Print this page

ዘፈቀዳዊው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትበትና የሚነሳበት አሠራር

ውብሸት ሙላት Mar 07 2018

 

 

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአባል ድርጅቶቹ ሊቃነ መናብርት ጋር በመሆን የግንባሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአሥራ ሰባት ቀናት ያደረገውን ግምገማ መሠረት በማድረግ ማብራሪያና መግለጫ እንደሰጡ ይታወሳል፡፡ በመግለጫውም የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በጥፋታቸው ምክንያት ጉዳያቸው በፖሊስ ምርመራ ላይ ያሉ ክስ ተመሥርቶባቸው በዓቃቤ ሕግ ክትትል ላይ ያለ፣ እንዲሁም የተፈረደባቸውንም ጨምሮ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ግለሰቦች የወንጀል ምርመራው እንደሚቋረጥ፣ ክሳቸው እንደሚነሳ ወይም ምሕረት እንደሚደረግላቸው አስታውቀው እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ ኋላ ላይ ምሕረት የተባለው ጉዳይ ቀረና በይቅርታ፣ ምርመራ በማቋረጥና ክስን የማንሳት ሒደት ቀጥሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ተከሳሾችና ፍርድኞች ተለቀዋል፡፡ በይቅርታም ይሁን የወንጀል ምርመራው ተቋርጦ ወይም ክሳቸው ተነስቶ ከማረሚያ (ከእስር) ቤት የተለቀቁትን በምናጤንበት ጊዜ በምን መሥፈርት እንደተለቀቁ ማወቅ የሚሳነን ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ መነሻው አገራዊ መግባባትና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በመቀጠልም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እንዳሳወቁት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የመናድ ድርጊት ውስጥ ያልተሳተፉ፣ ንብረት በማውደም ያልተጠረጠሩ፣ ያልተከሰሱ፣ ጥፋተኛ ያልተባሉ፣ እንዲሁም የሰው ሕይወት ያላጠፉ ወዘተ የሚሉ መሥፈርቶችም ነበሩ፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ውሎ አድሮ መሥፈርትነታቸው የቀረ ይመስላል፡፡ በእነዚህ መለኪያዎች ቢሆን ክሳቸው የማይነሳላቸው ሰዎች ክሳቸው እንደተነሳላቸው ይታወቃል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ መሠረት ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዳይመሠረት የሚያደርግበትና ክስ የሚያነሳባቸውን ሕጎች እንዲሁም አሠራሩን መፈተሽ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን በፖሊስ የምርመራ ውጤት ላይ

ዓቃቤ ሕግ የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ተፈጸመ በተባለ ወንጀል ላይ ከተጣራ በኋላ ቢደርሰውም፣ የወንጀል ክስ ለፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ሕግ ክስ ማቅረብን የሚከለክልባቸውን ሁኔታዎች መኖራቸውን በሚገባ ሳያጣራ ክስ በማዘጋጀት ለፍርድ ቤት ማቅረብ የለበትም፡፡ ክስ ማቅረብ የመጨረሻ አማራጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደደረሰው በበቂ ሁኔታ ያልተጣሩ ነገሮች ሲያጋጥሙት መዝገቡን መልሶ ለተጨማሪ ምርመራ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 38(ሐ) መሠረት መመለስ ይኖርበታል፡፡ ክስ ለማቅረብ የሚያጠራጥር ነገር ባጋጠመ ጊዜ ደግሞ መዝገቡን የሚመለከተው ዓቃቤ ሕግ የበላይ ዓቃቤ ሕግ መመርያ እንዲሰጥበት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሠረት ማስተላለፍ ይጠበቅበታል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደደረሰው በበቂ ሁኔታ ያልተጣሩ ነገሮች በሚያጋጥሙት ጊዜና እነዚህ ሁኔታዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 39 ሥር ከተመለከቱት ሁኔታዎች አንደኛቸው ከሆኑ ዓቃቤ ሕጉ የፖሊስ የምርምራ መዝገብን መዝጋት አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ መዝገቡን የሚያስዘጉት ክስተቶች የተከሳሹ መሞት፣ የዕድሜው ከዘጠኝ ዓመት በታች መሆን፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የዲፕሎማቲክ ከለላና በልዩ ሕግ መብት የተሰጠው መሆን ናቸው፡፡

