳቸውን ትርክት የሚያሳይ ማስረጃ ማሰባሰብና ማቅረብ ሲችሉ ነው የሚል አቋም ሲኖራቸው የአጣሪ ሥርዓት በሌላ በኩል እውነት የሚፈነጥቀው ማስረጃ የማቅረቡን ሂደት ባለጉዳዮቹ ሲቆጣጠሩት ሳይሆን ከነሱ ውጭ ገለልተኛ የሆነ ፍርድ ቤት በባለቤትነት ሲይዘው ነው የሚል አቋም ይይዛሉ። የኢትዮጵያ ሕግ መደበኛው የወንጀል ፍትሕ ሂደት በዋናነት የተሟጋች ሥርዓትን አስተሳሰብ በመከተል የምርመራ ሀላፊነት ለፖሊስ ሲሰጥ በወጣቶች ጉዳይ ግን ወደ ተሟጋች ሥርዓት በማዘንበል ምርመራ የፍርድ ቤት ተጨማሪ ሥራ እንዲሆን አድርጓል። ይህ ልዩነት ከምርመራ ሥርዓት ጀምሮ ባሉ ሂደቶች በግልፅ የሚታይ ነው። ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

 

. የክስ አጀማመር (setting justice in motion)

 

ወጣቶችን የሚመለከት የወንጀል ምርመራ በልዩ ሥርዓት የሚመራ ነው። እንደሚታወቀው በመደበኛ የወንጀል ጉዳዮች የፍትሕ ሂደት የሚጀምረው ማንም ሰው በሚያቀርበው ክስ ወይም አቤቱታ መነሻነት ነው (አንቀጽ 11) ። አቤቱታ ወይም ክስ ማቅረብ መብት ቢሆንም በፍትሐ ብሔር ሂደት እንደሚደረገው ክሱን ወይም አቤቱታውን ቀጥታ ለፍርድ ቤት ማቅረብ አይቻልም። ክስ ወይም አቤቱታ ማቅረብ የሚቻለው ለፖሊስ ነው። በመሆኑም የወንጀል የፍትሕ ሂደት የክስ አቀራረብ፣ ማስረጃ አሰባሰብና አቀርረብ ከፍትሐ ብሔሩ የተለየ ነው። በፍትሐ ብሔር የሙግት ሂደት ማስረጃ ማሰባሰብም ሆነ ለፍትሕ ተቋማት የማቅረብ ኃላፊነት በዋናነት የከሳሽና የተከሳሽ ነው። በመሆኑም ግለሰቦች (ከሳሽና ተከሳሽ) የራሳቸውን ጉዳይ የሚመለከት ማስረጃ የማሳባሰብ እንዲሁም ለፍርድ ቤት የማቅረብ የግል ኃላፊነት አለባቸው። የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ማስርጃ የማሰባሰቡም ሆነ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ ከግል ወደ መንግሥት ኃላፊነት በማዘዋወር ግለሰቦች ከዚህ ኃላፊነት ነፃ እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህ መሠረት ሕጉ በወንጀል ጉዳዮች ሪፖርት የማቅረብ መብት ለዜጎች ሲሰጥ ሪፖርቱን የመቀበል፣ የመመዘገብ እና የማጣራት ሥልጣንና ኃላፊነት የፖሊስ አካላት እንዲሆን አድርጓል። በመሆኑም የወንጀል ጉዳይ የሚጀምረው ለፖሊስ በሚቀርብ ክስ ወይም አቤቱታ መነሻነት ነው።  በቀረበው ጉዳይ ላይ ምርመራ የማካሄድ ሀላፊነት የፖሊስ በመሆኑ ሕጉ ይህን ሀላፊነቱን መወጣት የሚያስችል ተያያዥ የሕግ አቅም እንዲኖረው አድርጓል። ይህም መያዝን፣ መፈተሽን፣ ቃል እና የህክምና ማስረጃ እንዲሰጡ ማድረግን ያጠቃልላል። በዚህ ሂደት (በምርመራው ወቅት) ፍርድ ቤት ምርመራውን ከመቆጣጠር አልፎ ክሱን የመቀበልም ሆነ ማስረጃ የመሰብሰብ ሥልጣን የለውም። ፍርድ ቤቱ ሂደቱን የሚቆጣጠረው ተጠርጣሪው በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ፣ ለምርመራ ሲባል ፖሊስ ዘንድ በእስር የሚቆይበት ጊዜ፣ የመያዝና የብርበራ እንዲሁም ዋስትና ላይ ውሳኔ በመስጠት ነው። ከዚህ ውጭ በምርመራው ወቅት የፖሊስን ውስጣዊ አሠራር የመቆጣጠር ሥልጣን የለውም። ከዚህ የምንረዳው የወንጀል ስነስርአት ሕጋችን አደረጃጀት በተለያዩ የመንግሥት የፍትሕ አካላት መካከል የሥራ ክፍፍል በመፍጠር መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው። በዚህ ክፍፍል መሠረት ፖሊስ የሚቀርብለትን ሪርፖት መሠረት በማድረግ ምርመራ ያካሄዳል፣ ዓቃቤ ሕግ ማስርጃ መዝኖ ክስ ይመሰርታል፣ ፍርድ ቤት ግራቀኙን ሰምቶ ፍርድ እና ሌሎች አስፈላጊ ትእዛዞችን ይሰጣል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው አንድ ነጥብ ፖሊስ ምርመራውን በገለልተኝነት እንዲያከናውን የማይጠበቅበት መሆኑ ነው። ገለልተኝነት የሚጠበቀው በዋናነት ከዳኝነት ሲሆን በከፊል ደግሞ ከአቃቤ ሕግ ነው።

ወጣቶችን አስመልክቶ የተዘረጋው የወንጀል ፍትሕ ሂደት ከዚህ የተለየ ነው። ሂደቱ የሚመራው በሥራ ክፍፍል መርህ ሳይሆን ሀላፊነቱን ለፍርድ ቤት ጠቅልሎ በመስጠት ስሌት ነው። ይህን ሁኔታ ከሕጉ የተለያዩ ክፍሎች መገንዘብ ይቻላል። የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 16(1)

"ማናቸውም የወንጀል ክስ (ቁጥር 11) ወይም የክስ አቤቱታ (ቁጥር 13) ለፖሊስ ወይም ለዓቃቤ ሕግ ማቅረብ ይቻላል። አካለመጠን ባላደረሰ ወጣት ላይ የሚቀርብ ክስ ወይም የክስ አቤቱታ በቁጥር 172 መሠረት መቅረብ አለበት"

በማለት የመደበኛውና የወጣችቶ ጉዳይ በተለያየ ሥርዓት እንደሚጀምር ያሳያል። አንቀጽ 172 በሌላ በኩል ወጣት አጥፊዎች በወንጀል ገብተው ሲገኙ ጉዳዩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሳይሆን ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርብ መሆኑን ይደነግጋል። አንቀፁ

"አካለ መጠን ያላደረሰ ወጣት በወንጀል ነገር ውስጥ ገብቶ በተገኘ ጊዜ ፖሊሱ፣ ዐቃቤ ሕጉ፣ ወላጁ ወይም ሞግዚቱ በቅርብ ወደሚገኘው የወረዳ ፍርድ ቤት ወድውያኑ ይዞት ይቀርባል" 

በማለት ይደነግጋል። ከዚህ ድንጋጌ ይዘት በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው የወጣቶች ጉዳይ የሚጀምረው ክስን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ነው። በመደበኛው ሂደት ፖሊስ የሚቀርብለትን ክስ ወይም አቤቱታ ተቀብሎ ምርመራውን የመምራት ሥልጣን ሲኖረው በወጣቶች ጉዳይ ላይ ይህ ሥልጣን አልተሰጠውም፣ እንዲያውም ይህ ሥልጣን የተሰጠው ለፍርድ ቤቶች ነው። ስለዚህ ፖሊስ ገና ከጅምሩ የወጣቶችን ጉዳይ የሚስተናገድበት እድል የለም።  በአጠቃላይ ፖሊስ ወጣቶቹን ወድያውኑ ወድ ፍርድ ቤት ከመውሰድ ያለፈ ሥልጣን የለውም። ከዚህ ቀጥሎ እንደምንመለከተው ፖሊስ ክሱንም ሆነ አቤቱታውን ተቀብሎ የምርመራ መዝገብ የመክፈት ሥልጣን ስለሌለው በጉይዩ ላይ ማንኛውንም አይነት የምርመራ ሥራ ማከናወንም አይችልም። በመርህ ደረጃ ምርመራ የማከናወን አደራ የተሰጠው ለፖሊስ ተቋም ቢሆንም ሕጉ ወጣቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ይህ ኃላፊነት በፍርድ ቤት ቢከናወን ይበጃል የሚል አቋም የያዘ መሆኑን መገንዘብ አይከብድም። ይህን አቋሙን ወደ ተጨባጭ የሕግ ማዕቀፍ የቀየረው ደግሞ ወጣቶችን የሚመለከት የወንጀል ክስ ልክ እንደፍትሀብሄር ክስ ቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በማድረግ ነው። ይህ የክስ አጀማመር በቀጣይ የፖሊስ ስራዎችም ላይ ተፅእኖ አሳርፏል። ፍርድ ቤት በምርመራ ሂደት እንዲሳተፍ ማድረግ ተሟጋች የሙግት ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች የተለመደ ባይሆንም ፈረንሳይን በመሰሉ አጣሪ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች በመርህም ሆነ በተግባር ችግር የለበትም። አጣሪ ዳኛ (investigating magistrate) በመባል የሚታወቀው የፈረንሳይ የፍርድ ቤት አካል የዚህ አሠራር ማሳያ ነው።  ስለዚህ በወጣቶች ጉዳይ የወንጀል አቤቱታ በፍርድ ቤት እንዲጀመርና የፍርድ ቤት ሀላፊነት እንዲሆን ማድረጉ ስነስርአት ሕጉ ለአጣሪ አስተሳሰብ የቀረበ አሠራር መዘርጋቱን ያሳያል።

 

