Print this page

ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ያለምንም ማስረጃ መታሰራቸውን የፖሊስ የምርመራ ሒደት እንደሚያሳይ ጠበቃቸው አሳወቁ

EthiopianReporter Jun 19 2014

-ፖሊስ በየቀጠሮው የሚያነሳቸው የምርመራ ምክንያቶች በፍርድ ቤት ታገዱ

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ያለምንም ማስረጃ መያዛቸውን፣ ፖሊስ ለአራት ጊዜ ፍርድ ቤት በመቅረብ ለችሎት ከሚያስረዳው የምርመራ ሒደት መረዳት መቻሉን ጠበቃቸው አስታወቁ፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኰንን ይህንን የተናገሩት ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ለአራተኛ ጊዜ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበው በነበሩት ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ ጦማሪያንና መምህር ዘለዓለም ክብረት፣ አጥናፍ ብርሃኔና ናትናኤል ፈለቀ ላይ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ቀድሞ በተፈቀደለት 28 ቀናት ውስጥ ‹‹ሠርቻለሁ›› ያለውን የምርመራ ሒደት ተከትሎ ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) በእስር ላይ በቆዩባቸው 50 ቀናት ውስጥ አራት ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ በአንድ ቀጠሮ የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች የሆኑ ብቻ ሁለት ሁለት ሰዎች ችሎቱን እንዲታደሙ የተደረገ ቢሆንም፣ ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ግን ማንም ሰው ወደ ችሎት እንዳይገባ ተከልክሏል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ የፍርድ ቤት ውሎአቸውን ጨርሰው ሲወጡ ጠበቃቸውን አቶ አመሐን የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም ከቤተሰብ ጀምሮ ዲፕሎማቶች፣ ጓደኞቻቸውና ሌሎች በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገኙ ታዳሚዎች ከበቧቸው፡፡

‹‹ምን ተባሉ? ፖሊስ ምን ተጨማሪ ምርመራ አቀረበ?›› ለሚለው የሁሉም ታዳሚዎች ጥያቄ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ጠበቃ አመሐ፣ ‹‹ፖሊስ አዲስ ነገር አላቀረበም፤›› ካሉ በኋላ፣ ባለፉት 28 ቀናት ውስጥ ምን ምን ሥራዎችን እንደሠራ ፍርድ ቤቱ ጠይቆት የተወሰኑ የትርጉም ሥራዎችን እንዳሠራ፣ የተወሰኑ የባንክ ማስረጃዎችን እንዳገኘ፣ የተወሰኑ የቴክኒክና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን እንዳስረዳ ገልጸዋል፡፡ በርካታ ሥራዎች የሠራ ቢሆንም ከሥራው ውስብስብነትና ስፋት አንፃር በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩት በመግለጽ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን መጠየቁን አቶ አመሐ ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ‹‹በርካታ ሥራዎች›› በማለት በጥቅል የተናገረውን በሚመለከት የሠራውንና ያልሠራውን አንድ ሁለት ብሎ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ እንዳዘዘው የገለጹት ጠበቃው፣ የተወሰኑትን የምስክሮች ቃል ተቀብሎ የተወሰኑትን መቀበል እንደሚቀረው፣ ተባባሪዎች ወደ ክልል በመሄዳቸው የምርመራ አባላትን ልኮ እየተጠባበቀ መሆኑን፣ አዲስ አበባ ውስጥም ያልያዛቸው ተባባሪዎች እንዳሉና ለመያዝ እየሠራ መሆኑን፣ የተወሰነ ሰነድ ማስተርጐም እንደሚቀረው አስረድቶ የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ መጠየቁን አስረድተዋል፡፡