ከላይ የተገለጹት እንደተጠበቁ ሆነው የፖሊስ የምርመራ መዝገብ የደረሰው ዓቃቤ ሕግ ክስ ማቅረብ የማይችልባቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ፡፡ እነዚህም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 42 ሥር ተዘርዝረዋል፡፡

በዚህ አንቀጽ ሥር ከተዘረዘሩት ምክንያቶች የመጀመሪያው በወንጀል የተጠረጠረውን ሰው ጥፋተኛ ለማስባል በቂ ማስረጃ አለመኖር ነው፡፡ በቂ ማስረጃ ከሌለ ዓቃቤ ሕግ ክስ መቅረብ የለበትም፡፡ ማስረጃው መመዘን ያለበት ጥፋተኛ ለማስደረግ ከማስቻሉ አንፃር ነው፡፡ አንድን ወንጀል ለማቋቋም ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ነገሮች አንዱ የሆነው የፍሬ ነገር ሁኔታ መኖር ሳይረጋገጥ በምንም ዓይነት ሁኔታ ክስ መቅረብ የለበትም፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ የተከሰሰውን ሰው ለማግኘት የማይቻል ከሆነና ጉዳዩም በሌለበት ሊታይ የማይችል ከሆነ ነው፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ክስ ማቅረብ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክስ ከማቅረቡ በፊት በቅድሚያ የተከሳሹን መኖር ማጣራት ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ሊገኝ የማይችልን ተጠርጣሪ መክሰስ የዓቃቤ ሕግንም የፍርድ ቤትን ጊዜና ሀብት ከማባከን በስተቀር ምንም ፋይዳ የለውም፡፡

ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪም ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመመሥረቱ በፊት የወንጀል ድርጊቱ በይርጋ አለመታገዱን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ክስ ቢቀርብ በይርጋ የሚታገድ ከሆነ ክስ ማቅረቡ አሁንም ትርጉም አይኖረውም፡፡ ወይም ደግሞ ክስ የሚቀርብባቸው ድርጊቶች በይርጋ የማይታገዱ ወንጀሎች መሆን አለባቸው፡፡

የመጨረሻው ደግሞ በሁሉ ነገሩ ክስ ማቅረብ እየተቻለ፣ ተጠርጠሪውንም የሚያስከስሱት ምክንያቶች ቢኖሩም ዓቃቤ ሕጉ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ እንዳያቀርብ ከፍትሕ ሚኒስትሩ ወይም በአሁኑ አጠራር ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጉዳዩን ለሚከታተለው ዓቃቤ ሕግ ትዕዛዝ ያለፈለት እንደሆነ ነው፡፡

በእዚሁ ንዑስ አንቀጽ ላይ በተገለጸው አኳኋን  ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ነገር ውሎ ሲያድር ደግሞ መንግሥትን የሚጎዳ መሆኑ ከተረጋገጠ ክስ የመመሥረት ሒደቱ በድጋሜ  እንዲቀጥል ሚኒስትሩ/ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ማዘዝ ይችላል፡፡

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ አለመመሥረትና ማንሳት

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ እንዳይጀመር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ሊያዝ እንደሚችል ከወንጀልኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ በተጨማሪ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ላይም ተደንግጓል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6(3)(ሀ) ላይ ስለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ሥልጣንና ተግባር ሲገልጽ ‹‹በሕዝብ ጥቅም መነሻ… የወንጀል ምርመራ እንዲቋረጥ ወይም የተቋረጠው የወንጀል ምርመራ እንዲቀጥል ያደርጋል፤›› ይላል፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 42(1) (መ) መሠረት ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም ሲል ክስ የመመሥረት ሒደቱን ሊያቋርጥ እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ የሚሆነው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ ሪፖርቱንም ለዓቃቤ ሕግ አስተላልፎ ነገር ግን ክስ ከመመሥረቱ በፊት ነው፡፡ ክስ ተመሥርቶ ከሆነ ግን በዚሁ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 122 አማካይነት የክስ ሒደቱን ማቋረጥ ወይም ማንሳት ይቻላል፡፡ የክሱ ሒደት እየተከናወነ እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ክሱን ሊያነሳ ይችላል፡፡ ክሱ የሚነሳው በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲያነሳ ፍርድ ቤቱ ከመፍቀዱ በፊት ማረጋገጥ ያለበት ነገር ቢኖር ክሱ ላይ የተገለጸው የወንጀል ድርጊት በዓቃቤ ሕግ ክሱ የማይነሳ አለመሆኑን፣ እንዲሁም ዓቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲያነሳ ከመንግሥት የታዘዘ መሆኑን ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ላይ እንደተገለጸው በከባድ የግፍ አገዳደልና በከባድ የወንበዴነት ተግባር የተከሰሱ ሰዎችን ክስ ማቋረጥ ወይም ማንሳት አይቻልም፡፡ ተራ የሰው ግድያ ወይም በቸልተኝነት ሰው የመግደል ወንጀሎችን በሚመለከት ክስ ማንሳት ይቻላል፡፡

