Print this page

ጥንቃቄ የሚያሻው የወንጀል ስፍራ ምርመራ

Jul 30 2018

 

ይህንን ጽሑፍ እንዳስቀምጥ የገፋፋኝ ምክንያት በተደጋጋሚ በሀገራችን እያስተዋልኩት ያለው ጥንቃቄ ያልተሞላበት፣ በግድየለሽነት ላይ የተመሠረተ የወንጀል ስፍራ ምርመራ በማየቴ ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ በመስቀል አደባባይ ሁለት ትላልቅ ወንጀሎች ተፈፅመው የወንጀል ስፍራ ጥበቃው እና ምርመራው ክፍተት ያለበት፣ በሳይንስ ያልተደገፈ እና በቀጣይ ለሚካሄደው የታክቲክም ሆነ የቴክኒክ ምርመራዎች አሉታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በማየቴ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በዝች አጭር ጽሑፍ ስለ ወንጀል ስፍራ ምንነት፣ የወንጀል ስፍራ ጠቀሜታ፣ የወንጀል ስፍራ አጠባበቅ እና ተያያዥነት ያላቸውን ሃሳቦች በማንሳት እንደሚከተለው ቀርባል፡፡

የወንጀል ስፍራ ምንነት

የወንጀል ስፍራ ማለት ወንጀል የተፈፀመበት ቦታ ሆኖ ለወንጀል ምርመራው ጠቀሜታነት ያላቸው አካላዊና ሌሎች ማስረጃዎች ሊገኙበት የሚችል ሥፍራ ነው፡፡

የወንጀል ስፍራ ሰፋ ተደርጎ ሲገለፅ ወንጀሉን ለመፈፀም ዝግጅት የተደረገበት ቦታ፣ በተግባር ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታ እና ወንጀሉ ከተፈፀመ በኃላ ተጠርጣሪዎች ያመለጡበት ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ብዙውን ጊዜ ወንጀሉ በተግባር የተፈፀመበት ቦታ እንደ ዋና የወንጀል ስፍራ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ወንጀል በተለያየ ቦታ ሊፈፀም ይችላል ለምሳሌ በቤት ውስጥ፣ ከቤት ውጭ፣ በመኪና ውስጥ፣ በባቡርጣቢያ፡፡

የወንጀል ስፍራ ጠቀሜታ

የወንጀል ስፍራ ከተፈፀመው ወንጀል ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ማስረጃዎች ለመሰብሰብ ዋነኛ ምንጭ ነው፡፡ በተለይ አካላዊ የሆኑ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ተመራጭ ቦታ የወንጀል ስፍራ ነው፡፡

የወንጀል ስፍራ ተጠርጣሪው ከወንጀል ስፍራው ጋር ያለውን  ግንኙነት ለማወቅ ይረዳል፡፡ ይህ ማለት ጥንቃቄ የተሞላበት የወንጀል ስፍራ ጥበቃ እና ምርመራ ከተከናወነ ተጠርጣሪውን ከተጎጂው ወይም ተጠርጣሪውን ከወንጀል ስፍራው ጋር ማገናኘት የሚችሉ እና በቀጣይ ለሚደረገው ምርመራ ማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉ አካላዊ ማስረጃዎች ማግኘት ይቻላላ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዋቂው የፎረንሲክ ሳይንስ ባለሞያ እና የመጀመሪያውን የፎረንሲክ ላብራቶሪ የከፈተው ዶክተር ሎካርድ አንድ መሠረታዊ መርህ አስቀምጣል፡፡ ሁለት ነገሮች ቢጋጩ በተጋጩበት ቦታ ላይ የሆነ ነገር ጥለው ይሄዳሉ ከዚህ በተጨማሪ አንዱ አካል ከሌላው ይዞት የሚሄደው ነገር ይኖራል ይላል፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም ወንጀል በወንጀል ስፍራው ላይ፣ ከተጎጂው ላይ ወይም በተጠርጣሪው ላይ ጠቃሚ እና ለቀጣይ ምርመራ ሊያግዙ የሚችሉ አካላዊ ማስረጃዎች ጥሎ ይሄዳል ማለት ነው፡፡