. ማስረጃ ማሰባሰብ (investigation)

 

ከላይ እንደተመለከትነው ወጣቶች በወንጀል ገብተው ሲገኙ ፖሊስ ክስ ወይም አቤቱታ ተቀብሎ የማስተናገድ ሥልጣን የለውም። ይህም ማለት ፖሊስ የምርመራ ሂደቱን በክስ ወይም በአቤቱታ መነሻነት መጀመር አይችልም ማለት ነው፡፡ ይህ የሕጉ አቋም ፖሊስ በሚያከናውናቸው የምርመራ ሥራዎች ላይ ያለው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው። የፖሊስ ምርመራ ሥራ አንድን ክስ ወይም አቤቱታ ተክትሎ የሚከናወን ተግባር ሲሆን በዋናነት ከተለያዩ ምንጮች ገለልተኛ ባልሆነ መንገድ (non-neutral fact gathering) ወንጀሉን እና ተጠርጣሪውን የሚመለከት ማስረጃ ማሰባሰብን ያካትታል። ፖሊስ ማስረጃ ለማሰባሰብ የተለያዩ ምንጮችን መጠቀም ይችላል። ዋነኞቹ የማስረጃ ምንጮች ከሳሽ ወይም አቤቱታ አቅራቢ (አንቀጽ 24) ፣ ተጠርጣሪው (አንቀጽ 25)፣ ብርበራና መያዝ (አንቀጽ 32) እንዲሁም የሀኪም ማስረጃ (አንቀጽ 34) ናቸው። ፖሊስ በመደበኛው ሂደት እነዚህን የማስረጃ ምንጮች አስፈላጊና ተገቢ መስሎ በታየው መጠን ሊጠቀምባቸው ይችላል። ስለዚህ የማስረጃ ምንጭ አመራረጥ በፖሊስ ፍቅድ ሥልጣን ሥር እንጂ በፍርድ ቤት የቁጥጥር ሥልጣን ውስጥ የሚወድቅ አይደለም።

 

ወጣቶችን በሚመለከቱ የወንጀል ጉዳዮች ሂደቱ የሚጀምረው በፍርድ ቤት በመሆኑ ከላይ ከተጠቀሱት ምንጮች ማስረጃ የማሰባሰብ የፖሊስ ፍቅድ ስልጣን የተገደበ ነው። በአንቀጽ 172(2) እንደተደነገገው

"አካለመጠን ያላደረሰውን ወጣት ያመጣው ሰው የወንጀሉንና የምስክሮችን ዝርዝር እንዲገልፅና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ የአቤቱታ ማመልከቻውን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ይጠይቀዋል። የሚሰጠውንም ቃል እና አቤቱታ በመዝገብ ይፅፋል። ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ምርመራ የሚፈፅምበት ሁኔታ የሚገልፅ መመሪያ ይሰጣል"

 

ይህ ድንጋጌ ሁለት መሰረታዊ መልእክቶችን የያዘ ነው። በአንድ በኩል ክሱን በሚመለከት ቀዳሚውን መረጃ ፍርድ ቤት እንደሚቀበል ያመለክታል። በዚህ መሠረት ከአቤቱታ አቅራቢ የሚመነጭ መረጃ ሁሉ የሚቀርበውም ሆነ የሚመዘገበው ፍርድ ቤት ዘንድ ነው። ይህ ድንጋጌ አቤቱታውን የመመዝገብ ሥልጣን የፍርድ ቤት እንዲሆን በማድረግ በተዘዋዋሪ ፖሊስ ተመሳሳይ መረጃ እንዳይቀበል ከልክሏል። በሁለተኛ ደረጃ ፖሊስ ምርመራ የሚያከናውነው ፍርድ ቤት ትእዛዝ ሲስጠው መሆኑን ያመለክታል። ይህም ፖሊስ ምርመራ በራሱ ተነሳሽነት ማከናወን እንደማይችል ያመለክታል። ከላይ እንደተጠቀሰው አንድን ወጣት ይዞ የመጣ ሰው ወንጀሉንም ሆነ ምስክሮችን የሚመለከት መረጃ እንዲሁም አቤቱታውን የሚያቀርበው ለፍርድ ቤት በመሆኑ ፖሊስ ቀጣይ የምርመራ ሂደት ማከናወን የሚችልበት መነሻ አይኖረውም። ከዚህም በላይ ግን ጉዳዩ ከፖሊስ እጅ ወጥቶ በፍርድ ቤት መዝገብ ተከፍቶለት ሂደቱ የተጀመረ በመሆኑ የምርመራው ሂደት የሚቀጥለው በፍርድ ቤቱ አመራር ሥር ነው። ስለዚህ ወጣቶች በወንጀል ጉዳይ ገብተው ሲገኙ ጉዳዩ የፖሊስ ምርመራ (police investigation) መሆኑ ይቀርና ዳኝነታዊ ምርመራ (judicial investigation) ይሆናል ማለት ነው። ፍርድ ቤቱ ከመደበኛ የfact finding ሥራው በተጨማሪ ማስረጃ የማሰባሰብ fact gathering ኃላፊነትም አለው። ፍርድ ቤቱ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራውን የሚጀምረው ወጣቱን ወደ ፍርድ ቤት ይዞ ከመጣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ወላጅ ወይም ሞግዚት ወንጀሉን ወይም ምስክሮቹን የሚመለክት መረጃ በመቀበል ነው። ፍርድ ቤቱ በዚህ መልክ ያሰባሰበው መረጃ በቂ ከሆነ ቀጣዩን ሂደት ያከናውናል። የተሰበሰበው ማስረጃ በቂ አይደለም ብሎ ካመነ ግን በራሱ መንገድ ወይም ፖሊስን በመጠቀም ተጨማሪ ማስረጃ ሊያሰባስብ ይችላል። በዚህ ደረጃ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚመራው ፍርድ ቤቱ ስለሆነ ማስረጃ የሚሰበሰብበትን ሥርዓት የሚወስነውም ፍርድ ቤቱ ነው። ፍርድ ቤቱ ምርመራውን እንዲያከናውን ፖሊስን የሚያዘው ከጉዳዩ ባህሪይ አንፃር የፖሊስ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ ነው። ስነስርአት ሕጉ በዚህ መልክ በወጣቶች ጉዳይ ገለልተኛ ያልሆነው የፖሊስ ምርመራ ገለልተኛ በሆነ የፍርድ ቤት ምርመራ እንዲተካ አድርጓል።

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው አንዱ ነጥብ በአንዳንድ ወንጀሎች ፍርድ ቤቱ ከአቤት ባይ የሚሰበስባቸው መረጃዎች ተጨርማሪ የፖሊስ ምርመራ የግድ የማይሉ መሆናቸው ነው። በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ የፖሊስ እገዛ አያስፈልገውም። የፖሊስ እገዛ በሚያስፈልግበት ወቅትም ቢሆን የምርመራውን ሂደት በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ መመሪያ መስጠት ይችላል። ቀደም ሲል እንደተገለፀው በመደበኛው ሂደት ፖሊስ የማስረጃ ምንጮችን ዓይነትና መጠን የመወሰን ሥልጣን ያለው ሲሆን ወጣቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ምንጮችን የሚመርጠው ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ትእዛዝና መመሪያ መነሻ በማድረግ ነው።

ሌላው ነጥብ አንዳንዶቹ የማስረጃ ምንጮት በወጣቶች ጉዳይ አግባብነት የማይኖራቸው መሆኑ ነው። ስለዚህ ፖሊስ በወጣቶች ጉዳይ ምርመራ እንዲያካሄድ የሚፈቅድለት ቢሆንም አንዳንዶቹን ዘይቤዎች በምርመራው ሂደት መጠቀም አይችልም። የዚህ አንዱ አብነት በሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 24 መሠረት ከአመልካቹ የሚገኘው ማስረጃ ነው። በወጣቶች ጉዳይ ወጣቱ ቀጥታ የሚቀርበው ፍርድ ቤት በመሆኑ ፖሊስ በወጣቱ ላይ የምርመራ መዝገብ አይከፍትም። በመሆኑም በአንቀጽ 24 መሠረት የአመልካቹን ቃል መቀበል የሚችልበት እድል የለም። የምርመራ መዝገብ ስለማይኖር ፖሊስ ከተጠርጣሪው ወጣት በሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 27 መሰረታ ቃል የመቀበል እድሉም ዝግ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ለፖሊስ ቃላቸውን እንዲሰጡ የማድረግ አሠራር የሕግ ድጋፍ የለውም። ወጣቱ የሚናገረው ነገር አለው ቢባል እንኳን ይህን ቃሉን ለፍርድ ቤት እንጂ ለፖሊስ የሚሰጥበት የሕግ ማዕቀፍ የለም። ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ወጣቶች ወንጀል ውስጥ ገብተው ሲገኙ የምርመራው ሥራ የሚከናወነው በፍርድ ቤት መሪነት መሆኑ ነው። ይህ አሠራር በአጣሪ ሥርዓቶች መርማሪ ዳኛ (investigating magistrate) በሚባል የፍርድ ቤት ተሿሚ ከሚከናወነው ማስረጃ የማሰባሰብ ሥርዓት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። ይህ አሠራር የሚተችበት የራሱ ገፅታ ቢኖረውም ሂደቱ የተሻለ የመረጃ መሠረት እንዲኖረው በማድረግ እውነት ለማግኝት የተሻለ እድል ይፈጥሯል ይባልለታል።

 

. መያዝና ማሰር (arrest and detention)

 

