Print this page

ፓርላማው ከጉምሩክ አዋጅ ውስጥ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሥልጣን የሚጋፉ ድንጋጌዎችን በመሰረዝ አፀቀደ

EthiopianReporter Jul 07 2014

ፓርላማው በቀረበለት የጉምሩክ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የተካተቱ የሥነ  ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሥልጣን የሚጋፋ ድንጋጌዎችን በመሰረዝ ረቂቁን የጉምሩክ አዋጅ አፀደቀ፡፡

ባለፈው ረቡዕ ዕትም ፀረ ሙስና ኮሚሽን በጉምሩክ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተካተቱን ሥልጣኑን የሚጋፉና በዜጎች መካከል ልዩነትን ይፈጥራሉ ያላቸውን አንቀጾች በመቃወም፣ ለፓርላማው አቤት ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ባለፈው ሐሙስ በጉምሩክ ረቂቅ ሕግ ላይ የተወያየው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ‹‹የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 166 እና አንቀጽ 167 ተሰርዘዋል፡፡ ምክንያቱም በሥልጣን አላግባብ መጠቀም፣ ሥራን ማጓተትና መደለያ መስጠት በወንጀል ሕግ በግልጽ የተደነገጉ የሙስና ወንጀሎች በመሆናቸው፣ በዚህ አዋጅ ውስጥ ሰፍረው የጉምሩክ ዓቃቤ ሕግ እንዲከታተላቸው መደረጉ ተገቢ ባለመሆኑ ነው፤›› የሚል ማብራርያ ከምክር ቤቱ የበጀትና፣ ፋይናንስ ጉዳዮችና የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች  ቀርቦለታል፡፡
የጉምሩክ ረቂቅ አዋጁ የተጠቀሱትን አንቀጾች የጉምሩክ ወንጀል በማለት ወንጀሉን የፈጸሙ የጉምሩክ ሠራተኞች በሙስና ወንጀል እንዳይጠየቁ የሚያደርግ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል በሚል፣ ቀደም ሲል ተቃውሞ እንደቀረበበት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ፓርላማው የተጠቀሱትን አንቀጾች በመሰረዝና በሌሎች ላይ የቃላት ማስተካከያዎች በማድረግ ረቂቅ አዋጁን አፅድቆታል፡፡
Read 32622 times