ሌላው መንግሥት ክሱ እንዲቋረጥ የወሰነ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስችል ማስረጃ የመኖር አስፈላጊነት ነው፡፡ የክሱን መነሳት ሲፈቅድም ወይም ሲከለክል ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው ምክንያት የሆኑትን ነጥቦች መግለጽና መመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት መንግሥት ክስ የሚያነሳበትን ምክንያት የመመርመር ሥልጣን ፍርድ ቤት የለውም፡፡ መንግሥትም በምን በምን ምክንያት ክስ ማቋረጥ እንደሚችል አልተገለጸም፡፡ በዚህ ሁኔታ የተቋረጠ ክስ አንድም በሌላ አንቀጽ መልሶና ወዲያውኑ ክስ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ የተነሳውን ክስ መልሶ በሌላ ጊዜ በዚያው ክሱ ተመሥርቶበት በነበረው አንቀጽ ክሱን መቀጠል ይቻላል፡፡ በሌላ ጊዜ የክስ ሒደቱን ማንቀሳቀስን አይከለክልም፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ከሆነ መንግሥት ክሳቸውን በቅርቡ ያቋረጠላቸውን ሰዎችና ወደፊትም የሚያቋረጥላቸውን የዚህ ዓይነት ዕጣ ፋንታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ክስ አለመመሥረትም ማንሳትም ቢሆን ከዚህ ሥጋት ውጭ አይደሉም፡፡ 

እዚህ ላይ መንግሥት ክሱ እንዲቋረጥ ዓቃቤ ሕጉን ማዘዙን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ አለበት ብለናል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት የሚለው የሚያመለክተው ማንን ነው? መንግሥትንስ ወክሎ ትዕዛዝ የሚሰጠው? የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ፍርድ ቤቱ መንግሥት ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ የተረጋገጠ መሆኑን ለመረዳት ትዕዛዙ የተሰጠው በማን ሲሆን ነው?

ከላይ ለተገለጹት ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3)(ሠ) ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹የፌዴራል መንግሥትን በመወከል… ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፤ የተነሳውን ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ አገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ መመርያ ያወጣል፡፡›› ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ክስን የሚያነሳው መንግሥት ነው ቢልም በሕግ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ውክልና መሰጠቱን ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሁኔታው አገራዊ ይዘት ካለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመመካከር እንጂ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ብቻ ማንሳት አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ ሁለት አይቀሬ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንዱ ‘ለሕዝብ ጥቅም’ ማለት ምን ማለት የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ‘አገራዊ ይዘት ያለው የሕዝብ ጥቅም’ ምን ማለት ነው የሚለው ነው፡፡ በእርግጥ ስለሁለተኛው ጉዳይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ መመርያ ማውጣት ስለሚጠበቅበት መልሱን የምናገኘው ከሚያወጣው መመርያ ይሆናል፡፡

የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ክስ ላለመመሥረት ‘ለሕዝብ ጥቅም’ የሚል ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጥ ክስ ለማንሳት ግን ምንም የተገለጸ ቅድመ ሁኔታ የለም፡፡ በአዋጁ ላይ ግን ክስ ማንሳት ወይም ማቋረጥ የሚቻለው ‘ለሕዝብ ጥቅም’ ሲባል እንደሆነ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል አለ፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁም ቢሆን የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን እንደሆነ ትርጓሜም ይሁን ማሳያዎችን አልያዘም፡፡ ስለሆነም ክሱ ላለመመሥረትም ይሁን ለማንሳት ምክንያት የሆነው ጉዳይ የሕዝብ ጥቅም ነው ወይስ አይደለም የሚለውን የሚወስነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ነው፡፡ ክስ በሚነሳበት ወቅት ፍርድ ቤቶች የሕዝብ ጥቅም አለ ወይስ የለም የሚለውን የማጣራት ሥልጣን አልተሰጣቸውም፡፡

