Print this page

በስህተት ወንጀልን ስለመፈፀም ከህግ አንፃር

Mar 27 2018

 

 

 1. መግቢያ

ወንጀል በአጠቃላይ ፀር መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከክቡር የሰው ህይወት አንስቶ፣ ጤንነትን፣ ክብርን፣ ደህንነትን፣ ንብረትን፣ አስተሳሰብን፣ ሰላምንና አጠቃላይ የሀገርን ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ጥቁም ባህላዊ መረጋጋቶች ላይ ጥላ የሚያጠላና የሚያናጋ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት ጥበቃ የሚያደርጉ የተለያዩ ህጎች ቢኖሩም የወንጀል ህግ አይነተኛ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የወንጀል ህግ ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥበቃዎችን በሚያደርግበት ወቅት የማህበረሰቡንና የግለሰብን (ወንጀል አድራጊን) መብት ባማከለ መልኩ የሚቀረፀም የህግ አይነት ነው፡፡ በህግ ፍልስፍናውም ሆነ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ላይ ይህ አይነት ሚዛናዊነት (Balance) በአግባቡ የሚነሳና የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ከእነዚህ ሚዛናዊነት መካከል የግለሰቦች ነፃ ሆኖ የመገመት መብት (presumption of innocence) አይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከአለም አቀፍ ስምምነቶች እንደ International Convention on Civil and Political Rights (ICCPR)  እና በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 14(2) እና 20(3) እንደቅደም ተከተላቸው ነፃ ሆኖ የመገመት መብት ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑን ማየት እንችላልን፡፡ ነፃ ሆኖ የመገመት መብት የሚዘልቀው ወንጀል አድራጊው በፍ/ቤት ጥፋተኛ እስኪባል ድረስ ሲሆን እስከዚያ ድረስ ወንጀለኛ ተብሎ ሊጠራም ሆነ እንደወንጀለኛ ሊታይና ሊስተናገድ አይችልም፡፡ አንድ ግለሰብ ደግሞ በፍ/ቤት ጥፋተኛ የሚባለው ወንጀሉን መፈፀሙ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ወንጀል ተፈፀመ የሚባለው ደግሞ በወንጀል ህጋችን አንቀፅ 23(2) መሰረት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ነው፡፡

እያንዳንዱ ፍሬ ነገር ሰፊና ጥልቅ ሀሳብ ያዘሉ በመሆኑ ለዚህ ፅሁፍ አላማ ሲባል አጭር ማብራሪያ ብቻ ቀርቧል፡፡

 1. ወንጀልን ስለሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች

  • ሕጋዊ ፍሬ ነገር

ሕጋዊ ፍሬ ነገር የሚባለው ባጭሩ የሚከለክል ወይም የሚያስገድድ ህግ ሊኖር እንደሚገባ የሚያትት መርህ ነው፡፡ ለምሳሌ መስረቅ ክልክል እንደሆነ ካልተደነገገ የሌላን ግለሰብ ንብረት ያለፈቃድ መውሰድ ወንጀል ሊያሰኘው አይችልም፡፡ ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያክል ግብር መከፈል እንዳለበት የሚደነግግ ህግ ከሌለ ግብር አለመከፍል ጭራሹን ወንጀል ሊሆን አይችልም፡፡

 • ግዙፋዊ ፍሬ ነገር

ግዙፋዊ ፍሬ ነገር የሚባለው ደግሞ በወንጀል ህግ የተደነገገውን ወይም ከላይ ሕጋዊ ፍሬ ነገር ያልነውን መጣስ ነው፡፡ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ወይም ድርጊት የሚባለው በህግ አድርግ የተባለውን አለማድረግ (Omission) ወይም አታድርግ የተባለውን ነገር ማድረግ (Commission) ነው! ለምሳሌ፡- ከበደ 500 ብር ከአለማየሁ ቢወስድ፤ ያለአለማየሁ ፈቃድ መውሰዱ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ወይም በማድረግ የሚፈፀም ድርጊት ነው (crime by commission) ፡፡ አለማየሁ ግብር መክፈል እያለበት ባይከፍል፤ ግብር አለመክፈሉ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ወይም ባለማድረግ የሚፈፀም ድርጊት ነው (crime by omission) ፡፡

 • ሞራላዊ ፍሬ ነገር

ሞራላዊ ፍሬ ነገር ወይም ወንጀልን የማድረግ ሀሳብ ሲባል ሊጨበጥ፣ ሊዳሰስ ሊታይ የማይችል በወንጀል አድራጊ አስተሳሰብ ላይ ያነጣጠረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ሲባል ግዙፋዊ ፍሬ ነገሩን ያደረገው አስቦ፣ ቸልተኛ ሆኖ ወይም ያለሀሳቡና ያለቸልተኛነቱ በድንገተኛ አጋጣሚ (Accident) የመፈፀሙን ሁኔታ የሚያይ መሆኑን ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 57 እና ተከታዮቹ መረዳት ይቻላል፡፡