ጠበቃ አመሐ በበኩላቸው፣ መርማሪ ፖሊሶቹ ያቀረቡትን ሪፖርት በመቃወም መከራከራቸውን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪ ደንበኞቻቸው ከታሰሩ 50 ቀናት እንዳለፋቸው፣ አራት ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው እንደተፈቀደ፣ የፈለገ ውስብስብ ወንጀል ቢሆን እንኳን ከተያዙ ጊዜ ጀምሮ ምርመራ ቢጀመር 50 ቀናት ምርመራ ለማጠናቀቅ በቂ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ይኼ የሚያሳየው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን የያዛቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይኖረው መሆኑን ነው፤›› ያሉት ጠበቃ አመሐ፣ ተጠርጣሪዎቹን ዋጋ እያስከፈላቸውና ሕግን የጣሰ ተግባር በመሆኑ የመርማሪ ፖሊስን የምርመራ ውጤት ፍርድ ቤቱ ሊቀበለው እንደማይገባ በመናገር መከራከራቸውን አብራርተዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት የሚያነሳቸው የምርመራ ሒደቶች ማለትም ትርጉም ማስተርጐም በተርጓሚውና በፖሊስ መካከል የሚከናወን መሆኑን፣ የቴክኒክ ምርመራውም በራሱ በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ የሚሠራ በመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎቹን በእስር የሚያቆያቸው አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ በቂ ምክንያቶች አለመሆናቸውንና ተጠርጣሪዎቹም ቀሩ በተባሉት የምርመራ ሒደቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያደርሱ ስለማይችሉ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ጠበቃ አመሐ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የመርማሪ ፖሊሱ ሪፖርት ትክክል ነው ብሎ የሚያምን ከሆነም፣ የመጨረሻ የምርመራ ጊዜ ብሎ ትዕዛዝ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከሌሎቹ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለመርማሪ ፖሊሱ ተገቢ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ቀደም ብሎ ፖሊስ ለተጨማሪ ቀጠሮ ማስፈቀጃ ይጠቀምባቸው የነበሩትን፣ ‹‹ተባባሪ መያዝ ይቀረናል፣ ምስክሮች አልተቀበልንም፣ ሰነዶችን ለትርጉም ልከን አልመጣልንምና አሸባሪዎች ከላኩላቸው ገንዘብ ጋር በተገናኘ ከባንክ ማስረጃ ጠይቀን እየጠበቅን ነው፤›› የሚሉ ምክንያቶችን ማቅረብ እንደማይችል ማስታወቁን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከላይ ከተጠቀሱት ውጪ ከሆነ ግን ሊቀበል እንደሚችል የሚያሳይ ትዕዛዝ መስጠቱ፣ ፍርድ ቤቱ የምርመራ ሒደቱን ‹‹የመጨረሻ›› ብሎ ለመናገር አለመድፈሩን እንደሚያሳይ ጠበቃ አመሐ ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በግልጽ ችሎት ለምን ማየት እንዳልቻለ የተጠየቁት ጠበቃ አመሐ፣ በዝግ ችሎት መታየቱን ፖሊስ የሚፈልገው ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ‹‹ዝግ ችሎት ነው›› አለማለቱን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ችሎቶቹ በጣም ጠባብ መሆናቸውን እሳቸውም እንደተገነዘቡ አስረድተዋል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ የወገብ ሕመም እንዳለበት በተደጋጋሚ ገልጾ ወንበር እንዲሰጠው ቢጠይቅም፣ ምላሽ የሚሰጠው እንዳጣ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቆ፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹በጤና በኩል ምንም ድርድር የለም›› በማለት የምርመራ ማዕከሉ እንዲፈጽም ትዕዛዝ ማስተላለፉንም አስረድተዋል፡፡ ቤተሰብም የመጐብኘት መብት እንዳለው ፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ይኼም ተግባራዊ እንዲሆን ትዕዛዝ መስጠቱን አክለዋል፡፡

አንዳንድ የአስተዳደራዊ ችግሮች ካልሆኑ በስተቀር የምርመራ ማዕከሉ ሁሉንም ተገቢ የሚባሉ ነገሮችን እንደሚያደርግ መርማሪ ፖሊሱ ገልጾ፣ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደሚያከብርም መናገሩን ጠበቃ አመሐ ለታዳሚዎች አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ28 ቀናት ጥያቄ በመፍቀድ ለሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 32353 times