Print this page

ያለመያዝ እና ያለመታሰር መብት

Feb 27 2019

 

 

 

“የነፃነት መብት” መርህ ሲሆን “መያዝና  መታሰር”  ልዩ ሁኔታ ነው!”

 

መግብያ

መያዝ እና መታሰር በህግ ተለይተው በተቀመጡ ምክንያቶች እና በግልጽ በተዘረጋው ስርአት መሰረት በጥንቃቄ የሚከናወን ልዩ ሁኔታ ሲሆን ነፃነት መርህ ነው! የነፃነት መብት በተለያዩ አለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግጋት፣ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰምምነቶችና ሰነዶች መደንገጋቸውን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኢፌድሪ ህገ መንግስት ምእራፍ ሶስት “መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች” በሚል ርእስ በአንቀጽ 17 ስር ተደንግጎ የሚገኝና “የሰው ልጅ” ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ከተሰጡት ሰብኣዊ መብቶች አንዱ ነው፡፡የነጻነት መብት በዚሁ ህገ-መንግስት እና ሌሎች ህጎች ላይ የተደነገገው እንደ መንግስታዊ ስጦታ እንዲቆጠር ታስቦ ሳይሆን ሰዎች በተፈጥሮ ያገኙዋቸውን ሰብኣዊ መብቶች መንግስት እንዲያከብርና እንዲያስከብር ግዴታ ለማስገባት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግስት ሰብኣዊ መብቶችን መስጠት ሆነ መንጠቅ አይችልም፤እውቅና መስጠት፣ማክበርና ማስከበር ግን አለበት፡፡ይህ ማለት ግን የነጻነት መብት ፍጹም እና በህግ ሊገደብ የማይችል ነው ማለት አይደለም፡፡      

በዚህ አጭር ጽሁፍም የነጻነት መብት አጠቃላይ መርህ እና የነፃነት መብት የሚገደብበት ልዩ ሁኔታዎችን  መሰረት ባደረገ መልኩ ያለመያዝ እና ያለመታሰር መብት ከህግ አንጻር የሚተረጎምበት አግባብ በተለይም ደግሞ በወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በህግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችን ስለሚያዙበትና የሚታሰሩበት ህጋዊ ምክንያቶችን እና ስነስርአታዊ አካሄዶችን ከአለምአቀፍ  ህጎችና ልምዶች  እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህጎች  አንጻር በመቃኘት አጭር ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁኝ፡፡

ማንኛውም  የሰው ልጅ ፍጡር በየትኛውም ግዜ፣ቦታ እና አካል ሊገሰስ ሆነ ሊገፈፍ ወይም ሊደፈር የማይችል በተፈጥሮ የታደለውን የነፃነት እና የአካል ደህንነት መብት አለው ፡፡  ሁሉም ሰብአዊ መብቶች  እርስ በእርሳቸው ፍጹም የማይበላለጡና የማይነጣጠሉ ፣እኩል እና የሚደጋገፉ መሆናቸውን እንደተጠበቀ ሆኖ የነፃነትና የደህንነት መብቶችን ግን በሂወት ከመኖር መብት ቀጥለው ቁልፍና  መሰረታዊ የግለሰቦች  መብት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የነጻነት እና የደህንነት መብቶች ሳይከበሩ ሌሎች  መሰረታዊ የሰው ልጅ መብቶች ይከበራሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ሁሉም  ሰብኣዊ መብቶች እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ፣የሚደጋገፉ እና ፍፁም ሊነጣጠሉ የማይችሉ በመሆናቸው  የአንድ ሰብኣዊ መብት ጥሰት ለሌሎች ሰብኣዊ መብቶችን መከበር  አደጋ ላይ  የሚጥል እና በውጤት ደረጃ ሁሉንም ሰብኣዊ መብቶችን  የሚበክል እንደ ወረርሽኝ በሽታ  በቀላሉ የሚሰራጭ ነው፡፡ ወረርሽኝ በሽታ ነው ያልኩበት ዋና ምክንያት፡- አንድ የመብት ጥሰት ከተጀመረ በሌሎች መብቶች  ላይ የሚበተነው  መርዝ በቀላሉ የማይቆም በጅምላ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ስለሚያስከትል በመሆኑ ሲሆን በተለይ ደግሞ መንግስት መሰረታዊ መብቶችንና ነጻነቶችን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ  ለሰብኣዊ መብት ጥሰቶች ራሱ መሪ ተዋናይ በሚሆንባቸው ጉዳዮች ላይ ጉዳቱ ከፍተኛና አደገኛ ነው፡፡

 ጉዳዩ ግልጽ ለማድረግ ያህል፤ የጤና መብት ያልተከበረለት፣የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠለት፣የመኖርያ/ የመጠልያ መብት ያልተመቻቸለት ግለሰብ በሂወት የመኖር መብቱንም እንደሚነካ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም፤ በተጨማሪ የደህንነት መብቱን ያልተረጋገጠለት ወይም ሙሉ ዋስትና ያልተሰጠው ግለሰብ በሂወት የመኖር መብቱንም አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር ነው፡፡በተመሳሳይ መልኩ ከህግ ውጭ  ነጻነቱን የታፈነ ግለሰብ አያሌ መሰረታዊ መብቶቹ ሊነጠቅ ይችላል፤ለምሳሌ በተገቢው ጊዜ ፍርድቤት ያለመቅረብ በደል፣ የህግ አማካሪ የማግኘት መብትን መንፈግ  ፣በቅርብ ቤተሰቡ እና ጓደኞቹ እንዳይጎበኝ ማድረግ እንዲሁም ሌሎች ግፎች ፣ድብደባዎች፣ግርፋቶች፣ ኢ-ሰብኣዊ እና ክብሩን የሚያዋርዱ አያያዞች ሊደርስበት ይችላል፡፡ምክንያቱም ከጅምሩ  ከህግ ውጭ የተያዘ እና የታሰረ ሰው ከዚህ ቀጥለው ለሚደርሱበት የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን ህግ በመሀል ጣልቃ ገብቶ ያስቆማል ወይም ዋስትና ይሰጣል ብሎ ለመከራከር እምብዛም የሚያስተማምን አይሆንም፡፡ በሌላ አገላለጽ ከመጀመርያ ጀምሮ ከህግ ውጭ የተከናወነ የመያዝ እና የማሰር  ተግባር ሆኖ እያለ  ቀጥሎ የሚከናወነው ሂደት እና ውጤት ህጋዊ ሊሆን ይችላል ብሎ መናገር ምኞት ከመሆን አይዘልም፡፡   

