Print this page

አዲሱ የጉሙሩክ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ስለመጋጨቱ የሚጠበቀው ውሳኔ ተራዘመ

FanaBC Jul 20 2015

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋሀድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ 8 ግለሰቦችና 6 ኩባንያዎች በክስ ይነሳልንና ይቋረጥልን አቤቱታ ላይ የምክር ቤትን ምላሽ ለመጠበቅ የተያዘውን ቀጠሮ በአንድ ሳምንት አሸጋገረ። 

ችሎቱ አዲሱ የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንድ አንቀጽ ከህገ መንግስት አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 2 ጋር ስለሚቃረን ፤ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ስለሚያስፈልገው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለህገ መንግስታዊ ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ ይላክላቸው በማለት ማስተላለፉ ይታወሳል።

በዛሬው ዕለትም ይህንኑ ውጤት ለመጠባበቅ ቀጠሮ ይዞ ነበር፥ ይሁንና ትርጉሙ ስላልመጣለት ውጤቱን ለመጠባበቅ ለሀምሌ 22 ቀን 2007 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

ችሎቱ በሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም ውሎው በመዝገቡ የተጠቀሱ ተከሳሾች በሙስና ከተመሰረቱባቸው ክሶች ይቋረጡልን እና ይነሱልን በማለት ላቀረቡት አቤቱታ ምላሽ ለመስጠት ህገ መንግስታዊ ትርጉም መጠየቁ ይታወሳል።

ብይኑን የሰጠው ተከሳሾቹ አዲስ የተሻሻለውን የጉሙሩክ አዋጅ ከጉሙሩክ ማጭበርበርና ተያያዥ ጉዳዮችን ከወንጀል ነጻ አድርጎ በአስተዳደር ይለቀቁ የሚለው አንቀጽ ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 2 ጋር በመቃረኑም ነበር።

ተከሳሾቹም አዲስ የተሻሻለውን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ምክንያት በማድረግ ክስ ይነሳልን ይቋረጥልን ብለው ያመለከቱ ሲሆን ፥ ህዳር 30 2007 በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ የወጣው ይህ አዋጅ ከጉምሩክ ማጭበርበርና የቀረጥ ነጻ መብት ያለአግባብ መጠቀም የሚሉ በቀድሞ እንደ ህግ ጥሰት የሚቆጠሩትን በአስተዳደራዊ ውሳኔ በገንዘብ መቀጮ ይታለፍ በማለት መደንገጉ ይታወሳል።

በሰኔ 12 የችሎቱ ውሎም ክስ የማቋረጥና የማንሳት ስልጣን የከሳሽ አቃቤ ህግ መሆኑንና የፍርድ ቤት ሃላፊነት ክስ መሰረዝ እንደሆነ ማስረዳቱም ይታወሳል ። ያንን ለማድረግ ችሎቱ የተሻረውንና አዲሱ የጉምሩክ አዋጆችን ከህገ መንግስት ጋር አገናዝቧል።

በአዲሱ አዋጅ 859/2006 አንቀጽ 182 በግልጽ በሌሎች ህጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ አዲሱ አዋጅ ከጸናበት ቀን በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረው ህግ መሰረት ፍጻሜ ያገኛሉ ይላል ።

የህገ መንግስቱ አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ህግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ህግ ተፈጻሚነት ይኖረዋል ይላል።

በብይኑ መሰረት ውጤቱን ለመጠባበቅ ለሃምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም በያዘው ቀጠሮ መሰረት ነበር ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው።

Read 39692 times Last modified on Jul 20 2015