 • ቸልተኛነት /Negeligiance/

ቸልተኝነት በአጠቃላይ አንድ ግለሰብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለማድረጉን የሚያይ ክፍል ነው፡፡ አንድ ወንጀል አድራጊ ሆነ ብሎ ወንጀሉን ባያደርግም እንኳ ተገቢውን ጥንቃቄና ንቃት አክሎ ቢሆን ኖሮ ወንጀሉ አይፈፅምም ነበር የሚባልበት አይነት ሲሆን ነው፡፡ ቸልተኛነት ቀጥተኛና ኢ-ቀጥተኛ ተብለው ለሁለት ይከፈላሉ፡፡ በአጭሩ ቀጥታዊ ቸልተኛነት /Direct or Advertent Negligence/ የሚባለው ወንጀል አድጊው የሚያፈጽመው ተግባር ህገ-ወጥ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ቢያውቅም አይደርስም ብሎ ክዶ አልያም ግምት ወስዶ የፈፀመ ሲሆን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጀል አድራጊው የሚፈፅመው ተግባር ህገ-ወጥ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል የማያውቅ ሲሆን ነገር ግን ማወቅ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ እያለ ይሄን ባለመገመት ወይም ባለማሰብ በሚፈፅምበት ጊዜ ኢ-ቀጥታዊ ቸልተኝነት /Indirect or Inadvertent Negligence/ ይባላል፡፡ ለምሳሌ አለማየሁ መኪናውን በሚያሽከረክርበት ወቅት ከፍጥነት በላይ ቢያሽከረክርና በመንገደኛ ላይ አካል ጉዳት ቢያደርስ ቸልተኛ በመሆኑ ላደረሰው ጉዳት ይጠየቃል፡፡

 • አስቦ ወንጀል ማድረግ /Intention/

ሌላው የሀሳብ ክፍል አስቦ ወንጀል ማድረግ የሚባለው ክፍል ነው፡፡ ይሄ ከፍል ወንጀል አድራጊው ስለወንጀሉ ሙሉ ግንዛቤ ማለትም ዉጤቱን የሚያወቅ መሆኑና ለዚህም ፈቃደኛ የሆነ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ማለት ወንጀልን አስቦ ማድረግ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉት መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንደኛው አንድ ግለሰብ ሊያደርግ ያለው ድርጊት ምን ውጤት እንዳለው የመገንዘቡ ሁኔታ (full knowledge) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የወንጀሉን ውጤት ለመቀበል የወሰነ ወይም ለውጤቱ ፍላጎት ያለው (Will or Volition) መሆኑ ነው፡፡ የድርጊቱን ውጤት መገንዘብ ሲባል ሊያደርግ ባለው አንድ እንቅስቃሴ ምክንያት ተከትሎ የሚመጣውን ውጤት በአግባቡ መረዳት ሲሆን ምክንያቱም ሆነ ውጤቱ በሕግ የማይፈቀድ መሆኑን የተረዳ መሆኑንም ያሳያል፡፡ ለምሰሌ አንድን ግለሰብ በሽጉጥ ጭንቅላቱን ተኩሶ መምታት የሚገድል ተግባር መሆኑን የሚያውቅና የተገነዘበ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው የሀሳብ ክፍል ደግሞ ውጤቱን የተቀበለ ወይም የፈቀደ መሆኑ ሲሆን ውጤቱን ለማግኘት ተገንዝቦ የፈቀደ፣ ፍላጎት ያለው ወይም ይሁን ያለው ነው፡፡ ወንጀልን አስቦ የማድረግ ሀሳብ በሁለት የሚከፈሉ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ቀጥተኛ /Direct Intention/ የሚባለው ሲሆን ወንጀል አድራጊው በሚያደርገው ተግባር ሊገኝ የሚችለውን ዉጤት ተገንዝቦና ለማግኘትም ፈልጎ /full knowledge/ ድርጊቱን ፈቅዶ /will or volition/ ያደረገ እንደሆነ ነው፡፡  ኢ-ቀጥተኛ /Indirect Intention/ የሚባለው በአንፃሩ ደግሞ ወንጀል አድራጊው በሚያደርገው ተግባር ሊገኝ የሚችለውን ውጤት የተገነዘበ ሲሆን ነገር ግን ለውጤቱ ቀጥተኛ የሆነ ፍላጎት ባይኖረውም ድርጊቱን ከመፈፀም ከመታቀብ ይልቅ ውጤቱን የተቀበለና የመጣው ይምጣ ብሎ የተጓዘ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህን የሀሳብ ከፍሎች ከግለሰቡ ተግባር እና ከባቢያዊ ሁኔታዎች መገንዘብ የሚቻልና ከሳሽ ዐ/ህግ ይህን እርግጠኛ ሆኖ ክሱን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ከላይ ባየነው ምሳሌ ላይ ከበደ ገንዘቡን ሆነ ብሎ መውሰዱ የወንጀል አድራጊውን የሀሳብ ክፍሉን ወይም ሞራላዊ ፍሬ ነገሩን ያሳየናል፡፡

በሌላ በኩል ተገቢ የሆኑትን የትራፊክ ህግጋቶች ጠብቆ የሚያሽከረክር ግለሰብ ያለጥፋቱ በመንገደኛው ስህተት ቢገጭና ቢገድል ጥፋተኛ ሊሆን እንደማይችል የወንጀል ህጉ አንቀፅ 57(3) ይደነግጋል፤ ምክንያቱ ደግሞ ሞራላዊ ፍሬ ነገር ማለትም ችልተኝነትም ሆነ በማሰብ ወንጀልን የማድረግ ሀሳብ የለውምና፡፡