በአለም አቀፍ ደረጃ የሰብኣዊ መብቶች ተማጓች አካላት  በሚያቀርቡት የተለያዩ ጥናቶች መሰረት በአለም ሃገራት ካለምንም በቂ ምክንያት ለእስር እና ለሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ከህግ ውጭ ከተያዙ እና ለእስር ከተዳረጉ በኃላም ቢሆን አካላቸውን ነጻ ስለሚወጣበት እና በህግ መሰረት መብታቸውን የሚያስከብሩበት እድል እንደማይሰጣቸው ይጠቁማሉ፡፡ለመሆኑ ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ምንድን ነው?የህጋዊነት መርህስ ምን ማለት ነው? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ይዳሰሳሉ፡፡

1) የህጋዊነት እና የኢ-ህጋዊነት (lawfulness and arbitrariness) ፅንሰ-ሀሳባዊ እና ህጋዊ ትርጉም

1.1) ህጋዊነት (Lawfulness)

 

ማንኛውም ግለሰብ ነፃነቱ ሊገፈፍ ወይም ሊጣስ የሚችለው በግልጽ ተለይተው በተቀመጡ የህግ ማእቀፎች እና ህግን በተከተለ መንገድ  በሀገሪቷ በተዘረጋው ስርአት ብቻ በማከናወን  ነው፡፡  ማንኛውም ሰው  ከህግ ውጭ ነጻነቱን ሊገፈፍ ከቶ አይቻልም፣በህግ ባልተከለከለ ጉዳይ ሰዎችን ማሰር ፍጹም  የተከለከለና ህገ-ወጥ ተግባር  ነው፡፡ ስለሆነም የህጋዊነት መርህ  ማለት አንድ ተግባር ወንጀልነቱ እና አስቀጭነቱ በግልጽ በህግ የተደነገገ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝብ የወንጀል ህግ አጠቃላይ መርህ ነው፡፡ ይህን የህጋዊነት መርህ ወደ ጎን በመተው ማለትም በህግ መሰረት ወንጀልነቱን እና አስቀጭነቱን  ባለተደነገገ ጉዳይ ሰዎችን የመያዝ እና የማሰር ተግባር ከተከናወነ ውጤቱ ኢ-ህጋዊነት ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰትም ነው፡፡ ሀገራት የህጋዊነት መርህን ባልተከተለ መልኩ በግለሰቦች ላይ የመያዝና የማሰር ተግባር ያከናወኑ እንደሆነ  በአለም አቀፍ ህጎች መሰረት ተጠያቂ ናቸው፡፡

ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ምንነትና ይዘት፤ ዋና ዋና አንጓዎች(መገለጫዎች)እንዲሁም እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራትን የምንከላከልበት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተገቢነት ካላቸው የተለያዩ ህጎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው ሰፋ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁኝ፡፡

  

1.2) ከህግ ውጭ ማሰር (Arbitrariness)

 

ከህግ ውጭ ማሰር ማለት የህግ የበላይነትን በመጣስ ወይም ህግን እና ስርአትን ባልተከተለ መልኩ ሰዎችን መያዝ እና ማሰር ማለት ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ደግሞ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ መግለጫ በአንቀጽ 9(1) ላይ የተደነገገውን ይዘት ሰፋ ባለ መልኩ እንደሚከተለው ያብራራዋል፡፡

“Arbitrariness is not to be equated with against the law; but must be interpreted more broadly to include elements of inappropriateness, injustice, lack of predictability and the due process of law.”

ይህ የእንግሊዘኛ አነጋገር ወደ አማርኛ ሲመለስ “ከህግ ውጭ ማሰር ማለት በህግ የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ ወይም ህግን በጣሰ መልኩ ሰዎችን ማሰር ብቻ ሳይሆን አግባብነት በሌለው ፣ፍትሃዊነት በጎደለው ፣ሊተነበይ ወይም ሊገመት በማይችል ምክንያት ሰውን መያዝ እንዲሁም ህግን ባልተከተለ አሰራር ማሰርን” በሚያካትት መልኩ በሰፊው መተርጎም እንዳለበት ገልል (ትርጉም የራሴ)፡፡

በተጨማሪም አንድ ሰው በህግ አግባብ የተያዘ ቢሆንም የተያዘበትን ጉዳይ በህግ መሰረት የዋስትና መብት የማያስነፍግ ሆኖ እያለ ፖሊስ ምክንያታዊነት በጎደለው እና አስፈላጊነቱን ወይም ወቅታዊነቱን ሳያገናዝብ ተጠርጣሪው በፍርድቤት እያስቀረበ ተጨማሪ የቀጠሮ ጊዜ በመጠየቅ በእስር እንዲቆይ ማድረግ ከህግ ውጭ ማሰር ነው ሲል ኮሚቴው ይገልጻል፡፡ሆኖም ግን ተጠርጣሪው ከህግ ተጠያቂነት እንዳይሸሽ ለመከላከል የሚደረግ የእስር ተግባር ህገ-ወጥ የእስር ተግባር ልንለው አንችልም፡፡ ለምሳሌ፡- ተጠርጣሪው  ከሃገር ለመውጣት ሙከራ ሲያደርግ ከተነቃበት፤መረጃ እና ማስረጃ እንደሚያጠፋ አመላካች ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ከተረጋገጠበት ወይም ሀገራት በራሳቸው የወንጀል ስነስርአት ህጎች መሰረት ዋስትናን የሚያስከለክሉ ጉዳዮች ናቸው ተብለው የተዘረዘሩትን ሁኔታዎች  ተሟልተው ስለመገኘታቸውን ፍርድቤቱ በማስረጃ አረጋግጦ ተጠርጣሪውን በእስር እንዲቆይ  ከታዘዘ ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ነው ሊባል አይችልም፡፡

 ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር መጠኑ ይብዛም ይነስም በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ መኖሩ የማይቀር ነው፤ በተለያዩ ሁኔታዎች እና ዘዴዎችም ሊከናወን ይችላል፡፡ለምሳሌ የተጣሰ የወንጀል ህግ ሳይኖር፣ የህጋዊነት መርህን ችላ በማለት ሰውን መያዝ እና ማሰር፣ምክንያታዊነት እና አግባብነት የሌለው የእስር ተግባር ማከናወን እንዲሁም በአድልዎ እና በገደብ አልባ እስር ሰዎችን ካለ ፍርድቤት ትእዛዝ እና የቅጣት ውሳኔ ለረዥም ጊዜ ማሰርን ሊያካትት ይችላል፡፡እነዚህን ከህግ ውጭ የመያዝ እና የማሰር  መገለጫዎች አንድ በአንድ እንደሚከተለው ይብራራሉ፡፡

1.2.1) ኢ- ህጋዊነት (Unlawful Detention)

ሀገራት በህጎቻቸው ላይ በግልጽ ባላካተቱት ምክንያት ሰዎችን የሚያስሩ እና የሚያግቱ ከሆነ ይህ ተግባር የህጋዊነትን መርህን የሚጥስ የአምባገነን መንግሰት ባህርያዊ መገለጫ ነው፡፡ ፖሊስ ወይም ሌላ የህግ አስከባሪ አካል አንድን ግለሰብ ሲያስር እና በቁጥጥር ስር ሥያውል በግለሰቡ የተፈጸመው ድርጊት  አስቀድሞ በወንጀል እንደሚያስጠይቅ በህግ ተደንግጎ መሆን አለበት፡፡በህግ  በግልጽ ያልተከለከለን “ተግባር”(”ግድፈት”) ሰውን ለመያዝ ሆነ ለማሰር ምክንያት ሊሆን አይችልም ፤ፖሊስ ወይም ሌላ አካል ወንጀል ስለመሆኑ በህግ ባልተደነገገ ጉዳይ  አይነ ውሃው ስላልወደደው ወይም  ከተለያዩ ምክንያቶች ከሚመነጩ የጥላቻ መነሻዎች መሰረት በማድረግ  ብቻ ሰዎችን የሚይዝ ከሆነ ከህግ ውጭ የእስር ተግባር ተከናውኗል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደሞኮርኩት “ኢ-ህጋዊነት” ይባላል፡፡

  • -ምክንያታዊነት(Unreasonable Detention)

በህግ የሚያስጠይቁ ተግባራት ተፈፅመው ሲገኙም መያዝ እና ማሰር ግዴታ ላይሆን ይችላል፡፡በተጨማሪም በአንድ ወይም በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ተጠርጥሮ የተያዘ ሰውን  በግዜ ቀጠሮ ፍርድቤት ማቅረብ ኢ-ህጋዊ ባይሆንም ምክንያታዊ ላይሆን ግን ይችላል፡፡ለምሳሌ አንድ ተጠርጣሪ የእጅ እልፊት ወይም የስድብ እና ማዋረድ ወንጀል መፈጸሙን በተጎጂው አማካኝነት የግል አቤቱታ ቀርቦበት በፖሊስ ከተያዘ በኃላ ወደ ፍርድ ቤት “ጊዜ ቀጠሮ” ማቅረብ አግባብነት አይኖሮውም፤ጠቃሚም ምክንያታዊም አይሆንም፡፡ በመርህ ደረጃ አንድ ተጠርጣሪን ጊዜ ቀጠሮ በማቅረብ እና በዳኛ ፈቃድ በእስር በማቆየት ምርመራን ለማከናወን  (Remand in Custody) ፍርድቤትን  መጠየቅ የሚያስፈልገው ለመካከለኛ እና ከባድ ወንጀሎች ብቻ ነው፡፡ይህ እንዲሆን የተፈለገበት ዋና ምክንያትም ፖሊስ በከባድ እና በመካከለኛ ወንጀሎች የተጠረጠረን ግለሰብ በዋስትና እንዲለቅ የሚፈቅድለት ህግ ባለመኖሩ እንጂ ሁሉም ተጠርጣሪ ዋስትና ይከለከላል ማለት አይደለም፡፡በህግ መሰረት ዋስትና በሚያስከለክሉ ወንጀሎች ተጠርጥሮ በችሎት የቀረበ ተጠርጣሪን ፍርድቤቱም በህግ መሰረት ብቻ መከልከል ይኖርበታል፡፡የተፈጸመ ወንጀል ስለመኖሩ አጠራጣሪ ከሆነ ወይም ወንጀሉን በተጠርጣሪ ስለመፈጸሙ ፖሊስ  መነሻ ማስረጃዎች ማቅረብ ካልቻለም ዋስትናን መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪው የተያዘበት ጉዳይ በህግ መሰረት ዋስትና እንደሚያስከለክል ባይደነገግም የተያዘው ሰው ከሃገር እንዳይወጣ ለመጠበቅ፤ በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የተጠርጣሪው ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ለመከላከል እና ማስረጃዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማደረግ እንዲሁም በሌላ አስፈላጊ እና ህጋዊ  ምክንያት ተጠርጣሪውን በእስር ለማቆየት ጠቃሚ እና ምክንያታዊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ዋስትናን ለማስከልከል(ሊፈቀድለትም ላይፈቀድለትም ይችላል) ፍርድቤት ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡ስለሆነም ጊዜ ቀጠሮን መሰረት በማድረግ የሚከናወን የእስር ተግባር በህግ ምክንያት የሚከናወን መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊ፣ጠቃሚ እና አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡በሌላ አገላለጽ አንድ ግለሰብ በቀላል ወንጀል ተጠርጥሮ ከተያዘ ወይም የተጠረጠረበት የወንጀል ተግባር ቀላል ባይሆንም እንኳን አንድ የወንጀል ተግባር ስለመፈጸሙ እንዲሁም በተጠርጣሪው ስለመፈጸሙ አማላካች መረጃ ከሌለ ግለሰቡን በመያዝ እና በማሰር እንዲሁም በስመ “ጊዜ ቀጠሮ” ወደ ፍርድቤት በማመላለስ እና በማንገላታት የነፃነት መብት ጥያቄ ውስጥ መክተት ትክክል ስለማይሆን  መርማሪ ፖሊስ በራሱ መንገድ ህጋዊ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል ፡፡

  • አድልዎዊነት (Discriminatory Detention)

