Print this page

ከፀደቀ ሁለት ዓመት የሆነው የኢንቨስትመንት አዋጅ ተሻሻለ

EthiopianReporter Jun 24 2014

-አዋጁ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ሥልጣን ይሰጣል 

-ለውጭ ባለሀብቶች የተከለከሉ ዘርፎች እንዳስፈላጊነቱ ሊፈቀዱ ይችላሉ

በ2004 ዓ.ም. ፀድቆ ሥራ ላይ የዋለው የኢንቨስትመንት አዋጅ ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ በድጋሚ ተሻሻለ፡፡

አዋጁ ካካተታቸው ማሻሻያዎች መካከል በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የሚገኘውን የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ወደ ኮሚሽንነት ማሳደግ፣ የኮሚሽኑ የበላይ የሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ማቋቋም ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ልማት ቀጣና መቋቋም የሚቻልበትን ድንጋጌ ማሻሻያው አካቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ልማት ቀጣና በማለት ሲያብራራ የኢንዱስትሪ ዕድገትን፣ የአካባቢ ብክለት ተፅዕኖ መቀነስንና የከተሞች ዕድገትን በዕቅድና በሥርዓት የመምራት ዓበይት ዓላማዎችን የያዘ መሆኑን አዋጁ ያስረዳል፡፡ 

በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ልማት ቀጣና ከላይ የተጠቀሱት ዓላማዎችን ለማሳካት እንደ መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውኃና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችና የተለያዩ አገልግሎቶች ተሟልተውለትና ልዩ የማበረታቻ ዕቅድ ኖሮት አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ወይም ተመጋጋቢነት ያላቸው ኢንዱስትሪዎችን ለማልማት የሚቋቋም ድንበር የተበጀለት ቦታ እንደሚሆን ያስረዳል፡፡ በውስጡም ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና፣ የቴክኖሎጂ ፓርክ፣ የኤክስፖርት ማቀነባበርያ ቀጣና፣ ነፃ የንግድ ቀጣናንና የመሳሰሉትን እንደሚጨምር አዋጁ ያብራራል፡፡

የኢንዱስትሪ ልማት ቀጣናን ማልማት ወይም ማቋቋም የሚችሉት የፌደራል መንግሥት ወይም አስፈላጊነቱ ሲታመንበት በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች ቅንጅት ወይም በግል ባለሀብቶች ሊለማ እንደሚችል በአዋጁ ድንጋጌ ተካቷል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘው የኢንቨስትመንት አዋጅ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ የሚካሄዱ የሥራ መስኮች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰኑ የሚገልጽ ሲሆን፣ ቀጥሎ በወጣው ደንብ መሠረትም ለኢትዮጵያ ባለሀብቶች ብቻ ተብለው የተከለሉ የሥራ መስኮችን ይዘረዝራል፡፡

በዚህም መሠረት የባንክ፣ የኢንሹራንስና አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋም ሥራዎች፣ ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍና የመረከብ ውክልና አገልግሎቶች፣ የብሮድካስቲንግ አገልግሎትና የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች፣ የጥብቅናና የሕግ ማማከር አገልግሎት፣ አገር በቀል ባህላዊ መድኃኒቶችን ማዘጋጀት፣ የማስታወቂያ፣ ፕሮሞሽንና የትርጉም ሥራዎች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

በኢንቨስትመንት አዋጁ ላይ በተደረገው ማሻሻያ ግን ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ የተከለሉ የሥራ መስኮች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለውጭ ባለሀብቶችም ክፍት እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ሊፈቅድ እንደሚችል ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ቀጣናዎች አስተዳደርና ቁጥጥርን በበላይነት መምራትና የኢንዱስትሪ ልማት ቀጣናዎች ስለሚሰየሙበት አሠራር፣ ስለሚመደቡባቸው መሥፈርቶች፣ ስለድንበራቸው አወሳሰን፣ በቀጣናዎች ውስጥ ስለሚሰማሩ ባለሀብቶች መብትና ግዴታ፣ በኢንቨስትመንት አዋጁ መሠረት ከሚያገኟቸው ማበረታቻዎች በተጨማሪ ስለሚያገኟቸው ማበረታዎችና ሌሎችም ጉዳዮች ቦርዱ መመርያ የማውጣት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የፓርላማው የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን በመጥራት ባካሄደው ውይይት፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ኮሚሽኑ መሥራት የሚገባቸውን የኢንቨስትመንት ተግባራትን የማስፈጸምና መመርያዎችን የማውጣት ሥልጣን ለምን እንደተሰጠው ማብራርያ ጠይቆ ነበር፡፡

‹‹ለአብነት ያህል በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ አንድ ትልቅ የፋርማሲዩቲካል ኩባንያ ቢመጣና ኢትዮጵያን ማዕከል አድርጌ ወደ አፍሪካ መላክ ስለምፈልግ የመሬት ሊዝ ዋጋ በዚህን ያህል ብር ስጡኝ፣ የተቀመጠው ማበረታቻ አይበቃኝም ቢልና ሌሎች ጉዳዮችን ቢያነሳ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰበስበው ቦርድ መወሰን እንደሚገባው ለማድረግ ነው፡፡ እንደ ሁኔታው ምላሽ እየተሰጠ ባለሀብቱን መያዝ ካልተቻለና ሁሉንም በአንድ ዓይነት ሁኔታ እናስተናግድ ከማለት ይልቅ፣ የሚያስፈልግ ከሆነ ላላ በማድረግ ከፖለቲካውም አንፃር አይቶ ማቀላጠፍ ካልተቻለ ውጤቱ አመርቂ እንደማይሆንና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደማይቻል በማሰብ ነው፤›› በማለት ምሳሌ አዘል ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡

በማሻሻያ አዋጁ ላይ በኢንዱስትሪ ቀጣና ልማት ውስጥ ከሚካተቱት መካከል ነፃ የንግድ ቀጣና ትርጓሜ ግልጽ እንዲሆንለት ቋሚ ኮሚቴው በጠየቀው መሠረት፣ ‹‹በአንድ የተከለለ ቦታ ዕቃዎች ከውጭ ገብተውና በምርት ሒደት ውስጥ አልፈው ቁጥጥር ከተደረገባቸው በኋላ ወደ ውጭ የሚወጡበት ሒደት ነው፤›› በማለት የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች አብራርተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ማጣሪያና የማሻሻያውን አስፈላጊነት በመፈተሽ፣ ባለፈው ሐሙስ ለፓርላማው በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ማሻሻያው በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡  

Read 32408 times