የወጣቶች የወንጀል ፍትሕ ሂደት ከመደበኛው የሚለይበት ሌላው ነጥብ የመያዝና አስሮ የማቆየት ሥልጣንን በተመለከተ ነው። እንደሚታወቀው ፖሊስ በአንድ ጉዳይ ላይ ምርመራ ከጀመረና በቂ ጥርጣሬ አለ ብሎ ካመነ እንደነገሩ ሁኔታ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ተጠርጣሪውን መያዝና ይዞ የማቆየት ሥልጣን አለው። ይህ ሥልጣን የግለሰቦችን የመንቀሳቀስና የአካል ነፃነት የሚገድብ በመሆኑ በሁሉም የሕግ ሥርዓቶች ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው። መያዝም ሆነ ማሰር የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቀነስ ፍርድ ቤቶች ሂደቱን እንዲቆጣጠሩት ማድረግ በስፋት ሥራ ላይ የሚውል ዘዴ ነው። በዚህ መሠረት እንደየሀገሩ ሥርዓት መያዝና ይዞ ማቆየት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፍርድ ቤት የተለያዩ የቁጥጥር ዘይቤችዎን ተግባራዊ ያደርጋል። እያንዳንዱ አገር እንደሚከተለው የሕግ ባህል ፍርድ ቤት የሚኖረው ሚና ጥብቅ ወይም ላላ ያለ ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ግን የፖሊስ የማሰር ሥልጣን የወንጀል የፍትሕ ሂደት አንዱ አካል ሆኖ መቀጠሉ አልቀረም። መያዝና ይዞ ማቆየት የምርመራ አንዱ ገፅታ ሆኖ የሚቀጥለው ፖሊስ የወንጀል ሪፖርት የመቀበል፣ የመመርመርና በጉዳዩ ላይ ማስረጃ የማሰባሰብ ኃላፊነት የተሰጠው የመጀመሪያው ረድፍ የመንግሥት አካል በመሆኑ ነው። ስለዚህ የፖሊስ የምርመራ ሥራ እና መያዝ (arrest) እንዲሁም ይዞ ማቆየት(detention) የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

 

ወጣቶችን አስመልክቶ የተዘረጋው ሥርዓት ፖሊስ በምርመራው ሂደት ያለውን ተሳትፎ ከመቀነሱ ባሻገር የማሰርም ሆነ ይዞ የማቆየትን ሥልጣን የሚነፍግ ነው። የሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 171 ወጣቶችን አስመልክቶ የሚከናወነው የወንጀል የፍትሕ ሂደት በዛው ክፍል በተዘዘርዘሩ መንገዶች ብቻ እንደሚከናወን ይደነግጋል። በዚህ ክፍል ውስጥ ፖሊስ የመያዝ ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ የትም ተደንግጎ አይገኝም። ይሉቅንም በወንጀል ገብቶ የተገኘ ሰው በወላጁ፣ በአሳዳጊው ወይም በዓቃቤ ሕግ ቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚገባ ተደንግጓል። አንድ ወጣት በዚህ መልክ ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ሲደረግና ሂደቱ ሲጀመር ፖሊስ ስለጉዳዩ መረጃ ላይኖረው ይችላል። በሌሎች ጉዳዮች ፖሊስ ስለወንጀል መረጃ የሚያገኘው ዜጎች በሚያቀርቡት ክስ ወይም አቤቱታ መነሻነት ነው። በወጣቶች ጉዳይ ጉዳዩ የሚጀምረው በፍርድ ቤት ስለሆነና ፖሊስ በጉዳዩ ላይ እንዲሳተፍ የሚያስገድድ የሕግ ድንጋጌ ስለሌለ ምርመራ የማከናወን ሥልጣኑም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ፖሊስ በወንጀል ጉዳይ ውስጥ የገባ ወጣት መኖሩን መረጃ ሲያገኝ ወይም በራሱ መንገድ ሲደርስበት ማድረግ የሚችለው ወጣቱን ወድያውኑ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ ብቻ ነው። ይህ ሥልጣን ደግሞ ውላጅም ሊያደርግ የሚችለው ነገር ነው። ጉይዩ ፍርድ ቤት ከደረሰ በኋላ ያለው ነገር ሁሉ የፍርድ ቤት ኃላፊነት ነው።

 

ከላይ እንደተጠቀሰው መያዝም ሆነ ይዞ ማቆየት ፖሊስ ከምርመራ ጋር አያይዞ የሚያከናውናቸው ስራዎች ናቸው። የምርመራ ሥልጣን በሌለበት አውድ የመያዝ ሥልጣን ብቻውን ተንጠልጥሎ ሊቀር አይችልም። ስለሆነም ፖሊስ በወጣቶች ጉዳይ የመመርመር ሥልጣን ሲነፈግ የመያዝም ሆነ ይዞ የማቆየት ሥልጣኑ አብሮ እንደተነፈገ መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው መያዝም ሆነ ይዞ ማቆየት ሥልጣን ነው። ሥልጣን ሥራ ላይ ሊውል የሚችለው ደግሞ በሕግ በግልፅ የተሰጠ እንደሆነ ብቻ ነው። ከላይ በዝርዝር እንደተገለፀው በወጣቶች ጉዳይ ላይ ፖሊስ የመያዝ ሥልጣን ያለው መሆኑን የሚደነግግ አንቀጽ የለም። ለመደበኛው ሂደት የተዘረጋውና መያዝና ማቆየትን የሚመለከተው ሥልጣን በወጣቶች ጉዳይ ተፈፃሚነት እንደሌለው ሕጉ በግልፅ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው (አንቀጽ 22)። የነዚህ ድምር ውጤት ፖሊስ ማንንም ወጣት መያዝም ሆነ ይዞ ማቆየት ሥልጣን እንደሌለው የሚያስገነዝብ ነው።

 

በመደበኛ ጉዳዮች አንድ ተጠርጣሪ ፖሊዝ ዘንድ እንዲቆይ የሚደረገው ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ስለሚያስፈልገው ወይም ጉዳዩ ዋስትና ስለሚያስከለክል ነው። በወጣቶች ጉዳይ ቀጠሮ መስጠት አስፈላጊ ሲሆን ወጣቱ የሚቆየው ከወላጆቹ፣ ሞግዚቱ ወይም ከዘመዶቹ ጋር ነው። ስለዚህ ቀጠሮ ቢኖር እንኳን ወጣቱ ወደ ፖሊስ የሚመለስበት የሕግ አሠራር የለም። ወላጅ፣ አሳዳጊ ወይም ሞግዚት የሌለ ከሆነ ወጣቱ አሳዳጊ ተቋም ውስጥ ወይም ሌላ እምነት የሚጣልበት ሰው ዘንድ እንዲቆይ ይደረጋል (አንቀጽ 172(4) እንጂ ፖሊስ ይዞ እንዲያቆየው አይደረግም። ከዚህ የምንገነዘበው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የመቆየቱ እድል ዝግ ስለሆነ የዋስትና ሥርዓት በወጣቶች ጉዳይ ላይ ምንም ትርጉም የሌለው መሆኑ ነው። አንድ ወጣት በየትኛውም የወንጀል አይነት ይጠርጠር ዋስትና ሊነፈግ የሚችልበት የሕግ አንቀጽ የለም። ይህ ሁኔታ ሕጉ በምርመራው ሂደት የወጣቶችን መብትና ጥቅም ለመጠበቅ የሄደበትን ርቀት የሚያመለክት ነው።

 

ጠቅለል ብሎ ሲታይ ፖሊስ በወጣቶች የወንጀል የፍትሕ ሂደት ያለው ሚና ዝቅተኛ ነው። ፖሊስ በምርመራ ሂደት ተሳትፎ ማድረግ አለማድረጉ የሚወሰነው በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ብቻ ነው። የምርመራውን ሂደት ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው ፍርድ ቤት በመሆኑ ፖሊስ በሌሎች ጉዳዮች የሚኖረው ሥልጣንና የሚጠቀምባቸው የምርመራ ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግ አይችልም። በዚህ ምክንያት በመደበኛው ሥርዓት አግባብነት ያላቸው መያዝ፣ ማቆየት፣ ብርበራ፣ ዋስትና ወዘተ የመሳሰሉ የሕግ ፅንሰሀሳቦች በወጣቶች ጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት የላቸውም። ፖሊስ አንድን ወጣት ለ48 ሰዓታትም ቢሆን ማቆየት አይችልም። ስለዚህ በዚህ ረገድ በስፋት ሲሰራበት የሚታየው አሠራር የሕግ ድጋፍ ያለው አይደለም።

 

 3. ክስ ማቅረብ (charges)

 

በወንጀል ፍትሕ ሂደት ምርመራ የፖሊስ ሥልጣን የሆነውን ያህል ክስ ማቅረብ ደግሞ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣን ነው። ከሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 108 መገንዘብ እንደሚቻለው የክስ ቻርጅ ካልቀረበ በስተቀር ማንኛውም ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ ሊሰማ አይችልም። ስለዚህ የወንጀል የመስማት ሂደት በመጀመር ረገድ ዓቃቤ ሕግ ወሳኝ ድርሻ አለው። ዓቃቤ ሕግ ይህን ኃላፊነቱን የሚወጣው የክስ ቻርጅ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ነው። ይህ የክስ ቻርጅ ዓቃቤ ሕግ ተፈፅሟል ብሎ የሚያምነውን ድርጊት እንዲሁም የተከሰሰው ሰው በዚህ ሂደት ያለው ድርሻ ምን እንደሆነ የሚያሳውቅበት ሰነድ ነው። ዝርዝር ይዘታቸው ልዩነት ቢኖረውም የክስ ቻርጅ በወንጀል ሂደት ያለው ሚና የክስ ማመልከቻ በፍትሃብሄር ሂደት ካለው ድርሻ ጋር ይመሳሰላል። የክስ ማማልከቻ ወይም የክስ ቻርጅ ከሌለ ፍርድ ቤት በራሱ ተነሳሽነት ማንኛውንም ጉዳይ ሊያይ አይችልም።

 

ሆኖም ከሕጉ ይዘት መገንዘብ እንደሚቻለው የክስ ቻርጅ የሚያስፈልገው በመደበኛ ጉዳዮች ብቻ ነው። አንቀጽ 108 "አካለመጠን ባላደረሱ ወጣቶች ላይ የሚቀርብ ክስ በዚህ ሕግ በቁጥር 172 መሠረት ሌላ ትእዛዝ ካልተሰጠ በቀር በዚህ ምእራፍ መሠረት አይፈፀምም" ብሎ በመደንገግ የክስ ማመልከቻን የሚመለከተው ምዕራፍ በወጣቶች ጉዳይ ላይ አግባብነት እንደሌለው በግልፅ አስቀምጧል። ስለዚህ የክስ ቻርጅ ከሌለ ጉዳይ የለም የሚለው አባባል በነዚህ ወንጀሎች አይሰራም። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ የክስ ቻርጅ ከሌለ ወጣቶችን የሚመለከተው የወንጀል ፍትሕ ሂደት እንዴት ይጀመራል? የሚለው ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ወጣቶችን አስመልክቶ የተዘረጋው ሥርዓት መሰረታዊ ባህሪይ ማጤን ያስፈልግል።