ከህግ ውጭ ማሰር የተፈፀመውን  የወንጀል ተግባር መሰረት በማድረግ  ብቻ ሳይሆን ይህ ተግባር እንደ ሽፋን በመጠቀም  በአንጻሩ ሌሎች የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ በአድልዎ ሰዎችን ማሰር ሊያካትት ይችላል፡፡ለምሳሌ ሁለት ግለሰቦች ተመሳሳይ የወንጀል ተግባር መፈጸማቸው በበቂ ማስረጃ ተረጋግጦ እያለ አንዱን በማሰር እና ነጻነቱን እንዲያጣ በማድረግ ሌላኛውን ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይታሰር ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ በነፃነት እንደፈለገ መኖር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡”አድልዎ” በየትኛውም የአለም ክፍል ማስቀረት የማይቻል የሰዎች “አመለካከታዊ በሽታ” ነው፡፡ ሰዎች በዘራቸው/ በብሄራቸው፣በቋንቋቸው፣በፖሊቲካዊ አቋማቸው፣ በሀይማኖታዊ እምነታቸው እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን መድልዎ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ተግባር የእኩልነት መርህን ጥሰት የሚያስከትል፣መሰረታዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን አደጋ ላይ የሚጥል ህግን የሚቃረን አሰራር ነው፡፡ለምሳሌ፡- በኢፌድሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 25 ላይ የተደነገገውን የእኩልነት መብትን በመጣስ የሚከናወን ማንኛውም የመያዝና የማሰር ተግባር  አድልዎ መሰረት በማድረግ የተከናወነ ከህግ ውጭ እስር ነው ልንለው እንችላለን፡፡ማንኛውም ግለሰብ በህግ ክልከላ ያልተደረገበትን ተግባር(ግድፈት) በወንጀል ተጠርጥረኃል በሚል ሽፋን በዘሩ፣ በብሄሩ፣ በቀለሙ፣ በጾታው፣ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ በማህበራዊ አመጣጡ፣ በድህነቱ/በሃብቱ፣በትውልድ ቦታው ፣በፖለቲካዊ አመለካከቱ ወይም በሌላ  ግላዊ አቋሙ ምክንያት ብቻ ሊያዝ ወይም ሊታሰር አይገባም፡፡

  • ገደብ አልባ እስር (Indefinite Detention)

ካለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ  በውል ተለይቶ ላልታወቀ ጊዜ   ሰዎችን መያዝ እና ማሰር ከህግ ውጭ የማሰር ተግባሮች አንዱ ገፅታ ነው ፡፡ከዚህ በተጨማሪም ክስ ሳይቀርብ ወይም በዋስትና ጉዳይ ፍርድቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥ ሳይደረግ በፖሊስ ወይም በሌላ ባለስልጣን ትእዛዝ ብቻ ለረዥም ጊዜ ሰውን ማሰር(Detaining people with out the possibility of Charge and Bail)  ገደብ አልባ እስር ሊባል ይችላል፡፡ ፍርድቤቱ ከህግ ውጭ የታሰረን ግለሰብ ከእስር እንዲለቀቅ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ላልታወቀ ጊዜ የእስር ሂደቱ  ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህ ማለት  በመንግስት  ባለስልጣናት የሚፈጸሙ የእስር ተግባራት ብዙ ጊዜ ከፍርድቤት ትእዛዝ እና የቅጣት ውሳኔ ውጪ ስለሚከናወኑ ታሳሪዎች ከእስር የሚፈቱበት ጊዜ ሊያውቁ አይችሉም ፤ምክንያቱም  ሁሉም ነገር   በአንድ ባለስልጣን(ፖሊስ፣አቃቤ ህግ፡የፖለቲካ ሹመኛ ወዘተ…) ፈላጭ ቆራጭነት እና አምባገነናዊ ትእዛዝ ብቻ ስለሚከናወን ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድ ወቅት በሀገረ ሩዋንዳ  “በዘራቸው ምክንያት ኢ-ሰብአዊ አያያዝና ስቅያትን የሚያስከትል የድብደባ ወንጀል (Torture) የተፈጸመባቸው ዜጎች(በቱሲ እና በሁቱ መካካል በነበረው የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ቱሲዎች የደረሰባቸውን በደል በማስመልከት)  መንግሰትን በመቃወማቸው ምክንያት ካለምንም የፍርድቤት ውሳኔ በሀገሪቷ መንግስት ትእዛዝ ለረዢም ጊዜ መታሰራቸው   የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 6 ን የሚጥስ ከህግ ውጭ የተከናወነ ተግባር ነው” ሲል የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን   ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች አጠቃላይ የአንድ ሀገር ደካማ ስርአት እና ተቋማዊ አወቃቀር የፈጠሩት ችግር ሊሆን ይችላል፤ወይም ደግሞ ለሙያው ታማኝ የሆነ፣ነጻ እና ገለልተኛ ፖሊስ ፣አቃቤ ህግ፣ዳኛ ወይም ጠበቃ ያለመኖር ችግር የፈጠራቸው ሊሆንም ይችላል፡፡ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር ያለመኖር ወይም የአንድ መንግስት አምባገነናዊ ባህሪ የወለዳቸው ችግሮችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስለሆነም በአለምአቀፍ ህጎች ሆነ በሀገራት ብሄራዊ ህጎች የሰዎች መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶችን የሚያከብር እና የሚያስከብር የሰለጠነ የህግ  ባለሙያ መገንባት ፤የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሲያጋጥምም የህግ ተጠያቂነትን የሚዘረጉ የህግ ማእቀፎችና ጠንካራ ተቋማት እንዲኖሩ ማድረግ፤የመብቶቹ አከባበር እና አፈፃጸም የሚከታተል ወይም የሰብኣዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትም የሚጠየቁበት ሁኔታ በህግ መሰረት በአግባቡ  የሚከታተል ፣የሚያስፈጽም ፣የሚተረጉም እና ተገቢውን ቅጣት እና የእርምት እርምጃ  የሚወስድ ተቋማዊ እና ግለሰባዊ ነጻነቱን የጠበቀ የፍትህ አካል መኖር የግድ ይላል፡፡

