Latest blog posts

ጎሮ ሰፈራ አካባቢ ለወትሮው በሚታጠፍበት ቦታ ላይ ሲደርስ ከፊት ለፊቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች ሲፈተሹ ያያል፡፡ ስለዚህ ትራፊክ ፖሊሶቹ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ጨምሮ ስለመሟላታቸው ለሚቀርቡላቸው ጥያቄ አሽከርካሪዎች

ሲመልሱ ተራው ደርሶት በሒደቱ ውስጥ ለማለፍ መጠባበቅ ጀመረ፡፡ መጠባበቁ ከምክንያታዊ ጊዜ ሲያልፍ ወጣቱ ትራፊክ ፖሊሶቹ እንዲያስተናግዱት መጣራት ጀመረ፡፡ ሰሚ አጥቻለሁ ብሎ በማሰቡ ታጥፎ ለመንቀሳቀስ መንገድ ጀመረ፡፡ 

ድንገት ግን ‹‹ነውር አይደለም እንዴ?›› የሚል ጥያቄ ድምፁን ከፍ አድርጎ ከኋላ ከሚከተል የትራፊክ ፖሊስ ሰማ፡፡ ወጣቱም ተሽከርካሪውን ካቆመ በኋላ ‹‹ነውሬ ምንድን ነው?›› ሲል አጠገቡ የቆመውን ትራፊክ ፖሊስ ጠየቀው፡፡ ለጥያቄው ምላሽ መስጠቱን ወደ ጎን በማድረግ የሚፈልጋቸውን ሰነዶችና ጥያቄዎች አከታትሎ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ወጣቱ የተጠየቀውን ሁሉ ካሟላ በኋላ በድጋሚ የሠራው ነውር ምን እንደሆነ ለማወቅ እንደሚፈልግ ገለጸ፡፡ መንጃ ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎችን ለትራፊኩ ሰጥቶ የነበረው ወጣት ሳያስበው ፊቱ ላይ ተወረወሩበት፡፡ የሁለት ዓመት ሕፃን ልጁና ባለቤቱን ይዞ የነበረው ወጣት በፍጥነት ከተሽከርካሪው በመውጣት ትራፊክ ፖሊሱን ተከትሎ ‹‹ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ አሁንም ያልጠበቀው ምላሽ ገጠመው፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ በቦክስ መታው፡፡ 

ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈጸም የሚመለከቱት የአካባቢው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባዎችም ጭምር ነበሩ፡፡ ወጣቱ ትራፊክ ፖሊሱን ለመክሰስ እንደሚፈልግ በመግለጽ አሁንም መከተሉን አላቆመም፡፡ በአካባቢው የተሰባሰቡት አራት ተጨማሪ የትራፊክ ፖሊሶች ምን እንደተከሰተ እንኳን ለማጣራት ሳይሞክሩ ወጣቱን ይበልጥ በማዋከብና በመገፈታተር መንገዱን እንዲቀጥል አዘዙት፡፡ ‹‹አለቃችሁን ማግኘት እፈልጋለሁ?›› የወጣቱ ቀጣይ ጥያቄ ነበር፡፡ የክፍል አለቃው ራሱን አስተዋውቆ በተሻለ አቀራረብ አነጋገረው፡፡ የሆነውን ሁሉ በጥሞና ከሰማ በኋላ እሱም ቢሆን ጉዳዩን በእርቅ እንዲጨርስ ጠየቀው፡፡ ወጣቱ እንደ ትራፊክ ፖሊሶቹ ሁሉ የመንግሥት ሠራተኛ እንደሆነና አገሩን እንደሚያገለግል፣ የግለሰቡ ድርጊትም በምንም ዓይነት መንገድ አግባብ እንደሌለው እያስረዳ መታወቂያውን አሳየው፡፡ 