 

ከላይ እንደተገለፀው የወጣቶች ጉዳይ የሚጀምረው ለፍርድ ቤት በሚቀርብ ማመልከቻ በመሆኑ ፖሊስ የሚያከናውነው ምርመራ አይኖርም። ምርመራ እንዲያከናውን ሲታዘዝ የምርመራውን ውጤት የሚያቀርበው ለፍርድ ቤት እንጂ ለዓቃቤ ሕግ አይደለም። ስለዚህ ወጣቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዓቃቤ ሕግ ከፖሊስ የሚቀበለው የምርመራ ሪፖርት አይኖረውም። ከፖሊስ የተቀበለው የምርመራ ውጤት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ማስረጃ መዝኖ ለዳኝነት አካሉ የክስ ቻርጅ ሊያቀርብ አይችልም። በሌላ በኩል በሞት ወይም ከ10 ዓመት በላይ ፅኑ እስራት በሚያስቀጡ ወንጀሎች የክስ ቻርጅ እንደሚያስፈልግ ተደንግጓል። በወጣቶች ጉዳይ የክስ ቻርጅን በሚመለከት ሁለት ዓበይት ነጥቦችን መረዳት ተገቢ ነው።

 

አንደኛው የወጣቶችን ጉዳይ ፍርድ ቤት የሚሰማው የዓቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ሳይቀርብለት መሆኑ ነው። ወጣቶችን በሚመለከት ከተቀረፀው ሥርዓት መገንዘብ እንደሚቻለው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመስማት መነሻ ሆኖ የሚያገለግል የጽሑፍ ማመልከቻ አይቀርብለትም። ፍርድ ቤት መዝገቡን የሚያደራጀው ወጣቱን ይዘው ከመጡት ሰዎች የሚያገኘውን የቃልና ሌላ ዝርዝር መረጃ በመመዝገብ ነው። ስለዚህ በወጣቶች ጉዳይ ክስ ማቅረብ በዋናነት በቃል የሚከናወን ተግባር ነው። ፍርድ ቤቱ በዚህ መንገድ የሚያገኘው መረጃ የፍርድ ሂደቱን ለመቀጠል በቂ መሆኑን ካመነበት ዋናው የመስማት ሂደት ወዲያው ይቀጥላል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ምርመራውን ከፍርድ ሂደቱ የሚለይ የዓቃቤ ሕግ የክስ የማቅረብ ክንውን የሌለ መሆኑ ነው። ፍርድ ቤቱ የመስማት ሂደቱን የሚያከናውነው በዋናነት ቀደም ሲል በምርመራው ሂደት ያሰባሰበውን መረጃ መሠረት በማድረግ ነው። ይህም የሚያሳየው በወጣቶች ጉዳይ የቅድመ መስማት (pretrial) ስርዓቱና የመስማት ሂደቱ (trial) ብዙም የማይለይ መሆኑ ነው። በመደበኛው ሂደት ሁለቱም ራሳቸውን ችለው የሚከናወኑ የተለያዩ ደረጃዎች ናቸው።

 

በወጣቶች ጉዳይ የመስማት ሂደት የምርመራ ተቀፅላ ነው። ምርመራው በፍርድ ቤት መሪነት የሚከናወን በመሆኑ በዚህ ሂደት የተገኘ መረጃ ሁሉ ፍርድ ቤት የሚያውቀው ነው። ስለዚህ በመደበኛው ሂደት እንደሚታየው የመረጃ መንጠባጠብ የፍርድ ሂደቱን ሊያውክ አይችልም። ዓቃቤ ሕግ በመደበኛው ሂደት ክስ ሲመሰርት ከፖሊስ ያገኘውን መረጃ በሙሉ ለፍርድ ቤት አያቀርብም፤ የሚያቀርበው ወንጀሉ መፈፀሙን ያሳዩልኛል የሚላቸውን ፍሬ ነገሮችና ማስረጃዎችን ነው። በመሆኑም ወጣቶችን የሚመለከተው ሂደት በርከት ያለ ማስረጃ (ተጠርጣሪውን የሚጎዳም የሚጠቅምም) ለፍርድ ቤት የሚቀርብበት በመሆኑ እውነት ላይ ለመድረስ የተሻለ እድል የሚፈጥር ነው። ሰፋ ያለ የፍሬ ነገር መሠረት ይዞ የሚነሳ በመሆኑም የወጣቱን ሁለንተናዊ ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ውሳኔ ለመስጠት የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

 

ሁለተኛው ነጥብ ዓቃቤ ሕግ ክስ በሚያቀርብባቸው ጥቂት ጉዳዮችም ቢሆን የማስረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው የፍርድ ቤቱ መዝገብ መሆኑ ነው። ከአንቀጽ 172(3) መገንዘብ እንደሚቻለው ዓቃቤ ሕግ ከ10 ዓመት በላይ ፅኑ እስራት ወይም በሞት በሚያስቀጡ ወንጀሎች ክስ ማቅረብ የሚችለው "የክስ ማመልከቻውን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ" ሲሰጠው ነው። ተደጋግሞ እንደተገለፀው በወጣቶች ጉዳይ የምርመራ ሥራ በዋናነት በፍርድ ቤት ኃላፊነት ሥር የሚከናወን ነው። ስለዚህ ወጣቱ በነዚህ ወንጀሎች የገባ መሆኑ የሚታወቀው በዚህ ሂደት ነው። ፍርድ ቤት ለዓቃቤ ሕግ ትዕዛዝ የሚሰጠውም ራሱ ያከናወነውን የምርመራ ግኝት መሠረት በማድረግ ነው። ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ የክስ ቻርጅ የሚያዘጋጀው በፍርድ ቤት መዝገብ ከተገኘው መረጃ ተነስቶ ነው። ስለዚህ ዓቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ በሚያቀርብባቸው ጥቂት ጉዳዮችም ቢሆን የፍርድ ቤት ድርሻ የጎላ ነው።

 

 4. የመስማት ሂደት (Trial)

 

በወጣቶችና በመደበኛው ሂደቶች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ክስ በመስማቱ (trial) ሂደት ነው። መደበኛው የክስ መስማት ሂደት የተሟጋች ሥርዓት ባህሪያት የተላበሰ ሲሆን የወጣቶች የመስማት ሂደት ግን በአጣሪ ሥርዓት ባህሪያት የተቃኘ ነው። መደበኛው ሂደት ዋናውን ኃላፊነት ለከሳሽና ተከሳሽ በሚሰጥ መርህ (principle of party autonomy) የሚመራ በመሆኑ ፍርድ ቤት በመስማት ሂደት ያለው ድርሻ ውሱን ነው።  በወጣቶች ጉዳይ ግን የመስማት ሂደት ልክ እንደምርመራው ሂደት ሁሉ በፍርድ ቤት ዋና ተዋናይነት የሚከናወን ነው። በወጣቶች ጉዳይ የሚኖረው የክስ መስማት ሂደት የራሱ በርካታ ባህሪያት ያሉት ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ቀጥሎ ባሉት ጥቅል ሀሳቦች ሊጠቃለሉ የሚችሉ ነው።

 

ሀ. ችሎት

 

የመስማት ሂደት ፍርድ ሰጭና ተሟጋቾች ፊት ለፊት በተገናኙበት መድረክ (immediacy) ባለጉይዮች ማስረጃና ሙግት በቃል (orality) የሚያቀርቡበት ሂደት ነው። በመደበኛው ሂደት የችሎት አደረጃጀትም ሆነ አሠራር በነዚህ ሁለት መገለጫዎች የተቃኘ ነው። መደበኛው የወንጀል ሂደት ጥቂት የጽሑፍና በርከት ያሉ የቃል ክንውኖችን የሚያጠቃልል ነው። ክሱ በጽሑፍ የሚቀርብ ሲሆን ፍርድና ትእዛዝም የሚሰጠው እንዲሁ በጽሑፍ ነው። በክስና በፍርድ መካከል ያለው አብዛኛው ክንውን (ክስ ማንበብ፣ እምነት ክህደት፣ መቃወሚያ፣ መክፈቻ ንግግር፣ ምስክር መስማት፣ መዝጊያ ንግግር ወዘተ) የሚፈፀመው ግን በቃል ነው። አብዛኛው ሂደት በቃል የሚከናወን በመሆኑ በሙግት አቅራቢዎችና በፍርድ ሰጭዎች መካከል ያለው ግኑኝነት በዚህ የተቃኘ መሆኑ ግድ ነው። አሁን ከያዝነው ጉዳይ ጋር አግባብነት ያላቸው ሁለት የመደበኛው የወንጀል ፍትሕ ሂደት ባህሪያት የተከሰሰው ሰው በአካል ችሎት ውስጥ ዳኛው ፊት መገኘት ግዴታ መሆኑ እና ጉዳዩ የሚታየው በግልፅ ችሎት[1] መሆኑ ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ እንደሚታየው እነዚህ ሁለት ባህሪያት በወጣቶች ጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት የላቸውም።

 

ወጣቶች የገቡበት የወንጀል ጉዳይ እንደሌላው ጉዳይ በግልፅ ችሎት የሚታይ አይደለም። በሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 176(1) እንደተደነገገው 