በዚሁ መሰረት ሁሉም የአለም ሀገራት የሁሉም ሰዎች የነጻነት እና የአካል ደህንነት መብት በእኩል እንዲያከብሩ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ መብቶችን ጥሰው የተገኙ ሀገራት አለም አቀፍ ህጋዊ ሃላፊነት(Universal Legal Responsibility) ያስከትልባቸዋል፡፡ የነጻነት መብት ማለት ማንኛውም ሰው የእለት ተእለት የሂወት እንቅስቃሴው ውስጥ ካለምንም መሸማቀቅ እና ጣልቃ ገብነት ሙሉ የመንቀሳቀስ እና የመኖር  መብት የሚጎናፀፍበት የተፈጥሮ መብት ሲሆን  የደህንነት መብት ማለት ደግሞ ማንኛውም ሰው በሂወቱ ላይ ሊደርስበት የሚችል አደጋ ወይም ስጋት/ፍርሀትን መከላከል እና በነጻነት እንዲንቀሳቀስ መንግስታዊ ጥበቃ ወይም ዋስትና የሚያገኝበት ሆኖ የተያዘ ሰውም ቢሆን የአካል ደህንነቱን እንዲጠበቅ መንግስት እና የመንግስት አካላትን ግዴታ ውስጥ ማስገባትን የሚጨምር ተፈጥሮኣዊ መብት ነው፡፡በዚሁ መሰረት ሀገራት የማንኛውም ሰው የነፃነት እና የደህንነት መብት ለማክበር እና ለማስከበር ምክንያታዊ እና ተገቢ እርምጃ እንዲወስዱ አለም አቀፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡የነፃነት እና የደህንነት መብቶች በአጠቃላይ እንዲሁም እነዚህ መብቶችን የሚገደብባቸው ህጋዊ ምክንያቶችንና ልዩ ሁኔታዎችን ከአለም አቀፍ ህጎች፣ ከኢፌድሪ ህገ መንግስት እና ከወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ አንፃር እንደሚከተለው ይቃኛሉ፡፡

 

2)  አለም አቀፍ እና ብሄራዊ የህግ ማእቀፎች

የሰብአዊ መብቶች ሁሉ-አቀፍ መግለጫ

 

ይህ ሁሉ አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ በአንቀጽ 3 ላይ እያንዳንዱ ሰው የሕይወት ፣የነጻነት እና የተሟላ የድህንነት መብት እንዳለው ያሰፈረ ሲሆን በአንቀፅ 9 ደግሞ ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ ፣ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም በማለት በግልፅ ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ይህ ድንጋጌ በሌላ መልኩ ስናነበው-- ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ነፃነቱን ማጣት አይችልም የሚል አጠቃላይ መርህ ደነገገ እንጂ ሀገራት በህጎቻቸው ላይ በግልጽ ተለይተው በተቀመጡ ምክንያቶች እና በተዘረጉ የአያያዝ ስርአቶች መሰረት መያዝ ወይም ማሰር ክልክል ነው ማለት ግን አይደለም፡፡   

የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ ቃልኪዳን -

በዚህ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 9(1) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው የግል ነጻነቱ እና ደህንነቱ እንዲረጋገጥለት መብት አለው፡፡ማንኛውም ሰው ከህግ ውጭ አይያዝም ፣አይታሰርም ፡፡ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ምክንያት እና ስርአት ውጭ የግል ነፃነቱ አይገፈፍም፡፡ የተባበሩት የአለም ሃገራት ደርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ይህን አንቀጽ መሰረት በማድረግ የሰጣቸውን ትርጉሞችና አስተያየቶችን በጥቂቱ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡

ምሳሌ አንድ፡-አንድ ግለሰብ በከባድ የወንጀል ተግባር ተጠርጥሮ የተሰወረ ወንድሙን ፈልጎና መርቶ እንዲያስዝ ቢገደድም መፈጸም ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ ለአንድ ወር ቢታሰር ከህግ ውጭ መያዝና ማሰር በመሆኑ አግባብነት የሌለው ተግባርና የህጋዊነት መርህን የሚጥስ ነው ብሏል፡፡

ምሳሌ ሁለት፡-አንድ ግለሰብ የመያዣ ትእዛዝ ሳይቆረጥበት ወይም መጥርያ ሳይደርሰው ከተያዘ በኃላ ወደ ፍርድቤት ሳይቀርብ ለረዥም ጊዜ ማሰር የግለሰቡን የነፃነት መብትን ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ህገ-ወጥ የመያዝና የማሰር ተግባር ነው ብሏል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ግለሰብ በህጋዊ መልኩ ከተያዘ ወይም ከታሰረ በኃላም ቢሆን ፍርድቤቱ መለቀቅ አለበት ብሎ ካዘዘ በኃላ  በፖለቲካ ባለስልጣናት ወይም በሌላ አካላት ትእዛዝ ምክንያት በእስር ላይ እንዲቆይ ማድረግ ኢ-ህጋዊ ተግባር ነው ብሏል፡፡ 

) የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር (አንቀጽ 6)

ማንኛውም ሰው ነፃነቱ እና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው፡፡ቀድሞ በህግ በተደነገጉት ሁኔታዎች እና ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ነፃነቱን እንዲያጣ ሊደረግ አይችልም፡፡ በተለይም ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም፡፡

  • የአውሮፓ ሰብአዊ መብቶች መግለጫ እና የአሜሪካ ሃገራት ሰብኣዊ መብቶች መግለጫም ከላይ ከተጠቀሱት የህግ ማእቀፎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ ሆነ ሊታሰር እንደማይችል ደንግገዋል፡፡

) የኢፌድሪ ህገ መንግስት

የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 17(1) ስር እንደተመለከተው በህግ ከተደነገገው ስርአት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን /ቷን አያጣም /አታጣም በማለት ደንግጓል ፤በተጠቃሹ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር ሁለት ላይም ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርአት ውጭ ሊያዝ ፣ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሣይፈረድበት ሊታሰር አይችልም በማለት ደንግጓል፡፡

ሠ)የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት

 ማንኛውም  ሰው በህግ መሰረት ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው አንደኛ ሊያስይዘው ወይም ሊያስጠይቀው የሚችል የወንጀል ተግባር መፈጸሙ ሲረጋገጥ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተጠረጠረበትን/የተከሰሰበትን የወንጀል ተግባር በህግ መሰረት የሚያስይዘው/የሚያሳስረው መሆኑን ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 25፣ 26 እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው የስነስርአት ህጉ ድንጋጌዎች ይዘት እና መንፈስ ያስረዳሉ፡፡         

