የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን የጠበቆች አዋጅ በድጋሚ አሻሻለ

Mar 08 2015

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በ1996 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል የጠበቆች ፈቃድና ዲሲፕሊን ጉዳይ ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ቁጥር 86/1996 በ2005 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 182/2005 አሻሽሎ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ተሻሽሎ በወጣው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የጠበቆችና የህግ ጉዳይ ፀሐፊዎች ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 10 ሥር የሁለተኛ ወይም የአንደኛ ደረጃ የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት አመልካቾች

1.     በክልሉ የሥራ ቋንቋ መሥራት የሚችሉ፣

2.    የሐገሪቱንና የክልሉን ሕገ-መንግስትና ሕጎች የሚያከብሩና የሚያስከብሩ፣

3.    የጥብቅና ሙያ ፈተና ያለፉ፣

4.    ለፍትህ ሥርዓት አሠራር ጥሩ ሥነ-ምግባር ያለቸው፣

5.    የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ለመስጠት በሕግ ወይም በውሣኔ ያልተከለከሉ፣

6.    በአራት አመታት ውስጥ በዲሲፕሊን ጉድለት ተከሰው ያልተቀጡ፣

7.    በከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት ተከሶ ያልተቀጡ፣ እና

8.    ሥራቸውን ለቀው ስድስት ወር ወይም ከዚያ በላይ የቆዩ

መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህንኑ አዋጅ ተከትሎ በክልሉ የጥብቅና አገልግሎት መስጠት ለሚፈልጉ የሕግ ባለሙያዎች የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ሲፈትንና ፈቃድ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አንድ የጥብቅና ፈቃድ መውሰድ የሚፈልግ የሕግ ባለሙያ የጥብቅና ፈቃድ ለመውሰድ ከማመልከትህ በፊት ስትሰራበት ከነበረው መሥሪያ ቤት መውጣት እና ቢያንስ ስድስት ወር አለበለዚያ ከስድስት ወር በላይ መቆየት አለብህ መባሉ አጨቃጫቂ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ሥራቸውን ለቀው ስድስት ወር ወይም ከዚያ በላይ የቆዩ የሚለው መስፈርት የወጣው አንዳንድ ዓቃብያነ ሕግና ዳኞች በሥራቸው ያገኙት አጋጣሚ በመጠቀም ጉዳዮችን አመቻችተው በጥበቅና ለመያዝ እንዳይችሉ ከሚል መነሻ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ መስፈርት ለችግሩ መፍትሔ ነው ለማለት ግን የሚቻል እንዳልሆነ ለመገመት አይከብድም፡፡ ሲጀምር ማንኛውም ጠበቃ ከዚህ በፊት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያውቃቸውን ጉዳዮች በጥብቅና መያዝ እንደማይችል የጠበቆች ሥነ ምግባር ደንብ ግልጽ አድጎታል፡፡

የሆነው ሆኖ የክልሉ መንግሥት አዋጁ አንድ ዓመት ከ7 ወር ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ አዋጁን በአዋጅ ቁጥር 189/2007 አሻሽሎታል፡፡ በመሆኑም በክልሉ የጥብቅና ፈቃድ ማውጣት የሚፈልጉ ባለሙያዎች ሌሎች መስፈርቶች እንደተጠበቁ ሆነው ስድስት ወር ማረፍ ወይም መቆየት ሳይጠበቅባቸው ለፈቃድ ማመልከት ይችላሉ፡፡ የክልሉ መንግሥት ይህንን ሕግና ድንጋጌ ማሻሻሉ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

Read 42287 times Last modified on Mar 09 2015
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)