 1. የወንጀል ኢ-ሀላፊነት

የወንጀል ኢ-ሀላፊነት የሚባለው ወንጀል አድራጊው በወንጀል ህግ ተጠያቂና ተቀጪ ሊሆን የማይችልባቸው ሁኔታዎች ሲሆኑ የወንጀል ተግባር ወይም ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ተፈፅሞ ሞራላዊ ፍሬ ነገር ሊጓደል የሚችልባቸው ሁኔታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ከግለሰቡ ሞራላዊ ቅኝት አንፃር የሚታዩ ሲሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 48 እና 49 ላይ ተመልክተዋል፡፡ እስከ 9 ዓመት ድረስ ያሉ ልጆች፣ በሚያደርጉት ድርጊት የሚያስከትለውን ውጤት የማይገነዘቡ ወይም ውጤቱን ተገንዝበው ፍላጎታቻውን ወይም ፈቃዳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ የአእምሮ ህሙማን እና በሌሎች ስነ-ህይወታዊ ምክንያቶች የተግባራቸውን ውጤት አልያም የፍቃዳቸውን ሁኔታ መገንዘብ ወይም መቆጣጠር ያልቻሉ ግለሰቦችን በተመለከተ ተገቢው እርዳታ የሚደረግላቸው እንጂ የሚቀጡ እንዳልሆኑ ህጉ ይደነግጋል፡፡ (እዚህ ላይ ምንም እንኳ በኋላ በዝርዝር የምንመለከተው ቢሆንም በፍሬ ነገር መሳሳትን በተመለከተ አንቀጽ 48 እና 49 ላይ ያልተካተተ መሆኑን ልብ ይሏል!) ለምሳሌ አንድ የአእምሮ ህመምተኛ አንድን ግለሰብ ሊገል ካለው ጠላት እየተከላከለለት መስሎት ግለሰቡን ቢገድልና በእውነቱ ግን ይህን ግለሰብ ሊያጠቃ የመጣ ሌላ ግለሰብ ባይኖር ይህ የአእምሮ ህመምተኛ የተግባሩን ውጤትም ሆነ ለውጤቱ ፍላጎት የሌለው በመሆኑ በወንጀል ህግ ሊቀጣ አይችልም፡፡

 1. በህግ የተፈቀዱ፣ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ

ሌላው በወንጀል ሕጉ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ተፈፅሞ ነገር ግን ቅጣት ተፈፃሚ የማይሆንበት ሁኔታ እንዳለ ከአንቀፅ 68 እስክ አንቀፅ 81 ድረስ ያሉትን ድንጋጌዎች መመልከት እንችላለን፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ድርጊቱ እንዲፈፀም በሕግ የተፈቀዱ ወይም ክልከላ ያልተደረገባቸው ወይም የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሲሆኑ ከላይ ከህጋዊነት መርህ ወይም ፍሬ ነገር ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ናቸው፡፡ በህጋዊነት መርህ ላይ አታድርግም አድርግም ብሎ የሚያዝ ደረቅ የሆነ ህግ ባለመኖሩ ምክንያትና ብሎም ሁኔታዎችን መሰረት ባደረገ መልኩ ማድረግ የተፈቀደበት ሁኔታ መኖሩን ከሕጉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአንቀጽ 68 ላይ ወታደራዊ  ወይም መንግስታዊ ስራዎችን ለማከናወን የሚፈፀሙ ድርጊቶች የተፈቀዱ ድርጊቶች ወይም ያልተከለከሉ በመሆናቸው ሊያስቀጣ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ወታደር በጦር ሜዳ ውስጥ ለሚገድለውና ለሚያቆስለው እንዲሁም ለሚያወድመው ንብረት የሕግ ተጠያቂነት እንደሌለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንዲሁም በአንቀፅ 69 መሰረት የሙያ ግዴታን ለመወጣት ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተከትሎ እስከተከናወነ ድረስ የተፈቀደ ተግባር በመሆኑ ሊያስጠይቅ አይችልም፡፡ እንደምሳሌ የቀዶ ጥገና ህክምናን ሙያ ብንወስድ የአንድ ግለሰብ አካል ላይ ጉዳት አድርሶ የሚከናወን ህክምና ቢሆንም ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተከትሎ እስከተፈፀመ ድረስ የተፈቀደ ተግባር ነው፡፡ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ጥፋቶችን በተመለከተም የወንጀል ህጉ ከአንቀጽ 70 እስከ 81 ድረስ ደንግጓቸው እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሀሳቦች በመሰረቱ ወንጀልን ከሚያቋቁሙ ሶስት ፍሬ ነገሮች መካከል አንዱን የሚያጓድሉ ሁኔታ ሳይሆኑ ከተለያዩ ነገሮች በመነሳት ያለመቅጣትና ይቅርታን ተፈፃሚ የማድረግ ሁኔዎች ናቸው፡፡  ከነዚህም መካከል በስህተት ወንጀልን ስለማድረግ የሚያትተው የህግ ድንጋጌ በአንቀፅ 80 እና 81 ላይ ሲሆን በአንቀፅ 80 ላይ በፍሬ ነገር መሳሳትን በአንቀፅ 81 ላይ ደግሞ በሕግ ላይ መሳሳትን ደንግጓል /በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከአላማው አንፃር በህግ ላይ መሳሳት አልተካተተም/፡፡ በመቀጠል በፍሬ ነገር መሳሳትን በዝርዝር እንመልከት፡፡