ከላይ እንዳየነው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ምርመራን ለማቋረጥ በሕግ የተቀመጡ መሥፈርቶች የሉም፡፡ ክስን ለማንሳትም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን በርካታ ተከሳሾች ክሳቸው የተቋረጠ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በተመሳሳይ ወንጀል እንደውም በአንድ ክስ ከተከሰሱ ሰዎች ውስጥ የተወሰኑት ክሳቸው ተነስቶ የሌሎቹ ደግሞ ያልተነሳም አለ፡፡ ምናልባት ያልተነሳላቸው ለአገራዊ መግባባትና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚኖራቸው ሚና አነስተኛ ነው ተብሎ እንደሆነም የታወቀ ነገር የለም፡፡ እንዲህ ተብሎ ከሆነም ያው ሌላ አገራዊ አለመግባባትን ማስከተሉ አይቀርም፡፡

ረቂቅ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ይኼንን ክፍተት በመረዳት ይመስላል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትባቸውን ሁኔታዎች ዘርዝሯል፡፡ ክስ ማንሳትን በተመለከተ ግን በምን በምን ምክንያቶች ዓቃቤ ሕግ ክስ ሊያነሳ እንደሚችል ረቂቅ ሕጉም ላይ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ በረቂቅ ሕጉም ላይ ቢሆን ለአገራዊ መግባባት ወይም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚሉት ወይም እነዚህን የሚመስሉ አገላለጾች በሕዝብ ጥቅም ሥር አልተካተቱም፡፡

ለሕዝብ ጥቅምን አለመወሰን የሚያስከትላቸው ጣጣዎች

የሕዝብ ጥቅም ምንነት ግልጽ ካልሆነ ይኼንን የመለየትና የመወሰን ፍቃድ ሥልጣን (discretion) ያለው ያው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ነው ማለት ነው፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ በዚህን ሁኔታ የፍቃድ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም እንዳይመጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ አለመመሥረትን እንዲሁም ክስ ማቋረጥን ያለምንም መመርያ (ሕግ) ክፍት አድርጎ መተው ይህንን ሥልጣን አላግባብ ለመጠቀም መንገድ ከፋች ነው፡፡

በአንድ በኩል የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን እንደሆነ ሳያመላክቱ መተው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚሆነው ሰው እንዳሻው እንዲተረጉመው ብቻ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ከዚህ አንፃር ረቂቁ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በተሻለ ሁኔታ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትባቸውን ሁኔታዎች በመዘርዘር ለማሳየት ሞክሯል፡፡

ዓቃቤ ሕጋዊ አሠራር በማናቸውም መልኩ ሥርዓት ያለው፣ አርዓያ የሚሆን ደንቦችን ያሰፈነ፣ ውስጣዊ አሠራሩም ቢሆን ለሕዝብ ተጠያቂነትን ያመቻቸ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በአገሪቱ ያለውን ሕጋዊ አሠራር እንዳይጣስ የኖላዌነት ወይም እረኝነት ኃላፊነት የተጣለበት መሥሪያ ቤት ራሱ የሚሠራቸው ተግባራት ሲበዛ ግልጽ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምን ሕግ፣ በምን ሥርዓት እንደሚሠራ ማሳወቅ የባሕርይው መሆን አለበት፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተቋቋመበት አዋጅ በመግቢያው ላይ ካስቀመጣቸው ግቦች ውስጥ ወጥነት ያለው አገልግሎት መስጠት፣ የሕዝብ ተዓማኒነት ያለው ለሕዝባዊ ተጠያቂነት የሚገዛ እንዲሁም በግልጽነት የሚሠራ የዓቃቤ ሕግ ተቋም ማደራጀት አስፈላጊ የመሆኑ ጉዳይ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በአዋጁ መሠረት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ሲቋቋም ማሳካት ካለበት ግቦች መካከል ጥቂቶቹ ከላይ የተገለጹት ናቸው፡፡