በዚህ መሠረት ዶክተር ሎካርድ እንደሚያስቀምጠው እነዚህን አካላዊ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ እና እውነቱን የማግኘት ሥራ የመርማሪው ብቃት እና የሚጠቀማቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ስለዚህ አንድ ወንጀል ለመፈፀም ምንም እንኳን ከባድ የሆነ ጥንቃቄ ቢደረግም በወንጀል ስፍራው፣ በተጠርጣሪው ወይም በተጎጂው ላይ ጠቃሚ የሆኑ አካላዊ ማስረጃዎች መገኘታቸው የማይቀር ነው፡፡

ሆኖም አንድ ነገር መታወቅ ያለበት የወንጀል ስፍራውን አንዴ መርማሪው ለቆ ከሄደ በኋላ ተመልሶ መጥቶ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ልሰብስብ ቢል እጅግ በጣም ከባድ እና አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የወንጀል ስፍራው በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥራዊ ምክንያቶች ሊበላሽ እና ሊጠፋ ይችላል፡፡

በተለይ በቅርቡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላ የተፈፀሙት ወንጀሎች የወንጀል ስፍራ እጅግ በጣም ሰው እና መኪና የሚበዛበት ስለሆነ አካላዊ ማስረጃዎቹ በቀላሉ ሊበከሉ እና ሊበላሹ ስለሚችሉ ተመልሶ መጥቶ ተጨማሪ አካላዊ ማስረጃ ለመሰብሰብ ጥረት ማድረግ እጅግ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪው ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ጠቃሚ የሆኑ አካላዊ ማስረጃዎች በአግባቡ ሊሰበሰቡ ይገባል፡፡

ወንጀል ስፍራን እንዴት መጠበቅ ይቻላል

ወንጀል በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት ብዙውን ጊዜ ወንጀል ከተፈጸመ በኃላ መጀመሪያ የሚደርሰው አካል የአካባቢው ማህበረሰብ፣ ቤተሰብ ወይም በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ያለ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ሰዎች  ብዙውን ጊዜ ስለወንጀል ስፍራ ጥበቃ እና ምርመራ በቂ እውቀት ስለማይኖራቸው እና ትኩረታቸው የተፈፀመው ወንጀል ላይ ስለሚሆን በአካባቢው ያሉትን አካላዊ ማስረጃዎች በአግባቡ ላይገነዘባቸው ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግድየለሽነት እና ባለማወቅ እነዚህን አካላዊ ማስረጃዎች ሊበክላቸው እና ሊያበላሻቸው ይችላሉ፡፡

ስለዚህ እነዚህ የወንጀል ስፍራው ላይ መጀመሪያ የሚደርሱ ሰዎች ተጎጂው መሞቱን ካረጋገጡ በተቻለ መጠን በአካባቢው ያሉ የፀጥታ አካላት እንዲመጡ መረጃ ማስተላለፍ እና በአካባቢው ያሉ አካላዊ ማስረጃዎች እንዳይጠፉና እንዳይበላሹ ጥበቃ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ወንጀሉ ተፈፅሞ በአካባቢው ሊደርሱ የሚችሉ አካላት በአካባቢው ያሉ የወንጀል መከላከል ሥራ እያከናወኑ ያሉ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት አነሰም በዛም መሠረታዊ የወንጀል ስፍራ ጥበቃ እና ምርመራ ትምህርት ወስደዋል ተብሎ ይገመታል፡፡