መታወቂያውን በማየት ብቻ የትራፊክ ፖሊሶቹ ያሳዩት የአመለካከት ለውጥ ግን ወጣቱን ይበልጥ አስደነገጠው፡፡ ያዋክቡት የነበሩት ትራፊክ ፖሊሶች ወጣቱ ክሱን በመተው በእርቅ እንዲጨርስ ይወተውቱት ጀመር፡፡ አሁን ፖሊሱ ለምን ያህል ዓመት እንደሠራ፣ ልጆችና ትዳር እንዳለው በመጥቀስ ነገሩን እንዲረሳው ይማፀኑት ጀመር፡፡ ድርጊቱን መማርያ ለማድረግ የተነሳው ወጣት ግን ጥያቄያቸውን ችላ ብሎ ወደ ክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ አመራ፡፡ ወደ ቅጥር ግቢው ደርሶ ክስ የሚመሠረትበትን ክፍልና የምርመራ ኃላፊውን አገኘ፡፡ ኃላፊው የወጣቱን ጉዳይ ከሰሙ በኋላ መደብደቡን ሲገልጽላቸው ቀጣዩ ጥያቄያቸው ‹‹ከዚያስ?›› መሆኑ ወጣቱን ግራ አጋባው፡፡ ድርጊቱ በተከሰተበት ቦታ ያገኛቸው ሽማግሌ፣ የትራፊክ ፖሊሱ ባልደረቦች፣ መርማሪ ፖሊሶቹ፣ ዓቃቤ ሕጉ እንዲሁም የወጣቱ ጓደኞች ክስ መክሰሱ የበቀል ዕርምጃ እንደሆነና የሚያስተምረውም ሆነ የሚቀይረው ነገር እንደሌለ ማመናቸው ሊፈጽመው ያሰበው ነገር ትርጉም እንዲያጣ አደረጉት፡፡ ምንም እንኳን ከብዙ መንገላታት በኋላ በፖሊስ ጣቢያው ቃል መስጠትና ሚስቱን ማስመስከር ቢችልም፣ በጉዳዩ ለመግፋት ግን ተነሳሽነቱ እንዲሞት እንዳደረጉት ይገልጻል፡፡ 

ወጣቱ የሺዋስ ፈንታሁን ይህ አጋጣሚ የደረሰበት በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ እርግጥ ነው በፖሊስ ጣቢያዎች ሥር የተዋቀሩት የወንጀል መከላከል የሥራ ሒደት፣ የምርመራና ክትትል ሥራ ሒደት እንዲሁም የትራፊክና ደኅንነት ክፍል ባልደረቦች አደረሱት ተብሎ የሚሰማው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሺዋስን ከገጠመው በአብዛኛው ይልቃል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት ቸልተኝነትና ፍላጎት ማጣት፣ እንዲሁም በቁርጠኝነት ጥሰቶችን ለማረም ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፎች አለመኖር ሁኔታውን ማወሳሰቡ በሁሉም ጉዳዮች የጋራ ችግር እንደሆነ ኤክስፐርቶች ያስረዳሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱን በማክበርና በማስከበር ወንጀልንና የወንጀል ሥጋትን በመከላከልና በመቀነስ፣ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ በየአካባቢው እንዲረጋገጥ ማድረግና የሕዝቡን ሰላማዊ ኑሮና ደኅንነት ማስጠበቅ የፖሊስ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ግን ጥቂት በማይባሉ አጋጣሚዎች ራሱ ፖሊስ በወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ሆነ ተብሎ ሲነገር ይሰማል፡፡ 

በተለይ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች በፖሊስ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደረሰብን ማለታቸው የዜጎችን ትኩረት ከሳቡ የወንጀል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ በዘመናዊ መንገድ ተደራጅቶ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት በጥበቃ ሥር ላሉ ሰዎች የተለያዩ መብቶች ዕውቅናና ጥበቃ ይሰጣል፡፡ 

በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብቶች ተብለው በኢትዮጵያ ከሚታወቁት መካከል ያለመናገር ወይም ቃል ያለመስጠት መብት፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት፣ በዋስ የመለቀቅ መብት፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት፣ በሕግ ባለሙያ ወይም አማካሪ የመወከል መብት፣ ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝና ቅጣት የመጠበቅ መብት፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘት መብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ ሕገ መንግሥት፣ ዝርዝር ሕጎች፣ ተቋማትና አሠራሮችን ለመቅረፅ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ በወረቀት ላይ ከፍተኛ ምቾት የሚሰጡ መብቶች በአፈጻጸም ወቅት ምቾት እንደሚነሱ የዜጎች ምስክርነት ያሳያል፡፡

በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ‹‹በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብት አከባበር በኢትዮጵያ ፖሊስ ጣቢያዎች፡- የክትትል ሪፖርት›› በሚል ርዕስ ያወጣው ሪፖርት የእነዚህ መብቶችን አፈጻጸም የዳሰሰ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በአንዳንድ የፖሊስ አባላትና መርማሪዎች ያልተመጣጠነ ኃይል በመጠቀም ተጠርጣሪን መያዝ፣ ዛቻ፣ ስድብና ድብደባ በተጠርጣሪዎች ላይ መፈጸምና አስገድዶ ቃላቸውን መቀበል ‹‹በተወሰኑ›› ፖሊስ ጣቢያዎች መከሰቱን በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በአብዛኛው ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች በሚያዙበት ጊዜ ያለመናገር መብት እንዳላቸውና የሚናገሩት ማንኛውም ቃል ራሳቸው ላይ እንደማስረጃ ሆኖ እንደሚቀርብባቸው እንደማይነገራቸውም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

በጥበቃ ሥር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ

እነዚህን ክስተቶች በመጥቀስ በኢትዮጵያ ፖሊስ በጥበቃ ሥር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚያደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የመንግሥት ይሁንታ የተቸረውና ተቋማዊ አደረጃጀት ያለው ነው የሚሉ አሉ፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ፣ ሕጎችና አሠራሮች የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚዋጉ በመሆናቸው የግለሰቦች ጥሰት አጋጣሚ እንጂ የሥርዓቱ መገለጫ አይደለም በሚል በሌላ ወገን ክርክር ይቀርባል፡፡ የእነዚህ ሁለት ጽንፍ የያዙ ክርክሮች መቋጫ ጥፋት አጥፍተው በተገኙ የፖሊስ አባላት ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡

የፖሊስ ተጠያቂነት 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ስለሚባሉ ፖሊሶች በየጊዜው ዜና የሚሰማው ዜጋ፣ ለፍርድ ቀርበው ለድርጊታቸው ተጠያቂ መደረጋቸውን ግን ሪፖርት የሚያደርግለት ካላገኘ ተቋማዊ ጥሰት እንዳለ ቢያስብ እንደማይፈረድበት ያስረዳሉ፡፡ 

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አሠራር ተቋማዊ ጥሰትን አይቀበልም፡፡ ግለሰቦች የሚፈጥሯቸው ችግሮች በተቋሙ መፍትሔ እየተሰጣቸው እንደሆነ ያትታል፡፡

አቶ ምትኩ መኰንን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥበቃና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኮሚሽኑ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብትን መጣስ የፖሊስ ተቋም የያዘው አቋም እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ የደረሰው በሥራ ገጠመኞች የተነሳ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በፖሊስ አማካይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ ሪፖርት ተደርጎለት ምርመራ አድርጎ ጥሰቱን ባረጋገጠባቸው ጉዳዮች ሁሉ መንግሥት ዕርምጃ መውሰዱን አቶ ምትኩ ይመሰክራሉ፡፡ 

መንግሥት የወሰዳቸውን ዕርምጃዎች ለኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያደርግ ቢሆንም፣ ለኅብረተሰቡ መረጃውን የማድረስ ችግር እንዳለ ግን ይጠቁሉ፡፡ ‹‹ስህተት በሠሩ ፖሊሶች ላይ ዕርምጃ ሲወስድ ለኅብረተሰቡ የሚገለጽበት አሠራር የለም፡፡ በዚህ የተነሳ በተቋም ደረጃ የተሠራ ሊመስል ይችላል፤›› በማለትም ያብራራሉ፡፡ ይሁንና በተቋም ደረጃ ጥሰቶቹ የሚደገፉ ቢሆን ኖሮ ጉዳዮች ይደበቁና ይድበሰበሱ እንደነበር ይከራከራሉ፡፡ ‹‹እኛ የምናውቃቸውን ጉዳዮች መርምረን፣ ጥያቄ አቅርበን ያልተከሰሰና ዕርምጃ ያልተወሰደበት አላገኘንም፡፡ ከሥራ የተባረሩ፣ የብዙ ዓመት እስራት የተወሰነባቸው ብዙ ጉዳዮችን እናውቃለን፤›› ሲሉም የተቋማቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ 

የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን ለማሳለጥ ይረዳል የተባለው የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር በጥቅምት 2006 ዓ.ም. ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ባለድርሻ አካላትን የሚሠሯቸውን ሥራዎች በማቀናጀት በወረቀት ላይ ያሉ መብቶችን ወደ መሬት በማውረድ ለእያንዳንዱ ዜጋ ተደራሽ የማድረግ ዓላማ ያለውን ይህን ሰነድ አፈጻጸም የሚከታተለው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣ እንደ አቶ ምትኩ ሁሉ የአፈጻጸም ክፍተቶችና የግለሰቦች ስህተት ቢያጋጥምም ተቋማዊ የሆነ የፖሊስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ብለው እንደማያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የወደቁ ሥርዓቶችን የተካ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ተቋማዊ አሠራር ያደርጋል ብሎ መገመት አስቸጋሪ እንደሆነም አቶ ይበቃል ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ይሄ መንግሥት ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር የአገር ህልውና መሠረት አድርጎ ይወስዳል፤›› ሲሉም የሰብዓዊ መብት መከበር የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡ 

አቶ ይበቃል እንደ ሌሎች መብቶች ሁሉ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብቶች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና በመስጠት ሳይገደቡ ተጽፈው ብቻ እንዳይቀሩ አፈጻጸማቸውን ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ ተቋማዊ አደረጃጀቶች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ አደረጃጀቶቹ ስህተት የሚፈጽሙ የፖሊስ አባላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችሉ እንደሆኑም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በርካታ ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች፣ የማረሚያ ቤቶች አመራሮች መብት መጠበቅ አልቻላችሁም ተብሎ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል›› ሲሉም የፖሊስ ተጠያቂነት በወረቀት አለመገደቡን ይመሰክራሉ፡፡

የድርጊት መርሐ ግብሩ ፖሊሶች በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ሲያውሉ ተጠርጣሪዎቹ ያላቸውን መብት ሊገልጹላቸው እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ይህንን ያለማድረግ አስተዳደራዊ ዕርምጃ የሚያስወስድ እንደሆነ በፖሊስ ኮሚሽኖች የአባላት የሥነ ምግባር ደንቦች ውስጥ እንዲካተት ሥልጠናዎች እንዲሰጡም ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ አቶ ይበቃል ሁለቱንም ድርጊቶች ለማሳካት ጥረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

የወንጀል ጉዳዮችን በመያዝ ለታወቁት ጠበቃ አቶ አምሃ መኰንን ግን በዜጎች ዘንድ የፖሊስ ጥሰት ተቋማዊ እንደሆነ ተደርጎ መታሰቡ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ ‹‹ለምሳሌ ደንበኛዬ በፖሊስ ሲመረመር እንዳማክር ጥሪ ተደርጐልኝ አያውቅም፡፡ ይሄ የማይታሰብ ነገር ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በርካታ በፖሊስ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ታዝቤያለሁ፡፡ ነገር ግን ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ይልቅ ጉዳዩን ስታነሳ ቂም ይያዝብሃል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ምትኩም ሆኑ አቶ ይበቃል ያጠፉ ፖሊሶችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ በሚፈለገው መልኩ እየተሠራ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ የግለሰቦች ጥፋት እየተበራከተ ሲመጣ ተቋማቱ ግለሰቦችን መቆጣጠር እንደተሰናቸው ስለሚያሳይ ኃላፊነቱን እንደሚጋሩ በመጠቆም፣ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት ሊሳብ እንደሚገባ አቶ ምትኩ ይመክራሉ፡፡ 

የተራዘመ የምርመራ ጊዜ

ቀልብ በሳቡ ጉዳዮች ተደጋግሞ እንደታየው በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች በተራዘመ የምርመራ ሒደት ያልፋሉ፡፡ እንደ አቶ አምሃ ገለጻ፣ የችግሩ ዋና ምንጭ ፖሊሶች ወንጀል ተፈጽሟል ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸውን ማስረጃ ሳይዙ ተጠርጣሪዎችን ለማሰር የማያመነቱ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የፖለቲካ ትኩሳት ባለባቸው ጉዳዮችና የመንግሥት ልዩ ፍላጎት በሚንፀባረቅባቸው ጉዳዮች ላይ አላስፈላጊ መንዛዛቶች እንደሚስተዋሉ አቶ አምሃ ገልጸዋል፡፡ 

‹‹የወከልኳቸው የዞን ዘጠኝ ጉዳይ ክስ ሳይመሠረትባቸው 83 ቀናት ያህል በምርመራ ቆይተዋል፤›› ሲሉም አቶ አምሃ እንደ አንድ ማሳያ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ደንበኞቼ በጥበቃ ሥር እያሉ ለ20 ቀናት ያህል ልጎበኛቸው አይደለም በምርመራው ሒደት ላማክራቸው አልቻልኩም፤›› ሲሉም ይከሳሉ፡፡ 