ወጥነት ያለው አገልገሎት መስጠት ከተጓደለ ሕዝብ በተቋሙ ላይ የሚኖረው አመኔታ መቀነሱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ተቋሙ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ሕዝቡ ይህ ተቋም በምን መልኩ እንደወሰናቸው የሚያውቅበት ሥርዓት ከሌለ ግልጽነት የለም ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ አዋጁ ሲወጣ በግብነት ያስቀመጣቸው የሚፃረሩ ይሆናሉ፡፡

በዚሁ በአዋጅ አንቀጽ 11(3)(ሀ) ላይም ይህንኑ ሁኔታ አስፍሮት እናገኛለን፡፡ ዓቃቤ ሕጋዊ አሠራር ለሕዝብ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ መደራጀት፣ የሥራ አመዳደብ፣ የሥራ ዓይነቶቹ፣ ሥራዎቹ የሚመሩባቸው ሥርዓት ሁሉ ለሕዝብ ተጠያቂ መሆንን በሚያሰፍን መንገድ መሆን እንደሚጠበቅበት ተደንግጓል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በማይኖሩበት ወይም በሚድበሰበሱብት ወቅት  ለሕዝብ ተጠያቂ አለመሆንን ያስከትላል፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን በሚመለከትም ሥርዓት የለሽነትም ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው፡፡

የፍቃድ ሥልጣን አጠቃቀም በሕዝብ ዘንድ የማይገመት ሲሆን፣ ሕዝባዊ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሠራር እየመነመነ ሲሔድ ሕዝብ በተቋሙ ላይ የሚኖረው አመኔታ እየቀነሰ መሔዱ አይቀሬ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስነው አዋጅ ይኼንን ሁኔታ አስቀድሞ ከግምት በማስገባት የዓቃቤ ሕግ አስተዳደር ምን መምሰል እንዳለበት በሚዘረዝርበት አንቀጽ 11(3)(ለ) ላይ እያንዳንዱ ዓቃቤ ሕግ የሥራ አፈጻጸሙ ሁሉ ሳይቀር ከሚመዘንባቸው መሥፈርቶች አንዱ በሕዝብ ዘንድ በጎ ተፅዕኖ መፍጠሩ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው መሆኑ ነው፡፡

በአንቀጽ 11 ላይ የተዘረዘሩት የዓቃቤ ሕግ የውስጥ አሠራርን የሚመለከቱ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሚባልበት ጊዜ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉንም ምክትሎቹም እንደሚጨምር አዋጁ አንቀጽ 2(8) ላይ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኝ ዓቃቤ ሕግ እነዚህን አሠራሮች አበክሮ መከተል እንደሚጠበቅበት ሕጉ አስቀምጧል፡፡

በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ተከሰው የተወሰኑት ክሳቸው ተነስቶ የሌሎች አለመነሳቱ በራሱ የእኩልነት መብት ስለሚጋፋ አድሏዊ ይሆናል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በቅርቡ ክሳቸው ከተቋረጠላቸውና በይቅርታ ከተለቀቁት እስረኞች ውስጥ ከግንቦት ሰባት፣ ከኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) እና ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ጋር በተያዘ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ በርካታ ሰዎች እናገኛለን፡፡ ከእዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች በርካቶች በዚህ መንገድ ክሳቸው ያልተነሳና በይቅርታ ያልተለቀቁ ነገር ግን በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱና ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር በተገናኘ ተከሰው የነበሩ ሰዎችም እንዲሁ በዚሁ መልኩ የተለቀቁ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እርግጥ ነው የሃይማኖት አክራሪነት የሚባል ወንጀል የለም፡፡ የተወሰኑት ሲለቀቁ ሌሎች ደግሞ አልተለቀቁም፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠረር አድሏዊነትን የሚያስከትል መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

ለማጠቃለል ያህል የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉን አንቀጽ 42(1)(መ) ላይ ተመርኩዞ ክስ እንዳይመሠረት የማድረጉ ሒደት እንዲሁም በአንቀጽ 122 መሠረት ደግሞ ክስን የማንሳቱ ሥራ በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር የተጠረጠሩን፣ የተከሰሱን በአንድነት ሳይለያይ፣ ሳይነጣጥል እየተተገበረ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ…›› ዓይነት አሠራር መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ያስተላለፈውን አገራዊ መግባባትና የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ውሳኔ እንዳይሳካ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ የታሰበለትን ዓላማም እንዳያሳካ ጋሬጣም ይሆናል፡፡

Read 7760 times