"አካለመጠን ያላደረሰው ወጣት ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ ነገሩ በሙሉ የሚሰማው በዝግ ችሎት ውስጥ ነው፤ ነገሩ በሚሰማበት ጊዜ ከምስክሮች፣ በምስክርነት ቃላቸውን ከሚሰጡት ከልዩ አዋቂዎችና ከወላጆች ወይ ከሞግዚት ወይም ከበጎ አድራጎት ድርጅት አባሎች በቀር ማንም ሰው ሊገኝ አይችልም፤ ማንኛውም ነገር በከፍተኛው ፍርድ ቤት በሚሰማበት ጊዜ ዓቃቤ ሕጉ መገኘት አለበት"።

 

ከዚሁ ድንጋጌ  የወጣቶችን ጉዳይ ለሕዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት ማስተናገድ እንደማይቻል ግልፅ ነው። ይህ ሁኔታ የወንጀል ጉዳይ በግልፅ ችሎት ይከናወናል የሚለው መርህ ተቃራኒ ቢሆንም የወጣቶችን ልዩ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ተቀባይነት ያገኘ አሠራር ነው። ሆኖም ድንጋጌው ጉዳዩ በዝግ ችሎት እንዲከናወን በማዘዝ አላበቃም። ይልቁንም ችሎት ውስጥ ሊገኙ የሚችሉትን አካላት ዝርዝርም አስቀምጧል። በመስማቱ ሂደት እንዲገኙ ከተፈቀደላቸው አካላት ዝርዝር ውስጥ የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ ስም አለመጠቀሱ ሳይታሰብበት የሆነ ነገር አይደለም። ከላይ እንደተገለፀው ዓቃቤ ሕግ ክስ የሚያቀርበው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚቀርቡና አስር ዓመትና ከዚያ በላይ በሚያስቀጡ ወንጀሎች ነው። እነዚህ ወንጀሎች በአብዛኛው የሚታዩት በከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ እንዲርኖ የተፈቀደለት በዚሁ ፍርድ ቤት ብቻ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር በሚወድቁና ከአስር ዓመት በታች በሚያስቀጡ ቅጣቶች የመስማት ሂደቱ የሚከናወነው ዓቃቤ ሕግ ክስ ሳያቀርብ በመሆኑ የዓቃቤ ሕግ በችሎቱ መገኘት አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም። ኋላ በዝርዝር እንደሚታየው በወጣቶች ጉዳይ ላይ ዓቃቤ ሕግ ምስክር መጥራትም ሆነ ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ እንዲያቀርብ አይፈቀድለትም። ስለዚህ በአብዛኞቹ የወንጀል ጉዳዮች የዓቃቤ ሕግ በችሎት መገኘት አስፈላጊ ካለመሆኑም በላይ በሕግም የተፈቀደ አይደለም።

 

የፖሊስም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ተደጋግሞ እንደተገለፀው የወጣቶች ጉዳይ ገለልተኛ ባልሆነ ፖሊስ ምርመራ እንዲከናወንበት ሕጉ አይፈቅድም። ምርመራው የሚከናወነው ገለልተኛ በሆነው በዳኝነት ተቋም ነው። ከዚህ አንፃር ሲመዘን ፖሊስ በችሎት እንዲገኙ ከተፈቀደላቸው አንዱ አለመሆኑ የሚደንቅ አይደለም። የፖሊስ መገኘት የሂደቱን መደበኛ ያልሆነ (informal) ባህሪይ የሚያውክ ከመሆኑም ባሻገር የሚያቀርበው የራሱ ግብአትም ስለሌለው በሂደቱ እንዳይገኝ መደረጉ ተገቢ ነው። አልፎ አልፎ የምርመራ ሥራ እንዲያከናውን በፍርድ ቤት የታዘዘ ቢሆን እንኳን የምርመራውን ውጤት ለፍርድ ቤቱ በሬጂስትራር በኩል ከሚያቀርብ በስተቀር በመስማቱ ሂደት ችሎት ውስጥ እንዲገኝ አያደርገውም። በሆነ ምክንያት ሂደቱ ውስጥ በአካል ይገኝ ቢባልም በሂደቱ ላይ የሚጨምረው እሴት የለም፤ የሚያቀርበው ማስረጃ የለም፣ የሚጠይቀው ምስክር የለም፣ የሚሰጠው አስተያየትም የለም። ፖሊስም ሆነ ዓቃቤ ሕግ ችሎት ውስጥ እንዲገኙ ሊፈቀድላቸው የሚችለው በጉዳዩ ላይ የምስክርነት ቃል የሚሰጡ ከሆነ ብቻ ነው።

 

ጉይዮችን በዝግ ችሎት ማስኬድ በወጣቶች ጉዳይ ላይ ብቻ የሚታይ አይደለም። በመደበኛ ጉዳዮች ዝግ ችሎት ተፈፃሚ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ሆኖም የችሎቱ ዝግ መሆን የተሳታፊዎችን ቁጥር ከሚቀነስ በቀር የችሎቱን መሰረታዊ ገፅታ አይቀይርም። የችሎቱ አደረጃጀት፣ ሂደት፣ ሥነ-ሥርዓት ወዘተ ከመደበኛው የተለየ አይሆንም። በመሆኑም ሂደቱ ዝግም ቢሆን ክንውኑ የሚፈፀመው ችሎት ውስጥ ነው። በወጣቶች ጉዳይ ግን የመስማቱ ሂደት ዝግ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዳኞች ፅህፈት ቤት (judges chambers) መደበኛ ባልሆነ ሥርዓት (‘informal manner’) የሚከናወን መሆኑ ተጨማሪ ገፅታው ነው። ሕጉ የወጣቶች ጉዳይ የሚሰማበት ቦታም ሆነ ሥነ-ሥርዓት ከመደበኛው ሥርዓት የተለየ እንዲሆን ይጠይቃል። በመሆኑም የወጣቶች ጉዳይ ሌሎች ጉዳዮች በሚታዩበት በመደበኛው ችሎት ሊሰማ አይገባም፣ የችሎቱ ቁመና (ካባ፣ ፖሊስ፣ ወንበር፣ አውድ) ከመደበኛው የተለየ መሆን ይኖርበታል። ከሚሳተፉት ሰዎች አይነት፣ ከሕጉ ዓላማና ሂደቱ ከሚከናወንበት ቦታ አንፃር የመስማቱ ሂደት በችሎት ከሚከናወን ሙግት ይልቅ ይበልጥ ቢሮ ውስጥ የሚከናወን ሌላ ሥራ እንዲመስል እንደተፈለገ መገመት አይከብድም። ተመሳሳይ የሕግ ማዕቀፍ ያላቸው ሌሎች አገሮች ተመሳሳይ አደረጃጀት እንዳላቸውም ልብ ይሏል።

 

ችሎት ፊት በአካል የመገኘቱ ጉዳይ እንዲሁ ከመደበኛው ሂደት መጠነኛ ልዩነት ያለው ነው። በአንቀጽ 175 እንደተደነገገው በማስረጃነት የሚቀርበው ነገር ወይም ትችት የሚሰጥበት ጉዳይ ወጣቱ ሊሰማው የማይገባ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ወጣቱ ከችሎት እንዲወጣ ተደርጎ ጉዳዩ መሰማት ይቀጥላል። በመደበኛው ሂደት በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በማስረጃ ይዘት ምክንያት ከችሎት እንዲወጣ የሚደረግበት አሠራር የለም። ይሉቅንም የተከሳሽ በአካል ችሎት ውስጥ መገኘት ሕጉ እንዲሟሉ ከምጠይቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ነው። ስለዚህ በመደበኛው ሂደት የተከሳሹ በችሎት መገኘት ለጉዳዩ መሰማት ቅድመ ሁኔታ ሲሆን በወጣቶች ጉዳይ ግን አይደለም።

 

ለ. ተዋናዮች

 

የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሂደት በዋናነት ተሟጋች ገፅታ ያለው ነው። ይህ ቅኝት እውነት የሚነጥረው ሁለት ተፋላሚ ወገኖች የየበኩላቸውን ትርክት ሲያቀርቡ ነው ከሚል መሰረታዊ እሳቤ ስለሚነሳ ማስረጃ የማሰባሰብ (gathering) የማቅርብ (presentation) እና መመዘን (weighing) ለተለያዩ አካላት የሚሰጥ ነው። በዚሁ መሠረት ማስረጃ የማሰባሰብና የማቅረብ በዋናነት የከሳሽና የተከሳሽ ኃላፊነት እንደሆነ ሲቆጥር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ ያለው ድርሻ በተጨማሪነት ብቻ የሚታይ ነው። በመስማት ሂደት የሚሳተፉ ተዋናዮች ማንነትም ከዚህ መሰረታዊ ቀመር ጋር የተያያዘ ነው። በዚህም መሠረት በወንጀል የፍትሕ ሂደት ትልቁን ድርሻ የሚጫወቱት ዓቃቤ ሕግና ተከሳሹ እንዲሁም ጠበቃው ናቸው። የፍርድ ቤቱ ድርሻ ለፍትሕ አሰጣጥ ጠቃሚ ናቸው የሚላቸውን ማስረጃዎች በማሰባሰብና የቀረበውንም በመመዘን እንዲሁም አግባብነት ያለውን ሕግ ተፈፃሚ ማድረግን የሚመለከት ነው።

 

የወጣቶች የወንጀል ሂደት ተዋናዮች ከመደበኛው የተለዩ ናቸው። በወጣቶች ጉዳይ ላይ ትልቁ ተዋናይ ዳኛ ሲሆን ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ ነው። ዳኞች የምርመራ ሥራ ያከናውናሉ፣ ክስ ይመስረት አይመስረት የሚለውን ይወሰናሉ፣ በማስረጃ አቀራረብ የአንበሳውን ድርሻ ይጫወታሉ እንዲሁም ፍርድ ይሰጣሉ። ከፍርድ ቤቱ ቀጥሎ ጎላ ያለ ሚና ያላቸው ወላጆችና ሞግዚቶች ናቸው። ሞግዚቶችና ወላጆች ጉዳዩ እንደቀረበ ወዲያውኑ ጥሪ ተደርጎላቸው ይቀርባሉ (አንቀጽ 173)፣ ወጣቱን በየቀጠሮው የማቅረብ ኃላፊነት ይወስዳሉ፣ መጨረሻ ላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ትእዛዝም ይፈፅማሉ። ወጣቱ ጠበቆች ያሉት እንደሆነ በመጠኑም ቢሆን ተዋናይ ይሆናሉ። ቀጥሎ ካለው ክፍል እንደሚታየው ምስክር የሚጠየቀው በፍርድ ቤቱ በራሱ በመሆኑ የጠበቆች ድርሻ የመስቀለኛ ጥያቄ በማንሳትና የቅጣት ሀሳብ በማቅረብ የተገደበ ነው።

