Latest blog posts

ዳኞች በአንድ ሀገር የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የማይተካ እና ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ሕግ የመተርጎም፣ የሚቀርቡ ማስረጃዎችን የመመርመርና የመመዘን እንዲሁም በችሎቶች የሚካሄዱ የክርክር ሂደቶችን መምራት ዋነኛ የዳኞች ተግባራት ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዳኞች እውነት እና ፍትሕን በማፈላለግ ሂደት ገለልተኛ ውሳኔ ሰጪዎች ናቸው፡፡ 

የወንጀልና የፍትሐብሔር ጉዳዮች ታይተውና ተመርምረው ውሳኔ የሚሰጥባቸው በዳኞች በመሆኑ በተከራካሪ ወገኖች የሚቀርቡ የሰው፣ የሠነድ እና ሌሎች ማስረጃዎችን ተዓማኒነትና ተቀባይነት የመመርመር እንዲሁም የሚቀርቡ የሕግና የፍሬ ነገር ክርክሮችን በተገቢው ሁኔታ አድምጦ የመወሰን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እንደ አጠቃላይም ዳኞች በክርክር ሂደት በሚሠጧቸው ትዕዛዝ፣ ውሳኔና ፍርድ የተከራካሪ ወገኖችን ሕይወት፣ ነፃነትና ንብረት ላይ እንዲሁም በተከራካሪ ወገኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የመወሰን ሥልጣን ተሠጥቷቸዋል፡፡

በመሆኑም የፍትሕ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆኑ ዳኞች የሚቀርብላቸው ጉዳይ ላይ ትክክለኛውን ዳኝነት ለመስጠት በብዙ መልኩ ብቁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም ዳኞች ብቁና ውጤታማ ናቸው የሚባሉት ምን ምን መመዘኛዎች ሲያሟሉ ነው? የዳኞች አመላመልና አስተዳደርስ መመዘኛው ምን መሆን አለበት? የሚሉት ነጥቦች ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሀገራት ከዳበሩ ልምዶችና ሕጎች አንፃር በአጭሩ እንፈትሻለን፡፡

በዚሁ መሠረት በተለያዩ ሀገራት ዳኞች ከሹመት በፊትና በኋላ ብቁ እና ውጤታማ ናቸው ለማለት በዋናነት የሚከተሉትን መመዘኛዎች ሊያሟሉ ይገባል፡፡ እነዚህም፡ -          

1.  ለዳኝነት ሥራ የሚመጥን መልካም ጠባይ መላበስ፡- ዳኞች ሕጉን ከፍሬ ነገር አዛምደው የሚወስኑት ውሳኔ በተከራካሪ ወገኖች ላይ የሚያስከትለውን ውጤት የሚረዱት በዋናነት ከጠበቆች፣ ምስክሮች፣ ተከራካሪ ወገኖች እንዲሁም ሌሎች በዳኝነት ሥራቸው ከሚያገኟቸው ሠዎች ጋር እርጋታና አክብሮት በተሞላበት፣ የማዳመጥ ፍቃደኛነት ባለበት እና በተቻለ መጠን ሕግን ሳይጥሱ የተከራካሪ ወገኖችን ሀሳብ ከክርክሩ ጋር አዛምደው ሲመለከቱ ነው፡፡ ዳኞችም ከመሾማቸው በፊትና ከሹመት በኋላ በሥራ ላይ ትዕግስተኛ፣ አርቆ አሳቢ፣ ሰው አክባሪ፣ ብልህ፣ ታታሪ፣ ቀጠሮ አክባሪ፣ ነገሮችን በቀላሉ የሚረዱና ትሁት መሆናቸው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ዳኞችም እነዚህን የዳኝነት ጠባያት ሊያሳዩ የሚገባው ሁልጊዜ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሚያበሳጩና በሚያናድዱ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ትዕግስትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዳኞች ከሌሎች መመዘኛዎች ባልተናነሰ መልኩ መልካም ጠባይ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በቀደመ የሥራ አፈፃፀማቸውም ሆነ በአኗኗራቸው በሙሉ መልካም ስምና ጠባይ ያተረፉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የቀደመ የሥራም ሆነ የሕይወት ታሪካቸው ከኢ-ሞራላዊና መጥፎ ስም የፀዳ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

