የሚከተሉት ከመጽሐፉ የተወሰዱ ሀሳቦች ናቸው፤
- የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሸቀጦችን ወይም አገልግሎቶችን ከመግዛት እና ከመሸጥ ያለፈ ሰፊ እንቅስቃሴ ወይም ግንኙነትን የሚያቅፍ እንደመሆኑ የሕጉ ማዕቀፍ ተፈጻሚ የሚሆንበት ወሰን መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሕግ በመሰረታዊነት የኢንፎርሜሽን መረብ ሥራ፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና ኤሌክትሮኒክ የመንግስት አገልግሎት ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡
- የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሕግ ተፈጻሚነቱ ከሚወሰንበት ዋና መርህ አንዱ የፈቃደኝነት መርህ ነዉ፡፡ ማንኛውም ሰው ፈቃደኝነቱን እስካልሰጠ ድረስ በማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ወይም ከመንግስት ተቋማት ጋር ባለው ግንኙነት የኤሌክትሮኒክ መልዕክትን እንዲጠቀም፣ እንዲያቀርብ ወይም እንዲቀበል የማይገደድ መሆኑ በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጁ በግልፅ ተደንግጓል፡፡
- የኤሌክትሮኒክ ንግድ እንደ መደበኛው ንግድ የውል ግንኙነትን ተከትሎ የሚደረግ እንደመሆኑ የውል አመሰራረቱ ጉዳይ ዋና የሕግ ጥያቄን ያስነሳል፡፡ በመደበኛ ውል ውልን ለመመስረት ዋና መሰረታዊ ከሚባሉ አስፈላጊ ነገሮች ውስጥ ውል ለመዋዋል ተዋዋይ ወገኖች ያላቸው ፍቃድ፣ ውል ለመፈፀም የሚያስችል የሕግ ችሎታ፣ የውል ቅርጽ እና የውል ጉዳይ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ መሰረታዊ የውል መርሆች በኤሌክትሮኒክ መንገድ ከሚደረግ ውል አንጻር የሚኖራቸዉ ውጤት ምንድን ነው የሚለው መሰረታዊ የሕግ ጉዳይ ነው፡፡