 በረቂቅ ደረጃ ያለው የወንጀል ስነስርአት እና የማስረጃ ህግ በአንቀጽ 8 ላይ ስለመያዝና ማሰር በሚል ርእስ ስር እንደተመለከተውም “ማንኛውም ሰው ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ ጥርጣሬ ሳይኖር ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረደበት ሊታሰር አይችልም” በማለት ደንግጓል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት አጠቃላይ መንግስታዊ ግዴታዎች የሚያስገነዝቡን፤  በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሰው ካለ ምንም ህጋዊ ምክንያት ሊያዝ ወይም ሊታሰር እንደማይችል የሚያስረዱና የተፈጥሮ ችሮታ የሆኑ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች እንዲከበሩ እውቅና የሚሰጡ  አለም አቀፍ ግዴታዎችና ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ህገ-መንግስቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህጎችም ከአለም አቀፍ ህጎችጋር ተመሳሳይ አላማ በመያዝ የተቀረፁ ናቸው፡፡

በዚሁ መሰረት የነጻነት መብት ህገ መንግስታዊ መብት ከመሆኑ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህጎች እና በሌሎች ዝርዝር የስነ ስርአት ህጎቿ ላይ በግልጽ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይህ መርህ በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 17፣ በአለም አቀፍ ፖሊቲካ እና ሲቪል ስምምነት ሰነድ አንቀጽ 9፤በሰብአዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 3 እና 9፣በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 25 እና 26 እንዲሁም በረቂቁ የወንጀል ስነ ስርአት እና የማስረጃ ህግ አንቀጽ 8 ላይ እና ሌሎች ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ህጎች ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግን አንድ ግለሰብ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የሚፈለግ ከሆነ  አጠቃላይ የህብረተሰቡ ሰላም እና  ደህንነት ለመጠበቅ  ሲባል በህግ ተለይተው በተቀመጡ ስነስርአታዊ አካሄዶች መሰረት መያዝ ወይም ማሰር ይቻላል፡፡

ይህ ማለት አንድ ግለሰብ ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው  በአንድ ፖሊስ የግል ፍላጎት ወይም በባለስልጣን ፈላጭ ቆራጭነት ወይም በማንኛውም ግለሰብ ጥላቻዊ ጥቆማ ወይም ቂም በቀልነት ሳይሆን ጉዳዩ በአንድ ምክንያታዊ ታዛቢ ሰው ሲለካ እንዲሁም በግልጽ እና በሚያሳምን ሁኔታ እውነታዎቹ ሲታዩ እና ማስረጃዎቹ ሲመዘኑ ወይም ሲመረመሩ ለማስያዝ እና ለማሳሰር በቂ ሆኖው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ዝቅተኛ የህግ ግንዛቤ እና እውቀት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሃገራት ማሰር እና መያዝ  ካለምንም ገደብ እና ቅድመ ሁኔታ በዘፈቀደ ለፖሊስ የተሰጠ ስድ እና ያልተገራ ስልጣን የሚመስለው የህብረተሰብ ክፍል ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ብዙዎቻችን ደንብ ልብስ ለብሶ ካቴና ይዞ የመጣ ፖሊስ ሁሉ ህግን እያስከበረ ነው የሚል የተሳሳተ ህብረተሰባዊ እምነት እና ልማዳዊ አሰራር  ስለምናራምድ እና  ለዚሁ ጸረ-ነጻነት የሆነውን አሰራር ተገዢ ስለምንሆን  ለመብታችን ስንታግል አይታይም፡፡  ይህ ስል  ግን ራሳችንን  ከህግ ውጭ በማድረግ ለሚደርስብን ኢ-ፍትሀዊ ተግባር ኢ-ፍትሀዊ ግብረመልስ እየሰጠን ወደአላስፈላጊ እሰጣ እገባ እና ንትርክ ውስጥ በመግባት በህግ አስከባሪ አካላት ላይ ችግር የመፍጠር መብት አለን ለማለት  ሳይሆን ብያንስ ግን በህግ እና በመብታችን ላይ የተሟላ እውቀትና ግንዛቤ ኖሮን ህግን መሰረት በማድረግ መጓች እና ንቁ ዜጋን በመፍጠር አምባገነን መንግስትን እና ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣንን የምንከላከልበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ መንግስት ጠንካራ ስርአት እና ተቋም እንዲመሰርት፤ተጠያቂነት እና ሃላፊነት መሰረት በማድረግ ስራውን የሚያከናውን ባለሙያ(ባለስልጣን) እንዲኖር መንግስት በአንክሮና በቁርጠኝነት እንዲሰራ በር ለመክፈት ያስችላል፡፡

ስለሆነም አንድ ግለሰብ ሊታሰር የሚችለው በልዩ ሁኔታ በህግ መሰረት በግልጽ ተለይተው በተቀመጡ ዝርዝር ምክንያቶችና አካሄዶችን በጥብቅ በመከተል  ብቻ ሲሆን ኢትዮጵያም ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር ተመሳሳይ አቋም እና ይዘት ያላቸው ድንጋጌዎች በብሄራዊ ህጎቿ ላይ አስፍራለች፡፡  በዚሁ መሰረት አንድ ግለሰብ ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው በሚከተሉት ምክንያቶች ብቻ ነው፡፡

በወንጀል ተግባር ሲጠረጠር-

ማንኛውም ሰው ወንጀል ሊመፈጸም በሙከራ ላይ እያለ ፣ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ ጥርጣሬ መኖሩ  ወይም የወንጀል ተግባርን ሲፈፅም እጅ ተፍንጅ  ከተያዘ፣ወይም በህግ መሰረት ወንጀልን ለመፈጸም የመሰናዳት ተግባራት ያስቀጣሉ ተብለው በተደነገጉ ጉዳዮችን እንዳይፈጸሙ ለማስቆም/ለመከላከል በማሰብ እና ለዚሁም በቂ በሚባል ሁኔታ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር በህግ ተለይተው በተቀመጡ ስነስርአታዊ አካሄዶችን በጥብቅ በመከተል መያዝ ወይም ማሰር ይቻላል፡፡በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 17 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው ካለ ፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም ፡፡ሆኖም በህጉ መሰረት ተለይተው በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት አንድ በወንጀል የሚፈለግ ሰው ካለ፤ በፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ሊውል እንደሚችል፡ በዚሁ የህገ-መንግስት ድንጋጌ ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ አንድ በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረ ሰው የሚያዝበት ስርአትስ እንዴት ነው የሚል ጥያቄ መመለሱ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት በአንድ በኩል የተገራ  የፖሊስ ተግባር እንዲኖር እና ህግን የማስከበር ሃላፊነት በአግባቡ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የልተገራና እና ልቅ የሆነ ነፃነትን ከመገደብ አንጻር የሚፈጥረው ሚዛናዊ አካሄድ  የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ስለሚኖሮው በህግ የሚፈለግ ሰው የሚያዝበት አግባብ አጠር አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተለው  ማየቱ ይጠቅማል፡፡