2.  በቂ የሕግ ዕውቀት፡- ዳኝነት እንዲሰጥበት ከቀረበው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሕጎች ማወቅ፣ ሕጉን ተግባራዊ ማድረግ፣ ሕጉን ከጉዳዩ ጋር በተገቢው ሁኔታ አገናዝቦ ትንታኔ መስጠት እንዲሁም አዳዲስ ጉዳዮችንና ሀሳቦችን በፍጥነት መረዳት፣ መገንዘብና መላመድ ከዳኞች የሚጠበቅ መሠረታዊ የብቃት መለኪያ ነው፡፡

3.  የማንበብ ልምድ፡- ዳኞች በተከራካሪ ወገኖች የሚቀርቡ የክስ ማመልከቻ፣ መልስ፣ የሠነድ ማስረጃዎች እና ሌሎች ሠነዶችን እንዲሁም ዳኝነት ከሚሠጡበት ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሕጎች እና መጽሐፍት ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ አንብቦ የመወሰን ልምድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡     

4.  ሥነ ምግባር፡- ዳኞች የግልና የሙያ ሥነ ምግባርን ማክበር  ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዳኞች የግል ሥነ ምግባራቸውን በተመለከተ በኅብረተሰቡ የተሠጣቸውን ከፍ ያለ ከበሬታና ደረጃ የማይነካ ሥነ ምግባር ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን አሠራራቸውም ቢሆን የሙያውን ክብር የማይቀንስና በሙያው የተቀመጡ የሥነ ምግባር ደንቦችን ያከበረ ሊሆን ይገባል፡፡     

5.  ድፍረት እና ሀቀኝነት፡-

ድፍረት፡- ዳኞች መስራት እና መወሰን ያለባቸው ሕጉ በሚለው መሠረት እንጂ ብዙኃኑ ወይም አቅምና ሥልጣን ያላቸው ተከራካሪዎች በሚፈልጉት መሆን የለበትም፡፡ በመሆኑም ዳኞች ሕጉን በሥራ ላይ ለማዋል እንዲሁም ሊመጣባቸው የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ተፅዕኖና ጫና ተቋቁሞ ለመስራት የሚያስችል ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ሀቀኝነት፡- ዳኞች የሚሠጡት ውሳኔ በተከራካሪ ወገኖች ማንነት፣ ዘር፣ ፆታ፣ የፖለቲካ አመለካከትና ሥልጣን፣ ኃብት፣ ዝምድና እና የተከራካሪ ወገኖች ጠበቆች ማንነት ተፅዕኖ ሳያድርባቸው በሀቀኝነት ሕጉንና ማስረጃዎችን ብቻ አይተው መወሰን ይኖርባቸዋል፡፡

6.  የትምሕርት ደረጃ እና የሥራ ልምድ፡- ዳኞች ከሁሉም በላይ ሊያሟሉ የሚገባው ነገር የሕግ ትምሕርት እና የሥራ ልምድ ነው፡፡ ዳኞች ከመሾማቸው በፊት የሕግ ትምሕርት ያጠናቀቁ በተቻለ መጠንም በውጤታቸው የላቁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የዳኞች የትምሕርት ደረጃ ምን መሆን እንዳለበት እንደየሀገሩ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን የሚመደቡበት ችሎትም በልዩ ሁኔታ ካጠኑበት የሕግ ዘርፍ ጋር የተያያዘ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዳኞች ከመሾማቸው በፊት በሕግ መምሕርነት፣ የሕግ ባለሙያነት፣ የተለያዩ የሕግ ፅሁፎችና የምርምር ውጤቶችን ለኅትመት በማብቃት፣ በጠበቃነት፣ ዓቃቤ ሕግነት፣ ነገረ ፈጅነትና ሌሎች የሕግ ሥራዎች ላይ የካበተ ልምድ እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ ዳኞች ሊኖራቸው የሚገባው የሥራ ልምድና መጠኑ ተሹመው የሚሠሩበት ችሎትና ደረጃ ሊለያይም ይገባል፡፡