 1. በፍሬ ነገር መሳሳት /Mistake of Fact/

በፍሬ ነገር መሳሳት ማለት በማሰብ ሳይሆን ቅንና ሐቀኛ በሆነ መንገድ አንድ ሁኔታ፣ ክስተት ወይም ፍሬ ነገር በተጨባጭ ቢኖርም ባይኖርም የራስን ግንዛቤ በመያዝ የሚፈፀም ድርጊት ነው፡፡ በዚህ ትርጉም ውስጥ በአንድ በኩል የግለሰቡ ግንዛቤ በተጨባጭ ካለው ሁኔታ ጋር በከፊልም ሆነ በሙሉ የማይገናኝ እንደሆነ መረዳት የሚቻል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተጨባጭ ያለው ክስተት ወይም ሁኔታ ሊኖርም ላይኖርም የሚችል መሆኑን ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ፍሬ ነገሩ ሌላ ሆኖ የግለሰቡ ግንዛቤ ደግሞ ሌላ በመሆኑ ሳቢያ የተፈፀመውን ድርጊት በስህተት ላይ የተመሰረተ ያደርገዋል፡፡ ይህ እሳቤ የሚያጠነጥነው በግለሰቡ የሀሳብ ክፍል ላይ እንደሆነ ማየት የሚቻል ሲሆን የወንጀል አድራጊው የሀሳብ ክፍል ሕጋዊ ነገሮችን ለማድረግ ያሰበ ቢሆንም በስተመጨረሻ ላይ ግን ሕገ ወጥ ተግባርን የማድረግን ሁኔታን የሚያሳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ የግለሰቡ ግንዛቤና ፈቃድ ካደረገው ተግባር ጋር የሚጣጣምና የሚገናኝ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ሁኔታውን የተገነዘበ ቢሆን ኖሮ የወንጀል ተግባሩን እንደማያደርገው ወይም እንደማይፈፅመው የሚታወቅና እርግጠኛ ሊሆን የሚቻልበትን ሁኔታ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁኔታ በተከሰተበት ወቅት ግለሰቡ በሕግ የሚጠየቅበት ወይም የሚቀጣበት አግባብ አንደማይኖር የህግ ፍልስፍናውም ሆነ የሀገራት የወንጀል ህግ ያስገነዝቡናል፡፡ በሕግ ፍልስፍናው አንድ ግለሰብ ሊጠየቅና ሊቀጣ የሚገባው የሀሳብ ክፍሉ ሲሟላ እንደሆነ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ በዚህ መለኪያ መሰረት ደግሞ በስህተት የተፈፀመ ወንጀል የሀሳብ ክፍሉ እንደሌለው ማየት ይቻላል፡፡ አንድ ግለሰብ ሊያደርግ ያለው ድርጊት ምን ወጤት እንዳለው የመገንዘቡ ሁኔታ (full knowledge) በግንዛቤው ሳቢያ የተዛባ በመሆኑና የወንጀሉን ውጤት ያልተቀበለበት ሁኔታ በመኖሩ ወይም የወንጀሉን ሁኔታ ቢቀበልም እንኳን በህግ በተፈቀደለት መሰረት (ይህ ሁኔታ በጥንቃቄ በእያንዳዱ ጉዳዮች ሊታዩ የሚገባቸው መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል) ተግባሩን እየተወጣ መሆኑን ተረድቶ የወሰነ ወይም ለውጤቱ ፍላጎት ያለው (Will or Volition) በመሆኑ የሀሳብ ክፍሉን ስንኩል ወይም ያልተሟላ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወንጀል እንደተፈፀመ የማያስቆጥር በመሆኑ ግለሰቡ በሕግ ሊጠየቅም ሆነ ሊቀጣ አይችልም፡፡

በፍሬ ነገር መሳሳት ሁለት አይነት ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ ስህተትን መፈፀም /Fundamental mistake/ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መሰረታዊ ያልሆነ ስህተትን መፈፀም /Non-Fundamental/ ነው፡፡