 

ሐ. ማስረጃ አቀራረብ

 

የወንጀል የፍትሕ ሂደት መሰረታዊ ዓላማ እውነት ላይ በመድረስ ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ነው። እውነት ላይ የመድረስ ዕድል በማስረጃ አቀራረብ ሥርዓቱ የሚወሰን ነው። ይህ ሥርዓት ፍርድ ቤት እውነት ላይ ለመድረስ የሚጠቀምባቸው አሀዶች የሚቀርቡበትና የሚነጥሩበት በመሆኑ ዳኝነት አካሉ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያለውን እድል ሊያሰፋ ወይም ሊያቀጭጭ ይችላል። እስካሁን ባለው ልምድ ማስረጃ መሰብሰብና ማቅረብን በተመለከተ ሁለት ጎልተው የሚታዩ አማራጮች አሉ። የሁለቱም ልምዶች መሰረታዊ ልዩነት ማስረጃ የማቅረቡ ሂደት የማን ኃላፊነት ሊሆን ይገባል? ለሚለው ጥያቄ በሚሰጠው መልስ ዙርያ የሚሽከረከር ነው። አንደኛው ልምድ ከሳሽና ተከሳሽ ምን ዓይነት ማስረጃ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚቀርብ የመወሰን ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል የሚል አቋም ሲይዝ ሌላኛው ደግሞ ይህ ሀላፊነት የከሳሽም የተከሳሽም ሳይሆን መንግሥት በገለልተኝነት ሊያከናውነው ይገባል የሚል ጫፍ ይይዛል።  በሁለቱም አማራጮች መካከል ያለው የሀሳብ ፍትጊያ አሁንም ቀጥሏል። መንግስታት ግን አንዱን ወይም ሌላውን ወይም ደግሞ ከሁለቱም እያዋዙ የፍትሕ ስርዓታቸውን መቀመር ቀጥለዋል።

የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ሁለቱንም ባህሪያት በተለያየ መጠን የያዘ ነው። መደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ኃላፊነቱን በዋናነት ለተዋናዮች ሲተው፣ ወጣቶችን የሚመለከተው ክፍል ግን ይህን ኃላፊነት ከነሱ ነጥቆ ለዳኝነቱ አካል እንዲሰጥ አድርጓል። በዚህ ምክንያት በመደበኛውና በወጣቶች ጉዳይ መካከል ሰፊ የማስረጃ አቀራርብና አሰማም ልዩነት ሊኖር ችሏል። በመደበኛው ሥርዓት ፍርድ ቤት የቀረበውን ምስክር ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ ማንሳት ቢችልም ዞሮ ዞሮ ምስክሮቹ የከሳሽ ወይም የተከሳሽ ናቸው እንጂ የፍርድ ቤት አይደሉም። ፍርድ ቤት በራሱ የሚጠራቸው ምስክሮች መኖር ይህን እውነታ አይቀይረውም። ምስክሮቹ የባለጉዳዮቹ በመሆናቸው ዋና ጥያቄ የሚያቀርበው ምስክሩን የጠራው ወገን ሲሆን ከዋና ጥያቄ ቀጥሎ እንደነገሩ ሁኔታ መስቀለኛ ጥያቄ በሌላኛው ወገን ይጠየቃል (አንቀጽ 137)። ስለዚህ ምስክር የማቅረብም ሆነ የመጠየቅ ዋናው ኃላፊነት የሚያርፈው በዓቃቤ ሕግና በተከሳሹ ነው። ፍርድ ቤቱ ፍርድ የሚሰጠው ግራቀኙ ያቀረቡት ማስረጃ ሚዛን የሚደፋ መሆን አለመሆኑን በማጣራት ነው። ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ፍሬ ነገር በሚጠበቀው መጠን ማስረጃ ያልቀረበበት እንደሆነ የዚህ ገፈት ቀማሽ የሚሆነው ቀድሞውኑ ፍሬነገሩን የሚመለከት ማስረጃ የማቅረብ ኃላፊነት የነበረው ወገን ነው። ማስረጃ መሰብሰብም ሆነ ማቅረብ የባለጉዳዮቹ መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰብ እወነት ላይ ለመድረስ የሚመች ዘይቤ አይደለም የሚል የሰላ ትችት የሚቀርብበት ቢሆንም አሁንም ብዙ አገሮች የሚከተሉት ሥርዓት ነው። አንዳንድ ፀሀፊዎች ይህ ዘይቤ ፍትሕን ለማስፈን የሚጠቅም አይደለም በማለት አስተሳሰቡን የስፖርት ፍትሕ (sporting theory of justice) ነው ሲሉ ይሳለቁበታል።

 

የወጣቶች ጉዳይ የሚመራው ከዚህ በተለየ አጣሪ ዘይቤ ነው። ይህ ዘይቤ ሲቪላዊ ሥርዓቶች የሚጠቀሙበትና ፍርድ ቤት ማስረጃ ከመገምገም አልፎ በመሰብሰብም ላይ ድርሻ ሊኖረው ይገባል የሚል አቋም ያለው ነው። ይህ ዘይቤ ምስክሮች የባለጉዳዮች ሳይሆኑ የመንግሥት እንዲሆኑ ይፈልጋል፤ የሚጠየቁት በከሳሽና ተከሳሽ ሳይሆን በፍርድ ቤቱ እንዲሆን ያደርጋል። ይህ አካሄድ እውነት ላይ ለመድረስ የተሻለ ዘይቤ ነው በማለትም ይሟገታል። የወጣቶችን ጉዳይ በሚመለከት የኢትዮጵያ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ወደዚህ ዘይቤ አዘንብሏል። ከላይ እንደተጠቀሰው በወጣቶች ጉዳይ መንግሥትን ወክሎ የሚቆም ዓቃቤ ሕግ የለም (በጥቂት ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር)። በዚህ ምክንያት ከሳሽን ወክሎ ምስክር የሚጠራና ማስረጃ የሚያቀርብ የመንግሥት አካል የለም። ይህ ክፍተት የሚሞላው ፍርድ ቤት ይህን ሚና እንዲጫወት በማድረግ ነው። ስለሆነም በወጣቶች ጉዳይ ወንጀል መፈፀሙን የሚያስረዱ ምስክሮች የሚጠራው ፍርድ ቤት ነው። ሆኖም አንዱን ወገን የሚጠቅም ማስረጃ ብቻ ማሰባሰብ ከፍርድ ሰጭ አካል የሚጠበቅ ባለመሆኑ ፍርድ ቤት የሚጠራው ለፍትሕ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ምስክሮች በሙሉ ነው። ስለዚህ በወጣቶች ጉዳይ ምስክሮች በዋናነት የፍርድ ቤት መሆናቸው አይቀሬ ነው። ወጣቱ ወይም ጠበቃው ምስክሮች እንዲጠሩ መጠየቅ እንደሚችሉ አንቀጽ 176(5) ይደነግጋል። እነዚህ ምስክሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የተከሳሽ ናቸው ብሎ ማሰብ ይቻል ይሆናል። ሆኖም ሕጉ የዓቃቤ ሕግም ሆነ የተከሳሽ የምስክር አቀራረብ ቅደም ተከተል ያላስቀመጠ መሆኑና ምስክሮቹን ሁሉ በጥያቄ የሚመረምረው ፍርድ ቤቱ መሆኑን ("all witnesses shall be examined by the court and may thereupon be cross-examined by the defence" (አንቀጽ 176(6)) ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ድንጋጌ ሁለት ነገሮችን መገንዘብ ይቻላል። አንደኛው የምስክር መስማት ሂደት የፍርድ ቤት ዋና ጥያቄና የተከሳሽ መስቀለኛ ተብሎ በሁለት ብቻ የተከፈለ መሆኑን ነው። እንደመደበኛው ሂደት መጀመሪያ የዓቃቤ ሕግ ከዛ ቀጥሎ የተከሳሽ ምስክሮች የሚሰሙ መሆኑን አያሳይም። ሁለተኛውና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ነጥብ ዋና ጥያቄ በማቅረብም ሆነ መስቀለኛ ጥያቄ በማቅረብ ረገድ የዓቃቤ ሕግ ድርሻ በግልፅ ያለሰፈረ መሆኑ ነው።

 

 5. ፍርድ

 

ወጣቶችን የሚመለከተው ሂደት እንደሌሎቹ ሁሉ የሚጠቃለለው ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ፍርድ ነው (አንቀጽ 177) ። ሆኖም በወጣቶች ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ፍርድ በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ይለያል። አንደኛው ልዩነት ታሳቢ የሚደረጉ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። በመደበኛው ሂደት ፍርድ ማለት ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ማስረጃና ሕግ በማገናዘብ ሂድቱን የሚቋጭበት ክንውን ነው። የመቋጫው ይዘት የሚወሰነው በቀረበው ማስረጃና አግባብነት ባለው ሕግ ነው። በዚህ ሂደት ፍርድ ቤት የአንዱ ወይም የሌላው ጥቅም በተለየ ሁኔታ የሚመዝንበት እድል የለውም። ፍርድ ቤቱ ገለልተኛነት ከሚገለፅባቸው ጉዳዮች አንዱ የፍርዱ ይዘትና አሰጣጥ ነው። ፍርድ መወሰን ያለበት በሚቀርበው ማስርጃ ክበደትና አግባብነት ባለው ሕግ ይዘት ብቻ ነው። የወጣቶች ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ ቀመር አለው። ይኸውም ፍርድ ቤቱ ‘አካለ መጠን ላላደረሰው ወጣት የሚጠቅም ውሳኔ ለመስጠት’ (so as to arrive at a decision which is in the best interest of the young person) የሚያስችለውን ሥርዓት እንዲከተል የሚያስገድድ መሆኑ ነው። በመሆኑም የወጣቶችን ጉዳይ የሚመለከት ፍርድ ቤት እውነት ላይ መድረስ ወይም ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ብቻ ሳይሆን የሚሰጠው ፍርድ ለወጣቱ የሚጠቅም መሆኑንም ማረጋገጥ ይርኖበታል። ወጣቶችን በሚመለከት ገዢው ሀሳብ የወጣቶችን ጥቅም ማስጠበቅ በመሆኑ የፍርድ ትክክለኛነት የሚመዘነው ከፍሬ ነገር ወይም ከሕግ አንፃር ብቻ ሳይሆን ፍርዱ ለወጣቱ ካለው ጠቀሜታ አንፃርም ጭምር ነው።