7.  የሥራ ጫናን የመሸከም ብቃት፡- ፍርድ ቤቶች በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ከፍተኛ የመዝገብ መደራረብና የሥራ ጫና ይታያል፡፡ በመሆኑም ያለማቋረጥ የሚቀርቡ ጉዳዮችን ተመልክቶ የሥራ ጫናን ተቋቁሞ በተቀላጠፈ ሁኔታ ዳኝነት መስጠት ከዳኞች የሚጠበቅ የብቃት መለኪያ ነው፡፡

8.  የትምሕርት ደረጃን በየጊዜው ማሻሻል፡- ዳኞች የትምሕርት ደረጃቸውን በየጊዜው እያሻሻሉ ከአዳዲስ ሀሳቦች፣ የዳበሩ አስተሳሰቦች እና በየጊዜው ከሚለዋወጡ ሁኔታዎች ጋር እራሳቸው ብቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሥራ ላይ ያሉ ዳኞች ከተሸሙበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ የሚሾሙትም ከሹመት በኋላ የትምህርት ታሪካቸው አንፃር በየጊዜው ራሳቸውን በትምህርት ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚያደርጉት ጥረት የብቁ ዳኛ መለያ ነው፡፡ 

9.  የመግባባት ችሎታ፡- ዳኞች በችሎት ታዳሚ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር እንዲሁም በውሳኔና ትዕዛዝ አፃፃፍ ላይ ግልፅ፣ አጭር፣ ፍሰቱን በጠበቀና ትክክለኛ መንገድ በጽሑፍም ሆነ በቃል የመግባባትና ሀሳባቸውን የማስተላለፍ እንዲሁም ከተከራካሪዎችና ምስክሮች የሚነገራቸውንም ነገር በቀላሉ ተረድቶ ምላሽ የመስጠት ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የመግባባት ችሎታ ዋነኛው አካል የሆነውን የማዳመጥ ችሎታም ዳኞች እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ ዳኞችም እንደ አጠቃላይ የተከራካሪ ወገኖችን አቤቱታ፣ ቅሬታና፣ ክርክር በአግባቡ የማድመጥ የመናገርና የመፃፍ ችሎታ ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን በክርክር ሂደት ላይ ክስ የመስማት፣ የሚሠጡ ትዕዛዝና ውሳኔዎችን መፃፍ እንዲሁም የተፃፈውን ውሳኔ በሚገባና ቀላል በሆነ መልኩ ለተከራካሪ ወገኖች ማሳወቅ የመግባባት ችሎታ እንዲኖራቸው ግድ ይላል፡፡

እነዚህ ከፍ ብለው የተጠቀሱት መመዘኛዎች የዳበረ የፍትሕ ሥርዓት ባለቸው በተለያዩ ሀገራት ለዳኞች አመላመልና አስተዳደር እንዲሁም ብቁና ምርጥ ዳኞች ለመለየት በመመዘኛነት ያገለግላሉ፡፡ ከእነዚህ መመዘኛዎች በተጨማሪም የዕድሜ ሁኔታ፣ የጤና ሁኔታ፣ ዳኛ ሆኖ ለመስራት ፍቃደኝነት የማጣሪያ ፈተና ማለፍ፣ ቅድመ ስልጠና መከታተል የፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆን እና ሌሎችም ነጥቦች ለዳኝነት ሹመት ወይም ስራ በመመዘኛነት ይቀመጣሉ፡፡ 

ለመሆኑ በሀገራችን ያሉ ዳኞች ከፍ ብለው ከተጠቀሱት መመዘኛዎች ምን ያህሉን ያሟላሉ? አሠራራቸውስ ሁሉንም የምርጥ ዳኛ መለኪያዎች ያሟላል ወይ? ምን ያህሎቹ ዳኞቻችን የዳኝነት ጠባይ ተላብሰዋል? የተመደቡበት ችሎት ላይ የሚታዩ መዛግብት ላይ ለመወሰን በቂ ዕውቀት አላቸው? ምን ያህሎቱ ዳኞቻችን ውሳኔ የሚሰጡበትን መዝገብ እና ተያያዥ ሕጎችና መጻሕፍትን አንብበው ይወስናሉ? ግላዊና ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ይሠራሉ? በድፍረትና በሀቀኝነት ይሠራሉ? በሕግ ትምሕርት የበቁ እና በሚሠሩበት ችሎት ላይ የሚታዩ ጉዳዮችን ለመመልከት የካበተ ልምድ አላቸው? የሥራ ጫናን ተቋቁሞ የመስራት ብቃት አላቸው? ከተሸሙ በኋላስ የትምሕርት ደረጃቸውን ራሳቸውን ብቁ ያደርጋሉ? በቃልም ሆነ በጽሑፍ የመግባባት ችሎታ አላቸው? መልካም ጠባይ የተላበሱስ ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች በተከራካሪዎች፣ ጠበቆች፣ አንባብያንና ሌሎች አስተያየት እንዲሰጡበት በመተው ጽሑፌን አጠናቅቃለሁ፡፡  