 • መሰረታዊ ያልሆነ ስህተት /Non-Fundamental/

መስረታዊ ያልሆነ ስህተት /Non-Fundamental/ የሚባለው ወንጀሉ የተፈፀመበት ግለሰብ ወይም የግል ተበዳይ እና ወንጀል ለማድረግ ከታቀደበት ግለሰብ ጋር ልዩነት መኖሩ /Mistake of identity of Victim/ ሲሆን ሌላኛው ድርጊቱ የተፈፀመበት ነገር /Object/ ወንጀል ለማድረግ ከታሰበው ነገር /Object/ ጋር ልዩነት ያለው መሆኑ /mistake of Object of the Offence/ ነው፡፡ እንደ እንግሊዝና ካናዳ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ይህንኑ ሀሳብ የተሻገረ ወንጀል የማድረግ የሀሳብ ክፍል /Transferred Intent/ በሚለው የሚገልፁት ሲሆን ተመሳሳይነት ያላቸው ሀሳቦች ናቸው፡፡ ይህ አይነት ስህተት በወንጀል አድርጊው የሀሳብ ክፍል ውስጥ ያለው እሳቤ ለይቶ በሚያውቀው ግለሰብ ላይ ሊፈፅም የፈለገውን ድርጊት በሌላ ባላሰበው ግለሰብ ላይ የፈፀመው እንደሆነ ነው፡፡ ይህ አይነት መሳሳት መሰረታዊ ስህተት ሊባል የማይችል ሲሆን ወንጀል አድራጊውም በሕግ ተጠያቂ ሆኖ ሊቀጣ እንደሚገባ በወንጀል ሕጋችን 80(3) ላይ በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በዋናነት የወንጀል አድራጊው ወንጀል የማድረግ የሀሳብ ክፍል አልተሟላም ለማለት የማያስችል ሲሆን ግለሰቡ ሌላ ግለሰብን ለማጥቃት ያሰበና ውጤቱንም ተቀብሎ የፈቀደ በመሆኑ የተሟላ የሀሳብ ክፈል አዝሎ ተንቀሳቅሷል ሊባል የሚችል ነው፡፡ የወንጀል አድራጊው መሳሳት የግል ተበዳዮች መቀያያርን ብቻ ያስከተለ በመሆኑ መሰረታዊ ስህተት አያሰኘውም፡፡  የህጉ አላማ ግለሰቦችን ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወንጀል አድራጊው ያሰበው ግለሰብ ላይም ሆነ ያላሰበው ግለሰብ ላይ ጉዳት እስከ ደረሰ ድረስ ሕጉ ወንጀል አድራጊውን ይጠይቃል ይቀጣል፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ከበደ የተባለውን ለመግደል በማታ መሸጎ ጠብቆ ሳለ አየለ የተባለን ግለሰብ ቢገድል በሕጉ መሰረት ይጠየቃል፡፡ ሕጉ ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን የፈፀምኩት በስህተት ነው ሊል እንደማይችል በግልፅ ያስገነዝበናል፡፡ ሌላው መሰረታዊ ያልሆነው ስህተት በወንጀሉ አላማ ወይም ነገር ላይ የተፈፀመ ልዩነት /mistake of Object of the Offence/ ሲሆን ግለሰቡ አላማ አድርጎ የተነሳውን ፈፅሜያለሁ ብሎ ያሰብ ቢሆንም ነገር ግን እንደ እቅዱ ሳይሆን ከዛ በተለየ የወንጀል ፍሬ ቢይዝ ወይም ቢያገኝ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ እጅግ ውድ የሆነ እንቁ የሰረቀ መስሎት እውነተኛ ያልሆነ ወይም አርቴፊሻል እንቁ ቢሰርቅ በወንጀል ተጠያቂ ልሆን አይገባም ማለት አይቻልም፡፡ ሕጉ እንዲህ አይነት ስህተቶችን ከለላ ያልሰጣቸው ስህተቶች ናቸውና ተጠያቂነትን አስከትሎ ቅጣትን ተፈፃሚ ያደርጋል፡፡

 • መሰረታዊ ስህተት /Fundamental mistake/

ሌላው መሰረታዊ ስህተት /Fundamental mistake/ የሚባለው አይነት ሲሆን በወንጀል ህጋችን አንቀፅ 80(1) የተመለከተና ወንጀል አድራጊውን ከቅጣት ነፃ የሚያደርግና ይቅርታ የሚያሰጥ አይነት ስህተት ነው፡፡ ይህ አይነት ስህተት የወንጀል አድራጊውን ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ቀሪ የሚያደርግ በመሆኑ ግለሰቡን ያለሀሳቡ ተጠያቂ ማድረግ ስለማይቻልና ፍትሀዊ ስላልሆነ ከተጠያቂነት ነፃ የሚሆንበት የህግ ስርዓት ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ፍሬ ነገሩ ሌላ ሆኖ የግለሰቡ ግንዛቤ ደግሞ ሌላ በመሆኑ ሳቢያ የተፈፀመው ድርጊት እንደ መሰረታዊ ስህተት ተቆጥሮ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 80(1) መሰረት ተጠያቂነትንና ቅጣትን አያስከትልም፡፡ እዚህ ላይ የምንገነዘበው በወንጀል አድራጊው ተግባርና በወንጀል አድራጊው ግንዛቤ፣ ፍላጎት ወይም ፈቃድ መካከል ግኑኝነት የሌለ መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የወንጀል ድርጊቱ ኖሮ የሀሳብ ክፍሉ የሌለበት ሁኔታን የሚያሳይ ነው፡፡ መሰረታዊ ስህተት በሶስት አይነት መልኩ ሊንፀባረቅ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ የስህተት አይነት እውነታውና የወንጀል አድራጊው ግንዛቤ የተለያየ ሲሆን ነው፡፡ ይህ አይነት ስህተት በመሰረቱ ያልተፈቀደና ክልከላ የተደረገበት ተግባር የተፈፀመ ቢሆንም ሆን ተብሎ ያልተፈፀመ በመሆኑ ሕጉ የሚሰጠው ልዩ አስተያየት ነው፡፡ ለምሳሌ በካፌ ውስጥ አንድ ግለሰብ የራሱ የሞባይል ስልክ መስሎት የሌላን ግለሰብ ስልክ ይዞ ቢሄድ እንደማለት ነው፡፡