ይህ አቶ አምሃ ከልምዳቸው በመነሳት የሚገልጹት ሁኔታ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና በዘፈቀደ የመረጣቸው ዜጎች የሚጋሩት ነው፡፡ እንደ እነዚህ ሰዎች እምነት ፖሊስ በወንጀል የጠረጠራቸውን ሰዎች ለመመርመር ካልታሰሩ ሥራውን የሚሠራ አይመስለውም፡፡ በኢትዮጵያ ሕግም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ባላቸው አሠራሮች በመርህ ደረጃ ዜጎች ነፃነታቸው ተጠብቆና በቁጥጥር ሥር ሳይውሉ የተጠረጠሩበትን ወንጀል አጣርቶ አስተማማኝ መረጃ በቅድሚያ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

አቶ ምትኩ ሰው ታስሮ መረጃና ማስረጃ መሰብሰብ ተገቢነት የሌለው አሠራር መሆኑን ቢገልጹም፣ በተግባር ግን ፖሊስ ከእስር በኋላ መረጃና ማስረጃ የሚሰበስብበት አሠራር እንደሚስተዋል ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ምትኩ በኢትዮጵያ ባህል በወንጀል የተጠረጠረ ሁሉ ወንጀለኛ ነው የሚል እምነት መኖሩ፣ ፖሊሶችም አልፎ አልፎ አመለካከታቸው በዚያው እንዲቃኝ ሳያደርግ እንዳልቀረ ያመለክታሉ፡፡ ይህንን ለመቀየር በርካታ ቀሪ ሥራም እንዳለ ይገልጻሉ፡፡  

ለአቶ ምትኩም ሆነ ለአቶ ይበቃል ችግሩን ለመቅረፍ ትልቁ ቁም ነገር የፖሊሶችን ግንዛቤ ማሳደግ ነው፡፡ ‹‹ሰብዓዊ መብት እንደ ባህል ሊዳብር ይገባል፡፡ ከግንዛቤ እጥረት የሚነሱ የአፈጻጸም ክፍተቶች ይኖራሉ፡፡ ሰብዓዊ መብት በተፈጥሮው ሥር ለመስደድ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የሕግ ሥርዓት ተበጅቷል፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና አመለካከቶች በግልጽ ተተንትነው ቀርበዋል፣ ሕጎች ወጥተዋል፣ አሠራሮች ተዘርግተዋል፡፡ ሰብዓዊ መብትን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የአመለካከት አካል ለማድረግ ጊዜ ይወስዳል፤›› በማለት አገሪቱ ያለባትን ተግዳሮት የጠቆሙት አቶ ይበቃል፣ በድርጊት መርሐ ግብሩ አማካይነት የተሠሩት ሥራዎች ነገሮች በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንዳሉ እንደሚያሳዩ አስገንዝበዋል፡፡ ጽሕፈት ቤታቸውም ለፖሊስ፣ ለማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ ለፍርድ ቤቶች፣ ለፍትሕ ቢሮዎችና ለፍትሕ ሚኒስቴር ሰፊ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱንም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ግንዛቤ ማስጨበጥ ብቻ ሳይሆን እንዲፈጽሙት የቤት ሥራ እንሰጣለን፤›› በማለትም ጽሕፈት ቤቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴን ያገናዘበ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

አቶ አምሃ ግን ፖሊሶች የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙት ከግንዛቤ እጥረት እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የተጠርጣሪዎቹን መብት የማያውቅ መርማሪ አለ ብዬ አላምንም፤›› ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹መርማሪዎቹ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከውጭ ካሉ መረጃዎችና ማስረጃዎች ይልቅ ጥገኛ የሚሆኑት በእምነት ቃልና በምስክሮች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የምርመራ ጊዜውን ማራዘም ብቻ ሳይሆን ለሰብዓዊ መብት ጥሰትም ይጋብዛሉ፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ጥሰት ተፈጽሟል ብለው ባመኑበት አጋጣሚ ክስ ከሰው ያውቁ እንደሆነ በሪፖርተር የተጠየቁት አቶ አምሃ፣ የፖሊስ ባልደረባን ከሰው እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡ ማስረጃ የማግኘት ችግርና በተጠያቂነት ሥርዓቱ ላይ እምነት ማጣት ምክንያት እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ግለሰቡ ተጠያቂ ቢሆን የተቋሙ ስም የሚጠፋ ይመስላቸዋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ አቶ ምትኩ ፖሊሶችን ተጠያቂ ለማድረግ ማስረጃ ማግኘት ከባድ መሆኑን ይጋራሉ፡፡