በዚህ መሠረት  ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታ ላይ ሲደርሱ መጀመሪያ ማከናወን ያለባቸው አካባቢውን በጥሞና መመልከት ሲሆን ይህም በወንጀል ስፍራው ሌላ ተጨማሪ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ነገር መኖር እና አለመኖሩን እንዲለዩ ይረዳቸዋል፡፡ ከዛም በአካባቢው ሌላ ተጨማሪ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ከሌላ በወንጀል ስፍራው የተጎዱ እና የመጀመሪያ ህክምና ለሚስፈልጋቸው ተገቢውን እርዳታ እና ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የወንጀል ስፍራው ላይ መጀመሪያ የሚደርስ ሰውም ይሁን ፖሊስ የመጀመሪያው ሥራ መሆን ያለበት ህይወት ማዳን ነው፡፡ የተጎጂው ወይም ወንጀሉን የፈፀመው ግለሰብ ህይወት ከዳነ በቀጣይ ለሚደረገው የምርመራ ሥራ ጠቀሜታ ያላቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎችን መሰብሰብ ይቻላል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሐምሌ 19/2010 ዓ.ም የተፈፀመው ወንጀል ላይ ያለኝን ትዝብት በተመለከተ፤ በመስቀል አደባባይ አካባቢ ሰው መሞቱን እና ወንጀል መፈጸሙን መጀመሪያ ማን እንዳየ ግልጽ ባይሆንም በአካባቢው የወንጀል መከላከል ሥራ የሚሰሩ አባላት ስላሉ እነሱ ቀድመው ይደርሳሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ እነዚህ የወንጀል መከላከል አባላት ብዙውን ጊዜ ሁለት በመሆን ስለሆነ የሚንቀሳቀሱት የወንጀል ስፍራው ላይ እንደደረሱ አንደኛው ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የመኪናውን በር በመክፈት ተጎጂው መሞት እና አለመሞቱን ሲያረጋግጥ ሌላው በአካባቢው ካለው ሰው ጋር በመሆን ሰዎች ወደ ወንጀል ስፍራው እንዳይገቡ መከላከል ይችላል፡፡ ሆኖም ከተለያዩ ሚዲያዎች እንዳየነው እና እንደሰማነው ከሆነ ወንጀል ተፈፅሟል የተባለው በተዘጋ መኪና ውስጥ ስለሆነ የተጎጂውን ሕይወት ማለፍ እና አለማለፉን ማወቅ ትንሽ ከባድ ያደርገዋል፡፡

 

በዚህን ጊዜ መጀመሪያ የደረሱት የወንጀል መከላከል አባላት ሥራ መሆን ያለበት የተጎጂውን ሁኔታ በመስታወት አይቶ በህይወት መኖር እና አለመኖሩን በመገመት የወንጀሉን ሁኔታ በስልክ በማስተላለፍ ተጨማሪ ሃይል እስከሚመጣ ድረስ የወንጀል ስፍራውን በአግባቡ መጠበቅ እና በአካባቢው ያሉ አካላዊ ማስረጃዎች እንዳይጠፉ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል የወንጀል ስፍራ መርማሪዎች በአካባቢው ሲደርሱ ያዩትን፣ የሰሙትን እና ያሸተቱትን ነገሮች ለመርማሪዎቹ ማካፈል እና የወንጀል ስፍራውን የመጠበቅ ሥራ በአግባቡ ማከናወን ይሆናል፡፡

በወንጀል ስፍራው በሶስተኛ ደረጃ ሊደርሱ የሚችሉት የወንጀል ስፍራ መርማሪዎች እና ተጨማሪ የፖሊስ ሃይል አንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሠረት ወደ ወንጀል ስፍራው ሊገቡ የሚችሉት ይህንን ወንጀል የመመርመር ስልጣን ያላቸው ባለሞያዎች ብቻ መሆን አለባቸው፡፡ ለወንጀል ምርመራው ስኬታማነት ወይም ድክመት ሊጠየቁ የሚገባው እነሱ ስለሆነ ከነሱ ውጭ ወደ ወንጀል ስፍራው ማንም ሊገባ አይችልም፡፡

