የንግድ ሚኒስቴር የአባላት ቅርንጫፍን በማብዛት የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን እንደሚያስገኝ እየገለፀ ሲሰራ የነበረው ቲያንስ የተባለው ድርጅት ንግድ ፈቃድ ማገዱ ተሰማ፡፡ ድርጅቱ ከአሁን በፊት የወሰደው ፈቃድ እና እያከናወነ ያለው ተግባር የማይጣጣም በመሆኑ እንዲያስተካክል ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ከስህተቱ ሊታረም አለመቻሉን ሚኒስቴሩ ገልጾ ሕገ ወጥ ተግባር ሲያከናውን ስለነበረ ድርጅቱ መታገዱን ነው አስታውቋል፡፡
ቲያንስ ኢትዮጵያ ቢዝነስ በአውሮፓውያኑ 2006 ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ የቻይና የባህል መድሃኒትን መሠረት አድርጎ የሚቀምማቸውን እና የሚያመርታቸውን ምርቶች ለማሰራጨት ፈቃድ ውስዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ነው የተገለፀው። ሆኖም ኩባንያው የምርት ሽያጭን ለማከናወን "ፒራሚድ" ተብሎ የሚጠራውን የአባላት ቅርንጫፍን የማብዣ መንገድ መጠቀምን ከሚከለክለው አገሪቱ ካወጣቸው የንግድ እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ጋር በማይጣጣም መልኩም እየሰራ መሆኑም ተመልክቷል። እንዲህ ዓይነቱ የንግድ አሰራር እሴት የማይጨምር እና ከበርካታ ሰዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ጥቂቶችን ብቻ የሚጠቅም መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።