ሁለተኛው መሰረታዊ የስህተት አይነት የወንጀል አድጊው ድርጊት የተፈቀደ ወይም ክልከላ ያልተደረገበት ሆኖ ነገር ግን ድርጊቱ የተፈፀመው በህግ በተፈቀደው አግባብ (በወንጀል ሕጉ 68 እና 69) ባለመሆኑ ምክንያትና ግለሰቡ በህግ በተፈቀደው መሰረት ተግባሩን እያከናወነ መስሎት ያደረገው ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፖሊስ በሕጉ በተፈቀደለት መሰረት ወንጀል የፈፀመን ተጠርጣሪ ለመያዝ ብሎ ነገር ግን ወንጀል ያልፈፀመን ሌላ ግለሰብ ቢይዝ የወንጀል ሕጉ ይቅርታ የሚሰጥበት ሁኔታን ይመለከታል፡፡ ነገር ግን ይህ ግንዛቤ አግባብ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን በተመለከተ ፍ/ቤቱ ግላዊ፣ ከባቢያዊና ምክንያታዊ ሁኔታን ተመልክቶና የግለሰቡን ትክክለኛ ሀሳብ ለመገንዘብ ከታች የምንመለከታቸውን መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ የሚመዝነው ወሳኝ ጭብጥ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሶስተኛው መሰረታዊ የስህተት አይነት ሚባለው ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን ለማድረግ ወስኖ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በማክበጃነት የተመለከቱትን ፍሬ ነገሮች በፍፁም ያልተገነዘበውና ያልፈለገው ነገር ግን የፈፀመው ድርጊት ነው፡፡ ለምሳሌ ወንጀል አድራጊው አንድን ግለሰብ ቢሰድበውና ቢያዋርደው ነገር ግን ግለሰቡ የመንግስትን ስራ በማከናወን ላይ ያለ ቢሆን ወንጀል አድራጊው ይህን ጉዳይ እስካልተገነዘበ ድረስ በከባድ ድንጋጌ ማለትም በወንጀል ሕጉ 618 ሳይሆን የሚጠየቀውና የሚቀጣው ባወቀው ልክ ብቻ ማለትም በአንቀፅ 615 መሰረት ነው፡፡

መሰረታዊ ስህተት የማያስቀጣና ይቅርታ በሕጉ መሰረት የሚያሰጥ መሆኑ በመርህ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ ደግሞ በቸልተኛነት እና በሌላ አስከትሎ ባደረገው ወንጀል ልክ የሚጠየቅ መሆኑን በአንቀፅ 80(2) ላይ ያስቀምጣል፡፡ ምንም አንኳ ግለሰቡ ወንጀሉን የፈፀመው ሆነ ብሎ ባይሆንም ነገር ግን ሊወስድ የሚገባውን ጥንቃቄ ቢወስድ ኖሮ ወንጀሉን አይፈፅምም ነበር የሚያስብል እንደሆን ወንጀል አድራጊው በቸልተኛነት ወንጀሉን በመፈፀሙ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በሌላ ሁኔታ ደግሞ ምንም እንኳን በአንድ በኩል የተፈፀመው ወንጀል በወንጀል አድራጊው የሀሳብ ክፍል ውስጥ የሌለ ቢሆንም በሌላ መልኩ ደግሞ ሌላ ወንጀልን ሊያቋቁም የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ ይሀ አይነት ሁኔታ በአብዛኛው በተደራራቢ ወንጀሎች ላይ የሚንፀባረቅ ነው፡፡

ከላይ ያየናቸውን የፍሬ ነገር መሳሳት ጉዳዮች እንዴት መመዘን ይቻላል የሚለውን ቀጥሎ ድግሞ እንመልከት፡፡

 • በፍሬ ነገር የመሳሳት መመዘኛ

መሰረታዊ የፍሬ ነገር ስህተት /Fundamental mistake/ መኖር አለመኖር ለማወቅና ለማረጋገጥ በተለያዩ ሀራት የተለያዩ መመዘኛዎችን ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ መመዘኛዎች ከግለሰብ /ወንጀል አድራጊው/፣ ከወንጀል ህጉ አላማ እና ከማህበረሰቡ ደህንነትና ጥቅም አኳያ ሚዛናቸውን የጠበቁ መሆን እዳለባቸው ይታመናል፡፡ ሆኖም የተለያዩ ሀገራት ወደ አንዱ የሚያጋድሉበት ሁኔታዎች እንዳሉ የሚስተዋል ነው፡፡ በአለማችን ላይ ካሉ መመዘኛዎች መካከል ቅቡል እየሆኑ የመጡ ሁለት መመዘኛዎች ሲኖሩ የመጀመሪያው መመዘኛ ሀቀኝነት /Honest/ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ምክንያታዊነት /Reasonableness/ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሀቀኝነትና ምክንያታዊነት / Honest and Resonablness/ በጋራ ተግባር ላይ ሲወሉ እንደ ሶስተኛ መመዘኛ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታም አለ፡፡