በሃገራችን በሚታዩ የወንጀል ስፍራ ምርመራ ላይ ከሚታዩ ችግሮች አንዱ በወንጀል ስፍራው ላይ ሁሉም አካላት መግባት እና መውጣቱ ነው፡፡ በሐምሌ 19/2010 ዓ.ም  የተፈፀመውን ወንጀል በምሳሌነት ቢነሳ ተፈፅማል የተባለው ወንጀል ግድያ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ በአዲስ አበባ የግድያ ወንጀል ሲፈፀም የመመርመር ስልጣን ያለው ማነው የሚለውን መገንዘብ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሞተው ማነው የሚለውን ማወቅ የትኛው አካል የመመርመር ስልጣን አለው የሚለውን ለማወቅ ይረዳል፡፡

ሆኖም ከላይ በተፈፀመው ወንጀል ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደተመለከትኩት የተለያዩ የፖሊስ አካላት፣ የመንግስት ሃላፊዎች እና የመከላከያ ሰራዊት ጨምሮ በወንጀል ስፍራው ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ በጣም የሚገርመው የወንጀል ስፍራ መርማሪዎቹ ሙሉ የወንጀል ስፍራ መፈለጊያ ልብስ እንካን አልለበሱም ለምልክት ከላይ የሚለበስ እና አፍና አፍንጫቸውን ብቻ ሸፍነው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በወንጀል ስፍራው ላይ ያሉትን አካላዊ ማሰረጃዎች በአግባቡ እንዳይሰበሰቡ፣ እንዲበላሹ እና እንዲጠፉ ያደርጋቸዋል፡፡

 

በወንጀል ስፍራ ምርመራ የህዝብ ተሳትፎ አስፈላጊነት

በቴክኒክም ሆነ በታክቲክዊ የወንጀል ምርመራ ሂደት የህዝብ ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ማንኛውንም ወንጀል መመርመር እና እውነት ላይ መድረስ እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡

በዋነኝነት በወንጀል ስፍራ ምርመራ ወቅት የህዝብ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው፡፡ በወንጀል ስፍራው ከሚደረገው የአካላዊ ማስረጃ ፍለጋ እና ማሰባሰብ ጎን ለጎን የታክቲክ ምርመራም ይከናወናል፡፡ ይህ ማለት ወንጀሉ ሲፈፀም በአካባቢ ያዩ ወይም ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ቀድመው በቦታው ከተገኙ ሰዎች ስላዩት እና ስለሰሙት ነገሮች ሃሳባቸውን መቀበል ስፈልጋል፡፡ የህዝብ ተሳትፎ የሚያስፈልግበት ብዙውን ጊዜ ማንኛውም የወንጀል ድርጊት ሲፈፀም በድርጊቱ ቦታም ሆነ በአካባቢው ከፖሊስ ቀድሞ የሚገኘው ህዝብ በመሆኑ ነው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው ቀድሞ የሚደርስ ሰው ፖሊስ እስኪመጣ ማስረጃዎች እንዳይበላሹ የወንጀል ስፍራውን በአግባቡ ሊጠብቅ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የወንጀል ስፍራ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ አካላዊ ማስረጃዎች የሚገኙበት እና በቀጣይ ለሚደረገው ምርመራ አጋዝ የሆኑ ማስረጃዎች የሚገኝበት ቦታ ስለሆነ የፍትህ አካላቱም ሆነ ማህበረሰቡ ተገቢውን ጥበቃ እና ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡

 

Read 9278 times Last modified on Jul 30 2018
በኃይሉ ግርማ

ጦማሪው ከመቀሌ ዩንቨርስቲ በ2000 ዓ.ም በህግ የመጀመሪያ ድግሪ፣ በ2006 ዓ.ም በወንጀል ፍትህ ስርዓት እና በሰብዓዊ መብት ከባህር ዳር ዩንቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ሰርቷል፡፡ በአሁኑ ሰኣት በኢትዩጵያ ፖሊስ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ በወንጀል ምርመራ ዲፕሎማ ፕሮግራም ማናጀር እና በመምህርነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ጽሐፊውን በኢሜል አድራሻው destabehaylu@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