 

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ሁለተኛው ነጥብ በወጣቶች ጉዳይ የሚሰጥ ፍርድ ተከሳሹን ብቻ ሳይሆን የወጣቱን ወላጆች ወይም ሞግዚቶች የሚመለከት ትእዛዝ ሊያጠቃልል የሚችል መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ ከመደበኛው አሠራር ወጣ ያለ ነው። በመደበኛው ሂደት የወንጀል ክስ ያልቀረበበት ሰው ጥፋተኛ ሊባል አይችልም። የወጣቶች ጉዳይ ግን ወጣቱ ጥፋት ውስጥ ሊገባ የቻለው ወላጆቹ ወይም ሌሎች ኃላፈነት ያላቸው ሰዎች ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከተረዳው በነዚህ ሰዎች ላይ አስፈላጊ መስሎ የታየውን ‘ማስጠንቀቂያና ምክር ሊሰጣቸው ወይም ሊወቅሳቸው ይችላል (አንቀጽ 178)። ይህ ሁኔታ ከጅምሩ ቅሬታ ያልቀረበባቸውና ምናልባትም በሂደቱ ውስጥ የመከላከል እድል ያላገኙ ሰዎች በስተመጨረሻ ላይ ለወጣቱ ጥቅም ሲባል እንዴት ትእዛዝ ሊተላለፍባቸው እንደሚችል ያሳያል።

 

 6. ፍርድ ማረሚያ ሥርዓት (Review)

 

የወንጀል ፍትሕ ሥርዓታችን የሚመራው ፍርድ የመጨረሻ ነው (finality principle) በሚል መርህ ነው። በመሆኑም ፍርድ ቤት ፍሬነገርንም ሆነ ሕግን በማስመልከት የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻና አስገዳጅ ነው። ፍርድ ቤት አንድን ጉዳይ ተመልክቶ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ከመሆኑ የተነሳ በይግባኝ ፍርድ ቤት ካልሆነ በስተቀር ውሳኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት (court of rendition) በራሱ እንደገና ሊታይ የሚችልበት እድል ዝግ ነው። ስለዚህ የፍትሕ ሥርዓታችን ዋናው የማረሚያ ስልት የይግባኝ (በውስን ጉዳዮች ደግሞ የሰበር) ሥርዓት ነው። የይግባኝ ሥርዓት በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠውን የፍሬ ነገር ይሁን የሕግ ግኝት እንደገና የመመርመር ሙሉ ሥልጣን የሚሰጥ ቢሆንም ይግባኝ ሥርዓቱን ለመጠቀም ለሚፈልግ ሰው ግን ተጨማሪ ጊዜና ውጭ የሚጠይቅ ነው። እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓዝንም የግድ የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪ በወንጀል ፍትሕ ሂደት ይግባኝ ማቀረብ መብት ቢሆንም የመብቱ አጠቃቀም ገደብ የለሽ አይደለም። ይግባኝ የሚቀርብበት ጊዜ፣ የሚያቀርበው ሰው ማንነት፣ የማስረጃ አቀራረብ ወዘተ ላይ ያሉ ገደቦች የዚህ ማሳያ ናቸው።

 

ወጣቶችን የሚመለከተው ልዩ ሥርዓት በማረሚያ ሂደቱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ አድርጓል። አንቀጽ 180 "አካለመጠን ባላደረሰው ወጣት ላይ ትእዛዝ የሰጠ ማንኛውም ፍርድ ቤት በራሱ አስተያየት ወይም አካለመጠን ያላደረሰው ወጣት፣ ኃላፊ የሆነለት ሰው ወይም አድራ የተሰጠው ሰው ወይም ድርጅት ባመለከተ ጊዜ ለወጣቱ ጥቅም አስፈላጊ በሆነው መሠረት ትእዛዝ መለወጥ ወይም ማሻሻል ይችላል" በማለት ይደነግጋል። ከድንጋጌው ለመገንዘብ እንደሚቻለው የዚህ ለውጥ መሰረታዊ መነሻ የወጣቶችን ጥቅም የመጠበቅ ፍላጎት ነው። በመሆኑም ለወጣቱ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቀደም ሲል የተሰጠ ትዕዛዝ ቀለል ባለ ሥርዓት መለወጥ ወይም ማሻሻል የሚቻልበት እድል ተፈጥሯል። ይህ ሥርዓት በበርካታ ምክንያቶች ከመደበኛው ሂደት ይለያል። ዋና ዋናዎቹ ልዩነቶች ቀጥሎ ያሉት ናቸው።

 

ሀ. ትእዛዝ የሰጠ ፍርድ ቤት ትእዛዙን መቀየር መቻሉ፤ በመደበኛው ሥርዓት አንድ ውሳኔ እንደገና ሊታይ የሚችለው ውሳኔውን በሰጠው ሳይሆን በሌላ የይግባኝ ፍርድ ቤት ነው። ውሳኔውን የሰጠ ፍርድ ቤት የራሱን ጉዳይ መልሶ ማየት አይችልም። በወጣቶች ጉዳይ ግን ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት ራሱ ጉዳዩን እንደገና የመመልከት ሥልጣን ተሰጥቶታል።

 

ለ. ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በራሱ አነሳሽነት ማንቀሳቀስ መቻሉ፤ በመደበኛው ሥርዓት ፍርድ ቤት በወንጀል ሂደት የተሰጠን ትእዛዝ በራሱ አነሳሽነት የመቀየር ሥልንጣ የለውም። ይህ የሆነው በprinciple of party disposition የሚመራ በመሆኑ ነው። ይህ መርህ ፍርድ ቤት ወደ ሂደት የሚገባው በተከራካሪ ወገኖች ጠያቂነት ብቻ መሆኑን አፅንኦት የሚሰጥ ነው። በዚህ መርህ መሠረት ከባለጉዳይ ጥያቄ እስካልቀረበ ድረስ በአንድ ጉዳይ ላይ ዳኝነታዊ ጉዳዮች ማከናወን አይቻልም። በዚህ መርህ መሠረት የትኛውም ፍርድ ቤት አንድ ውሳኔ ስህተት መሆኑን እንኳን ቢረዳ በራሱ አነሳሽነት የተሰጠውን ውሳኔ መቀየር አይችልም። ውሳኔው እንዲሻሻል ከተፈለገ ከባለ ጉይዮች አንዱ ማመልከቻ ማቅረብ አለበት። በወጣቶች ጉዳይ ይህ መርህ ከሞላ ጎደል አይሰራም። ከማንም ጥያቄ ባይቀርብለትም ለወጣቱ ጥቅም አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ ፍርድ ቤቱ በራሱ አነሳሽነት የሰጠውን ትእዛዝ መቀየር ይችላል። ይህ ሁኔታ ፍርድ ቤቱ በወጣቶች ጉዳይ ላይ ያለው ተሳትፎ ውሳኔ በማስተካከልም ረገድ የላቀ መሆኑ የሚያሳይ ነው።

 

ሐ. የጊዜ ገደብ የሌለው መሆኑ፣ የይግባኝ ማቅረብ በሕገ መንግሥት እውቅና ያገኘ መብት ነው። ሆኖም ይህ መብት ተግባራዊ መሆን የሚችለው በተወሰነ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ለሚመለከተው አካል ማመልከቻ ከቀረበ ብቻ ነው። ስለዚህ የይግባኝ መብት እንድሌሎቹ በርካታ መብቶች ገደብ ያለው ነው። በሕጋችን መሠረት አንድ ውስኔ በይግባኝ ይለወጥልኝ የሚል ጥያቄ ለማቅረብ የተፈቀደው ጊዜ በ60 ቀን ብቻ ነው። የወጣቶች ጉዳይ ግን በዚህ የጊዜ ገደብ አይገዛም። ወጣቱ ወይም ተወካዮቹ ለፍርድ ቤት ጥያቄ የሚያቀርቡበት የጊዜ ገደብ አልተቀመጠም፣ ፍርድ ቤትም ቢሆን ጥያቄውን በራሱ አነሳሽነት እስከመቼ ድረስ ማንሳት እንደሚችል የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የለም። ለወጣቱ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ ጉዳዩ በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ የሚቻል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ ሥርዓት ሂደቱ የወጣቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሄደበትን ርቀት ያመለክታል።

 

መ. ዕድሉ ለወጣቶች እንጂ ለዓቃቤ ሕግ የማያገለግል መሆኑ፣ እንደሚታወቀው የእርምትሥርዓት ከሳሽም ተከሳሽም እኩል የሚጠቀሙበት ሥርዓት ነው። ከሁለቱ አንዳቸው ወይም ሁለቱም በተሰጠው ውሳኔ ቅር ከተሰኙ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤቱ የማቅርብ መብታቸው የተጠበቀ ነው (የዓቃቤ ሕግ ይግባኝ የማቅረብ ሥልጣን ከሕገ መንግስቱ ሳይሆን ከሥነ-ሥርዓት ሕጉ የሚመነጭ ነው) ። ወጣቶችን በማስመልከት የተዘረጋው የእርምት ሥርዓት ግን ወጣቶቹ ወይም ተወካዮቻቸው እንዲሁም እነሱን የሚጠብቁ ተቋማት እንጂ ዓቃቤ ሕግ ሊጠቀምበት አይችልም።