እነዚህ ሁለት መመዘኛዎች በአንዳንድ ሀገራት በተናጥል ሲጠቀሙባቸው ሌሎች ሀገራት ደግሞ በአንድነት የጠቀሙባቸዋል (ሶስተኛ መመዘኛ)፡፡ ለዚህ መለያየት በዋናነት በፍሬ ነገር መሳሳት የሚታይበትና የሚስተናገድበት ሁኔታ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች ወንጀል ከማድረግ ሀሳብ ክፍል ጋር እጅጉን በማቆራኘት መሳሳቱ እስከተፈጠረ ድረስ ከሳሽ ዐ/ህግ ይህ ስህተት ወንጀል የማድረግ ሀሳቡን ቀሪ እንዳላደረገ ተግቶ ማስረዳት እንዳለበት ሲያስገነዝቡ /ይህ አይነቱ ሀሳብ ከወንጀል ህጋችን አንቀጽ 48 እና 49 አንፃር ሊታይ ይገባዋል/ ሌሎች ሀገሮች ደግሞ ይህ አይነቱ ስህተት ተከሳሹ ሊከላከልበትና ለፍ/ቤቱ ሊያስረዳ የሚገባው እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ሊታይ በጠባቡም ሊተረጎም እንደሚገባ ያስቀምጣሉ /In other words, where some regard mistake of fact in relation with negation of guilty intention others see it as an affirmation of positive defense by the accused/፡፡

ሀቀኝነት /Honest/ የሚባለው መመዘኛ ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን በሚፈፅምበት ወቅት የነበረው የሀሳብ ክፍል ወንጀል የማድረግ ሀሳብ እንዳልነበረውና ፍፁም ቅንነትና ሀቀኝነት የተሞላበት መሆኑን ብቻ የሚያይ ነው፡፡ ተንኮል አለው ወይስ የለውም የሚለውን ያያል፡፡ ምንም እንኳ አንድ ምክንያታዊ ሰው ወንጀል አድራጊው በተረዳው መንገድ ሊረዳው እንደማይችል ቢታወቅም ብሎም ወንጀል አድራጊው የተረዳበት መንገድ ጭራሹን የሚያስቅ ቢሆን እንኳን ሀቀኛ /Honest/ እስከነበረ ድረስ በወንጀል ሊጠየቅና ሊቀጣ እንደማይገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይሄ መመዘኛ መሰረት የሚያደርገው የግለሰቡን የወንጀል የማድረግ ሀሳብ በራሱ አለው ወይስ የለውም የሚለውን ግላዊ /Subjective/ መመዘኛን ነው፡፡ (ይህ አይነት መመዘኛ በሀገራችን እድሜያቸው ከ9 ዓመት በታች እና በስነ-ህይወት ሳቢያ ሀሳብና ፈቃድ የሌላቸውን ግለሰቦች ብቻ የሚመለከት መለኪያ እንደሆነ ልብ ይሏል) ለዚህ መመዘኛ አይነተኛ ምሳሌ የምትሆነን ሀገር ካናዳ ነች፡፡ የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ የወንጀል አድራጊው እምነት ወይም ሀቀኝነት ሊታይ የሚገባ እንጂ አድራጎቱ ምክንያታዊ ነበር የሚለው መመዘኛ ግምት ውስጥ ሊገባ እንደማይገባ አስገንዝቧል፡፡ ነገር ግን የግለሰቡን ሀቀኝነት ለመመዘን ከባቢያዊ ሁኔታዎችን መፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ፍተሻ ወቅት ወንጀል አድራጊው ሀቀኛ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን ለማወቅ ምከንያታዊነትን ከግምት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ አለ፡፡

ሌላው መመዘኛ ምክንያታዊነት /Reasonableness/ ሲሆን ይህ አይነት መመዘኛ የግለሰቡን ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ሀቀኛ ነበር ወይስ አልነበረም ከሚለው ባሻገር ተጠራጣሪ የሆነና ወንጀል አድራጊው የደረሰበት ግንዛቤና ድምዳሜ ላይ አንድ ምክንያታዊ ሰው በቦታው እና በሰዓቱ ቢኖር ኖሮ ተመሳሳይ ግንዛቤና ድምዳሜ ላይ ይደርስ ነበር ወይ የሚለውን ይፈትሻል፡፡ በዚህ መለኪያ መሰረት የወንጀል አድራጊው ሀሳብ የሚፈተሸው በአንድ ምክንያታዊ ሰው /Reasonable Man/ አስተሳሰብ ሲሆን አስቂኝ አረዳዶች ብሎም ከምክንያታዊው ሰው በታች ያሉ ግንዝቤዎች ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በመሰረቱ የአንድን ግለሰብ የሀሳብ ሁኔታ ፈትሾ ማወቅ እጅግ አዳጋች ሲሆን በተለይ ፍተሻው ያለመመዘኛ ወይም ከራሱ ከወንጀል አድራጊው በመነሳት ፍተሻ የሚደረግ እንደሆን የወንጀል ህጉን አላማና የህብረተሰብን ጥቅም በእጅጉ ችግር ውስጥ የሚከትና የፍትህ መጓደልን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የምክንያታዊነት /Reasonableness/ መመዘኛ ግላዊ ያልሆነ /Objective/ ሲሆን ይህን አይነት መለኪያ የሚጠቀሙ ሀገሮች የፍሬ ነገር መሳሳትን በልዩ ሁኔታ የሚያዩና በመከላከያነት የሚቀርብ /Affirmative Defense/ መሆኑን በህጋቸው የደነገጉ ሀገራት ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሕጉ ወንጀል አድራጊው ጥፋት አላጠፋም የሚለውን ሀሳብ ለማንፀባረቅ ሳይሆን ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት የቅጣትን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በይቅርታ ማለፍን የመረጠ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝና በጠባቡ የሚተረጎም የህግ ፍልስፍና ነው፡፡  አሜሪካ የምክንያታዊነትን /Reasonableness/ መለኪያ የምትገለገል መሆኑን ከተለያዩ ፅሁፎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ሲባል የግለሰቡን የወንጀል የማድረግ ሀሳብ መኖር አለመኖሩን የምትመዝነው በምክንያታዊው ሰው / Reasonable Man Standard/ አስተሳሰብ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል (The Mistake of Fact Defence and the Reasonable Requirment, Margaret F. Brinig)፡፡