1. መጥርያ

በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረ ግለሰብን  በመጀመርያ ደረጃ  ፖሊስ በመጥርያ  እንዲያቀርብ ማድረግ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ለምሳሌ ፖሊስ ፍርድቤት ድረስ በመሄድ ፍቃድ ለማግኘት የሚያባክነው ጊዜ እና ጉልበት ይቀንስለታል፤ተጠርጣሪው በመጥርያ የሚቀርብ ከሆነ በፖሊስ ላይ ሊያደርሰው የሚችል ተቃውሞ ሆነ ለህግ  አልታዘዝም ባይነት አይኖርም፤በሌላ አገላለጽ ተጠርጣሪው በፍላጎቱ እስከ ቀረበ ድረስ በህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ሊያደርሰው የሚችል ጥቃት ወይም ተቋውሞ አይኖርም…. ወዘተ፡፡ እንደ እነ እንግሊዝ የመሳሰሉ የኮመን ሎው የህግ ስርአት የሚከተሉ ሃገራት  በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረ ግለሰብ በፖሊስ መጥርያ ከቀረበ ፍርድቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ እስከሚሰጥ  ድረስ  አይታሰርም፡በሙሉ ነፃነት እና ካለምንም ገደብ በውጭ ሁኖ ወደ ፍርድቤት እየተመላለስ ጉዳዩን እንዲከታተል ፍርድቤቱ ይፈቅድለታል፡፡ በኢትዮጵያ የህግ ስርአት ግን ለቀላል ወንጀሎች ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥሮ በፖሊስ መጥርያ መሰረት ቢቀርብም ሊታሰር ወይም በገደብ-ለምሳሌ በዋስትና -ሊለቀቅ ይችላል እንጂ በፖሊስ መጥርያ በመቅረቡ ብቻ ላለመታሰሩ ዋስትና ሊሆነው አይችልም ፡፡መርማሪ ፖሊስ በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረን ግለሰብ በመጥርያ ይቀርባል ብሎ ግምት ከወሰደ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት አንቀጽ 25 መሰረት መጥርያ ማድረስ ይችላል፡፡በዚሁ መሰረት የቀረበ ተጠርጣሪ የተጠረጠረበትን የወንጀል ተግባር ክብደቱ እና ቅለቱ ታሳቢ በማድረግ ፖሊስ በራሱ ህጋዊ  ስልጣን ተጠርጣሪውን በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት አንቀጽ 28 መሰረት በዋስትና መልቀቅ ወይም ተጠርጣሪውን ከተያዘበት ሰአት ጀምሮ በሚቆጠር በ 48 ስአታት ውስጥ ወደ ፍርድቤት በማቅረብ በዋስትና ላይ እልባት እንዲያገኝ ከልብ የመነጨ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ 

2. የመያዣ ትእዛዝ

ፖሊስ የመያዣ ትእዛዝ በማውጣት ተጠርጣሪን መያዝ የሚችለው ተጠርጣሪው  በመጥርያ ለመቅረብ ፍቃደኛ ሣይሆን ሲቀር ወይም እንደማይቀርብ እርግጠኛ ሲሆን ብቻ መሆን አለበት፡፡የመያዣ ትእዛዝ የሚፈቀድበት መደበኛ  ስነ ስርአት በወንጀለኛ  መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 53 እና 54 ላይ በግልጽ የተደነገገ ሲሆን በዚሁ መሰረትም ማንኛውም ፍርድቤት ትእዛዙን የመስጠት ስልጣን ቢኖሮውም በመርማሪ ፖሊስ የቀረበ ጥያቄ ሳይኖር ግን  መስጠት አይችልም፡፡መርማሪ ፖሊስ የመያዣ ትእዛዝ መጠየቅ የሚችለውም አንደኛ ተጠርጣሪው በፍርድቤት መቅረቡ ፍጹም አስፈላጊ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ተጠርጣሪው ወደ ፍርድቤት የሚቀርብበት ሌላ አማራጭ አለመኖሩን መረጋገጥ ሲቻል  ብቻ ነው፡፡የተጠርጣሪው መቅረብ ፍጹም አስፈላጊነት(The criterion of Absolute Necessity) እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠበት ዋና ምክንያት ተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸሙ የሚያሳዩ መነሻ ማስረጃዎች (Minimum standards of evidences) ስለመኖራቸው በገለልተኛ ፍርድቤት እንዲረጋገጥ በማሰብ ነው፡፡በሌላ አነጋገር ማንኛውም ሰው በስስ ማስረጃ ወይም ካለምንም ማስረጃ እንዳይያዝ /እንዳይታሰር ለመከላከል ፍርድቤቱ በመርማሪ ፖሊስ በኩል የሚቀርብ የእስር መያዣ ማመልከቻን በአግባቡ እንዲመረምር  ስለሚፈለግ ነው፡፡ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ማረጋገጡ ያስፈለገበት ዋና አላማ ደግሞ ተጠርጣሪው መርማሪ ፖሊስ የሚያደርስለትን መጥርያ ሣይቋወም ህግን አክብሮ የሚቀርብበት ሁኔታ ካለ እድሉን ለመጠቀም ሲሆን ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት  የመጥርያ ጠቀሜታ ከአዘገጃጀቱ፣ አደራረሱና ውጤቱ አንፃር ሲለካ በፍትህ ዘርፉ ላይ የላቀ አስተዋፅኦ ስላለው የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ከመውጣቱ በፊት መጥርያ የመጀመርያ አማራጭ እንዲሆን ስለተፈለገ ነው፡፡     

