የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ16ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ መወሰኑ ይታወሳል።
ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ አዋጁ ላይ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ዝርዝር ውይይት በማካሄድ ሪፖርትና የመነሻ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚአብሄር አርአያ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መቋቋም የወጡ ሕጎችን በአግባቡ ተግባራዊ መሆናቸውን ለመከታተል ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት መሠረት በማድረግም የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎችና አስተያየታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በቋሚ ኮሚቴውና በፍትሕ ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጦባቸዋል።
ምክር ቤቱ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ከመረመረ በኋላ ረቂቅ አዋጁ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ተጠሪነቱ ለፌዴራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የነበረው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በተሻሻለው አዋጅ ለጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆን መደረጉ ኃላፊነቱ የበለጠ እንዲወጣ እንደሚያስችለው ኮሚቴው ገልጿል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተጠሪ እንዲሆን መደረጉም የተሻለ የሥራ ትስስር፣ ድጋፍና ክትትል የሚያገኝበት አሠራር በመፍጠር ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያደርገው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴው አመልክቷል::