ሌሎች ሀገሮች ደግሞ ሁለቱንም መመዘኛ በአንድ ላይ ይገለገሉበታል፡፡ እንግሊዝ ሁለቱንም መመዘኛ የምትገለገል ሀገር መሆኗን ማወቅ ይቻላል (Mistake of fact, Canadian Bar Association, National Justice Section Committee on Criminal Code Reform)፡፡ ይህ መለኪያ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት መለኪያዎችን በጋራ ተግባር ላይ የሚያውል ከመሆኑ ባሻገር የትርጉም ልዩነት የለው፡፡

ኢትዮጵያ በፍሬ ነገር መሳሳትን በተመለከተ በወንጀል ህጓ አንቀጽ 80 ላይ የደነገገች መሆኑን ቀደም ሲል አይተናል፡፡ ይህ መሳሳት ከላይ ካየናቸው 2 (ወይም 3) መመዘኛዎች አንፃር ህጉ የቱን ይደግፋል የሚለውን ማየት ተገቢነት አለው፡፡ በአንድ በኩል ድንጋጌው በቀጥታ ሲታይ የወንጀል አድራጊውን የተሳሳተ ግንዛቤ መሰረት በማድረግ የሚታይ መሆኑን (ሀቀኝነትን /Honesty/) ሲያስገነዝብ በሌላ በኩል ደግሞ የህጉ አደረጃጀት በመከላከያነት /Affirmative defense/ የሚቀርብ እና በጠባቡ የሚተረጎም ልዩ አይነት ድንጋጌ እንደሆነ ከክፍሉ መገንዘብ ይቻላል (የወንጀል ህጉ ክፍል ሁለት የሚለውን ርዕስ ይመለከተዋል)፡፡ ይህ መሳሳት በአንቀጽ 48 እና 49 ላይ ከተመለከቱት ፍሬ ጉዳዮች (ማለትም እድሜንና የስነ-ህይወትን ጉዳይ ከተመለከቱት) ውስጥ ይልተካተተና በልዩ ሁኔታ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 80 ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ማለት ሕጉ በመከላከያነት ከሚቀርቡ  /Affirmative defense/ ፍሬ ጉዳዮች ጋር እንዲታይና እንዲስተናገድ አልሞ ያሰፈረው ሀሳብ ነው፡፡  ይህ እንደሆን ደግሞ የማስረዳት ግዴታን በተከሳሹ ላይ የሚጥል በመሆኑ ልቅ ሆኖ የሚተረጎም ሳይሆን ምክንያታዊነትን /Reasanableness/ መሰረት አድርጎ የሚታይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ህጉ ከአደረጃጀቱና ከድንጋጌው በመነሳት ቅይጥ መለኪያን ይተገብራል ቢባል መሳሳት አይሆንም፡፡ ይህም ሲባል የሀቀኝነትን /Honest/ እና የምክንያታዊነትን /Resonableness/ መመዘኛዎች በጋራ ህጉ አካቷል ለማለት ነው፡፡ በተጨማሪ የወንጀል ሕጉን አቀራረፅ ብንመለከት ከ1949 ዓ.ም ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በፍሬ ነገር የመሳሳትን ጉዳይ በሁለቱም ህጎች ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ህግን የቀረፁት ፊሊፕ ግሬቨን /phillipe Graven/ የፍሬ ነገር መሳሳትን ምዘና ለማድረግ ሁለቱን መመዘኛዎች ባማከለ ሁኔታ የተደነገገ መሆኑን በፅሁፋቸው ሲያስገነዝቡ አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀል ህግም ከቀድሞ የተቀዳ በመሆኑ በዚህኛውም ህግ መለኪያው ተመሳሳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ በፍሬ ነገር በመሳሳት የሚፈፀም ወንጀል መሰረታዊ ስህተት መሆን እንዳለበት፤ የሀቀኝነትን /Honest/ እንዲሁም የምክንያታዊነትን /Resonableness/ መለኪያ በጋራ በመየዛ ሊመዘን የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን መመዘኛዎች ግልጋሎት ላይ ለማዋል የወንጀሉ አፈፃፀም፣ ቀጥታዊና ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባትም የሚገባ ይሆናል፡፡

Read 10077 times Last modified on Mar 27 2018
Gemechis Demissie

ጸሐፊው በ2004 ዓ.ም ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪውን (LLB) ያጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪውን በሕግ (LLM) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ/ም አግኝቷል፡፡ ጸሐፊው በፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በዐቃቤ ሕግ ሙያ የሠራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በፍትሕ ሚነስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ዐቃቤ ሕግ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

The writer earned his first law degree (LLB) in 2012 with distinction from Haramaya University and his second degree (LLM) from Addis Ababa University in 2020. The writer has worked as a public prosecutor in Federal Ethics and Anti-Corruption Commission and is currently a public prosecutor in the Federal Ministry of Justice, the Office of Attorney General. The blogger can be reached at lawbuffet@gmail.com