3. ያለመያዣ ትእዛዝ

ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ካለ ፍርድቤት ትእዛዝ ሊያዝ እንደሚችል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 17 እና በተለያዩ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ድንጋገጌዎች ላይ በግልፅ ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡ከእነዚህ መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉት የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች (Flagrant Offences) ናቸው፡፡የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች በትርጉም ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 19 እና 20 ላይ የተቀመጡ ሲሆን ስነስርአታዊ ውጤታቸው ደግሞ በአንቀጽ 20 እና 50 ላይ በግልጽ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡በተጨማሪም ተጠርጣሪው ወንጀሉን ሲፈጽም እጅ ተፍንጅ ባይያዝም እንኳ የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ እስከሚወጣበት ድረስ ሊሰወር ወይም ሊያመልጥ ይችላል ተብሎ ለመገመት የሚያስችሉ አመላካች(ጠቋሚ) መረጃዎች ካሉ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ባገኘበት ቦታ መያዝ ይችላል፡፡ለምሳሌ ከሃገር ለመሸሽ ሙከራ ሲያደርግ ከተያዘ ፖሊስ ለጊዜው  የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ማውጣት ሳይጠበቅበት ሌሎች በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ ላይ የተቀመጡትን  ህጋዊ ጥንቃቄዎችና  እርምጃዎችን በመከተል ከፍትህና ህግ ለማምለጥ የሚሞክር ማንኛውም ተጠርጣሪን መያዝ ይችላል፡፡      

) ስልጣን ባለው ፣ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ ፍርድቤት ሲፈረድበት ወይም ሲወሰንበት

አንድ ተጠርጣሪ በአንድ የወንጀል ተግባር ተጠርጥሮ ህጉና ስነ ስርአቱ በሚፈቅደው መሰረት በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ በፍርድቤት የመጨረሻ ውሳኔ  ተወስኖበታል ማለት አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው በከባድ የወንጀል ድርጊት እንኳ ቢጠረጠር ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠርና ወደ ፍርድቤት ለማድረስ የሚፈጀው ጊዜ ሣይታሰብ በ48 ስአታት ውስጥ  ፖሊሰ  ተጠርጣሪን ወደ ፍርድቤት የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡አንድን ተጠርጣሪ ወደ ማረሚያቤት እንዲላክ ፣በነፃ እንዲለቀቅ፣ በገደብ እንዲፈታ ወይም በዋስትና እንዲወጣ ማዘዝ የሚችለው ስልጣን ያለው፣ነፃና ገለልተኛ የሆነ ፍርድቤት ሲወስን ብቻ ነው፡፡በሌላ አነጋገር የፖሊስ መጥርያ ደርሶት በፍላጎቱ የቀረበ ተጠርጣሪ ይሁን በፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ወይም ካለምንም የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ለፖሊስ እጁን የሰጠ ተጠርጣሪ ነፃነቱን ተገፎ ወደ ማረሚያ ቤት የሚላከው ፍርድቤቱ እንዲታሰር ሲወስንበት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚከናወን የእስር ተግባር ህጋዊ አይደለም፡፡

መደምደሚያ

ማንኛውም ሰው በመንግስት አካላት ሆነ በሌላ ማንኛውም ሰው ሊታፈን፣ሊጣስ ፣ሊገፈፍ ወይም ሊገሰስ የማይችል በተፈጥሮ የታደለው የነጻነት እና የደህንነት መብት ቢኖሮውም ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው  አለም አቀፍ እና አህጉራዊ  የሰብአዊ መብቶች  ህግጋት እንዲሁም በኢፌድሪ ህገ መንግሰት በተደነገገው አጠቃላይ መርህ እና ይህን የበላይ ህግ መሰረት በማድረግ በወጡ ግልጽ ህጎች እና ስነስርኣታዊ ሂደቶች  የነፃነት መብት  ሊገደብ የሚችልባቸው  ምክንያቶች በግልፅ ተደንግገዋል፡፡

ሀገራት ነፃነትን በመገደብ ሰውን መያዝ እና ማሰር የሚችሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካገኙ የሰብኣዊ መብቶች ህግጋት እና እነዚህ  መሰረታዊ እና ስነስርአታዊ ህግጋትን ጋር በሚጣጣም መልኩ በብሄራዊ ህጎቻቸው ላይ በተደነገጉት  ግልጽ ህጎች እና ስነስርአታዊ አካሄዶች መሰረት በማድረግ መሆን ስላለበት ህግን በማክበር እና ስርአትን በጥብቅ በመከተል ብቻ  መሆን ይኖርበታል፡፡ከዚህ ውጭ የሚከናወን የመያዝ እና የማሰር ሂደት ብሄራዊ እና አለም አቀፋዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም ሰዎችን የመያዝ እና የማሰር  ስልጣን ምንም አይነት ምክንያት ሳይኖር  በዘፈቀደ የሚከናወን ገደብ አልባ ተግባር አይደለም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በግልጽ  የተጣሰ የህግ ድንጋጌ እና የተፈጸመ የወንጀል ተግባር መኖር አለበት፡፡ በመቀጠል ከፖለቲካዊ ሴራ እና ጥቃት የፀዳ፣ምንም አይነት አድልዎ የሌለበት፣ ምክንያታዊነቱ  እና  አስፈላጊነቱ ከአጠቃላይ የህዝብ ጥቅም አንጻር ተለክቶ ህግ እና ህግን ብቻ የተከተለ መሆን አለበት ፡፡ በሌላ አገላለጽ አንድን ግለሰብ ለመያዝ ወይም ለማሰር የህጋዊነት መርህን መከተል እንደተጠበቀ ሁኖ ህጎች እና የህጎች ተፈጻሚነትም ፍትሃዊ እና ከምንም አይነት አድልዋዊ አሰራር ነጻ ለማድረግ  ተገቢነት ያላቸው እና ከኢ-ምክንያታዊት የፀዱ (Appropriate and Reasonable) ፣ተገማችነት እና ተመጣጣኝነትን (Foreseeable and Proportionality)  እንዲሁም ህግን የተከተለ አሰራር (Due Process of Law) መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን  ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡

ለምትሰጡኝ  ገንቢ አስተያየቶችን ከወዲሁ እያመሰገንኩኝ በሌላ ጽሁፍ እስክንገናኝ ሰላም!   

Read 10941 times Last modified on Feb 27 2019
ገብረእግዚአብሔር ወልደገብርኤል

ጸሐፊው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዓቃቤ ሕግ ሲሆኑ በስልክ ቁጥር -0914505008, 0947931110 ወይም ኢ-ሜይል wgebregziher@gmail.com ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