Editors Pick

Criminal Law Blog
              መግቢያ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ወንጀል የዚች ዓለም እውነት ነው፡፡ ቃኤል አቤል መግደሉ ከተሰማበት ይህን ጽሑፍ እርሶ እያነበቡ እስካሉት ቅፅበት ድረስ ወንጀል በሰው ልጆች ላይ በሰው ልጅ በራሱ ይፈፀማል፡፡ ይህ ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር መሳ የሆነ ታሪክ ያለው ወንጀል ወደፊትም ማቆሚያ የሚኖረው ...
16756 hits
Arbitration Blog
  It would be appropriate to begin by saying few words about the New York Convention for the Recognition and Enforcement of Foreign Arbitral Awards which came into being in 1948. By the way, our Civil...
7120 hits
Opinion/Critiques/Case Comment/Public Lecture
  ይህን ለመጻፍ ያስገደዱኝን እና የገጠመኙን ሁኔታዎች በቅድሚያ ላብራራ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው አንድ ሰራተኛ አሰሪው በነበረው ድርጅት ላይ ህገ-ወጥ የስራ ውል መቋረጥ ተፈጽሞብኛል በማለት ላቀረበው ክስ አሰሪው ድርጅት በተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ ሰራተኛው የስራ ውሉን ስላቋረጠ ካሳ እንዲከፍለኝ የሚ...
13635 hits
Intellectual Property and Copy Right Blog
  መግቢያ የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎች የአንድ ሀገር ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ልማትን በማፍጠን ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የዚህ ሥራ ፈጣሪዎች የሚበረታቱበትንና አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያበረክቱበት ምቹ ሁኔታ...
14155 hits

Top Blog Posts

Labor and Employment Blog
  ዓለማችን ላይ የፈረንጆቹ 2020 የተወሳሰቡ ችግሮችን ይዞባት መጥቷል፡፡ ከቻይና ውሃን በትንሹ ተነስቶ በወራት ውስጥ ዓለምን ካዳረሰው የኮሮና ቫይረስ የሚስተካከል ችግር ግን ይመጣል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ይህ ቫይረስ በቀጥታ በሰው ልጆች ጤና እና ህይዎት ላይ እያሰከተለ ከሚገኘው ኪሳራ እና ውድመት በሚስተካከ...
Taxation Blog
  በዚህ ጽሑፍ ስለ ግብር ስወራ ምንነት፣ በተለያዩ የግብር ዓይነቶች ሥር የግብር ስወራ ስለሚያቋቋሙ ድርጊቶች፣ ለግብር ስወራ መነሻ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምክንያቶች እንዲሁም የመከላከያ መንገዶቹ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጉምሩክና ታክስ ወንጀል ችሎት...
About the Law Blog
  መግቢያ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀደም ሲል አውጥቶት የነበረውና የተከራየን ሰው ማስወጣት (በርግጥ ደንቡ ይህን ድርጊት አልከለከለም) እና የኪራይ ዋጋን መጨመር ለማገድ የወጣውን የደንብ ቁጥር 122/13 ማራዘሙን በድጋሜ አስታዉቋል፡፡ ይህ ደንብ የቤት አከራዮች ያከራዬት ቤት ላይ ዋጋ እንዳንይጨምሩ ...
Taxation Blog
It is perplexing for me, as a tax lawyer having worked for close to 10 years on Ethiopian tax laws, to see how the investment and finance community in Ethiopia is not worrying enough about the tax on ...