 

 7. ማጠቃለያ

 

ወጣቶች ወንጀል ውስጥ ሲገቡ ጉዳያቸው የሚታይበት ስርአት ከሌላው የተለየ ነው። ይህ ልዩነት የሚታየው ሁለቱም በተለያዩ የሕግ አስተሳሰብ የተቃኙ በመሆኑ ነው። መደበኛው ስርዓት በተሟጋች አስተሳሰብ የተቃኘ በመሆኑ ማስረጃ አሰባሰብን፣ አቀራርብን፣ ምዘናን በሚመለከት የወሰደው አቋም በወጣቶች ካለው የተለየ ነው። ወጣቶችን የሚመለከተው ክፍል በሌላ በኩል በተሟጋች ሳይሆን በአጣሪ አሰተሳሰብ የተቃኘ ነው። በዚህ ምክንያት የምርመራ፣ የክስም ሆነ የመስማት ሂደቱ በፍርድ ቤት ንቁ ተሳትፎና ቁጥጥር ስር የሚከናወን ነው።  አብዛኛው ክንውን በፍርድ ቤት እንዲከናወን የተደረገ በመሆኑ ፖሊስ እና ዓቃቤ ሕግ በወጣቶች ጉዳይ ውስጥ ያላቸው ሚና በጣም ውስን ነው።  ፖሊስ ወጣቶችን የሚመለከት ሪፖርት ተቀብሎ ምርመራ ማከናወን ስለማይፈቀድለት ሌላ ጊዜ የሚያከናውናቸው በርካታ ስራዎች መፈፀም አይችልም።  ምርመራ የሚከናወነው በፍርድ ቤቱ መሪነት በመሆኑ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ ገለልተኛ በሆነ ስርዓት ይከናወናል። ይህ ማስረጃ የማሰባሰብ ስርዓት ፍርድ ቤቱ ከመስማት ሂደት በፊት ሁሉንም ማስረጃ እንዲያውቅ እድል የሚሰጥ ነው። ወንጀል መፈፀሙን ብቻ ሳይሆን ለወጣቱ ጠቃሚ የሆኑ ማስረጃዎች ጭምር እንዲቀርቡ ሰፊ እድል የሚሰጥም ነው። በዚህ ምክንያት ከተለመደው የፖሊስ የምርመራ ሂደት ይልቅ እውነት ላይ ለመድረስ የተሻለ እድል ሊሰጥና የወጣቶችን ጥቅም ለመጠበቅ የተሻለ ሊሆን ይችላል።  ይህ አሠራር በምርመራው በሚሳተፉት ዳኞች አይን ወጣቱ ጥፋተኛ ሆኖ የመገመት ሁኔታ ስለሚፈጥር አሉታዊ ተፅእኖዎችም ሊያሳርፍ ይችላል። ዞሮ ዞሮ አሁን በሕግ እውቅና ያገኘው አሠራር ፖሊሶች ወጣቶችን እንዲመረምሩ፣ እንዲይዙ፣ እንዲያስሩ፣ እንዲፈትሹም ሆነ ከተከሳሹ ቃል እንዲቀበሉ የማይፈቅድ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ፖሊስ ከነዚህ መካከል አንዱንም ማከናወን የሚችለው ፍርድ ቤት መመሪያ ከሰጠው ብቻ ነው።

 

የዓቃቤ ሕግ ድርሻም እንዲሁ ውሱን ነው። ፍርድ ቤት መደበኛው የክስ ማመልከቻ መቅረብ ሳያስፈልግ የወጣቶችን ጉዳይ መስማት ስለሚችል የዓቃቤ ሕግ ክስ የማቅረብ ሀላፊነት ያነሰ ድርሻ እንዲኖረው አድርጓል። ክስ በሚያቀርብባቸው ውሱን ጉዳዮችም (ለከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚቀርቡ ጉዳዮች) ቢሆን ዓቃቤ ሕግ በሌሎች ጉዳዮች ያለውን ያህል ሚና የለውም። ይህ የሚሆነው የማስረጃ መስማት ሂደት በተከራካሪዎች ሳይሆን በፍርድ ቤቱ ባለቤትነት ስለሚከናወን ነው። በወጣቶች ጉዳይ ምስክሮች የፍርድ ቤት ናቸው፤ የሚጠይቃቸውም ፍርድ ቤት ነው። ስለዚህ እንደ መደበኛው ሂደት የባለጉዳይ ምስክር የለም። ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ሲጨርስ ዓቃቤ ሕግ መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ የሚችል መሆኑን የሚደነግግ አንቀጽ የለም። ይህ ሁኔታ በአጣሪ ሥርዓቶች የተለመደ አካሄድ በመሆኑ ሕግ አውጭው የዓቃቤ ሕግ ድርሻ ያነሰ እንዲሆን ሆን ብሎ የቀየሰው ስርዓት እንደሆነ ይገመታል።

የዳኝነት ተቋማት በወንጀል ክርክር ሂደት የጎላ ሚና እንዳላቸው እሙን ነው። ሆኖም በወጣቶች ጉዳይ ላይ ከመደበኛውም ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ የተቀነሰው ስልጣን ፍርድ ቤቱ ደርቦ እንዲሰራው ተደርጓል። ለወትሮው በምርመራ ሂደት ከቁጥጥር ያለፈ ድርሻ የሌለው ፍርድ ቤት በወጣቶች ጉዳይ ላይ የሂደቱ ማዕከል እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም ምክንያት ፖሊስን ተክቶ ሪፖርትና አቤቱታ ይቀበላል፣ የምርመራ ሂደቱን ይመራል፣ ክስ እንዲመሰርት ዓቃቤ ሕግን ያዛል።  ሌላ ጊዜ ለፍትሕ ሲባል ተጨማሪ ማስረጃ ብቻ መጥራት የሚችለው ፍርድ ቤት በወጣቶች ጉዳይ ላይ የማስረጃ አቀራረብ ሂደት እምብርት እንዲሆን ተደርጓል። ምስክር ይጠራል፣ ይጠይቃል ፍርድም ይሰጣል። የዳኝነቱ አካሉ ሀላፊነት ሲመዘን በሥነ-ሥርዓት ሕጉ ውስጥ ካለው ስርዓት ይልቅ በሌሎች አገሮች ያለውን የሲቪላዊ አገሮች ባህሪ ይመስላል

 

በአጠቃላይ ወጣቶችን በማስመልከት የተዘረጋው ስርዓት ከመደበኛው ሂደት መሰረታዊ በሆኑ ጉይዮች ይለያል። የልዩነቱ መነሻ የወጣቶች ጥቅም የማስጠበቅ ፍላጎት እንደሆነ ይገመታል። ሕጉ በፈለገው መጠን የወጣቶችን ጥቅም ማስጠበቅ የሚቻለው ሕጉ ያስቀመጠውን ስርዓት በመከተል ነው።  ሆኖም የወጣቶች ሂደት በአፈፃፀም ከመደበኛው ብዙም የማይለይ በመሆኑ የሕግ አውጭው ዓላማ ተጨናግፏል።  ሕጉን ተክቶ ስራ ላይ የተንሰራፋው ልማዳዊ አሠራር ወጣቶችን ከፍርድ ቤት እይታ በማስወጣት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደርጋል። ወጣቶች ከሕግ ውጭ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ፣ ዋስትና እንዲከለከሉ ይፈቅዳል።  ፖሊስ የምርመራ ስራ ጨርሶ ጉዳዩን ለዓቃቤ ሕግ እንዲያስተላልፍም ያደርጋል። ይህ አሠራር በመደበኛው ሂደት ተቀባይነት ያለው ቢሆንም በወጣቶች ጉዳይ ግን እውቅና የተሰጠው አይደለም። በአጠቃላይ ወጣቶች ልማዳዊ አሰራሩ ወጣቶች ላልተገባ የፖሊስ ስልጣን እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል። ፖሊሶች ወጣቶችን መመርመር መደበኛ ስራቸው አድርገው ከመውሰዳቸው የተነሳ ተጨማሪ የምርመራ ቦታዎች እንዲገነቡላቸው እስከመጠየቅ ደረሰዋል። ይህ ሁኔታ ህጋዊ ያለሆነው አሠራር ምን ያህል የበላይነት እንዳገኘ ያሳያል። ወጣቶችን በማስመልከት የሚሰሩ አንዳንድ ጥናቶች ልማዳዊ አሰራሩን ከመሞገት ይልቅ እሱን እንደቅቡል አሠራር ወስዶ ማሻሻያ ሀሳብ ማቅረብን እንደተሻለ አማራጭ ወስደውታል።

 

የፍትሕ ተቋማት መመራት የሚኖርባቸው በሕግና በሕግ ብቻ ነው። ስለዚህ ከሕግ ያፈነገጡ አሰራሮችን ለማረም ቁርጠኝነቱ ሊኖራቸው ይገባል።  በሕግ የሰፈሩ ድንጋጌዎች ተቀባይነት የሌላቸው እሳቤዎችን ይዘዋል ሊባል ይችላል። ወጣቶችን የሚመለከቱ አንዳንድ ድንጋጌዎች ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይሄዱም ማለትም ይቻል ይሆናል። ሆኖም ይህ ሁኔታ ለወጣቶች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሕጎችም የሚሰራ ከመሆኑም ባሻገር የሕግ ማሻሻያ ሀሳብ ለማቅርብ መነሻ ከሚሆን በቀር ሕጉን ጭራሽ ስራ ላይ እንዳይውል ለማድረግ በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም።

Read 5886 times Last modified on Oct 26 2019
መንበረጸሐይ ታደሰ (PhD)

ጸሐፊው በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር  እና የደመር ፍትሕ ጉዳዮች ጥናት ኃ/የተ/የግ/ማ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በኃላፊነት ካገለገሉበት ሥራዎች መካከል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት የኮሜሳ ዳኛ እና የሕግና ፍትሕ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ይጠቀሳሉ፡፡ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው menberetadesse@yahoo.com ማግኘት ይችላሉ፡፡

Latest from መንበረጸሐይ ታደሰ (PhD)