ወጣቱ የሺዋስም ከትራፊክ ፖሊሱ ጋር በገጠመው ሁኔታ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ይህን ችግር እንዳስተዋለ ጠቁሟል፡፡ ‹‹ከሥራ ባልደረቦቻቸው አንዱን ለመርዳት ማሰቤን ብቻ ነበረ ያስተዋሉት፤›› ሲልም ክስ የመክሰስ ሐሳቡን እንዲተው ያስቻለውን ነጥብ ያመለክታል፡፡ 

አቶ ይበቃል የዜጎችን አመለካከት መቀየር ቁልፍ በመሆኑ ከአፈጻጸም ጎን ለጎን ግንዛቤ ማስጨበጥ ተጠናክሮ እንደሚሠራ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ምትኩ በተጨማሪ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ችግርን ይጠቅሳሉ፡፡ ሌሎች የመንግሥት ቁርጠኝነት የበለጠ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ያጎላሉ፡፡     


Editors Pick

Criminal Law Blog
1.  ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia) ፅንሰ ሃሳብ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት (Trial in absentia) ማለት ተከሳሹ በወንጀል ክሱ በፍርድ ቤት ጉዳዩ በመታየት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ተከሳሹ ግን በአካል በፍርድ ቤት ሳይገኝ ጉዳዩ በሌለበት በመታየት ላይ የሚ...
10604 hits
Contract Laws Blog
Does the law of sales applicable to contract for supply of software? Assume a government authority has bought a software from a software company. A defect in the software led to massive loss of money....
13739 hits
International Law Blog
I will try to make this short essay as perceptive as possible and I will try to avoid legal jargon. Legal jargon is thought to make a writer’s essay water-tight, however, I think this is a mispercepti...
9432 hits
International Law Blog
    ሳፔቶ ሩባቲኖ የተባለ ኩባንያን በማቋቋም ወዲያው የባህር ንግዱን ማጧጧፍ ጀመረ፡፡ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ የኢጣሊያ መንግሥት የጂቡቲን ጠረፋማ አካባቢ እንዲሁ በገንዘብ በመግዛት ከራስ ዱሜራ እስከ ራስ አሊ ከተቆጣጠረችው ፈረንሣይ ጋር ለመሻማት ኩባንያውን ከነካፒታሉ በመግዛት የአሰብን ጠረፋማ አካባቢዎች ተ...
10377 hits

Top Blog Posts

Labor and Employment Blog
  ዓለማችን ላይ የፈረንጆቹ 2020 የተወሳሰቡ ችግሮችን ይዞባት መጥቷል፡፡ ከቻይና ውሃን በትንሹ ተነስቶ በወራት ውስጥ ዓለምን ካዳረሰው የኮሮና ቫይረስ የሚስተካከል ችግር ግን ይመጣል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ይህ ቫይረስ በቀጥታ በሰው ልጆች ጤና እና ህይዎት ላይ እያሰከተለ ከሚገኘው ኪሳራ እና ውድመት በሚስተካከ...
Taxation Blog
  በዚህ ጽሑፍ ስለ ግብር ስወራ ምንነት፣ በተለያዩ የግብር ዓይነቶች ሥር የግብር ስወራ ስለሚያቋቋሙ ድርጊቶች፣ ለግብር ስወራ መነሻ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምክንያቶች እንዲሁም የመከላከያ መንገዶቹ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጉምሩክና ታክስ ወንጀል ችሎት...
About the Law Blog
  መግቢያ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀደም ሲል አውጥቶት የነበረውና የተከራየን ሰው ማስወጣት (በርግጥ ደንቡ ይህን ድርጊት አልከለከለም) እና የኪራይ ዋጋን መጨመር ለማገድ የወጣውን የደንብ ቁጥር 122/13 ማራዘሙን በድጋሜ አስታዉቋል፡፡ ይህ ደንብ የቤት አከራዮች ያከራዬት ቤት ላይ ዋጋ እንዳንይጨምሩ ...
Taxation Blog
It is perplexing for me, as a tax lawyer having worked for close to 10 years on Ethiopian tax laws, to see how the investment and finance community in Ethiopia is not worrying enough about the tax on ...